Saturday, 20 April 2019 15:02

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ሆስዕና-1
                                     (ያህያ ስንከላ)

        ይሄ ቡላ አህያ . . .
              የተሰነከለው፣
የፊት የግራ እግሩ
ከኃለኛው ጋራ 
            በጠፍር የታሰረው፣
ነጂ ፣
ጫኝ፣
አለቃው፣
ለኛ ንደነገረን . . .
    ‹ ያህያ ያልሆነ › ሃሣብ ስላለው ነው ፡፡
                   . . . // . . .
ነጂው የነገረን በቀላጤ ቋንቋ 
              በቱርጁማን ልሣን ፣
‹ ያህያ ያልሆነ › ሃሳብ ብሎ ሲባል
         ነገሩ ‘ንዲገባን ፣
እንዲለይ ልባችን
እንዲህ ያለው ጉዳይ
እውነት ለሰንካላ
             ለስር እንዲያበቃ፣
አስተርጓሚው ቀርቶ ብንሰማ ደግ ነበር
ያህያን ካህያ
ከሚሆን በስሚ
           ከበላይ ካለቃ፡፡
            . . . // . . . 
የመናገር እድል ጉዳይ የመተንተን
      ሃሣብ የማብራራት ፣
የመፈረጅ ስልጣን
ሁል ጊዜም የሚሰጥ 
ለነጂው ነውና 
           በምልአት በስፋት ፣
ያው በሰማ ባለው
እንግዲህ እንስማ
ሃሣብ የተባለን
             ያህያ ያልሆነ፣
በህሊና ሚዛን  ነገሩን እያየን
ሃቅ ብጤ ንዳለው 
      እውነት እንደሆነ ፡፡
         . . . // . . .
ነጂውን ያሰጋ ያሣብ ሁሉ አወራ
ባለቀው ሲነገር በጫኙ ሲወራ ፡፡   . . . 1

 መጮኽ ያለ ፍቃድ ፣
ለተነጂ ፍጡር
ከቶ  ማይገባ  ባህልና ልማድ ፡፡

ስልጣን ስለሌለው
     ደርሶ የመወለን ፣
ሁሌም ለተነጂ
ማሳወቅ ግድ ነው
 ለመጮኽ መለመን ፡፡

መናገር ያሰበ  እምነቱን አውጥቶ ፣
ማስፈቀድ አለበት ካላቀው ፊት ወጥቶ  ፡፡
ሸክም በዛ ብሎ
 ወይም ሰርዶ ጠፋ  ፣
አይገባምና በግላጭ በይፋ
       አህያ ሊያናፋ  ፣
እንዲህ ያለ ድፍረት
 ማሰብ መሞከሩ  ፣
ባለቃ ምልከታ
ፍፁም አህያዊ
አይሆንም ነገሩ፡፡  አይሆንም ምግባሩ፡፡
ከተነጂ መሃል
ድምፁን ከፍ አድርጎ
           ሃሳቡን ያብራራ ፣
በነጂው ብያኔ 
ሊገጥመው ግድ ነው
የሰንከላ ብይን
 የእስር መከራ፡፡

ነጂውን ያሰጋ ያሳብ ሁሉ አውራ
ባለቃው ሲነገር በጫኙ ሲወራ ፡፡ . . . 2

ጭነት በዛ ማለት 
 ሸክማችን ከበደ ፣
እንደምን ላህያ
 እንዴት ተፈቀደ ?

በተጫኞች ማበር 
በተነጂ ዕድር
መጫኛ ያላላ
 ሸክም ያዘነበለ ፣
በከበደኝ ምክንያት
          ጭነት ያጋደለ ፣
የፊት የግራ ግሩ
ከኃለኛው ጋራ
   የተሰነከለ፡፡  . . .        ስንት አለ ! ;

የሚገርመው ጉዳይ
በሰንሰለት ብዛት
 ሃሣብ ላይገታ ፣ 
የሚገርመው ጉዳይ
በጠፍር በገመድ
 ወኔ ላይመታ፣
የሚገርመው ጉዳይ
በግረሙቅ ካቴና
 እውነት ላትረታ ፣
ነጂ አበሣ  አየ
ስንቱን እያሰረ !
 ስንቱን  . . . እየፈታ  ! ! ;

ነጂውን ያሰጋ ያሳብ ሁሉ አውራ
ባለቀው ሲነገር በጫኙ ሲወራ  ፡፡ . . . 3

ተራራ እያቀሰትን
 ዳገትና ቀበት ፣
ገደል እየናጠን
 ተዳፋት ቁልቁለት ፣
ሜዳ የዳከርን
 ተጭነን ዳውላ ፣
ቀልባችን ፈርቶታል
አለቃ ነጂያች
 የያዝከው ዱላ ፣ . . .
በሚል ጥርጣሬ
ጉዞ እያጠፈኑ 
      መንገድ እያሰፉ ፣
አቅጣጫ እያበዙ
ምርጫ የጨመሩ
        ከይታ የጠፉ ፣
እንዲህ ያለ ሃሣብ
ስላልሆነ የነርሱ
       ከሰንካላም ኃላ ፣
ሊያገኙ ግዱ ነው
 የሸሹትን ዱላ ፡፡
       . . . // . . .
ነጂውን ያሰጋ
 ጫኚውን ያስፈራ
         ያሳብ ሁሉ አውራ ፣
እንደዚህ ይመስላል
ከብዙ በጥቂት
በበላይ ሲነገር
          በአለቃ ሲወራ ፡፡

ሆሣዕና-2
( ፍቱና አምጡልን )
........................
የመናገር ዕድል
ጉዳይ የመተንተን
 ሃሣብ የማብራራት ፣
ሁልጊዜም የሚሰጥ
ላለቃ ነጂ ነው 
         በስፋትምልአት ፡፡ . . .
የሚለውን ትተን
እንዲህ ያለ ጊዜ
 ብራ ወቅት ሲጋጥመን፣
በውርንጭላ ቀን
በውርንጭላ ድምፅ
በአህያ ቋንቋ 
 እንዲህ እንላለን፡፡
በገጠር ቀበሌ
              በከተማ ሸንጎ 
መቀፍደድ መሰንከል
 ሃሳብ ሰበብ አርጎ ፣
ቢመስልም ጉዳዩ 
አሣቢ መርማሪ 
 ጠያቂ የሌለበት፣
እንደመፃፉ ቃል
እንዲህ ባለ ጊዜ
ሆሣዕና ሲደርስ
ነገሩ መታየት
 መጣራት አለበት፡፡
በዝንጥፍ ዘንባባ
በቀጤማ ጎዝጓዝ
 በልልታና ሆታ ፣
ሸማ ያነጠፍን
እንድንቀበለው
መጪው ትንሳኤ ነው
የተሰነከለ የታሰረ ሁሉ
  ይለቀቅ ይፈታ ፡፡

Read 1655 times