Saturday, 27 April 2019 10:13

ህይወት ሳይሳከር እንዲሰምር (በፀጋዬ ግጥም መነፅር)

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

 የግጥሙ ውበት ወይም ልዕልና ከርዕሱ ይጀምራል፡፡ “መሸ ደሞ፣ አምባ ልውጣ” ይላል ርዕሱ፡፡ በአንድ ምሽት ውስጥ ብዙ ምሽቶችን ሰንቆ፣ በአንድ ድርጊት ውስጥ የዘወትር የኑሮ ምህዋር አቅፎ፣ ከነስሜቱና ከነክብደቱ፣ በእውን ብልጭ እንዲልልን የሚያደርግ ድንቅ ርዕስ ነው፡፡  እውነት ነው፣ በአንድ በኩል፣ የዛሬው ምሽት ላይ ነው ቁምነገሩ ወይም ጉዱ፡፡
ነገር ግን፣ ከዚያም በላይ የጠነከረ ወይም የከበደ ነገር ነው ጉዳዩ፡፡ ደርሶ ዛሬ ብቻ የተከሰተ ተራ አጋጣሚ፣ ወይም በአንድ ምሽት የሚያበቃለት አላፊ ጉዳይ አይደለም፡፡
አዎ፣ እንደ አዲስ ድንገት ደራሽ እና እንደ ዱብዳ አጣዳፊ ገጠመኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ድንገተኛነቱ እለት በእለት ደራሽ፤ አጣዳፊነቱም በየምሽቱ እየቀሰቀሰ ከጨለማና ከአቀበት ጋር የሚያታግል ነው፡፡ የዘወትር የኑሮ ምህዋር፣ ከሰብዕና ጋር የተዋሀደ የሕይወት ቀመርና ድምር ሆኗል፡፡
እንደ ድንገተኛ ውጋት አጣዳፊ የመሆኑን ያህል፣ እንደቁራኛም ስር ሰድዶ የከረመ የሕይወት ጣዕም ወይም ፅኑ ህመም ነው፡፡ ሻል ሲል ያመለጡት የተገላገሉት፣ ረገብ ሲል ያመለጠና የተከለለ ይመስላል፡፡ ግን መሰረቱ እየፀና ወይም ስር እየሰደደ፣ የአንድ ምሽት ብቻ ሳይሆን የምሽቶች ሁሉ ጉዳይ ወይም ጉድ ሆኗል … በየእለቱ “መሸ ደሞ” የሚያስብል አይነት፡፡
መሸ ደሞ፣ አምባ ልውጣ!
አምባ ወጥቼ እኩለሌት፣ ስለት ገብቼ በስሟ፣
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፣ ልገላገል ከህመሟ፣
“መሸ ደሞ” ያለው፣ አለምክንያት አይደለም፡፡ የከረመ ነው ነገሩ፡፡ “ልገላገል ከህመሟ” ብሎም ነው አምባ የሚወጣው፡፡ ብርቱ ሕመም ቢሆንበት ነው፡፡
ህመሟ ቢበረታበትም ግን አይወቅሳትም፡፡ ሰይጣን ነው ያሳተኝ ይላል - ራሱንም እሷንም ነፃ ለማውጣት፡፡ በዚያ ላይ ከህመሟ ለመገላገል ስለት የገባው፣ በሷ ስም ነው፡፡
መላ በሚያሳጣ ጉዳይ የተያዘ ይመስላል፡፡ ከህመሟ ለመገላገል፣ ከሷ ለመለየትና ለመራቅ … ወደ አምባ ያወጣል፡፡ ግስጋሴው ግን፣ የሚወጣው፣ እሷው ዘንድ ለመድረስ ነው - ከአጠገቧ ለመሆን .. ከሷ ጋር ለመገናኘት፡፡ በውድቅት ሌሊት አቀበት ቁልቁለት የሚታገለው ከህመሟ ለመላቀቅ እንደሆነ ያስባል፡፡ በተግባር ግን የማታ ማታ ግስጋሴው አብሯት ለመታደምና ለማጣጣም ነው፡፡ ግጥሙ እንዲህ ይላል፡፡  
ጠበሏ አፋፍ፣ በጨረቃ፣ ደጋግሜ፣ ማሕሌት ቆሜ፣
ደጅ ሰላሟን፣ ባራት እግር፣ ተንበርክኬ፣ ተሳልሜ
ሆዴ ቃትቶ ባርባር ብሎ፣ እርቃኔን ከሷ ታድሜ
በስጋዬ እሚነደውን፣ በፀሎት ላቤ አጣጥሜ …
ይላል ግጥሙ፡፡ ይሄ፣ እፁብ ድንቅ ዓለም፣ ያማረ የለመለመ ደማቅ ሕይወት ነው፡፡ ታዲያ፣ እንዲህ እጅግ ከሚያከብረውና ከሚያደንቀው ውብ ዓለም ለመለየት ነው ሃሳቡ? እንዲህ በጣም ከሚሳሳለትና ከሚጓጓለት ድንቅ በረከት ተነጥሎ ለመራቅ ነው ስለቱ ከነፍስና ከስጋው ጋር ባዋሀደ፣ መንፈስና ስሜቱን ባዋደደ፣ በዚህ በውብ ዓለም ውስጥ፣ ውድ የሕይወት ማዕድ ማጣጣም፣ እንደምን ሆኖ እንደ ስህተት ይቆጠራል? ከቶስ በምን ምክንያት፣ “ደሞ መሸ” የሚያስብል የሰቀቀን ሰበብ ይሆናል?
ነፍስና ስጋውን፣ ከሃሳብና ከህሊናው ጋር እየተጋጩ፣ “መለየትን” እና “መገናኘትን” “መገላገልን” እና “ታድሞ ማጣጣምን” እስከማምታታት የደረሰ ሃይለኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡
ለጊዜያዊና ለአላፊ ተራ ስሜት የመሸነፍ አመል ይዞት፣ በዚሁ ግፊት ርካሽ ድርጊት እየፈፀመ ቢሆን ኖሮ፣ ከሃሳብና ከህሊና ሚዛን ጋር መፋለስና መጋጨት መፈጠሩ አይገርምም ነበር፡፡  
በየአጋጣሚው፣ ትናንት ይህችኛዋን፣ ዛሬ ያችኛዋን፣ ነገ ሌላኛዋን እያመጣ፣ እንደ ስካር  አንዷን እያስረሳ ሁለተኛዋን እያቆነጀ የሚያጃጅል፣ ከአንድ ምሽት በላይ የትንኝ ያህል እድሜ የሌለው፣ ተለዋዋጭና መናኛ ስሜት ቢሆን ኖሮ፣ ለትውስታ ያህል የሚቀር ቁምነገር እንኳ አይኖረውም ነበር፡፡ በማግስቱ ቀፋፊ ድብርትን ማከናነብ ብቻ ነው - ቅርሱ፡፡ “ደሞ መሸ” የሚያስብለው ጉዳይ ግን፣ ከዚህ የተለየ ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ የከበደም ነው፡፡
በዛሬው እለት ከህሊና ጋር ሲያታግል የሚውል፣ አመሻሽ ላይ ቁጭ ብድግ የሚያስብል፣ የሚያንጐራድድና በውድቅት ሌሊት ሽቅብ የሚያንደረድር በእለት ብርቱና አጣዳፊ ፈተና ነው፡፡ ግን ደግሞ ዛሬ ምሽት ብቻ ሳይሆን፣ ሳያሰልስ ዘወትር የሚመላለስ ዘወትርም የሚያመላልስ  የኑሮ ምህዋር ሆኗል - ነገርዬው፡፡ ለአፍታ በሚያቅበዘብስ ስሜት ተክለፍልፎ፣ በአፍታ ስሜቱን ሲያስተነፍስ፣ ቀፋፊ ድብርትንና የቆሸሸ አስጠሊታ ስሜትን የመከናነብ ጉዳይ አይደለም፡፡
ይሄማ ፍሬ አልባ ብናኝ ገለባ ነው፡፡ ባዶ፡፡ ልክ እንደዚያው፣  ፍቅር አልባ ወሲብ፣ ብቃት አልባ ማዕረግ፣ ለአፍታ የውሸት ስሜትን መፍጠር ቢችሉም፤ የመቆሸሽ ያህል አስቀያሚ ድብርትን፣ የእዳ ያህል ፋታ የማይሰጥ የስጋት ጓዝን አሸክመው ይጠፋሉ፡፡
እየዋሹ ማሳመን፣ እየሸፈጡ መታመን ለጊዜው ቀላልና አስተማማኝ መንገድ ቢመስልም፣ ሁሌም በጨለማ ውስጥ ብርሃን ብልጭ ባለ ቁጥር እየደነበሩ እንደመኖር ነው፡፡
መሰረተ ቢስ ግንብ፣ ስር አልባ ግንድ … እነዚህ ሁሉ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ በአፍታ ሽውታ የሚፈርሱ፣ የሚጠፋ ናቸው - ፍርስራሽና ብስባሽ እያሸከሙ፡፡
ግጥሙ ውስጥ የምናየው ዓለምና ሕይወትስ?  ከምሽቱ ብርቱ የስሜት ማዕበል በኋላ፤ ውብ መንፈሱ ብን ብሎ ድራሹ አልጠፋም፣ ተንጠፍጥፎ አልደረቀም፡፡ ብርቱው የስሜት ማዕበል ሲረጋ፣ ሰፊ የፍቅር ባህር ተንጣልሎ እንደማየት ነው፡፡ ምስጋናና አድናቆትን፣ አክብሮትና ውበትን የተላበሰ ጥልቅ የፍቅር ባህር ነው በሚታየን፡፡
በሌላ አነጋገር ከፍቅር ባህር የመነጨ ነው የምሽቱ የፍቅር ማዕበል፡፡
እውነትን ከመመስከር የመነጨ ተዓማኒነት፣ እውቀትን ከማስተማር የመነጨ ተሰሚነት፣ ከግል ብቃት የመነጨ አድናቆት፣ ከውጤታማ ጥረት የመነጨ ሀብት … መሰረት የያዙ ነገሮች ብልጭ ብለው አይጠፉም፡፡ ሽው እልም አይሉም፡፡ ወደ አምባ የሚያቀናው፣ በአንዳች አጋጣሚ ሳይሆን፣ ከእለት እለት ኑሮውና ከነፍሱ ጋር በተዋሃደው ሃያል ምህዋር ነው፡፡
ወደ አምባ የሚያቀናው፣ ብልጭ ብሎ ድሹሽ ለሚጠፋ መናኛ ስሜት በመቅበዝበዝ ሳይሆን፣ ከስብዕናው ጋር በተዋሃደ ክብር እና ፍቅር ነው፡፡
የፍቅር ባህር እስካለ ድረስም፣ የስሜት ማዕበል ይኖራል፡፡ ስሜትና ተግባር …ከባህርይና ከስብዕና ጋር ሰምረዋል፡፡ ይሄም ተገቢ ነው፡፡ ውጫዊ ገፅታ ከውስጣዊ ሰብዕና ቢመነጭ ተገቢ ነው፡፡ ሃኪም ለእለት ተእለት ሙያው ቢጓጓ፣ በተግባርም ህክምናን ቢሰጥ፣ ስፖርተኛ በደስታ ስፖርት ቢሰራ … ከዚህም ጋር እንደየብቃታቸው አድናቆትና ክብር፣ ተመራጭና ስመ ጥር ቢሆኑ ተገቢ ነው፡፡
ታዲያ ምንድነው ችግሩ?
የየእለት ስሜቱና ድርጊቱ፣ ከሰብዕናውና ከባህርይው (ከመንፈሱና ከዝንባሌው፣ ወይም ከልማዱና ከአመሉ) ጋር መዛመዳቸው ተገቢ ቢሆንም፣ በቂ ግን አይደለም፡፡
ከእለት ተእለት ሃሳቡና ከእውቀቱ ጋር፣… ከሚያከብራቸው የስነ ምግባር መርሆቹ እና ከጠቅላላ አስተሳሰቡ ጋርም ጭምር … ካልተጣጣሙ ከችግር አያመለጥም፡፡ ይሄው ነው፣ አስቸጋሪ አጣብቂኝ የሆነበት፡፡  
ፍቅሩን፣ በድናቆትና በውዳሴ ይገልጻል፡፡ ግን ደግሞ እንደ ህመም ይቆጥረዋል፡፡
ፍቅሯን ለመታደም ሽቅብ አምባ ይወጣል፡፡ አብሯት ለመታደም ከእልፍኟ ለመግባት፡፡ ግን ደግሞ፣ “ልገላገል ከህመሟ” ይላል፡፡ ከውስጣዊ የፍቅር መንፈስ፣ አካላዊ የፍቅር ስሜት መፈጠሩን እንደ ስህተት ይቆጥረዋል፡፡ … “የቁም ህልም” ነው ብሎ ያስባል፡፡ የደፈረሰና ጤና ያጣ፣ እውነተኛን መንገድ የሳተ ነው ብሎ ስሜቱንና ድርጊቱን ይወቅሳል፡፡
በአጭሩ፣ ሃሳቡና የስነ ምግባረ መርሁ፣ … ከስሜቱና ከድርጊቱ ጋር አይጣጣሙም፡፡
በስጋዬ እሚነደውን በፀሎት ላቤ አጣትሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፣ ውዳሴዋን ደጋግሜ
ገና ከደጇ እልፍ ሳልል፣ ደሞ ይምጣ የቁም ህልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፣ … ነጋ፣ … ደፈረሰ ደሜ
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ። አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል። ባሳር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ። መሸ ደሞ አምባ ልወጣ!
ይላል አስደናቂው የፀጋዬ ግጥም  
ግጥሙ፣ ፍቅርንና ወሲብን ከነሃሳቡ የሚያሳይ ቅኔ ሊመስል ይችላል፡፡ የግጥሙ ውስጠ ሚስጥር (የቅኔው አስኳል፣ ወይም ከግጥሙ ተፈልቅቆ የሚወጣው ወርቅ) በዘይቤ የተሸፈነ ወይም በዘይቤ  ተውቦ የሚያብረቀርቅ የወሲብ ትዕይንት ነው የሚሉም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሄ ግን፣ ግጥሙን በቅጡ ካለመረዳትና የላቀ ውበቱን ካለማየት የሚመጣ ስህተት ነው፡፡
አዎ፣ ወሲብን የሚያመለክት ይዘት አለው፡፡ አዎ፣ ወሲብን ብቻ ሳይሆን የፍቅር መንፈስንም ያሳያል፡፡ አዎ፣ ወሲብንና ፍቅርን ከነሃሳቡ ጭምር አስተሳስሮ፣ ምሉዕ፣ ጉልህና ሕያው ዓለምን ይፈጥራል፡፡ ይሄ፣ የትኛውም ገጣሚ ሊመኘው የሚገባ ድንቅ ብቃት ነው - እንደ ወርቅ የከበረ ጥበብን ፈጥሯልና፡፡  ለፀጋዬ ግን፣
ይሄ እንደ ደጀ ሰላም ነው - ወይም እንደ መግቢያ፡፡ የቅኔው ውጫዊ ውበት ነው ይሄ - የቅኔው ሰም፡፡ ውስጣዊው ውበትና የቅኔው ወርቅ፣ ሰፊና ግዙፍ ነው፡፡
ስነ ምግባር መርህን፣ ተግባርንና ባህርይን፣
ሃሳብን፣ ድርጊንና ስሜት፣
የእለቱን፣ ከዘወትሩና ከዘለቄታው ጋር
ጠብታውን፣ ከጅረቱና ከባህሩ ጋር
በስምረት ተሰናስለውና ተዳምረው፣ አልያም ተሳክረው፣ ተፋልሰውና ተተብትበው በእውን ምንኛ ድንቅ ወይም ምንኛ ፈታኝ፣ እንደሚሆኑ በገለፃ ሳይሆን በጥበብ የሚያሳይ ግጥም ነው፡፡ በግጥሙ እንደምናየው፣ መፋለስና መጣረስ ሲኖር መፍትሔ አለው ወይ ነው ጥያቄው፡፡ አዎ አለው፡፡

Read 1942 times Last modified on Saturday, 27 April 2019 10:23