Saturday, 27 April 2019 10:27

የአጥንት መሳሳትና የወር አበባ መቋረጥ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 በእንግሊዝኛው Osteoporosis በመባል የሚታወቀው የአጥንት መሳሳት በሽታ በተለይም በሴቶች ከወር አበባ መቋረጥ menopause ጋር ተያይዞ የሚያስከትላቸውን ችግሮች የተለያዩ በዚህ ዙሪያ የተሰሩ ጥናታዊ ስራዎች ያሳያሉ፡፡ ዌብ ሜድ የተሰኘው ድረ ገጽ ለንባብ ያለውን ታነቡ ዘንድ በዚህ እትም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ከላይ በስተግራ የምትመለከቱዋቸው የሳሱ አጥንቶች ስእል ነው፡፡ በስተቀኝ በኩል ያሉት ሰዎች ስእል ደግሞ አጥንት እየሳሳ ሲሄድ ሰዎች እንዴት እየጎበጡ እንደሚሄዱ የሚያሳይ ነው፡፡
የአጥንት መሳሳት ሲባል ከውጭ በኩል በቀላሉ በአይን የሚታይ ምልክት የሌለው ሲሆን የውስጥ የአጥንት ምስል ግን ልክ በስእሉ እንደሚ ታየው የተቦረቦረ ሽክላ ይመስላል:: አጥንቱ በተፈጥሮው የነበረውን ወጥ የሆነ ወይንም ጥቅጥቅ ያለ አካል በማጣት በስእሉ ላይ እንደምትመለከቱት የተፈረፈረ ሲመስል በዚያው ልክ ጥንካሬውን ያጣል:: በዚህም ምክንያት ሰዎች በቀላሉ መውደቅ፤ መሰበር፤ ወይንም የአጥንት መሰንጠቅ የመሳሰሉት ይደርስባቸዋል:: የአጥንት መሳሳት አጥንቱ አቅም አጥቶ በመዳከም የሚያስከትለው የመውደቅ የመሰበር አደጋ ሲከሰት ካልሆነ በስተቀር አስቀድሞ ሕመሙን ለይቶ ማወቅ የሚቻልበት መንገድ የለም:: ችግሩ የሚከሰተው ሽንጥ፤ ዳሌ፤ የጀርባ አጥንት ላይ ሲሆን እነዚህ አካላት ላይ መውደቅን ተከትሎ የሚደርሰው ችግር የከፋ ነው፡፡ የአጥንት መሳሳቱ በእግር አጥንት ላይ በመሳሰሉት ሁሉ ሊከሰት ይችላል፡፡ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የአጥንት መሳሳት ችግር ሲደርስባቸው ከጀርባቸው እየጎበጡ እያጎነበሱ የመሄድ ሁኔታ እየዋለ እያደረ ይከሰትባቸዋል፡፡
የአጥንት መሳሳት ከወር አበባ መቋረጥ ጋር እንዴት ይያያዛል?
menopause እና Osteoporosis እንዴት ይያያዛሉ ለሚለው በጋራ የተቀመጠላቸው ምክንያት ኢስትሮጂን የተሰኘው ንጥረ ነገር መመረት አለመመረት ነው:: ኢስትሮጂን የወር አበባ ከመቋ ረጡ በፊት ማለትም ሴትየው እድሜዋ 45- አመት ሳይሞላት ሰውነት በሚያስፈልገው መጠን ይመረት የነበረ ሲሆን እድሜዋ ሲደርስ ግን የሆርሞን መጠኑ ስለሚያንስና ንጥረ ነገሩም መመ ረቱ እየቀነሰ ስለሚሄድ ተያይዞ የአጥንት ጥንካሬ እየሳሳ እየደከመ ይሄዳል፡፡
የአጥንት መሳሳት በሕክምና ባለሙያዎቹ አጠራር ድምጽ ሳያሰማ የሚከሰት ወይንም የሚኖር ሕመም ነው:: ምልክቱ ይህ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ሰዎች አጥንታቸው የመሳሳት ችግር እንደደ ረሰበት እና ሕመም ላይ እንደሆኑ የሚረዱት በመውደቅ ምክንያት እንደመሰበር ያለ አደጋ ሲደር ስባቸው እና በሕክምና ባለሙያዎች ሲገለጽላቸው ነው፡፡ ከመሰበር ውጭም ከፍተኛ የሆነ የጀርባ ሕመም ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ የቁመት ልክ መቀነስ ወይንም ቀድሞ የነበረ የሰውነት አቋም ወይንም ቅርጽ ሊለወጥ ይችላል፡፡
የአጥንት መሳሳትም ሆነ የወር አበባ መቋረጥ በተለይ ሴቶችን ሊያገኙዋቸው ይችላሉ የሚባል ባቸው ምክንያቶች እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
እድሜ፡- አጥንት የመኖር፤ የማደግ፤ የመጠንከር ባህርይ በየዘመኑ እያሳየ ምናልባትም እስከ   ሰላሳ አመት ሊቆይ ይችላል፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን ለማደግ ወይንም ለመጠንከር የሚያደርገውን ጥረት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
ጾታ፡- ሴቶች በእድሜያቸው ከ50-አመት በላይ ሲሆኑ ለአደጋው ተጋላጭነታቸው ያይላል፡፡ ሴቶች በሕመሙ ለመጠቃት ከወንዶች ይልቅ አራት እጥፍ ደረጃን ይይዛሉ:: ሴቶች በተፈጥ ሮአቸውም አጥንታቸው ሳሳ፤ ቀጠን ያለ አጥንት ያላቸው ስለሆነ ለአደጋው ተጋላጭነታቸው የሚያይልበት ምክንያት ተደርጎ የሚወሰድባቸው ምክንያቶች መሆናቸውን ጥናቶች ያብራራሉ፡፡
ዘር፡- የአጥንት መሳሳት ችግር መብዛት ማነስ በትውልድ አካባቢ እና በዘር ሁኔታም ሊወሰን እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ለምሳም የኤሽያ ሴቶች ይበልጥ በአጥንት መሳሳት ተጎጂ እንደሚሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአጥንት አፈጣጠር እና የሰውነት ክብደት፡- ሌላው ለአጥንት መሳሳት ምክንያት እንደሚሆን የሚጠቀስ ነው:: ሴቶች ሰውነታቸው ከበድ የሚል እና የሰውነታቸው አፈጣጠር ተለቅ ያለ ከሆነ አጥንት መሸከም ግዴታው ስለሆነ እግረ መንገዱን እንዲጠነክር ያግዘዋል፡፡ አጥንቶቻቸው ቀጫ ጭን የሆኑ ሰዎች ግን ለችግሩ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፡፡  
የቤተሰብ ታሪክ፡- ለአጥንት መሳሳት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል  የቤተሰብ ታሪክ አንዱ ነው፡፡ ወላጆች ወይንም አያት ቅድመ አያቶች የአጥንት መሳሳት ችግር ይታይባቸው ከነበረ ልጆቻቸውም ጊዜውን ጠብቆ ሊይዛቸው እንደሚችል አስቀድሞ ማወቅ ይገባል፡፡
በሕመም ምክንያት ካንሰርን ጨምሮ የሚወሰዱ አንዳንድ መድሀኒቶች፡- እንደነዚህ ያሉ መድሀ ኒቶች የአጥንት መሳሳት ችግርን ሊያባብሱ ወይንም ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሴቶች እድሜ ያቸው 65-እና ከዚያ በላይ ሲሆን በተለያዩ ማለትም ለችግሩ ሊያጋልጡ በሚችሉ የአኑ ዋኑዋር ሁኔታዎች ውስጥ ካሉ ለችግሩ ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡ የወር አበባ የተቋረጠባቸውና የአጥንት መሰንጠቅ ደርሶባቸው የነበሩ ሴቶች ከአመጋገብም ሆነ የሰውነት አካል ማጠንከሪያ እንቅስቃሴ በማድረግ አስቀድመው መከላከል እና ስጋቱን መቀነስ ይችላሉ፡፡
የአጥንት መሳሳት ችግርም ሆነ  ከወር አበባ መቋረጥ ጋር በተያያዘ የጤና እውክታ ለሚደር ስባቸው ሴቶች የተለያዩ የህክምና ዘዴዎች መኖራቸውን ጥናታዊ ስራዎች ያብራራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች መመረት ያቆመውን ኢስትሮጂን የተባለ ሆርሞን በሕክምና ለመውሰድ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ግን ለአጥንት መሳሳት ነው ወይንስ ለወር አበባ መቋረጡ የሚለውንና ለአንደኛው ብቻ መድሀኒቱ ቢወሰድ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ ከሕክምና ባለሙያ ጋር መነጋገር ግድ ይሆና ል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን በአመጋገብና በተለያዩ መንገዶች አካልን በመጠበቅ ችግሩ እንዳይፈጠር ወይንም ከተፈጠረም በሁዋላ ቢሆን ጉዳቱን ለመቀነስ የሚቻልባቸውን መንገዶች ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፡- በቋሚነት የሰውነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ፕሮግራም ማዘጋጀት ይገባል:: የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጡንቻዎችንና አጥንትን ጠንካራ ለማድረግ ችግሮች እንዳ ይደርሱም ይረዳል:: ሰውነት ቀለል እንዲልና ጤናማ ሆኖ  እንደፈለጉት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲቻል ሰውነት በፈለጉት መንገድ እንዲታዘዝም ያግዛል፡፡  
አመጋገብ፡- በካልሲየም የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ አጥንት ጠንካራ እንዲሆን ስለሚረዳ የአጥ ንት መሳሳት እንዳይኖር ይረዳል፡፡ በተለይም የወር አበባ መቋረጥ እድሜ ላይ ለደረሱ ሴቶች በየቀኑ ካልሲየም ያላቸውን ምግቦች ማለትም ወተት እና የወተት ውጤቶች የሆኑ መግቦች፤ እንደ ሰርዲን የመሳሰሉ የአሳ ምግቦች፤ አረንጉዋዴ ቅጠላቅጠሎች፤ ብሮኮሊ፤ ብርቱካን እና ከካልሲየም ውጤት የተዘጋጁ ዳቦዎችን መመገብ ጠቃሚ ነው፡፡
ቫይታሚን ዲ የተሰኘው አጥንትን የሚያጠነክረው ከምግብ ብቻም ሳይሆን ከፀሐይ ብርሀን ስለሚገኝ በቀን ቢያንስ ለሀያ ደቂቃ ማግኘት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
እንደ አልኮሆል እና ሲጋራ የመሳሰሉ ነገሮችን መጠቀም ላይ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ የዚህም ምክንያት የአጥንትን ጤንነት የሚጠብቀው ኢስትሮጂን የተባለው ሆርሞን በበቂ እንዳይመረት ስለሚያደርግ ነው፡፡ አልኮሆልን በብዛት መጠቀም አጥንት ጥንካሬውን እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ውጭ አንዳንድ በምግብ መልክ ለድጋፍ የሚሰጡ እንደ ካልሲየም፤ ኢስትሮጂን፤ የመሳሰሉትን ለመውሰድ ሐኪምን ማማከር ይገባል፡፡

Read 8873 times