Saturday, 20 April 2019 13:33

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ከዓለማችን 100 ተፅእኖ ፈጣሪ መሪዎች አንዱ ሆኑ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ለ2019 የሠላም የኖቤል ሽልማት ታጭተዋል

              ታይም መፅሔት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ከ100 ተፅእኖ ፈጣሪ መሪዎች መካከል አንዱ አድርጎ መረጣቸው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት በአገራቸው ፈጣን ለውጥ ባመጡ መሪዎች ዘርፍ ነው፡፡  እሳቸው በተካተቱበት ዘርፍ ውስጥ የአሜሪካ ኮንግረስ አፈጉባኤ ናንሱ ፔሎሲ፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ፖፕ ፍራንሲስ፣ የኒውዝላንድ ም/ሚኒስትር ጆሲንዳ አርደን መካተታቸውም ታውቋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ጋር ከአፍሪካ በዚህ ዘርፍ የተካተቱት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሳይረል ራማፎሳ ናቸው:: በዚህ ዝርዝር ከተካተቱት ተጨማሪ መሪዎች መካከል የእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትኒያሁ የተባበሩት ኤምሬት ልኡል መሃመድ ቢን ዛይድ እና የፓኪስታኑ ጠ/ሚር ኢምራን ካሃን ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባከናወኗቸው የፖለቲካ እና ማህበራዊ ሪፎርሞች በተለያዩ አካላት ሙገሳ ከማግኘታቸው ባሻገር እውቅና እና ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ መሪዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ በጎ እውቅናዎችን ያገኙ ብቸኛው መሪ እንደሚያደርጋቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ወደ ስልጣን ከመጡ በ3ኛ ወራቸው በኡጋንዳ ብሔራዊ በአል ላይ የተገኙት ጠ/ሚኒስትሩ በስ ስርአቱ ላይም ለአፍሪካውያን በመላ ተስፋን የሰነቀ የለውጥ እንቅስቃሴ ለመፍጠር እና ሃገራቸውን ከአደጋ በመታደግ የሃጊቱን ከፍተኛ የጀግና አርበኞች ሜዳሊያ ተሸልመዋል፡፡
ደፋር የዲፕሎማሲ እርምጃ ወስደውበታል ተብሎ ስማቸው በበጎ በሚነሳበት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ዳግም እውን እንዲሆን ላበረከቱት አስተዋፅኦም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ከሳውዲ አረቢያ መንግስታት የክብር ሜዳሊያ እና ኒን ሽልማቶችን አግኝተዋል፡
ከክብር ሽልማቶቹ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገራቸው የፖለቲካ ሪፎርም ማካሄዳቸው በጎ እውቅናን አስገኝቶላቸው የአፍሪካን ሜጋዚን የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ሰው አሸናፊም ለመሆን በቅተዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አሁንም በሌላ ተጨማሪ ከፍተኛ እውቅና እና ሽልማት እየተጠበቁ ነው፡፡ ለታላቁ የኖቤል ሽልማት ታጭተዋል፡፡ የታጩበት ዘርፍም የሰላም ሽልማት ዘርፍ መሆኑ ታውቋል፡፡
ለ2019 የሰላም ኖቤል ሽልማት ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ 223 ግለሰቦች እና 78 ተቋማት በእጩነት የተጠቆሙ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ህዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም በኖርዌይ ኦስሎ የሽልማት ስነ ስርአቱ ይከናወናል፡፡

Read 7488 times