Saturday, 13 April 2019 13:13

አቶ ጌታቸው አሰፋ በሌሉበት ሊከሰሱ ነው

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(5 votes)

 በአገር ውስጥ ተቀምጠው በሌሉበት መከሰሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል
                            
      የቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደህነንት መሥሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና ለዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሞት ተጠያቂ ናቸው ተብለው  የተጠረጠሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ፤ በሚቀጥለው ሳምንት በሌሉበት ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑን ምንጮች ጠቆሙ፡፡  
የቀድሞው የደህንነት መ/ቤቱ ሃላፊ የነበሩት  አቶ ክንፈ ገ/መድህን በሞት መለየትን ተከትሎ፣ ከ1993 ጀምሮ በደህንነት መ/ቤት በዋና ዳይሬክተርነት ሲሰሩ የቆዩት አቶ ጌታቸው አሰፋ፤የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ  ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከሃላፊነት ከተነሱ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፉ ናቸው፡፡
 ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከደረሰው የቦንብ አደጋ ጋር ተያይዞ እጃቸው እንዳለበት እንዲሁም በዜጎች  የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሞት ተጠርጥረው ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑ ከጥቂት ወራት በፊት ተገልጦ ነበር፡፡ ፡  
በደህንነትና መረጃ  መ/ቤት የስልጣን  ቆይታቸው ወቅት ከመንግስት እውቅና ውጪ የራሳቸውን እስር ቤት በመፍጠርና ህጉ ከሚያዘው ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መልኩ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጣረሱ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ ትእዛዝ ሰጥተዋል፤በቀጥታም ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩት አቶ ጌታቸው፤ ሌሎች በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ የቀድሞው የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በፍርድ ቤት ክስ ቢመሰረትባቸውም፣ እሳቸው ግን የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከለላ ስለሰጣቸው ሊከሰሱ አለመቻሉን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ  ለፓርላማ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በህግ የሚፈለጉት አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ ሃላፊ ሆነው  መሾማቸው አነጋጋሪ ሆኖ ቢቆይም፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል  በቅርቡ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ አቶ ጌታቸው አሰፋ አልተሾሙም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው በወቅቱ  የት እንደሚገኙ የተጠየቁት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ”ተደብቀዋል” ማለታቸው አይዘነጋም:: ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ አቶ ጌታቸው አሰፋን ለህግ ለማቅረብ የክልሉ መንግስት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ለሁለተኛ ጊዜ መጠየቃቸውን ለማወቅ ባይቻልም፣ በሌሉበት ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሏል፤የክሱ ይዘት በትክክል ባይታወቅም፡፡  
ምንጮች እንደሚሉት፤ ከጠ/ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ፣ በእስረኞች ላይ ከሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ከሙስና ጋር የተያያዙ ክሶች ሊመሰረትባቸው ይችላል፡፡  


Read 10341 times