Saturday, 13 April 2019 14:01

በሆላንድ ገንዘብ ከፍለው ከሴተኛ አዳሪ ጋር የሚተኙ እንዲቀጡ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


                  ከ42 ሺህ በላይ ሆላንዳውያን ወጣቶች፣ በአገሪቱ ገንዘብ ከፍለው ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር የሚተኙ ቅጣት እንዲጣልባቸው የሚጠይቅ ፊርማ በማሰባሰብ ለፓርላማ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሴተኛ አዳሪዎችን የሚጎበኙ ዜጎችን በህግ የማስጠየቅ አላማ ባነገበውና የአገሪቱ ወጣቶች በማህበራዊ ድረገጾች በከፈቱት ዘመቻ ከ42 ሺህ በላይ ሆላንዳውያን ሃሳቡን ደግፈው ፊርማቸውን ማስፈራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ ደግሞ የእንጀራ ገመዳችንን የሚበጥስ ነው በማለት ዘመቻውን የተቃወሙት ሴተኛ አዳሪዎች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡
ጉዳዩ በማህበራዊ ድረገጾች የመነጋገሪያ ርዕስ መሆኑን ተከትሎ አምስተርዳም ውስጥ ወደሚገኝና ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት ወደሚገኙበት ሞቅ ያለ ሰፈር በማቅናት የሴተኛ አዳሪዎችን ስሜት ለመገምገም እንደሞከረ የጠቆመው የቢቢሲው ዘጋቢ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴተኛ አዳሪዎች “ምርጫችን ከሆነ መብታችን ነው” በማለት ተቃውሟቸውን እንደገለጹለት አትቷል፡፡  
ከሴተኛ አዳሪነት ጋር በተያያዘ ላላ ያለ ህግ ካለባቸው አገራት አንዷ እንደሆነች በሚነገርላት ሆላንድ፣ እድሜያቸው ለወሲብ የደረሰ እስከሆኑና እስከተስማሙ ድረስ ገንዘብ ከፍሎ ወሲብ መፈጸም ህጋዊ እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ስዊድን፣ ኖርዌይና ፈረንሳይን በመሳሰሉ አገራት በአንጻሩ፣ ገንዘብ ከፍሎ ወሲብ የሚፈጽም በህግ እንደሚቀጣና ይህም በመሆኑ በአገራቱ ገንዘብ ከፍለው ወሲብ የሚፈጽሙ ሰዎችና በሴተኛ አዳሪነት የሚበዘበዙ ዜጎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1436 times