Saturday, 27 April 2019 09:47

ሲራክ ስዩም ወደ ኤቨረስት ጫፍ ጉዞውን ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)


    • ዋና ካምፑን 5400 ሜትር ላይ አድርጓል፤ ባለፈው ሰሞን 6090 ሜትር ከፍታ ላይ ያለውን ሌቡቼ ተራራን ወጥተዋል፡፡
    • በዋናው ካምፕ የቴዲ አፍሮ እና የሮፍናን ሙዚቃዎች እየተሰሙ ናቸው፡፡
    • የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ፤ ሁለተኛው ምስራቅ አፍሪካዊ እንዲሁም 8ኛው አፍሪካዊ
    • ቀጣይ እቅዱ ፓኪስታን ውስጥ የሚገኘው ኬቱ ተራራ 8,611 ሜትር


          ኢትዮጵያዊው የተራራ ኦሎምፒያን እና የኤሌክትሪካል ምህንድስና ባለሙያ ሲራክ ስዩም   ኤቨረስትን  በሚወጣበት ሙሉ መርሃ ግብር መንቀሳቀስ ከጀመረ ሶስት ሳምንት አልፎታል:: ሲራክ የሚገኝበትና በሳቶሪ አድቬንተርስ እና ኤክስፒዲሽን የሚመራው ቡድን ዋናው ካምፑን 5400 ሜትር ላይ ያደረገ ሲሆን የቴዲ አፍሮ እና የሮፍናን ሙዚቃዎች አጃቢ ሙዚቃዎቻቸው ሆኗል፡፡  የእነ ሲራክ ቡድን ወደጫፉ የሚያደርገውን ግስጋሴ በተለያዩ  ዙሮች  በሚረግጣቸው እና የተለያየ ከፍታ ላይ በሚገኙ ተራራዎችና ካምፖች ላይ በመድረክ ከተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ እየደረሰ አስደናቂውን ጉዞ ቀጥለዋል፡፡ ባለፈው ሰሞን 6090 ሜትር ላይ የሚገኘውን ሌቡቼ ተራራ ረግጠዋል፡፡
ሰሞኑን ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ኤቨረስት ካምፑ ላይ ሆኖ ባደረገው አጭር ቃለምልልስ ሲራክ እንደሚለው ተራራውን በመውጣት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መሆኑን መገንዘቡን ሲሆን ስፖርት አድማስ የተመለከተው የሂማሊያን ዳታ ቤዝም ይህን ታሪኩን አረጋግጦታል፡፡ ሲራክ ስዩም ኤቨረስትን በመውጣት ክብረወሰን የሚያስመዘግበው የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ በመሆን ብቻ አይደለም፤ ሁለተኛው ምስራቅ አፍሪካዊ እንዲሁም 8ኛው አፍሪካዊ ነው፡፡
ኤቨረስትን ለመውጣት ከ10 ዓመት በፊት ማቀዱን ሲራክ ለቢቢሲ ሲናገር “በጣም ደስ የሚል መጽሐፍ አንብበን ስንጨርስ፤ ሌላ ማንበብ እንደሚያሰኘን ሁሉ፤ ተራራ መውጣትም እንደዚያው ነው” በማለት  በኢኳዶር የሚገኘውን ቺምፖራዞን ተራራ ከወጣ በኋላ ተራራ የመውጣት ፍቅር እንዳደረበትም ተናግሯል፡፡
የእነ ሲራክን የኤቨረስት ጉዞ በሚያስተባብረው ሳቶሪ አድቬንቸርስ ኤንድ ኤክስፒዲሽን ዘጠኝ የተለያየ ዜግነት ያላቸው  ሰዎች ማሳተፉን የጠቀሰው የቢቢሲ ዘገባ፤ አብዛኞቹ ተራራውን ከአንድም ሁለት ሶስቴ የወጡ በመሆናቸው ለሲራክም ተጨማሪ ልምድ የማግኘት ዕድልን ፈጥሮለታል ብሏል::  ዘንድሮ በሳቶሪ አድቬንቸርስ እና ኤክስፒዲሽን ኤቨረስትን በመውጣት ላይ ከሚገኙት ተራራ ወጭዎች ሲራክ ስዩም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ከመካከላቸው ይጠቀሳል፡፡ በሌሎች ቡድኖች ኤቨረስትን ከሚወጡት መካከል ትኩረት የሳቡት ለ23ኛ ጊዜ የሚወጣው ካሚ ሪታ የተባለ የኔፓል ሼርፓ፤ ለ14ኛ ጊዜ የሚወጣው እንግሊዛዊ ኬልተን ኩል፤ ያለኦክሲጅን ድጋፍ የምትወጣው ላቲን አሜሪካዊቷ ቪሪዲና አልቫሬዝ  ሌሎቹ ናቸው፡፡
ኤቨረስት ጫፍ ለመድረስ ሲነሳ ከቤት የወጣው ሁለት ትላልቅ ሻንጣዎች መሆኑን ለቢቢሲ አማርኛ የገለፀው ሲራክ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የታሰረበት ከአልሙኒየም የተሰራ የበረዶ መቆፈሪያን ፤ ጫማው ላይ በረዶውን ቆንጥጦ የሚይዝ አስር ሹል ነገሮች ያሉት ብረት፤ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት የሚሰጡ አልባሳት፣ ጓንት እንዲሁም የታሸጉ ሙቀት የሚሰጡ ኬሚካሎች፣ ሌሎች መጠባባቂያ እቃዎችን ስንቅ ማድረጉን ምግብን በተመለከተ ከተፈራረመው አንድ የእንግሊዝ ኩባንያ እንደሚቀርብለት ገልጿል፡፡
ኤቨረስት ተራራ ለመውጣት ሲሞክሩ በኦክስጅን እጥረት፣ ተንሸራተው በመውደቅና በሌሎች ምክንያቶች በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ የአካል ጉዳትም አጋጥሟቸዋል የሚለው ሲራክ “ብዙዎቹ ለዚህ የሚዳረጉት ራሳቸውን በመኮፈስ በቂ የሥነ ልቦና ዝግጅትና ልምምድ ሳያደርጉ ስለሚጀምሩ ነው” ይላል ሲራክ፡፡
በተራራው ግርጌ ያለው የእነ ሲራክ ቡድን ዋና ካምፕ 5400 ሜትር ላይ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ካምፕ ሆነው ልምምድ ያደርጋሉ፤ አየሩን ይለማማዳሉ፡፡ ሌሎች ተራራሮችን ይወጣሉ፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 6090 ሜትር ከፍታ ያለውን ሎቦቼ ተራራን መውጣታቸው የሚጠቀስ ትልቁ ስኬታቸው ነው፡፡
ቢቢሲ አማርኛ እንደፃፈው ሲራክ ተራራውን ለመውጣት የተነሳው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ያገለግል የነበረውንና መሃሉ ላይ የአንበሳ ምልክት ያለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ነው:: አንበሳ የኢትዮጵያ ምልክት ነው የሚለው ሲራክ፤ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ባደረጉት አስተዋጽኦ ምክንያት የአፍሪካ አንድነት ምልክት ሆኖ ይሰማኛል፤ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት እጅ አለመውደቋን ያስገነዝበናል፤ በመሆኑም ሁል ጊዜ በልቤ ተጽፎ ይኖራል” ይላል፡፡ የኢትዮጵያን ስም ማስጠራትና ሰንደቅ ዓላማዋን ተራራው ጫፍ ላይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ አገሪቱ ያላትን የርሃብና የኋላቀርነት ታሪክ መለወጥ ዓላማው እንደሆነ ይናገራል። ሲራክ ስዩም ኤቨረስትን እስከጫፉ ከወጣ በኋላ ፓኪስታን ውስጥ የሚገኘው ኬቱ 8,611 ሜትር (28,251 ጫማ) ከፍታ ያላቸው ፈታኝ ተራራዎችን የመውጣት እቅድ እንዳለውም ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
ሲራክ ስዩም የኤቨረስት  ተራራ ግርጌ ባለው ዋና ካምፕ ውስጥ ሆኖ ጉዞውን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያው በፎቶ፤ በአጫጭር ንግግሮች እና የቪድዮ ምስሎች ማቅረቡን ቀጥሏል፡፡ የቢቢሲ አማርኛ ክፍልም ሰሞኑን ያቀረበውን ዘገባ የሰራው በዚሁ መንገድ ሁለት ኔፓላውያን ‘ኤቨረስት ሊንክ’ በሚባል ተራራውን ለሚወጡት ደንበኞቻቸው በፈጠሩት የኔትወርክ ስም ነው፡፡ ለሁለት ጊጋ ባይት የኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት 75 የአሜሪካ ዶላር በውድ እየገዙ መሆናቸውን ሲራክ ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
ከኤቨረስት ተራራ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስደናቂ ታሪኮች፤ መረጃዎች፤ ሪከርዶችና ክብረወሰኖች ተመዝግበዋል፡፡ የሲራክ ስዩም ልዩ ክብረወሰን በኔፓል በኩል የሚመዘገብ ታሪክ በመሆኑ ከዚህ በታች የቀረቡ መረጃዎች በዚያው ያተኮሩ ናቸው::   በቻይና ግዛት ቲቤት ባለው የተራራው ክልል የተመዘገቡም በጥቂቱ ተጠቅሰዋል፡፡ በኔፓል የኤቨረስት ተራራ ላይ  ተወላጅ የሆኑ ሼርፓዎች ብዙዎቹን ሪከርዶች እና አስደናቂ ታሪኮች ቢያፅፉም  ከዓለማችን ታላላቅ ተራራ ወጭዎች መካከል አንዳንዶቹ የየራሳቸውን ሪከርዶች እና ክብረወሰኖች በተለያዩ ሁኔታዎች አስመዝግበዋል፡፡
ከ1924 እኤአ ወዲህ ባለፉት 95 ዓመታት በኔፓል እና በቲቤት የኤቨረስት ተራራ መውጫዎች 295 ተራራ ወጭዎች በተለያዩ ሁኔታዎች ህይወታቸው አልፏል:: የሂማሊያን ዳታቤዝ እንደሚያመለክተው ከ1953 እስከ 2017 እኤአ ባሉት ዓመታት ኤቨረስትን የወጡ የ105 አገራት ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፤ አንደኛ ደረጃ የሚወስዱት ኔፓላውያን ሲሆኑ ብዛታቸው 1288 ነው፡፡ 598 አሜሪካውያን፤ 355 ህንዳውያን፤ 337 እንግሊዛውያን፤ 298 ቻይናውያን ፤ 180 ጃፓናውያን፤ 127 ሩስያውያን፤ 116 ደቡብ ኮርያውያን፤ 111 ካናዳውያን እንዲሁም 109 ፈረንሳውያን ተራራ ወጭዎች እስከ ኤቨረስት ጫፍ መድረሳቸውን ነው፡፡ ሲራክ ስዩም ኤቨረስትን ከወጡት አፍሪካውያን 8ኛው ሆኖ የሚመዘገብ ሲሆን ከእሱ በፊት ከአፍሪካ ተራራ ወጭዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሚሆኑት  3 ጊዜ የወጡት ሞሮካውያን ሲሆን ከአልጄርያ፤ ከቱኒዚያ ፤ ከታንዛኒያ እና ከግብፅ አንዳንድ ተራራ ወጭዎች በሂማሊያን ዳታ ቤዝ ተመዝግበዋል፡፡
ባለፉት 10 ዓመታት ከ14 በላይ ሰዎች በመውጣት ላይ እያሉ በሚያጋጥም ድንገተኛ የተራራ ወረርሽኝ ህይወታቸው ማለፉን ነው፡፡ ዘንድሮ በኔፓል የሚገኘውን ኤቨረስት ተራራ እስከ ጫፉ ለመውጣት በዋናነት ጉዟቸውን የጀመሩት 60 ተራራ ወጭዎች ሲሆኑ  ሌሎች በኤቨረስት ተራራ ዙርያ ገባውን የሚገኙ ላሆትሴ፤ የማካሉ እና አናፑራና ተራሮች ላይ ለመውጣት ይሞክራሉ ፡፡ በአጠቃላይ በኔፓል በኩል 374 የሌሎች አገራት ዜጎች፤ በቲቤት በኩል 364 የሌሎች አገራት ዜጎች ሲሆኑ ከእነሱ መካከከል 208 የኔፓል ሼርፓዎች እና 12 የቻይና ተራራ ወጭዎች በኤቨረሰት ከትመዋል፡፡
ኤቨረስትን ለመውጣት ለልምምድ እና ዝግጅት 8ሺ ዶላር፤ የተራራ መውጫ አልባሳት ጫማዎች፣ ቁሳቁሶች እና ሌሎች እቃዎች እስከ 10ሺ ዶላር፤ ኤቨረስትን ለመውጣት ከኔፓል መንግስት ፈቃድ ለማውጣት በሚፈፀም ክፍያ፣ ሼርፓዎችን ለጉዞ ድጋፍ ሰጭነት ምግብ አብሳይነት ተሸካሚነት እና ለተለያዩ ስራዎች በሚፈፀም ክፍያ ከ35ሺ እስከ 100ሺ ዶላር፤ ለስልክ ለኢንተርኔት እና ለተለያዩ መገናኛዎች እስከ 4ሺ ዶላር ወጭ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከዓለማችን ከፍተኛ ተራራሮች በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ኤቨረስት 8,848 meters (29,029 ft) ርዝማኔው ሲሆን የአኮናካጋዋ ተራራ Aconcagua 6,960.8 m (22,837.3 ft)፤ የማክኒሊ ተራራ McKinley 20,320 feet (6,194 m)፣ የኪሊማንጃሮ ተራራ 5,895 meters or 19,341 feet እንዲሁም የፒኮ ክሪስቶባል ኮለን ተራራ Pico Cristóbal Colón 5,700 meters (18,700 ft) እሰከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
4550 ሜትር ወይም 14928 ጫማዎች ከፍታ ያለው ዳሸን ተራራ በኢትዮጵያ አንደኛ፤ በአፍሪካ 10ኛ እንዲሁም በዓለም 23ኛ ነው:: ሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራሮች  ቱሉ ዲምቱ 4377 ሜትር፤ አቡነ ዮሴፍ 4260 ሜትር፤ ጉጌ 4200 ሜትር ጉና 4120 ሜትር፤ ታታ የተራራ ጫፍ 4073፤ ጭላሎ 4036 ሜትር ፤ አቡዬ ሜዳ 4000 ሜትር፤ አምባላጌ 3949 ሜትር እና ባያላምቱ 3777 ሜትር ናቸው፡፡
ኤቨረስትን በመውጣት በዚያው በመኖር  የሼርፓ ህዝቦች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ተራራወጭ ቡድን እስከ 30 ሼርፓዎች ይሰማራሉ፡፡
ከሼርፓዎች አንዱ ቱኒዚንግ ኖርጊ እና እንግሊዛዊው ኤድመንድ ሂላር ኤቨረስትን ለመጀመርያ የወጡት  ናቸው፡፡ ሰር ኤድመንድ  ሂላሪ ንብ አርቢ ገበሬ ነበር፡፡ በኤቨርስት ገድሉ ከሼርፓዎች እኩል የሚነሳ ታሪክ የሰራ ተራራ ወጭ ነው፡፡ ሰር ኤድመንድ በኒውዝላንድ እና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎችና ተራሮችን በመውጣት ከፍተኛ ልምድ ካካበተ በኋላ  ሂማሊያ ሰንሰለታማ ተራሮችን ዙርያ የሚገኘየ ከፍተኛ ቦታዎችን 11 ጊዜ በመውጣት የመጀመርያውን ኤቨረስት ጫፍ ደርሷል፡፡
በ2004 እ.ኤ.አ ላይ ከሼርፓዎች አንዱ የሆነው ፔምባዶር በ8 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ሙሉ ለሙሉ ኤቨረስትን ወጥቶ ጫፍ በመድረስ በኔፖል መንግስት ከፍተኛ እውቅና የተሰጠውን ክብረወሰን አግኝቷል፡፡ ሌሎች  ሼርፓዎች ደግሞ አፓ እና ፕሁር አባ የተባሉ ወንድማማቾች  ሲሆኑ እያንዳንዳቸው 21 ጊዜ ኤቨረስትን እስከ ጫፍ በመውጣት ክብረወሰን ነበራቸው፡፡
ጃፓናዊቷ ጹንብ ታባይ በ1975 እ.ኤ.አ ላይ የኤቨረስት ተራራን የወጣች የመጀመሪያዋ ሴት ስትሆን ፉጂ ተራራን በጃፓን እንዲሁም ማተሪዮን በስዊዘርላንድ እስከ ጫፍ የወጣች ናት፡፡
አውስትራሊያዊው ክርስቲያን ስታንግል በኤቨርስት ተራራራ ጫፍ ላይ ለ16 ሰዓታት ከ45 ደቂቃዎች በመቆየት ሪኮርድ ያስመዘገበ ነው፡፡ ክርስትያን ከኤቨረስት ባሻገር የላቀ ከፍታ ያላቸውን የዓለማችን ታላላቅ ተራሮች በድምሩ እስከ 43.316 ሜትር ከፍታ ያላቸውን በ58 ሰዓታት ከ45 ደቂቃዎች በሆነ ጊዜ እስከ ጫፍ ወጥቶ የጨረሰ ነው፡፡
ዩቺሪ ሚውራ በ2013 እኤአ ላይ በ80 ዓመታቸው በእድሜው አንጋፋ እንዲሁም አሜሪካዊው ጆርደን ሮሜሮ ደግሞ  በ13 ዓመቱ በ2010 እኤአ ላይ በእድሜው ታዳጊ የኤቨረስት ወጭዎች ሆነው ክብረወሰኖች አስመዝግበዋል፡፡

Read 13192 times