Saturday, 02 June 2012 09:25

ማካቬሊያዊ ግጥሞች

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

ህዝቡን ማን መምራት አለበት? ለሚለው ጥያቄ መልሱ አስቀድሞ ተሰጥቷል አይደል?...እኔ በመልሱ ላይ ተጨማሪ መልስ ለመስጠት ነው ዛሬየመጣሁት፡፡ መልሱ ህዝቡን የሚወክለው፣ በህዝቡ ምርጫ የተመረጠው…ህዝቡን የሆነው ግለሰብ ነው፡፡ ወይንም ፓርቲ፡፡ ጥያቄው ህዝቡ ማን ነው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በተመለሰው መልስ ላይ ተጨማሪ መልስ የምሰጠው እዚህ ላይ ሆናል፡፡ መልስ የምሰጠው በመጀመሪያ ደረጃ (እንደ ሁልጊዜውም) ለራሴ ነው፡፡ እናንተ ማለት እኔ ናችሁ፡፡ አንድ ያደረገን ሐበሽነታችን ነው፤ የሐበሽነት መንፈስ፡፡ ወይንስ ሰው መሆናችን ነው አንድ ያደረገን?ጥቂቶቹ ልሂቃን ብዙሐኑን ደቂቃን ይምሩ ወይንስ ከብዙሀኑ ደቂቃን መሀል አንዱ ደቂቃ ተነስቶ አመታት ሆኖ ይንገስብን? የሚለው አያሳስበኝም፡፡ ምክንያቱም ደቂቁም ልሂቅ ነው እና ተገላቢጦሽ፡፡ ከሀ-ፐ ያለው ፊደል “ሀ“ ም “ፐ” ም ነውና፡፡ ኦሊጋርኪም ሆነ ሞናርኪ፣ አናርኪም ሆነ ፓትሪያርኬዲሞክራሲ ናቸው፤ ለአበሻ፡፡

ስለዚህ አበሻን ማን ይምራ ለሚለው ጥያቄ መልሴ “ገጣሚው”…”ባለቅኔው” የሚል ይሆናል፡፡ ጠማማ ግኝትም ቢሆን በጠማማ ማሰብ የአበሻነት ውርሴ ስለሆነ…እንደ ተፈጥሮዬ አርፌ ባስብ ይሻላል፡፡ የሚሻለውን ፊትለፊት በመሸሽ አይደል፤ እንቆቅልሽ ሆነን የቀረነው፡፡ ነብሩን ከታሰረበት አጥር (Cage) ነፃ ማውጣት ይቻላል፡፡ ነብሩን ቆዳው ላይ ካለው ነጠብጣም (ሸንተረር) ነፃ ማውጣት ግን አይታሰብም፡፡ የማይታሰበውን በማሰብ ገጣሚነት ይገኛል፡፡ አበሽነት ገጣሚነት ነው፡፡ አየርላንዳዊያን “a nation of poots” ይባላሉ፡፡ ግን አበሻ ነው ባለቅኔ ህዝብ፡፡  ቅኔ ሰም እና ወርቅ አለው፡፡ ውጭ እና ውስጥ፡፡ ላዕላይ እና ታዕታይ…እውነት እና ውሸት…የሆነው እና ለመሆን የሚፈልገው…ግልጽ እና ድብቅ…አበሻነት፡፡ ከአበሽነት የሚመነጭ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ያም ነገር ግጥም ነው፡፡ ቅኔ፡፡ አይጥ ለማጥመድ ሰአሊው በሸራው ላይ ወጥመዱን ስሎ ይጠብቃል…፡፡ የሳለውን ወጥመድ በር ክፍት አድርጐ፡፡ አይጥ ሲገባለት የወጥመዱን በር ስሎ ይዘጋዋል፡፡ ተጨባጭ ወጥመድ መስራት እና አይጥ ማጥመድ የማይችል ሰው እንዴት ፈጣሪን ወይንም እውነትን ወይንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ውበቶችን (በአይጥ ወጥመድ የማያይዙትን) ለማጥመድ በጥበቡ ይችላል? እንቁራሪት ለፈጣሪ ምስጋናን አቅርብ ቢባል … Lord how you made me jump! ከሚል ዝቅታ የበለጠ ሊተነፍስ አይችልም፡፡ ይኼንንም የሚተነፍሰው አንደበት ሲኖረው አይደል?!የሚመነጨው ነገር የሚመጣው ከምንጩ ነው፡፡ አፈሩ ላይ ያደገ ዘር፤ የአፈሩን ንጥረ ነገር ማፍራቱ አይቀርም፡፡ ፍሬው ከዛፉ ርቆ አይወድቅም፡፡ ፍሬው ግጥሙ ነው፡፡ የአበሻዊነት መንፈስ፡፡ መንፈስ በስጋ ውስጥ የተሸነቆረ እና የስጋውን ባህሪ አይደለሁም ለማለት የሚሞክር ነገር ነው፡፡ እንደ እንቆቅልሽ…ግጥም ማለት ይኸው ነው፡፡ “ግጥም ከስሜት ቸርነት ወደ አላማ ብልጠት ለእኔ ያደላብኛል” ያለው ሰለሞን ደሬሳ ነው፡፡ አባባሉ ከላይ ያሳየሁት እሳቤዬን ቁልጭ አድርጐ የሚልጽ ነው፡፡ እሱ ግን ያልገለፀውን እኔ በበለጠ ድፍረት አፈካዋለሁ፡፡ የስሜት ቸርነት የሚመስለው ግጥም የተሰራው በአላማው ብልጥ በሆነ አእምሮ ነው፤ ለማለት ነው ነገሩ፡፡ የዋህነትን በግጥሙ የሚልፀው ገጣሚ የዋህ አይደለም ማለቱ ነው በአጭሩ፡፡ የውጭ የዋህ የውስጥ ብልጥ የሆነ ሁሉ ገጣሚ ነው፤ ከእንግዲህ ለኔ፡፡ ይህንን ቅኔ የተላበሰ በጥበበኛው እና ጥበቡ መሀል ያለውን የቁርኝት መንፈስ ለመረዳት የማካቬሊን “ልዑል” ማንበብ በቂ ነው፡፡ ማካቬሊ ግልጽ በሆነ መንፈስ የፖለቲካ ስልጣን እና ሃያልነትን እንዴት መጨበጥ እንደሚቻል ያትታል፡፡ ስልጣን ጨብጦ ለመቆየት ባለስልጣኑ ለህዝቡ መስሎ የሚታየው እና የሆነው ሰም እና ወርቅ መሆን አለባቸው፡፡ ስልጣን ለመያዝ ስልጣን መንጠቅ ይኖርበታል፡፡ ከመወደድ ይልቅ መፈራት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡ ለእውነት ብሎ እንደ ክርስቶስ ከመሰቀል ይልቅ ለእውነት የተሰቀሉ መስሎ ስልጣን ላይ መሰቀል የተሻለ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ፖለቲካ ነው፡፡ ግጥም ነው፡፡ ሀ’ም ነው፤ ፐ’ም ነው፡፡ ሀ ራሱ ከሀ - ፐ ያለውን ፊደል ነው፡፡ ሁሉም አበሻ ገጣሚ ቢሆንም አንዳንድ ገጣሚዎች ግን የበለጡ ገጣሚ ናቸው፡፡ ሁሉም አበሻ በልኩ ፖለቲካ ቢኖርም፤ አንዳንድ ፖለቲከኞች ግን ከሌላው የበለጠ የልባቸውን ፖለቲካ በተሳካ የስልጣን ስንኝ አዋድደው የስልጣን ቆጡ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ … ሌሎቹን አስነስተው እነሱ ይቀመጣሉ፡፡ ነብሩን ከነጠብጣቡ ነፃ ያወጡት መስለው … ከነጠብጣቡ ይቅርና ከታሰረበት የብረት እስር ቤት ሳያወጡት ይቀራሉ፡፡ ሁሉም አንድ ሆኖ … ግን አንዱ
ከብዙሀኑ የበለጠ ቅኔ በማወሳሰብ በሚፈጥረው … የተስፋ ግጥም፣ ባረጀው ገጣሚ ፈንታ እሱ ስልጣን ላይ ይወጣል፡ … ግጥሙ ሙሉነት ነው፡፡ ፍቅር ነው፡፡ ልዕለ ሰብ ነው፡፡ ግጥሙ ወርቅ ነው፡፡ ገጣሚው ግን ያው ስሙ ነው፡፡ ምድራዊ ነው፡፡ ሰው ነው፡፡ ያው … አበሻ፡፡ ግን እዚህ ላይ ገጣሚው ነው ግጥሙ ግልፁ? … ግልፁ ስም ከሆነ ለአበሻ ግን ግልፁ አበሽነቱ ነው ድብቅ የሆነበት፡፡ እየተዋወቀ እንዳልተዋወቀ የሚሆነው፡፡ እየተቸገረ እንዳልተቸገረ … እየሞተ እንደኖረ … ማንም እንዲበልጠው ሳይፈልግ እንደፈለገ… ፍቅር ሳይኖረው እንዳፈቀረ … ፍቅር እግዚአብሔር እንደሆነ የሚሆነው፡፡
አበሻ መሆንን ይመኛል፡፡ “ሰው ማለት … ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ሰው የጠፋ ለት” ይላል፡፡ ይመስለኛል የተመኘውን ሰው የሚሆነው ውስጥና ውጪ፤ ሰም እና ወርቁ አንድ ሆነው የገጠሙለት ነው፡፡ ህልሙ ይህ ነው፤ እውን ሆኖለት ግን አያውቅም፡፡ በመሰረቱ በእኔ እምነት (የእኔን እምነት እየገለፅኩ እንደሆነ ይታወቅ!) የአለም ህዝብ በሙሉ … ሰው ለመሆን የሚሞክር እንጂ የሆነ አይደለም፡፡ ሰው እስካሁን ከሌለ እንዴት በሰው መኖር ወይንም ሊኖር ይችላል በሚል እምነት እስካሁን ተስፋ ጥለን ቆየን? የሚል ጥያቄ ይመጣል፡፡ እንግዲህ ጀግኖቻችን ናቸው ሰዎቻችን፡፡ … ሰውዬውን ፍላጐቱን በተለያዩ የሰው አይነቶች ሲያመልክ ቆይቷል፡፡ የሰው ልጅ (ወይንም የዝንጀሮ) ከፊሉ፤ እነዚህን የሰው ምሳሌዎቹን በአምላክ ስም ይጠራቸዋል፡፡ አሊያም በነብያት፡፡ ሌላው በሰማዕታት … ሌላው በአርአያ … ሌላው ደግሞ በጀግና … ከሁሉም የበለጠው የሰው አይነት የትኛው እንደሆነ ግን በንፅፅር ደረጃ እንጂ እቅጩ የታወቀ ነገር ያለ አይመስልም፡፡ … ሁሉንም አይነት ሰው የመሆን ህልም ያስተሳሰረ አንድ ግጥም እንደሌለ ሁሉ … አንድ ብቸኛ ምልኡ ሰው ታይቶ አይታወቅም፡፡ የማይታወቅ ከሆነ ለምን መፈለጉን አንተውም? የሚል ግን የለም፡፡ ዛፍ ወደ ላይ ማደግ፣ እስኪቆረጥ ድረስ ማቆም እንደማይፈልገው ሁሉ ሰውም ምልዑ የመሆን የህልም ፍላጐቱን ሊተው አይችልም፡፡ ስብከቱ እንጂ ሰባኪው ጉድለት ያለበት ነው፡፡ ጥበቡ እንጂ ጥበበኛው ተጓዥ ነው፡፡ ፍልስፍናው እንጂ ፈላስፋው ማስተማሪያ አይሆንም፡፡ ግን ከጐዶሎ ውስጥ ሙሉ ነገር እንዴት ይወጣል፤ ጐዶሎው ነገር ከውስጡ የወጣውን ሙሉነት የእኔ ነው እንዴት ሊል ይችላል?... ፍጡሩን ፈጣሪው ከየት አምጥቶ ፈጠረው?! ሰአሊው ለመሳል ከፊለፊቱ ያስቀመጠውን የበሰበሰ ፍራፍሬ አውጥቶ በመስኮት መወርወር ሳይችል፣ ግን በመስኮት ፍራፍሬ አውጥቶ የሚወረውር ሰው እንዴት ሊስል ይችላል? … ምኞቱን በቅርቡ በተጨባጭ ሳያሳካ … የሩቅ ህልም እንዴት አይቶ ለመጠበብ ይችላል? ለፈጣሪስ የተለየ ምን ይለዋል? … በፀሎቱ … ሰው ለሰው በአፉ እና በተግባሩ መናገር /ማከናወን ችሎ
ከፍ ያለ የእውነት እርከን ላይ ካልደረሰ? …)  ማካቬሊ ወርቁን ሰም ነው ያደረገው፡፡ በጠመዝማዛ መንገድ ወደቀጥተኛው መድረስ፡፡ በውሸት ቋንቋ
እውነትን የተናገረ መምሰል፡፡ በእርግጥ አካፋን ተጠቅሞ ከህዝቡ ማንኪያ ጋር እየጠለቁ ገንፎን እንዴት መብላት እንደሚቻል እና እየተበላበት ያለ ህዝብም በፍርሃት ምንም ሳያጉረመርም ማስበላቱን እንደሚቀጥል ነው ማካቬሊ…ቁልጭ አድርጐ በprince መጽሐፉ ያሳየን፡፡ አካፋን አካፋ ብሎ እየጠራም ቢሆን ቅኔን መፍቻ እና ቅኔን መስሪያ እና መደበቂያ መንገድ ነው የጠቆመን፡፡ በግልጽ ቋንቋ ሰውነታችንን ነው ያስረዳን፡፡ ሁለት አይነት ሰዎች እንዳሉ ተረዳሁ፡፡ ሁለት የአእምሮ ክፍል ስላለኝ ሊሆን ይችላል … ሁሉንም ነገር በሁለት የምከፍለው፡፡ ወደ ላይ ማሰብ/ማደግ መሆን የሚፈልገውን… እውነት/ፍቅር/ነፃነት/እውቀት/ሁነት/ደስታ/እምነት/… የወደላይ ህልም አቅርበውለት የበታቹን ደረጃውን ለራሳቸው ከፍታ መወጣጫነት ለመጠቀም የሚፈልጉ (ከወደ አላማ ብልጠት የሚያደሉት) እና እውነተኛውን ግጥም/እውነት/ፍቅር/ነፃነት በህልም ሳይሆን በተጨባጭ መልክ በራሳቸው ላይ በመሞከር ቅኔነታቸውን ወደ አንድ ፍቺ ለማምጣት ተንቀሳቅሰው፣ የታችኛውን ማንነታቸውን የሚያጡት ናቸው፡፡ እንደ ማህተማ ጋንዲ - ራሱንበመምራቱ ሌሎቹን ማስከተል እንደቻሉት አርዓያዎች፡፡ ማህተመ ጋንዲም ተገደለ፡፡ ክርስቶስም ተሰቀለ፡፡ ሶቅራጥስም መርዙን ተጋተ፡፡ ጥበበኛው ከጥበቡ ጋር አንድ ሲሆን ሞት ቅርብ ነው፡፡ ፖለቲከኛውም ከፖለቲካው፣ አማኑም ከእምነቱ፡፡ ነብስ እና ስጋ አንድ ሆነው በአንድ አላማ አድረው ሲዋሃዱ…መስዋእትነት ቅርብ ነች፡፡ ለምንም አይነት አላማ መስዋእትነትን መክፈል በዚህ መልኩ ሲሆን…”ሰው ማለት” የሚለው ትርጉም ይገኛል፡፡

 

 

Read 2616 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 09:40