Monday, 06 May 2019 12:04

ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ ፀጋዬ ገ/መድህን

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
        የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
        እዚያው እወንዙ ዳር እያለ ጎርደድ
        አንድ አዝማሪ አገኘ ሲዘፍን አምርሮ
        በሚያሳዝን ዜማ ድምፁን አሳምሮ
        “ምነዋ ሰው” ምን ትሰራለህ?”
        ብሎ ቢጠይቀው “ምን ይሁን ትላለህ?”
        አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
        እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
        ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ፤
        አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
        ነገሩስ ባልከፋ ውሃውን ማወደስ
        ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
        ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
        ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ
                                          ***
        ምክር
        ተግሳፅም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
        መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ
        ከበደ ሚካኤል
                                         ***
ከበደ ሚካኤል በዚህ “አዝማሪና ውሃ ሙላት” በሚል ግጥማቸው ብዙ ብለውናል፡፡ ውሃውም ግጥምና ዜማ ሊሰማ ሲቆም፣ አዝማሪው ወንዙን ያቋርጣል ለማለት ነው፡፡ ያም ሆኖ ውሃው መገስገሱን እንደማይተው መንገደኛው እየመከረው ነበር፡፡ አንድም ተፈጥሮን በጥበብ የመቆጣጠሩን ነገር በይቻላል - አይቻልም ከራሳችን ጋር  ሙግት እንገጥም ዘንድ በሩን ሲከፍቱልን ነው! ተፈጥሮን በጥበብ መቃኘት ምን ያህል ይቻላል? ጥበበኞቻችን በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሀሳብ ይኖራቸው ይሆን? ማንስ ለውይይት ይጠራቸዋል? እንደ ሎሬት ፀጋዬ፤
“ዝም ብንል ብናደባ ዘመን ስንቱን አሸክሞን
የጅልነት እኮ አደለም፣ እንድንቻቻል ነው ገብቶን”
(ማነው ምንትስ?)
ወይም፡-
የማይሰማ ወጪት ጥጄ እፍ ስል
የከሰመ ፍም
የሰው ቁስል ስዘመዝም
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም”
ዞሮ ዞሮ ያው በጥበብ አፍ ህይወትን መግለፅ ነው፡፡
ጥበብ አንደበቷ ይፈታ ዘንድ ዲሞክራሲና ፍትህ - ርትዕ በማያወላዳ መንገድ የነፃነት መገለጫ መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው፡። ለሀገራችን ኢ-ዲሞክራሲም፣ የይስሙላ-ዲሞክራሲም (Pseudo-democracy) አይበጃትም፡፡ ሀቀኛውንና ለእኛ ሁነኛ ነው የምንለውን ዲሞክራሲ ልቅም፣ ንጥር አድርገን ማወቅ ከብዙ አባዜ ያድነናልና እንምከርበት፡፡ አይዞን አልፈረደም፡፡ ለኢትዮጵያ የሚረፍድ ጊዜ የለም፡፡ አምላኳ ይጠብቃታል፡፡ ራሳችንን ካላፈረስን አገራችን አትፈርስም፡፡ በማንም ትከበብ በማን ማንነቷን የሚነጥቃት አንዳችም ኃይል አይኖርም፡፡ ተዓምራቷ ገና ያልተገለጠ አገር ናት! ገና ያልተገለጠን ተዓምር መገደብ አይቻልም፡፡ ፍፁም ልብ ያለውን ህዝብም ልቡናውን መንጠቅ አይቻልም፡፡ ልቡናው ከፍቅር፣ ከአንድነትና ከጀግንነት ድርና ማግ የተዳወረ ነውና፡፡
ብዙዎች ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ኖረውላታል፡፡ ብዙዎች ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ሞተውላታል፡፡ ብዙዎች ያልተዘመረላቸው በመኖርና በመሞት መካከል አሳር አበሳቸውን አይተውባታል፡፡ ደረጃዋን ጠብቀውና ዕድሜዋን አትብተው ፍሬ የሚያፈሩላት አንበሶች ግን መቼም አጥታ አታውቅም! ያኖሯትም እኒሁ ጀግኖች ልጆች ናቸው! እኒህን ጀግኖች ይባርክልን፡፡ ባለፈው ስራችን ትንሳኤ ያስፈልጋታል ብለን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ዳግማይ ትንሳዔ ያስፈልጋታል፡፡ የኢኮኖሚ ትንሳዔ ያሻታል፡፡ የባህል ትንሳኤ ያሻታል፡፡ የፖለቲካ ዳግማይ ትንሣዔ ግዴታዋ ነው፡፡ ሁሉ ነገር ሲጀመር ያለቀ የሚመስለንን ስሜት ካልገታነው፣ ወደፊት የመራመድ ሀሳባችንን ያኮላሽብናል! ስለዚህ እንጠንቀቅ፡፡ መንገዳችንን እንወቅ፡፡ ህልውናችንን እንለይ!
በሀገራችን ሰራን ከምንለው ያልሰራነው እንደሚበዛ ልባችን ያውቀዋል፡፡ ካጠናነውም ያላጠናነው እንደሚበረክት ማንም ጅል አይስተውም፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ አደብ የገዛ፣ ልቡ የበዛ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልገን ጧት ማታ ልናስብበት የሚገባን ሥርዓተ - ዕሳቤ ነው!
ፀጋዬ ገ/መድህን (ሎሬት) በአፄ ቴዎድሮስ መንፈስ ውስጥ ሆኖ፤
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው ሚቆጨኝ”
የሚለን እናቱም አባቱም ይሄው ነው፡፡ ቃለ - ህይወት ያሰማልን!

Read 11158 times