Saturday, 27 April 2019 11:10

በዘንድሮው የፋሲካ ገበያ የበሬ ዋጋ ንሯል

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

 ለዘንድሮ የትንሳኤ በዓል የ3ሺ በሬዎችና የ1ሺ በግና ፍየል እርድ እንደሚያከናውን የገለፀው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፤ ለአንድ በሬ የእርድ ዋጋ 500 ብር፣ ለበግ ደግሞ 100 ብር እያስከፈለ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ጠቁሟል፡፡
በፋሲካ የበዓል ገበያ፣ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ሲሆን፤ በተለይ የበሬ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ንሯል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የአንድ በሬ ዋጋ እስከ 100ሺህ ብር ደርሷል፡፡
ገርጂ አካባቢ በሚገኘው ገበያ የደብረብርሃን፣ የጅማና የወሊሶ በጐች ከ2ሺ500 -7ሺ ብር ድረስ ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡ የሀረርና የጅማ ፍየሎች ከ4ሺ ብር -10ሺ ብር እየተሸጡ ነው - እስከ ትላንት ድረስ ባደረግነው የገበያ ቅኝት፡፡
በዘንድሮው በዓል ከፍተኛውን ጭማሪ ያሳየው የበሬ ገበያ ሲሆን፤ በኮተቤ 40 ማዞሪያ የበሬ ገበያ አንድ በሬ በ100ሺ ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
በገርጂ ገበያ የወላይታ ዶሮ ከ400-500 ብር የሚሸጥ ሲሆን፤ በሾላ ገበያ ከ250-350 ብር ይገኛል፡፡ በሾላ፣ በገርጂ ገበያና በአትክልት ተራ በአይሱዙ ለሽያጭ የቀረቡ ዶሮዎች ከ150-200 ብር ሲሸጡ፤ እንቁላል ከ3ብር  እስከ 3ብር ከ50 ሣንቲም በመሸጥ ላይ ነው፡፡
በሾላ ገበያ የሸኖ ቅቤ ለጋው 350 ብር፣ መካከለኛው 280 ብር፣ የበሰለው ደግሞ 260 ብር ይገኛል፡፡ ከ50 በመቶ በላይ የዋጋ ንረት የታየበት የዘንድሮ የበዓል ገበያ፤ በጣም የተቀዛቀዘ መሆኑን ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች ገልፀዋል፡፡
በሾላ ገበያ ዶሮዎችን በመነገድ የሚተዳደረው ደረጀ ያለው እንደ ገበያተኛው ፍላጐት ዶሮዎች አርዶና በልቶ አልያም ከነ ነብሳቸው ይሸጣል፡፡ ከ13 አመት በላይ በስራው መቆየቱን የገለፀልን ደረጀ፤ የበዓል ገበያ ትዕዛዝ ያጨናንቀው እንደነበር አስታውሶ፤ አሁን ግን ገበያው መቀዛቀዙን ተናግሯል፡፡
ለበዓል ሸመታ ወጥታ ያገኘናት እቴነሽ የተባለች የቤት እመቤት ከአንድ ሳምንት በፊት 12 ብር የገዛቸውን የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርት፣ አሁን በ18 ብር መግዛቷን በመግለጽ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲህ አይነት ለውጥ አልጠበቅኩም ነበር ብላለች፡፡
በሾላ ገበያ  የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርት 18 ብር ሲሸጥ፣ በአትክልት ተራ ደረቁ 18 ብር፣ እርጥቡ 15 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የሀበሻ ቀይ ሽንኩርት ደግሞ በኪሎ 30 ብር ይገኛል፡፡ በአትክልት ተራ ደግሞ 27 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ነጭ ሽንኩርት አንድ ኪሎ 65 ብር ሲሆን፤ ዝንጅብል በኪሎ ከ70-80 ብር እየተሸጠ ነው፡
አንድ ሊትር የታሸገ የውጪ ዘይት 80 ብር ሲሆን የኑግ ዘይት 55 ብር በሊትር ይገኛል፡፡  
የስንዴ ዱቄት (ፉርኖ) እንደ ዱቄቱ አይነት ዋጋው የሚለያይ ሲሆን የአንድ ኪሎ ዱቄት ዋጋ ከ24-25 ብር እንደሚደርስ በቅኝታችን ለማወቅ ችለናል፡፡ 

Read 3260 times