Print this page
Saturday, 13 April 2019 13:20

ሲራክ ስዩም ኢትዮጵያዊው የተራራ ኦሎምፒያን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)


 • የዓለማችን ከፍተኛውን ተራራ ኤቨረስት እየወጣ ነው፡፡ ከባህር ወለል በላይ 8848 ሜትር (29029 ጫማዎች) ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡፤  በሳምንት ውስጥ ከቡድኑ ጋር ከ5300 ሜትር በላይ ወጥተዋል፡፡
 • ኤቨረስት ለተራራ ወጭዎች በፈታኝነቱ የሚታወቅ  ነው፡፡ ጫፉ ላይ ለመድረስ በቂ ዝግጅት፤ የዓላማ ቁርጠኝነት፤ የስነልቦና ጥንካሬ እና የተሟላ የአካል ብቃት አስፈላጊ ናቸው፡፡
 • ትውልዱና ዕድገቱ በጎንደርና በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ነዋሪነቱ በአሜሪካ፡፡ በሙያው ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ሲሆን ፕሮፌሽናል ተራራ ወጭም ነው፡፡
 • በተራራ ወጭነት  ከ11 ዓመታት በላይ ልምድ አለው፡፡ በሰሜን አሜሪካ ከ27 በላይ ተራራዎችና ሌሎች ከፍተኛ ቦታዎችን አንዴና ደጋግሞ ወጥቷቸዋል፡፡ በደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ ከ4ሺ ሜትር በላይ የሆኑ ተራራዎችንም በቅርብ ዓመታት እስከጫፍ ደርሶባቸዋል፡፡
 • በየተራሮቹ ጫፎችም የኢትዮጵያን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የሚያወለበልብ ሲሆን በኤቨረስት  ጫፉ ላይ በመድረስም በታሪክ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ሆኖ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለማውለብለብና አዲስ ተስፋውን ለማንፀባረቅ  አቅዷል፡፡
 • ባለፉት 56 ዓመታት የኤቨረስት ተራራን በተሳካ ሁኔታ እስከ ጫፍ ለመውጣት የተቻለው ለ4883 ጊዜ ነው፡፡ እሰከ 300  ተራራ ወጭዎች በጉዟቸው ላይ ተሰውተዋል፡፡
 • ከልጅነቱ ጀምሮ ለስፖርት ልዩ ፍቅር ያለው ሲሆን የማራቶኑ ጀግና አበበ ቢቂላ፤ የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ ተምሳሌቶቹ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ጀግኖች ለእነ ኃይሌ፤ ቀነኒሳ እና ሌሎችም ልዩ አክብሮት አለው፡፡
 • እግር ኳስ፤ሩጫ ፤የበረዶ ስፖርት፤ ሜዳ ቴኒስ ፤ ብስክሌት፤ መረብ ኳስ፤ ዋና እና ሌሎች ስፖርቶችን ዝንባሌዎቹ አድርጎ ያዘወትራቸዋል፡፡


            እንደ መግቢያ
ሲራክ ተወልዶ ያደገው በጎንደር እና ለአዲስ አበባ ከተሞች ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሳለፈውን ልጅነት ከታዲያስ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ሲያስታውስ  ዛፎችን መውጣት ኮርብታና ጉብታ ጫፍ ላይ መድረስን ያዘወትር እንደነበር ተናግሯል፡፡ በታዳጊነቱ የሚያበዛቸው እነዚህ ጀብዶቹ ምክንያትም  አያቱ በተደጋጋሚ ወጌሻ ጋር እየወሰዱ ከባዱን ህመም በታሸባቸው ግዚያት ሁሉ መጋፈጡንም አይረሳውም፡፡
ለስፖርት ልዩ ፍቅር ያደረበት ገና በልጅነቱ ነው፡፡  ኢትዮጵያዊውን የማራቶን ጀግና አበበ ቢቂላ እንዲሁም ብራዚላዊውን የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ ተምሳሌቶቹ ያደርጋቸዋል፡፡  ለኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ጀግኖች ለእነ ኃይሌ፤ ቀነኒሳ እና ሌሎችም ልዩ አክብሮት እንዳለውም ገልጿል፡፡ ህይወቱን ሙሉ ከስፖርት እንቅስቃሴ አልተላቀቀም፡፡ እግር ኳስ፤ሩጫ ፤የበረዶ ስፖርት፤ ሜዳ ቴኒስ ፤ ብስክሌት፤ መረብ ኳስ፤ ዋና እና ሌሎች ስፖርቶችን  ዝንባሌዎቹ  ናቸው፡፡ ዛሬም ያዘወትራቸዋል፡፡
አባትና እናቱ የፒኤችዲ ምሩቆች ናቸው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ለስፖርት ያለውን ፍቅር ቢገነዘቡም በትምህርቱ ላይ በማተኮር ጥሩ ደረጃ እንዲደርስላቸው ይፈልጉ ነበር፡፡ ስለሆነም በአሜሪካዋ የሚቺጋን ግዛት መኖር ከጀመረ በኋላ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ   ከሚችጋን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ነዋሪነቱን በፓስፊስካ ካሊፎርንያ  ያደረገ ሲሆን፤  በካሊጋሪ ኢንኮርፕሬትድ ኩባንያ በመስራት ላይ ይገኛል::  በሄንደረስን ኔቫዳ በሚገኘው   የታይታነም ሜታል ኮርፖሬሽን በኤሌክትሪካል ኢንጂነርነት ለ10 ዓመታት  ያገለገለም ነው፡፡
ሲራክ ስዩም በአሁኑ ወቅት የሚገኘው በኤቨረስት ተራራ ላይ ነው፡፡ የዓለማችን ከፍተኛው ተራራ ኤቨረስት ከባህር ወለል በላይ 8848 ሜትር (29029 ጫማዎች)  ላይ ይገኛል፡፡  ባለፈው 1 ሳምንት ሲራክ የሚገኝበት የሳቶሪ አድቬንቸርስ ኤንድ ኤክስፒዲሽን ቡድን ከ5300 ሜትር በላይ ወጥተዋል፡፡
 ሲራክ ስዩም የሚገኝበት እና በሳቶሪ አድቬንቸርስ ኤንድ ኤክስፒዲሽን የሚመራው ቡድን በደቡብ ምስራቅ ኤሽያ የምትገኘውን ኔፓልን ከረገጠ ሳምንት አልፎታል፡፡  ባለፉት  56 ዓመታት 8306 ጊዜ ኤቨረስትን ለመውጣት የተሞከረ ሲሆን  4883  ጊዜ ተራራው ጫፍ ተደርሷል፡፡
 ከዋናው ካምፕ 5380 ሜትር  ላይ
ኢትዮጵያዊው ሲራክ ስዩም የሚገኝበት የተራራ ወጭዎች ቡድን አጠቃላይን ጉዞን የሚያስተባብረው  ‹ሳቶሪ አድቬንቸርስ ኤንድ ኤክስፒዲሽን›› የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ የቡድኑ አባላት የኤቨረስት ተራራን ለመውጣት ወደ ኔፓሏ ዋና ከተማ ካታሙንዱ የደረሱት ከ10 ቀናት በፊት ነው፡፡ ሲራክ  በፌስቡክ ገፁ ጉዞውን በተመለከተ አጫጭር ማስታወሻዎች እና  የቪዲዮ ምስሎችን  በተከታታይ እያቀረበ በመሆኑ  አጓጊውን ጉዞ የትም ዓለም ሆኖ ለመከታተል አመቺ ሆኗል፡፡  የእነሲራክ ቡድን ወደ ኤቨረስት ጫፍ የሚያደርገውን ጉዞ የመጀመርያ ምዕራፍ የከፈተው ከካታሙንዱ ወደ ሌላኛዋ ከተማ ሉካላ በማቅናት ነበረ፡፡ ሉካላ በኤቨረስት 2860 ሜትር ከፍታ ላይ ናት፡፡  ከዚያም በተጓዦች ከሚጨናነቁ  ተንጠልጣይ ድልድዮች አንዱ ፓሃካደንግ በተባለ ስፈራ አጋጥሟቸው ተሻግረዋል:: በፓሃካንድ ምሽቱን ካሳለፉ በጉዟቸው ላይ አስገራሚ ቆይታ የነበራቸው በታዋቂው የቢርማቼ ባዛር ከተማ ነበር:: የኤቨረስት ተራራን የሚወጡ ሁሉ የሚወዷት ስፍራ ናት፤ ቢርማቼ ፡፡  ለቡድኑም ይህን ምቹ ሁኔታ ፈጥራላችዋለች:: ሲራክም ከ3 ዓመት በፊት በኔፓል ያደረገውን ጉብኝት ያስታወሱ አንድ ኔፓላዊ አግኝቷል፡፡ እኝህ ኔፓላዊ ‹‹ኢትዮጵያ›› ብለው በመጥራት በጉዞው መልካሙን ሁሉ እንዲገጥመው አበረታተውታል፡፡ ከቢርማቼ በኋላ  የኤቨረስት ተራራን ሁለገብ የአየር ንብረት ለመለማመድ ከ6 እስከ 8 ቀናት ወደሚከትሙበት ዋና ካምፕ ለመድረስ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ የእነ ሲራክ ቡድን ጉዞውን በጀመረ በሶስተኛው ቀኑ 12220 ጫማ ላይ ደርሰዋል:: በዚሁ ከፍታ ላይ ሆነው የኤቨረስት ጫፍ ለመመልከት ቢሞክሩም በደመና በመሸፈኑ ምንም አልታያቸውም ነበር፡፡ በዚሁ ከፍታ ላይ በከተማው ከሚታወቁ የሼርፓ ሰዎች አንዱን ለሃኪም ስናም ሴርም ተገናኝተዋል፡፡ ለሲራክ ትልቅ አጋጣሚ ነበር፡፡ በተሸከመው የጉዞ ሻንጣ ላይ የተለጣጠፉትን የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት እና ሌሎች የታሪክ ማስታወሻዎች ተመልክተው  ‹‹አዲስ አበባ›› ይሉት እንደነበር ነው በፌስቡክ ገፁ ያሰፈረው፡፡ ከዚያ በኋላ መድረሻቸው የሆነው ቴንግቦቼ ገዳም ነው፡፡ በደመና ሙሉ ለሙሉ ተሸፍኖ የነበረው ኤቨረስት ቴንግቦቼ ላይ ሲደርሱ ፍንትው ብሎ መታየት ጀመረ፡፡ በመንገዳቸው ላይ አንዲት ትንሽ ልጅ በእናቷ ፀጉሯን እየተሠራች ተመልክተው ትኩረታቸውን ስባለች፡፡ ከቡድኑ  ጋር አብራ ፎቶ እንድትነሳ ቢፈልጉም በመጀመርያ ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ሲራክ ከተሸከመው ግዙፍ ቦርሳ ውስጥ  ቼኮሌት አውጥቶ ሰጣትና ሙሉ ፈገግታዋ ተመለሰ፡፡ ስሟን ጠይቆ እየተዋወቃት በኋላ ግን ከእነ ሙሉ ፈገግታዋ ከእናቷ ጋር የማስታወሻ ቪድዮና ፎቶ አንስቷታል፡፡  ቀጣዩ መድረሻ የሆነው ደንግቦቼ ሲሆን 4410 ሜትር ላይ ይገኛል፡፡ በኤቨረስት ዙርያ ገብ ያለውን አየር ለመጀመርያ ጊዜ ለመለማመድ  ለ2 ቀናት ይቆዩበታል፡፡ በዚሁ ከፍታ ላይ እንደደረሱ ሲራክ በፌስቡክ ገፁ የለጠፈው ቪድዮና አጭር ማስታወሻ የአገር ቤት ምግብ እንደናፈቀው የሚያመለክት ነው፡፡ ስንቁን በአገልግል መያዙን ከጠቀሰ  በኋላ ምስር ወጥ፣ ፍርፍር፣ ጐመን፣ ሽሮ፣ ጥቅል ጐመን፣ ድንች ወጥ ከእርጐ ጋር ማሰሩንም ገለፀ፡፡ የአገልግል ስንቁን በጉዞ ማስታወሻ ላይ ያወሳው ራሱን ለማበረታታት እንጅ እውነትም አሳስሮ ይዞ አልነበረም፡፡ ይህን አስመልክቶ በቀረፀው ቪድዮ አገልግሉን ከአገር ቤት በሆነ መንገድ የሚያቀርብለት ካለ አልጠላም ነበር ያለው፡፡ ዲንቦቼ 5130 ሜትር ከፍታ ላይ ሲደርሱ የስፔን ዜግነት ያላቸው ተራራ ወጭዎች እና የጉዞ መሪያቸው የቴዲ አፍሮን ‹‹ኢትዮጵያ›› ሙዚቃ በመስማት እየተዝናኑ ሲጓዙ  የሚያሳይ አጭር ቪድዮ ነበር በፌስ ቡክ ገፁ ሲራክ የለጠፈው ፡፡   ከዚያም ጉዟቸውን ከጀመሩ ከሳምንት በኋላ የናጋሩጂን ጫፍ ከትናንት በስቲያ ረግጠዋል፡፡ ወደ ኤቨረስት ተራራ ጫፍ የሚያደርጉት የመጀመርያው ምዕራፍ የሚያበቃው ዋናው ካምፕ ሲደርሱ ነው፡፡ በዚህ ካምፕ በሳቶሪ የተሟላ ዝግጅት ውስጥ ሆነው በተመሰረለተላቸው ካምፕ የኤቨረስትን አየር ንብረት ለመላመድ  እስከ ስምንት ቀናት የሚቆዩበት ነው፡፡ ይህ ዋናው ካምፕ 5,380 ሜትር 17,700 ጫማ ላይ ይገኛል፡፡
ተራራ መውጣት እንዴት ጀመረ?
ሲራክ  ተራራ ወጭነቱን የጀመረው አብሮት የሚሰራ ጓደኛው በሰጠው ልዩ ምክር ነው፡፡ ከታድያስ መፅሄት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ እንደተጠቀሰው፡፡ የዓለማችንን ረጅሙ ተራራ ኤቨረስት በመውጣት የኢትዮጵያን ባንዲራ ጫፉ ላይ ሆነህ ብታውለበልብ ትልቅ ስኬት እንደሚሆን ጓደኛው ነግሯታል፡፡ አባት እና እናቱም የተራራ ወጭነት ህልሙን ገና ከጅምሩ ደግፈውለታል፡፡ ከ8 ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አባቱ ዶ/ር ስዩም ታቲቼፍ በሙያቸው ፓራሳይቶሎጂስት የነበሩ ሲሆን ታላላቅ ተራሮችን ለመውጣት የነበረውን ፍላጎት የሚደግፉ እንደነበሩ የማህበረሰብ ጤናና ትምህርት ባለሙያ የሆኑት እናቱ ዶ/ር ፋንታዬ መክብብ ደግሞ የተራራ ወጭነቱ ቁጥር 1 አድናቂውና ደጋፊው መሆናቸውንም ይናገራል፡፡
ሲራክ ተራራ ወጭነቱን የጀመረው በሄንደርሰን፤ ኔቫዳ የሚገኘውንና 1552 ሜትር ከፍታ ያለውን ››ብላክ ማውንቴን›› ለመውጣት በመወሰን ነበር፡፡ ተራራውን በወጣበት ወቅት ውሃ እና ቀለል ያሉ ምግቦችን አብዝቶ ይዞ ነበር፡፡ የተሸከመው ቦርሳ እስከ 22 ፓውንድ የሚከብድ መሆኑ ተራራውን በሚወጣበት ወቅት ተገንዝቦታል::  ይህን ሁኔታን በማስታወስ ለታዲያስ መፅሄት ሲናገር ሸክሙ ከመብዛቱ የተነሳ ኩንታል የተሸከመ ይመስለው እንደነበር ነው የገለፀው፡፡ ብላክ ማውንቴንን በመውጣት ያገኘው ልምድ ከሌሎች ተራራ ወጭዎች የተለየበትን አቋም የያዘበት ሆነ፡፡  ሌሎች ተራራዎችን ለመውጣት ሲያቅድ የተራራ ጉዞውን ለማቅለል ብሎ መሸከም ያለበትን ክብደት እንደማይቀንስ ራሱን በማሳመን ነበር:: ይሄ የጉዞ ሁኔታውም ከዓለም ተራራ ወጭዎች በልዩ ሁኔታው የሚያስጠቅሰው  ይሆናል፡፡ በቂ ስንቅ እና ምቹ አቅርቦቱን ስለሚፈልግ በእያንዳንዱ የተራራ ጉዞው ላይ እስከ 22 ፓውንድ ከባድ ሸክም ይዞ የሚጓዝ ተራራ ወጭ ነው ሲራክ፡፡ ብላክ ማውንቴንን በስኬት በመውጣት ጫፉ ላይ ለመድረስ ከቻለ በኋላ በኔቫዳና በካሊፎርኒያ የሚገኙ በአማካይ ከ3-4ሺ ሜትር ከፍታ ያላቸውን ተራራሮች አከታትሎ እስከጫፎቻቸው ድረስ ወጥቷቸዋል፡፡
ከኤቨረስት በፊት የነበሩት ልምዶች
ሲራክ ስዩም በተራራ ወጭነት ያካበተው ልምድ ከፕሮፌሽናል ተራራ ወጭዎች ተርታ ያሰልፈዋል፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት የላቀ ከፍታ ያላቸውን  ታላላቅ ተራሮች በተለያዩ ክፍለ አህጉራት እየተዘዋወረ በመውጣትና በየተራሮቹ ጫፎችም የኢትዮጵያን ባንዲራ በማውለብለብ ስኬታማ ሊሆን ችሏል፡፡  ከኤቨረስት በፊት በሰሜን አሜሪካ በተለይም በኔቫዳና ካሊፎርንያ ግዛቶች የሚገኙ ከ27 በላይ ተራራዎች እና ከፍተኛ ቦታዎችን አንዴ እና ደጋግሞ ወጥቷቸዋል፡፡ በደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ ከ4ሺ ሜትር በላይ የሆኑ ተራራዎችንም በቅርብ ዓመታት እስከጫፍ ወጥቷቸዋል፡፡
ከዓለማችን ታላላቅ ተራራ ወጭዎች ተርታ የሚያሰልፈው ሌላው ብቃት የወጣቸው ተራሮች ከፍታ   በ2015 ላይ በፔሩ  6354 ሜትር ከፍታ ያለውን ቾፒካልኩዊ  እንዲሁም 5752 ሜትር ከፍታ ያለውን የፒስኮ ተራራን የወጣ ሲሆን፤ በአይስላንድ 6189 ሜትር ከፍታ ያለውን ተራራ ወጥቷል፡፡
የኤቨረስት ተራራን ለመውጣት ቡድኑ፤ በጀቱና ዝግጅቱ
ሲራክ ስዩም በ2019 ኤቨረስትን ለመውጣት በሳቶሪ አድቬንቸር ኤንድ ኤክስፒዲሽን  በሚመራው ቡድን የተካተተው ዓለም አቀፍ ልምዱ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው፡፡ በጉዞ ኩባንያው ልዩ ድጋፍ ከሶስት ዓመት በፊት የጎበኛትን ኔፓልን መልሶ መርገጡ እና ኤቨረስትን የሚወጣበት እቅድ ለመተግበር በመቻሉ ተደስቷል:: በተራራ ወጭነት ሙሉ ዕውቀትና ዝግጅት እንዳለው የሚያስመሰክርበት አጋጣሚ ነው፡፡ የኤቨረስት ተራራን በመውጣትና ጫፉ ላይ  በመድረስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሚሆንበት ታሪክ ያጓጓዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን በአዲስ ተስፋ ሊያነቃቃበትም ፈልጓል፡፡
በሰሜንና እና ደቡብ አሜሪካ በርካታ ተራሮችን በመውጣት ያካበተው ልምድ ፕሮፌሽናል ተራራ ወጭ መሆኑን ቢያመለክትም፤ ኤቨረስትን ለመውጣት ከልምድ ባሻገር ወሳኙ እንቅስቃሴ ለጉዞ የሚያስፈልገውን በጀት ማግኘት ነበር፡፡ ስለሆነም  በGofundme በኩል በጓደኛው አባተ ሰብስቤ አማካኝነት የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ልዩ ዘመቻ ተዘጋጅቶ  ያለፉትን ወራት እንቅስቃሴ ተደርጎበታል:: የኤቨርስት ተራራን ለመጀመርያ ጊዜ የሚወጣ ኢትዮጵያዊ በሚል ርእስ በድረገፁ ላይ በተሞከረው የገቢ ማሰባሰብ ዘመቻ 30ሺ ዶላር ተጠይቆ ነበር፡፡ ከተለያዩ የማበረታቻ አስተያየቶች ባሻገር ከተለያዩ 18 ድጋፍ ሰጭዎች  የተገኘው 2500 ዶላር ብቻ ነው፡፡ የጎፈንድሚ እንቅስቃሴ አላዋጣም:: የኤቨረስት ተራራን ለመውጣት በሲራክ የተያዘው  በጀት  ከ65330 ዶላር ላይ ስለነበር ከላይ ከተጠቀሰው የበጀት መጠን   40700 ዶላሩን  ለመሸፈን ወስኖ ጉዞውን ጀምሮታል፡፡ በበጎፈንድሚ በተካሄደው ዘመቻ ጎን ለጎን  የበጎ ፍቃድ ስራን እንደሚያከናውን ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር 2865 ታዳጊዎችና ወጣቶችን ከጎዳና ለማንሳት የሚሰራበትን ፕሮጀክት ለመደገፍ  ነው፡፡ ተራራ ወጭነቱን ከዚህ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ጋር ለማስተሳሰር ይፈልጋል፡፡
ኤቨረስትን በአጭሩ
ኤቨረስት የሂማሊያ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ የሚገኝ የዓለማችን ከፍተኛው ተራራ ሲሆን ሁለት አገራት ያዋስኑታል፡፡ የቻይናዋ ግዛት ቲቤትና  ኔፖል ናቸው፡፡ በኔፓል ኤቨረሰትን  ሳጋርማታሃ ብለው የሚጠሩት ሲሆን የሰማይ ግንባር እንደማለት ነው፡፡ በቲቤት ደግሞ እናት ምድር ወይም እናት አለም ብለው ይጠሩታል፡፡ በ1841 ላይ ጆርጅ ኤቨረስት በተባለ ግለሰብ በመገኘቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ ስያሜውንም ከዚያው አግኝቷል፡፡ ኔፓል የተራራውን ከፍታ ከባህር ወለል በላይ 8848 ሜትር መሆኑን በይፋ ብትገልፅም በቻይና በኩል ከፍታው  8850 ሜትር መሆኑን የሚገልፁ አከራካሪ መረጃዎች አሉ፡፡
በየዓመቱ  በዚህ ወቅት ላይ ከ60ሺ በላይ ተራራ ወጭዎች፤ ቱሪስቶችና የጉዞ መሪዎቻቸው የኤቨረስት ተራራን ለመውጣት እና ለመጎብኘት በኔፓል እና በቲቤት ይገኛሉ፡፡ በተለይ ኔፓል የፀደይ ወራት ስለሚገባ ታላቁን የኤቨረስት ተራራን ለመውጣት አመቺ ይሆናል፡፡   ለዚህም ዋናው ምክንያት በተራራው ዙሪያ የሚነፍሰው ሃይለኛ ነፋስ በአሁኑ ወቅት ላይ ጋብ ስለሚል ነው።
በመጀመርያ ደረጃ ኤቨረስትን ወጥቶ ጫፉ ላይ ለመድረስ በቂ ዝግጅት፤ የዓለማ ቁርጠኝነት፤ የስነልቦና ጥንካሬ እና ብቁ የአካል ብቃት አስፈላጊ ናቸው:: የኤቨረስት ተራራን በመውጣት ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ማስቀመጥ የሚፈልጉ ሁሉ ተራራውን ከመውጣታቸው በፊት ከ10 ወር እስከ 1 ዓመት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለብዙዎቹ ተራራውን እስከጫፍ በመውጣት ልዩ መልክዓ ምድርና የብርሃን ፀዳልን መላበስ የሞራል ስንቃቸው ነው፡፡ በየቡድኖቻቸው ከተራራው ጫፍ ደርሰው አብረው የተጓዙ ጓደኞቻቸው፤ ወላጆቻቸው ፣ ዘመዶቻቸው አገራቸው ለማስታወስ በመጓጓት ተነሳሽነቱን ይፈጥራሉ፡፡ በኤቨረስት ጫፍ ላይ የአገራቸውን ባንዲራም የሚያውለበልቡበት ባህልንም ለማሳካት ይነሳሳሉ፡፡
8,848 ሜትር ከፍታ ያለው ኤቨረስት በተለያዩ ሁኔታዎች ለተራራ ወጭዎች አስቸጋሪ እና  አደገኛ ነው። ተራራው ላይ ሲወጣ ያልተጠበቁ የመደርመስና የናዳ አደጋዎች፣ የበረዶ ግግር በመቅለጥ የሚፈጠረው ናዳ፤ ሃይለኛ አውሎንፋስ ፤ አተነፋፈስ ችግር እና ከበረዶ ጋር የሚያያዙ ድንገተኛ በሽታዎች ያጋጥማሉ፡፡
ተራራው በተለያዩ ከፍታዎች ላይ ፈታኝ ሁኔታዎች የሚጋረጡበት ሲሆን በአብዛኛው የተራራው ክፍል ኦክሲጅን የባህር ወለል ላይ ከሚገኘው በሲሶ ማነሱ፤ አፋጣኝ ህክምና እና የዶክተር ድጋፍ ማግኘት የሚቻለው እስከ 5400 ሜትር መሆኑንም መጥቀስ ያስፈልጋል:: በሌላ በኩል 7500 ሜትር ላይ የተራራው የሞት ዞን ያለ ሲሆን ሲሆን ከበረዶ ግግር በተያያዘ የሚከሰቱ በሽታዎች ለሞት ስለሚያጋልጡ ነው፡፡ ቢቢሲ በቅርቡ እንደዘገበው የኤቨረስት ተራራ ላይ ያሉት የበረዶ ግግሮች በየጊዜው ከመቅለጣቸው ጋር ተያይዞ በተራራው የተለያዩ ክፍሎች አስክሬኖች መታየት ጀምረዋል፡፡ በተራራው ላይ ህይወታቸው ያለፉ ተራራ ወጭዎችን አስክሬን ለማንሳት በሰው እስከ 60ሺ ዶላር ማስፈለጉ የቢቢሲ ዘገባ ጠቅሷል፡

Read 7142 times