Saturday, 13 April 2019 13:36

ቃለ ምልልስ አጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካ የትም አያደርሰንም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

• የፖለቲካ ልሂቃኑ ከሚጋልቡት ፈረሶች ወርደው ቁጭ ብለው መነጋገር አለባቸው
 • የሁሉም ግጭቶች መነሻ ለውጡ መሀል የሚዋልሉ ሃይሎች መበራከታቸው ነው


                 ከሠሞኑ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ፣ ከ”አርበኞች ግንቦት 7” ሊቀ መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና ከ”ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)” ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታ ጋር በመሆን፣ ወደ ጀርመን አቅንተው፣
የምርጫ አፈፃፀምና ስርአተ መንግስት ጉዳይ ላይ ጉብኝትና የልምድ ልውውጥ ያደረጉት ፕ/ር መረራ ጉዲና፤ ጀርመናዊያን ጠንካራ መንግስታዊ ስርአትና ጠንካራ የምርጫ ስርአት መመስረታቸውን ይናገራሉ፡፡ በጀርመን ጉዟቸው የምርጫ ማስፈፀሚያ ተቋማትንና ፓርላማውን በተመለከተ ሠፊ የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከጀርመን ጉብኝታቸው መልስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ፣ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ
ቅድመ ዝግጅት፣ በለውጥ ሂደቱ ተግዳሮቶች እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ እነሆ፡-


                 ከዚህ ቀደም የምርጫ ሂደት ውስጥ መግባት ሀገሪቱን ሊያረጋጋ ይችላል ብለው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የምርጫ ቦርድን የማደራጀትና የምርጫ ህግን የማውጣት ሂደት ተጀምሯል:: እስካሁን በዚህ ረገድ ያለውን እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
አሁን በሀገሪቱ እንደሚታየው ሠፋፊ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመሻገር አንዱ መፍትሄ፣ ከዚህ በፊትም እንዳልኩት፣ የምርጫ ሂደት ውስጥ መግባት ነው፡፡ እርግጥ ነው አሁን የምርጫ ህግ የመሳሰለውን ማሻሻል ተጀምሯል፡፡ ለኔ ይሄ ሂደት አሁንም ዘገምተኛ ነው፡፡ ፍጥነትና ቅልጥፍና የለውም፡፡ በተረፈ ግን የተጀመረው ሂደት ላይ ብዙም ቅሬታ የለኝም፡፡ ዋናው በፍጥነትና በጥራት ማከናወኑ ላይ ነው፡፡ እየተፈጠሩ ከሚገኙ ችግሮች አንፃር አሁንም ይበልጥ ወደ ምርጫ አጀንዳዎች መግባት አለብን፡፡ ለውጡን እመራለሁ የሚለው ኢህአዴግም አንድ ነው ወይስ አራት ነው የሚለውም ጥያቄ ነው፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን ሂደቱ ተስፋ ሰጪ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚያው ልክ ግን ስጋትም አለ፡፡ አሁንም የለውጥ ሂደቱ ለመኮላሸት ቅርብ ነው፡፡ የመኮላሸት አደጋዎች በለውጡ ላይ እንደተጋረጡ እየተመለከትን ነው:: ይሄ አሳሳቢው ጉዳይ ነው፡፡
በእርስዎ አመለካከት የለውጥ ሂደቱ የተጋፈጣቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አሁንም ቢሆን ሀገሪቷ መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት፡፡ ይሄ መስቀለኛ መንገድ ደግሞ አራትና ከዚያ በላይ እድሎች ነው ያሉት፡፡ ወደ ፊት የመጓዝ፣ ወደ ኋላ የመመለስ፣ ወደ ጐን የመውደቅ፣ ባሉበት የመቅረት እድሎች አሉት:: ስለዚህ አሁንም በዚህ መንገድ ላይ ቆመን ግራ እንደተጋባን ነው ያለነው፡፡ ተስፋዎችንና ስጋቶችን በእኩል ይዘን ነው እየተጓዝን ያለነው:: መሠረታዊ ጉዳዩ፣ በተለየ ገዥው ፓርቲ፣ በሙሉ ልቡ ለውጡ ውስጥ ገብቶ ለውጡን ወደፊት እየገፋ ነው ወይስ የገመድ ጉተታ ውስጥ ነው? የሚለው ነው፡፡ ይሄ በደንብ እየታየ አይደለም:: በአጠቃላይ በሚያጠግብ መንገድ ለውጡ እየተጓዘ አይደለም፡፡ የገዥው ፓርቲ ተሳትፎም አናሳ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ቦታ ችግሮች የሚጫሩት በገዥው ፓርቲ ነው ወይም በየአካባቢው ያሉ ገዥዎች እጅ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል፤ በብዙ ቦታዎች፣ ዜጐች እኛ ጋ ለውጡ አልደረሰም የሚል ድምጽ በስፋት ያሰማሉ፡፡ እኔ በተንቀሳቀስኩባቸው ቦታዎች በሙሉ እንዲህ ያሉ ብሶቶችን ስሰማ ነው የከረምኩት፡፡ በሃዲያ፣ አርሲና ሌሎች ቦታዎች ላይ ከሰሞኑ እንኳ ስንንቀሳቀስ ለውጡ እኛ ጋ አልደረሰም የሚሉ በርካታ ድምፆችን አዳምጫለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር በየአካባቢው ያለው ህዝብ በለውጡ ተስፋ እንዳይቆርጥ መጠንቀቅ ያሻል፡፡ “ለውጡ እኛ ጋ አልደረሰም፤ ለእነ ዶ/ር ዐቢይ ንገሩልን” የሚሉ ድምፆች በርካታ ናቸው፤ “ድሮም ሲዘርፉን፣ ሲገርፉን የኖሩ ናቸው ዛሬም እየመሩን ያሉት” ሲሉ ይደመጣል፡፡ እነዚህ ብሶቶች እየቆዩ ሲሄዱ አደጋ መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ ተስፋ መቁረጥ ይመጣል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች ናቸው፤ እነዚህ በጣም አሳሳቢ ናቸው:: ውሎ አድሮ ከዚህ የበለጠ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል:: በአራተኛ ደረጃ የማስቀምጠው ችግር፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ከተፈራረምነው የቃል ኪዳን ሰነድ ባለፈ ለውጡን ወደፊት ለመምራት፣ ለመውሰድና ወደ መሬት ለማውረድ የቀረጽነው የተግባባንበት የጋራ አጀንዳ የለንም፡፡
 የፖለቲካ ሃይሎች በለውጡ ፍኖተ ካርታ ላይ መሠረታዊ ስምምነት ላይ ደርሰው ያንን ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ አይታይም፡፡ እስካሁንም የጋራ ስምምነት በለውጡ ላይ የለንም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይም ምን አይነት ፌደራሊዝም እንከተል የሚሉ ጥያቄዎች ቀጥለዋል፡፡ ምናልባት ዛሬ ላይ መነሳት የሌለባቸው የህገ-መንግስት ይቀየር ጥያቄዎችን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ አሁን እነዚህ ጥያቄዎች በይደር እየታለፉ እየተወሳሰቡ ከሄዱ የበለጠ ችግር በቀጣይ ሊገጥመን ይችላል፡፡ ይሄን በአጉሊ መነጽር ተመልክቶ ወደ መፍትሔዎች መሄድ ይገባል፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ተስፋዎቹም ስጋቶቹም አሁን በእኩል ጐን ለጐን እየሄዱ ስለሆነ፣ ወደዚህኛው ያደላ እድል ነው ያለን ብሎ ለመደምደምም አስቸጋሪ ነው፡፡
አንዳንድ ወገኖች “ዶ/ር ዐቢይ ሀገሪቱን መምራት አልቻሉም” ይላሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
የዚህ ለውጥ አመራርን የማስፋት ሁኔታ አንስተን ጠይቀን ነበር፤ ግን ምንም መልስ አልተሠጠውም፡፡ ከዚህ አንፃር በአመራሩ ስፋት ላይ ጥያቄዎች አሁንም አሉ፡፡ በአንድ በኩል ለውጡ የሚመራው በኢህአዴግ ነው፤ በዚያው ልክ ይሄን ሁሉ ውጥንቅጥ ያመጣውም ኢህአዴግ ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ ኢህአዴግን ለማስተካከል አሁንም እየጣረ ነው፡፡ ይሄ ጥረትም ቀላል የሚሆን አይመስልም፡፡ ለዚህ ነው ለውጡ እታች አልወረደም የሚል ቅሬታ የሚቀርበው፡፡ ለውጡን በሙሉ ልብ ለመደገፍ የሚንቀሳቀስ ሰውም ግራ የሚጋባው ለዚህ ነው፡፡ ለውጡን ለማደናቀፍ ምክንያቶችን እየፈጠረ የሚሯሯጥ ሃይልም አለ፡፡ ስለዚህ ይህ አመራር ችግሮች እንዳሉበት አይተናል፡፡ ዶ/ር ዐቢይን አልቻሉም ብለው የሚከሱትም ቢሆኑ ምናልባት የራሣቸውን የሚጋጩ ህልሞች በጉያቸው አዝለው ነው፡፡ ወደ ክስ የሚሮጡትም፣ የሚጋጩ ህልሞቻቸውን ወደ መድረኩ ለማምጣት አልተሳካልንም ከሚል ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ግን እውነተኛ ስጋት ያላቸው ወገኖችም አሉ፡፡ እንግዲህ ይሄ ሁሉ ስሜት ነው እየተደበላለቀ እየሄድን ያለነው:: ሂደቱም በዚህ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ማን ይችላል ማን አይችልም የሚለው አልለየለትም፡፡
ከሰሞኑ በከሚሴ፣ አጣዬ፣ ማጀቴ በተፈጠሩ ግጭቶች በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል:: በሀገሪቱ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን ማስቆም  ያልተቻለው ለምን  ይመስልዎታል? መፍትሄውስ?
ትልቁ ችግር ኢህአዴግ በሙሉ ልቡ ለውጡ ውስጥ አለመግባቱ ነው፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አባላት ከዚህ ለውጥ ምን እናገኛለን? ምና እናጣለን? የሚል ውዝግብ ውስጥ ናቸው፡፡ የሚያገኙትንና የሚያጡትን ነገር አሁንም በማስላት ላይ ናቸው፡፡ መደመርና መቀነስ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በሙሉ ልብ ለውጡ ውስጥ አልገቡም፡፡ ስለዚህ ለውጡ የበለጠ ተስፋ በሚሰጥ መንገድ ወደ መሬት መውረድ አልቻለም፡፡ ከዚህ በመነጨ ነው ግጭቶቹ የሚፈጠሩት፡፡ ለውጡን እየመራሁ ነው የሚለው አካል ሙሉ ለሙሉ ወደ ለውጥ አስተሳሰብ ውስጥ ባለመግባቱና መንታ መንገድ ላይ በመቆሙ ነው ግጭቶች እየተፈጠሩ ያሉት:: የሁሉም ግጭቶች መነሻ ለውጡ መሀል የሚዋልሉ ሃይሎች በመበራከታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ለውጡን ህዝቡ እንደሚጠይቀው ወደ ታች ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ መደመርና መቀነስ ስሌት ውስጥ ያሉትም ሚናቸውን እንዲለዩ ማድረግ ነው፡፡ ኢህአዴግ፤ ከኢህአዴግ ከታረቀ ግጭት ማስቆሙ ቀላል ነው የሚሆነው፡፡
የብሔር አክራሪነትና ዘረኝነት ጉዳይ አስጊ ሆኗል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ?
ይሄን ክስ የሚያቀርቡ ወይም እንዲህ የሚለውን ሃሳብ የሚያራግቡ ሃይሎችም አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያለ ይመስለኛል፡፡ በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ፣ የሚጋጩ ህልሞችን ይዞ አሁንም አንዱ ሌላውን የመክሰስ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ከሣሹም ተከሳሹም የሚጋጩ ህልሞች በውስጡ ይዞ ነው የሚወዛገበው እንጂ ራሱን ከፖለቲካ ቡዳ ለመከላከል ሲጥር እያየሁ አይደለም፡፡ ከግራና ቀኝ ለውጡን እንመራለን የሚሉትም፣ በመሃልም ድጋፍ አለን የሚሉትም፣ ቋሚ ድጋፍ ሲያገኙ የማናየው ለዚህ ነው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ፤ አሁን ከሳሾችም በዝተዋል፣ ታጋዮችም በዝተዋል፡፡ ስለዚህ ከሣሾቹ የሚከሱትን አውቀው ካልከሰሙ ራሣቸውን ነፃ አድርገው ሌላውን ቡዳ ካደረጉ፤ ጥያቄ እያበዙ የሚሄዱትም ጥያቄዎቻቸውን መቼ ሊመለስ እንደሚገባው እያወቁ ካልሄዱ፣ ሀገሪቷን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊመሯት ይችላሉ፡፡ የሶቪየት ህብረቱ መሪ ሌኒን፤ “የሞኝ ሩጫ ፍጥነትን አይጨምርም” ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ ክስ እያበዙ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ራሣቸውን በሞኝ ሩጫ ውስጥ እያስገቡ ነው፡፡ ህልሞቻቸውን ብቻ ተከትለው መጋለብ እንጂ እንዴት የሰከነ ስራ እንሠራለን፤ እንዴት ሃገሪቷን ወደ ብሔራዊ መግባባት እንመራለን፤ እንዴት ሁላችንም ወደ መሀል መንገድ እንመጣለን፣ እንዴት ሁሉንም ህልሞች ቢቻል በገደብ ማስኬድ ይቻላል፣ የሚለውን የሚያስተውል እንደሌለ እያየሁኝ ነው፡፡
መፍትሔው ታዲያ ምንድን ነው?
ዋናው መፍትሔ የፖለቲካ ልሂቅ የሚባለው ቁጭ ብሎ፣ በሰከነ ስሜት መነጋገር መደራደር መቻል አለበት፡፡ ሌላ ምንም አስማታዊ ቀመር የለም፤ ተቀምጦ እየተነጋገሩ መደራደር ነው፡፡ የፖለቲካ ልሂቁ መስማማት የማይችልባቸውን ጉዳዮች ወደ ህዝቡ መውሰድ ይቻላል፡፡ አሁን ግን ያለው ችግር በሙሉ የፖለቲካ ልሂቃኑ ስለሆነ፣ የፖለቲካ ልሂቃኑ ተቀምጠው፣ ከሚጋልቡት ፈረሶች ወርደው መነጋገር አለባቸው፡፡ በመጨረሻም ህዝቡ የሚሰጠውን ዳኝነት መቀበል ነው፡፡ አጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካ ከዚህ በኋላ የትም አያደርሰንም፡፡ ሀገሪቷን ውድ ዋጋ ማስከፈል አይገባም፡፡ ልሂቃኑ የሚጋጩ ህልሞቻቸውን አሁንም ገደብ እንዲያበጁና ወደ መሃል መጥተው መነጋገር እንዲችሉ  ነው የምመክረው፡፡


Read 3442 times