Saturday, 27 April 2019 10:50

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግሮችና ተግዳሮቶች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ - በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ማዕከል፣የጂኦፖሊቲክሰና ሶቫል ጂኦግራፊ ፕሮፌሰር


                 የዛሬ አንድ አመት ገደማ ከኢሕአዴግ ውስጥ ፈንቅሎ የወጣው ኃይል (implosionary force) ለኢትዮጵያ ትልቅ እድልን ፈጥሮላታል:: የለውጥ ኃይሉ አገሪቱን ወደ ገደል ጫፍ እየገፋት የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት እንዲረግብ ያስቻሉ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ እነኚህ ድሎች በተለያዩ ሚዲያዎች በተደጋጋሚ እየተዘከሩ ስለሆነ እዚህ መዘርዘሩ አስፈላጊ አይመስለኝም:: ሥልጣኑ፣ ቢሮክራሲው፣ መከላከያው፣ ደህንነቱ፣ ሐብቱ በተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች በሞኖፖል ተይዞ በነበረበት ሁኔታ እነኚህ እርምጃዎችና ስኬቶች ካለምንም እንቅፋት ይጓዛሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ በኔ እይታ ለውጡ አሁን ከምናየው በላይ ብዙ መሰናክሎችና ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙት ይችሉ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች አገሪቷ መስቀለኛ መንገድ (cross-road) ላይ ነች የሚሉት፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸውን ውስብስብ ሁኔታዎች አቅልሎ በማየት ወይም ባለመጠበቅ እንዲሁም የለውጡን ውጤቶች አሁኑኑ ለማየት ከመጓጓት የተነሳ አላስፈላጊ ንትርክና ግጭቶች ውስጥ ለመግባት ተገደናል፡፡ ለውጥ ሂደት (process) ስለሆነ ሰፋ ያለ ጊዜና ትዕግስትን ይጠይቃል:: ‹ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም› እንደሚባለው ሁሉ ሁሉም የሚመኛትና የሚፈልጋት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያም በአንድ ጀምበር ልትፈጠር አትችልም፡፡ የለውጥ ኃይሉን ቢያንስ ጊዜ በመስጠት ካላገዝነው፣ ለውጡ በሚፈለገው ጊዜና በለውጥ ኃይሉ ላይ በሚደረገው ጫና ምክንያት የሚፈጠረው ክፍተት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይወስደን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ወደፊት ልናያት የምንፈልጋትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብና ቁመና ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ቁመና የታነፀ እይታ (vision) ከሌለን ወደኋላ ተንሸራተን ወደጀመርንበት ቦታ ላይ እንመለሳለን (back to square one)፡፡ ይህንን ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይ ደግሞ ይህ ለውጥ እንዲመጣ የታገሉ ወጣቶች ማየት የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡
የለውጥ ኃይሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አለመቻል፣ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ሃገሪቷን ከራሳቸው ዓላማ በላይ ማየት ባለመፈለጋቸው/ባለመቻላቸው አገሪቱን አደጋ ላይ መጣል፣ ወጣቱ የትግሉን ፍሬ አሁኑኑ ለማየት መቸኮል፣ ስልጣን ሳያስቡትና ሳይገምቱት ከጉያቸው ስር አፈትልኮ ያመለጣቸው ኃይሎች አርፎ ያለመተኛት አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም አድርጓታል:: ከዚህ ውስብስብ ሁኔታና አጣብቂኝ ለመውጣት የፖለቲካ ቡድኖች፣ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ቆም ብለው በጥሞና ማሰብ ይጠበቅባቸዋል:: ይህ ካልሆነ ሁሉም ተሸናፊ የሚሆንበትና ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ሁኔታ (lose-lose situation or zero-sum game) ውስጥ እንገባለን፡፡
በእኔ እይታ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያጋጠሟትን ችግሮችና ተግዳሮቶች በሚከተሉት ዋና ዋና ጉዳዮች ከፍዬ ለማየት እሞክራለሁ፡፡
1. ማህበራዊ ሚዲያውን (ፌስቡክ ወዘተ) አግባብ ባልሆነ መንገድ አፍራሽ ለሆኑ ተግባራት መጠቀም
የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ብዙ አገሮችንም እያተራመሰ ይገኛል:: በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የማይወጣ አሉባልታ፣ በሬ ወለደ የሚል የፈጠራ ወሬ፣ የተሳሳተ ዜና እና የግልና የቡድን ስሜት የለም፡፡ አፍራሽ ማህበራዊ ሚዲያዎች ዘዴ ካልተፈጠረላቸው እሳት ለመጫርም ሆነ ነዳጅ ለመጨመር እድሉ እንዳላቸው መታወቅ አለበት፡፡ የፌስቡክና የመሳሰሉትን አፍራሽ ተግባራት ለመቀነስና ለመቆጣጠር ራሱን የፌስቡክን ኩባንያ ትብብር መጠየቅ ይቻላል ወይንም የኢትዮጵያ መንግስት አቅሙን አዳብሮ ቁጥጥር ማድረግ መቻል አለበት፡፡
ፌስቡክ የራሱ ሕግ አለው፡፡ ለምሳሌ አንደኛው ሕግ እንዲህ ይላል - ‹‹ግለሰቦችና ድርጅቶችን ለማጥቃት የሚቃጡ፣ ጥላቻ የሚያስፋፉ እና የማይፈልጓቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲገለሉ የሚያደርጉ በፌስቡክ ቦታ የላቸውም›› ፌስቡክ እንዲህ አይነት ድርጅቶችና ግለሰቦችን አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ አክራሪዎችን የሚያደንቁና የሚደግፉ ግለሰቦችና ቡድኖች አገልግሎቱን እንዳያገኙ ያግዳል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከሰሞኑ 12 የሚሆኑ የእንግሊዝ ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ላይ ፌስቡክ ማዕቀብ ጥሏል፡፡ አንድ ሦስቱን ለመጥቀስ ያህል ብሪቲሽ ብሔራዊ ፓርቲ (British National Party)፣ የእንግሊዝ መከላከያ ሊግ (The English Defence League) እና ብሔራዊ ግንባር (National Front) ይገኙባቸዋል፡፡
 2. አዲስ አበባ ‹የኔ ነች› ‹ያንተ አይደለችም› የሚለው ጊዜውን ያልጠበቀና ብዙ ነገሮችን ያላገናዘበ ንትርክ
በኔ እይታ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ታሪክ፣ አፈ-ታሪክ፣ ትርክትና ቀዶ ጥገና የተካሄደበት ታሪክ (doctored history) ተደባልቀው ነው ሕዝቡን ግራ እያጋቡ ያሉት፡፡ አሁን ብዙ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እያሉ ለምን የአዲስ አበባ ይገባኛል ጥያቄ አሁን እየተነሳ መሆኑ ያጠያይቃል፡፡ የሽግግር ጊዜው አልፎ፣ አገር ተረጋግቶ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ከተካሄደ በኋላ በሰከነ መንፈስ ተረጋግቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያቀፈ ውይይት አካሂዶ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
3.ጋዜጠኝነትና ፖለቲካ ተንታኝነት በተሳሳተ መንገድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆን
እነኚህ ሁለት የተለያዩ ሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተደበላልቀዋል፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ (journalism) እና ፖለቲካዊ ተንታኝነት (political analyst) የሚገናኙበት ነገር ቢኖርም ራሳቸውን የቻሉ ሙያዎች ነው፡፡ ለዚህም ነው በዓለም አቀፍ ዜና አውታሮች (CNN, Al Jazeera, BBC ወዘተ) የሚሰሩ ጋዜጠኞች የተለያዩ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ሲኖሩ የተለያዩ ፖለቲካ ተንታኞችን እያቀረቡ የሚያወያዩት፡፡ ይህ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ላለፈው አንድ ዓመት የማየው ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆኑ ሙያቸው ከፖለቲካ እውቀት ራቅ ያሉ ሰዎች ሁሉ ተንታኝ ሆነው የተሳሳተ ትንተና ሲሰጡን ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ፖለቲካ ተንታኞች ስላልሆኑ ወገንተኝነት ያጠቃቸዋል እንዲሁም ትንተናቸው ሚዛኑን ያልጠበቀ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የሆነ ውዥንብር ይፈጥራል፡፡ ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት የተለያዩ አቅጣጫዎችን የማየት እድል ቢኖራቸውም ከሙያቸው የሚጠበቀው ሚዛናዊነት እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች ከወገንታዊንት የነፃ ሂሳዊ ድጋፍ (critical support) ቢሰጡ ለአገርም ለሕዝብም ይጠቅማል እላለሁ፡፡
4. የለውጡ ኃይሉ ዋልታ በረገጡ ኃይሎች መሃል መገኘት
ሃገሪቱን እየመራ ያለው ኃይል ከተወጠረባቸው ችግሮች አንዱ ይመሯቸው ከነበሩት ክልሎች ሳይቀር በተለያየ አቅጣጫ እና ሊታረቁ የሚችሉ በማይመስሉ አስተሳሰቦች መሀል መገኘት ነው፡፡ ገሚሱ ‹ለውጡ ተቀልብሷል› ሲል ሌላው ‹ቀድሞውንም ከዘር ስሌት የማይወጣ ጅምር ነበር ይላል››:: የፖለቲካ ሂደት ነውና የለውጥ ሃይሉ ይህን መሰል ጉዳዮች አይጠብቅም ነበር ብሎ መናገር ስህተት ይመስለኛል፡ ዋናው ጉዳይ ግን ጫፍና ጫፍ ተይዞ የሚጎተት ነገር ላለመበጠሱ ዋስትና ስለሊለው የለውጥ ሃይሉን ሂሳዊና ገንቢ ድጋፍ (critical support) ብንሰጠው::
5. የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ (genocide) ባስተማሪነቱ ሳይሆን ‹እኛም ወደዛ እየሄድን ነው› ‹አገሪቷ እንደአገር መንቀሳቀሷን አቁማለች› (failed state ሆናለች) የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች መፈጠር (doom and gloom የሚሰብኩ)፡-
እነኚህ እሳቤዎች እጅግ አሳሳቢ ናቸው:: በአስተማሪነታቸው ቢጠቀሱ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ከ800,000 እስከ 1 ሚሊዮን ሕዝቦችን ሰለባ ያደረገውን የሩዋንዳውን ዘር ማጥፋት በኢትዮጵያ ሊደገም ነው/ይችላል እያሉ ማነፃፀሪያ የሚያቀርቡ ሰዎች አንድ ነገር ከማለታቸው በፊት ሁለቴ ቢያስቡ የተሻለ ነው እላለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ጨለምነተኝነትን በቋፍ ላይ ባለችው አገራችን ላይ መለጠፍ አንድምታው ጥሩ አይሆንም፡፡
በዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው ጊዜ በሩዋንዳ የነበረው ሁኔታና አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በብዙ መልኩ አይመሳሰሉም፡፡ ሩዋንዳ ውስጥ የቤልጅየም ቅኝ ገዥዎች ቀብረውት የሄዱት ፈንጂ ነው እ.ኤ.አ በ1994 በመፈንዳት ያን ሁሉ ሕዝብ ሰለባ ያደረገው፡፡ የቤልጅየም ቅኝ ገዥዎች የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ሁቱዎችንና ቱትሲዎችን ለመከፋፈል ይረዳቸው ዘንድ የፊት ቅርፅን በመሳል፣ የአፍንጫ ስፋትንና የከናፍር ውፍረትን በመለካት ሁቱ፣ ቱትሲ እያሉ መታወቂያ ያድሉ ነበር፡፡ በኋላ በዘር ማጥፋት ዘመቻው ጊዜ ላይ እንደታየው ያ የብሔር ማንነትን የያዘ መታወቂያ ብዙ ቱትሲዎች እንዲታረዱ አድርጓቸዋል፡፡
እርግጥ ነው እኛምጋ ሕዝቡ የተጣመረባቸውን ማህበራዊ እሴቶች (social capital) ጭምር የሚፈታተኑ ንግግሮችና አቅጣጫዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህን ለመግታት ሩዋንዳን መደጋገም አስተማሪ አይሆንም፡፡ ሌሎች ገንቢ የሆኑ ሂደቶች ለምሳሌ ያህል የሕዝቡን ባህልና ልምዱን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ይጠቅማል፡፡ እንደኔ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ምን እንደሚመስልና መዘዙ ምን ያህል የከፋ መሆኑን ለማስገንዘብ የተወሰኑ የዘር ማጥፋቱን ዘመቻ የሚያሳዩትን እትሞችን ተርጉሞ ማቅረቡ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል ካናዳዊው ጀነራል ዳሌር (General Dallaire) በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ጊዜ የUNAMIR (UN Assistance Mission for Rwanda) ኮማንደር የነበሩት የፃፉት መጽሐፍ በኋላ ፊልም የሆነው - ‹‹Shaking Hands with the Devil›› እንዲሁም ‹‹Ghosts of Rwanda›› የሚለው ፊልም በማስተማሪያነቱ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡
6. የአገሪቱ ጤናማ ያልሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታና የሥራ አጥነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር
የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እንዲሁም ወደ ከተሞች በተለይም ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ ጤናማ ኢኮኖሚ እንዲኖረን ከተፈለገ እንዲሁም ወጣቱ ሥራ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ካሰብን አገሪቷ መረጋጋት አለባት፣ ሰዎች በፈለጉበት ቦታ ሄደው መስራት መቻል አለባቸው፣ ማንም ሰው ካለስጋት ጠዋት ወጥቶ ወደ ሥራ መሰማራት ማታ ካለስጋት ወደቤት መግባት መቻል አለበት፣ አገሪቷ ኢንቨስተሮችን መሳብ የምትችል መሆን አለባት፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች በጥሩ ሁኔታ ላይ ስላልነበሩ ኢኮኖሚው ተዳክሟል፣ የዋጋ ግሽበት (inflation) እና የኑሮ ውድነት (cost of living) ወደላይ አሻቅበዋል፡፡ መንግሥት እነኚህ ነገሮችን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አገር ማረጋጋትንና ሕግ ማስከበርን ተግባራዊ ካላደረገ ኢኮኖሚው የባሰ ዘጭ ይላል፤ እንዲሁም ሥራ አጥነቱ ያሻቅባል፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሕዝብን ወደ አመፅ ሊመሩ ይችላሉ፡፡
7. ዞኖች ክልል እንሁን የሚሉበት ሁኔታ መፈጠር
እንደኔ እይታ ፌዴራሊዝም በራሱ ችግር የለውም፡፡ በቅርብ የማውቃቸው አገሮች - ጀርመንና ስዊዘርላንድ - የፌደራሊዝም አወቃቀራቸውና አተገባበራቸው በጥናትና ልምድ ላይ (በእውቀት ላይ) ተመርኩዞ ስለትሰራ ሕዝቡም እድል ተሰጥቶት ተሳታፊ አንዲሆን ተደርጎ ስለነበር አገሮቹ በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመውበታል እየተጠቀሙበትም ነው:: የእኛው አገር ብሔር-ተኮር ፌደራሊዝም አላማውም፣ አወቃቀሩም፣ አተገባበሩም ችግር ያለበት ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ለመቆየትም ያገለገለም ይመስለኛል፡፡ አወቃቀሩም ግራ ያጋባል - ብዙዎቹ የአገራችን አካባቢዎች ቋንቋን ማዕከል ያደረገ የፌዴራሊዝም አወቃቀር ሲኖራቸው የደቡብ ክልል ግን መልክአምድርን ታሳቢ አድርጎ የተዋቀረ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሲዳማን የሚያክል በሕዝብ ብዛትም ሆነ በቆዳ ስፋት ከብዙ ክልሎች የማያንሰውን አካባቢ የፌደራል አወቃቀሩ ዞን ሲያደርገው ትንሽዋን city-state ሐረሪን ደግሞ ክልል አድርጓታል፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም አወቃቀር እርስ በራሱ የሚጋጭና አንድ ወጥ ያልሆነ ነው:: አተገባበርና በጀት አመዳደቡም ላይ ከፍተኛ ችግር ያለውና ብዙ ጥያቄዎችን የሚጭር ነው:: ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ‹ሲዳማ› እና ሌሎችም በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖች ክልል እንሁን ብለው ቢጠይቁ የሚያስደንቅ አይመስለኝም:: እንዲያውም ወደፊትም ቁጥራቸው እየጨመረ ሊሄድ ይችላል፡፡ አሁን ትልቁ ችግር የአንዱ ጥያቄ በተመለሰበት ሁኔታ ሌላው ባይስተናገድ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ማሰብ አለብን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ላለፉት 25 ዓመታት የደቡብ ክልል ርዕሰ ከተማ ሆኖ ያገለገለው ‹የሃዋሳ ጥያቄ› በምን ሁኔታ እንደሚስተናገድ ካሁኑኑ ማሰብን ይጠይቃል:: ‹ምን መሆን አለበት› እና ‹የት› የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ብዙ ስራ ይጠብቀናል፡፡ እንደኔ ‹ክልል› የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ራሱ አግላይ (exclusionary) ነው፡፡ አሁን የሚታየው ‹የኔ› እና ‹ያንተ› ጣት መጠቃቆም እና ‹የውጡልኝ› ጥያቄ የዚህ ሰንካላ ፅንሰ-ሐሳብ ውጤት ነው:: ይህ ራሱ በፅኑ ታስቦ መስተካከል አለበት እላለሁ፡፡
8. ወደኋላ እያዩ ወደፊት ለመሄድ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መኖር
እንደሚታወቀው በታሪክ በዓለም ላይ የተለያዩ ነገስታትና መሪዎች አገር ለማስፋፋት ሲፈልጉ፣ ቅኝ ገዥ ለመሆኑ ሲመኙ፣ ኃያልነታቸውን ለማሳየት ሲፈልጉ ወዘተ በሰው ልጆች ላይ የተለያዩ በደሎችን ፈፅመዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ እንኳን ደቡብ አፍሪካ ከጫንቃዋ ላይ የጣለችው የአፓርታይድ አገዛዝ በጥቁሮች፣ በሕንዶችና ‹ከለርድ› በሚባሉ ክልሶች ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍና በደል ለብዙ ዘመናት ፈፅሟል፡፡ ይህን ያየ ከአፓርታይድ ፍፃሜ በኋላ ጥቁሮች ከነጮች ጋር በሰላም ይኖራሉ ብሎ ለማሰብ አዳጋች ነበር፡፡ ግና ሆኗል የኋላውን ትተው ይቅርታ በመጠያየቅና በመቻቻል አበረው እየኖሩ ነው፡፡
ምንም እንኳን ባሁኑ ጊዚ የትኛው ትክክለኛ ታሪክ፣ የትኛው አፈታሪክ፣ የትኛው ትርክት፣ የትኛው ቀዶ ጥገና የተደረገለት ታሪክ መሆኑን ለመለየት አዳጋች ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥም አነሰም በዛም በታሪካችን ችግሮች እንደነበሩ መካድ አይቻልም:: ትልቁ ነገር ከኋላው ታሪካችን ተምረን፣ ስህተቶች እንዳይደገሙ መተማመን ላይ ደርሰን ማየቱ ብቻ ነው ለአገሪቷም፣ ለሕዝቧም የሚበጀው እላለሁ፡፡
ፀሐፊውን በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ኢ-ሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡፡  

Read 3351 times