Monday, 06 May 2019 11:50

Thyroid ወይንም እንቅርት በሴቶች ላይ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

   ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ በማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ሐኪም እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጽንስና ማህጸን ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰርነት አስተማሪ ናቸው፡፡ ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ በዚህ እትም እንግዳ የሆኑበት ምክንያት ለአንባቢዎች መረጃ እንዲሰጡ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው Thyroid የሚባለው በአማርኛው ደግሞ እንቅርት ይባላል፡፡ ነገር ግን እንቅርት የሚለው ትርጉም ብዙ ጊዜ ስራ ላይ የሚውለው በአንገታቸው ላይ እብጠት ያለባቸው ወይንም ሕመሙ እንደያዛቸው ለመግለጽ ሲባል ነው፡፡
ዶ/ር ማህሌት እንደሚሉት ግን Thyroid ወይንም እንቅርት ለሰውነት እጅግ ጠቃሚ የሆነ ኬሚካል የሚያመነጭ በአንገታችን በፊት ለፊት ክፍል ላይ በተለምዶ የአዳም ፍሬ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ከውስጥ በኩል ያለች በእንግሊዝኛው Tyrocsin ታይሮክሲን የተባለውን ለሰውነት እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነውን ንጥረነገር የምታ መነጭ የሰውነት አካል ነች፡፡
የሰውነት ኡደትን በተፈለገው መንገድ መሄዱን የሰውነት ሴል በቀን በቀን እድገትን እና መስራትን የሚቆጣጠር በጣም በትንሹ አስፈላጊ የሆነውን ንጥረ ነገር በሁሉም እድሜ ክልልና ጾታ እንዲኖር የሚያደርግ አካል ነው፡፡ Thyroid የሰውነት አካል ከአእምሮ ጀምሮ የልብ ምትን የጡንቻ አካሄድን አተነፋፈስን መራባትን የመሳሰሉትን ሁሉ የሚቆጣጠር ንጥረ ነገር አመንጪ አካል ነው፡፡  እንቅርት በአገራችን እንደተለመደው ለታማሚዎች ብቻ መገለጫ ሳሆን በተፈጥሮ በማንኛውም ሰው አንገት ከውስት በኩል የሚገኝ አካል መሆኑን ከታች ባለው ስእል ደመቅ ብሎ ይታያል፡፡
እንቅርት የተሰኘው የሰውነት አካል አንድ ሰው ሲፈጠር ገና በእናቱ ማህጸን እያለ ከአራት ወር እድሜው ጀምሮ የሚፈጠረው ልክ እንደልብ እና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ የሰውነት አካሎቻችን እሱም አስፈላጊ ስለሆነ  ነው፡፡ ነገር ግን  በእኛ አገር እንቅርት በሚል ደረጃ አንገት ስር አብጦ
የሚታይበት ምክንያት አዮዲን የሚባል ነገር እጥረት በሚኖርባቸው አካባቢዎች ነበር፡፡ የአዮዲን እጥረት በአሁኑ ወቅት በእጅጉ እየተቀረፈ ስለሆነ የታማሚዎችም ቁጥር እይነሰ መሄዱ እውን ቢሆንም አሁንም ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ይታያል፡፡ የአዮዲን መጠን በምግብ ውስጥ እጥረት በሚኖርበት ጊዜ እጢው ባለው አዮዲን መጠን ለመስራት ወይንም በጎደለው አዮዲን ለመስራት ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ እንዲሁም መጠኑ እየጨመራ ይሄድና ያድጋል፡፡  በዚያ ጊዜ አንገት ስር እብጠቱ ጎልቶ ይታያል፡፡ ሰውነት ታይሮክሲን የተባለውን ንጥረ ነገር ለማምረት የሚያስፈልገውን አዮዲን በማጣቱ ምክንያት የሚፈጠረው እብጠት እንቅርት ተብሎ መጠራቱ የተለመደ ነው፡፡
የአዮዲን እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ሰዎች እንቅርት ያለባቸው ሲሆን በተያያዥም ቁመታቸውም አጭር ነው፡፡ ምክንያቱም ታይሮክሲን የተባለው ንጥረ ነገር በሰውታቸው ውስጥ በበቂ ስለማይመረት የሰውነታቸው እድገትና ክህሎትም ሊያገኙ አይችሉም፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ የአእምሮ ዝግመት ነው፡፡ በታይሮክሲን እጥረት ምክንያት እንቅርት የገጠማቸውና የሰውታቸው እድገት አዝጋሚ የሆነባቸው ሰዎች አእምሮአቸውም በትክክለኛው መንገድ አይሰራም፡፡ ማሰብ ወይንም አንድ ሰው ሊያደርገው የሚገባው ነገር በራሳቸው አቅደው ማድረግ ይሳናቸዋል፡፡  
እንቅርት በሴቶች ላይ፡
ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ እንዳብራሩት እንቅርት ወይንም Thyroid በሴቶች ላይ  ሁለት አይነት ባህርይ አለው፡፡
1/ የእንቅርት ተግባር ታይሮክሲን የተሰኘውን አስፈላጊ ንጥረ ነገር ለሰውነት በጣም በትንሹ ማም ረት ነው:: ዋናው የታይሮክሲን ጥቅም እያንዳንዱ ሴል በትክክል ኃይሉን በመጠ ቀም እለታዊ ክንውኑን እንዲያከናውን ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ጠቃሚ ንጥረ ነገር ታይሮክሲንን ለማግኘት ሲባል እንቅርት ያንን ለማሟላት ከልክ በላይ ስለሚሰራ ሰውነት ከሚገባው በላይ አቅሙ እንዲባክን ወይንም ኃይል እንዲያጠፋ ይሆናል፡፡
የታይሮክሲን መብዛት በሴቶች ላይ ከሚያስከትሉዋቸው ነገሮች መካከል፤
ብስጩ መሆን ወይንም ከሰዎች ጋር አለመግባባት፤
እኔ ብቻ አውቃለሁ ማለት፤
ሰርተው ሰርተው የማደክማቸው ኃለኛ ሰራተኛ መሆን፤
ምግብ ስለማይበሉ ሰውነታቸው እየከሳ ይመጣል፡፡ ነገር ግን ጉልበት አላቸው፡፡
ስለዚህም በቤተሰብ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ እንደአእምሮ ሕመምተኛ መታየት ወይንም  
እንደሱሰኛ መቆጠር ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ባህሪያቸው ድንገት
ስለሚለዋወጥ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በሴቶች ላይ፤-
የወር አበባ መዛባት ማለትም ቶሎ ቶሎ እንዲመጣ ወይንም እንዲቀርም ሊያደርግ ይችላል፡፡
የወር አበባን ለዘለአለሙ እንዲቀር ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ሳፈስ እንዲቆይ ማድረግ እና መጣ
ሄድ የማለት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም እርግዝናን ሊከለክል ይችላል፡፡
የሚረገዘውንም በተደጋጋሚ እንዲወርድ ያደርጋል::
ልጁም ካለቀኑ እንዲወለድ ያደርጋል፡፡ ኪሎአቸው በጣም ትንሽ የሆኑ ልጆች እንዲወለዱ ያደርጋል፡፡
ስለዚህም ጉዳቱ ከእናት ወደልጅ እየቀጠለ ይሄዳል:: ልጁ ከአራት ወር በሁዋላ እራሱ እንቅርት ስለሚኖረው ከእናትየው የሚወርሰው ችግር የለም፡፡ ነገር ግን ከተወለደ በሁዋ ወዲያውኑ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ ማስተካከል ከተቻለ ልጁ ጤነኛ ልጅ ይሆናል፡፡  
2/ ሁለተኛው አይነት ደግሞ ታይሮክሲንን በበቂ ሁኔታ አለመስራት ሲሆን ነው፡፡ ይህ በሚፈጠርበት ጊዜ ሰውት የእለት ተእለት ስራውን በበቂ ሁኔታ እንዳሰራ እና ዝግመት እንዲኖረው ስለሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ማለትም ታሮክሲን በብዛት መመረቱም ወይንም ማነሱም ሴቶች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡  
በታይሮክሲን ማነስ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች፡-
ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ እንዳሉት በታይሮክሲን ማነስ ምክንያት የሚከሰተው ችግር በመብዛቱ ጊዜ ከሚከሰተው በተቃራኒ ነው፡፡
ስራ መስራት አይፈልጉም፡፡ መተኛት ይፈልጋሉ፡፡
ስራ ስለማይሰሩ በሰውነታቸው ውስጥ በተለይም እግራቸው እና ሆዳቸው ላይ ስብ እየተጠራቀመ ይመጣል፡፡
ከባድ ድብርት ውስጥ ይገባሉ፡፡ታይሮክሲን ማነስ መሆኑ ሳይታወቅም የድብርት መድሀኒት ስለሚሰጣቸው የአእምሮ ሕመምተኛ ይመስላሉ፡፡
ስራ የመስራት ፍላጎት ስለማኖራቸው በመስሪያ ቤታቸው ውስጥ እንደሰነፍ ይቆጠራሉ፡፡
የወር አበባ መዛባት የታይሮክሲን ማነስ የገጠማቸውም ያጠቃቸዋል፡፡
ከማህበራዊ ጉዳይ በጣም እራሳቸውን ያርቃሉ፡፡
የማርገዝ እድላቸውንም ያሳጣቸዋል፡፡
ስለዚህ ሴቶች ላይ በስነተዋልዶ ጤናም ይሁን በአጠቃይ ኑሮአቸውን በሚመለከት ጫናው ከወንዶች ይልቅ ከፍተኛ ነው ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ እንዳብራሩት፡፡


Read 10767 times