Saturday, 06 April 2019 15:55

በአለማችን ከ113 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በከፋ ረሃብ ተጠቅተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 በአለም ዙሪያ በሚገኙ 53 አገራት ውስጥ የሚኖሩ ከ113 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የከፋ የምግብ ዋስትና ችግርና የረሃብ ተጠቂ መሆናቸውንአንድ አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአመቱ በአለማችን እጅግ በከፋ የምግብ እጥረት ቀውስ የተመታችው ቀዳሚዋ አገር የመን እንደሆነች ባለፈው ረቡዕ በብራስልስ ይፋ የተደረገው የተመድና የአለም የምግብ ድርጅት የ2019 አለማቀፍ የምግብ ቀውስ ሪፖርት አስታውቋል፡፡ከየመን በመቀጠል እንደቅደም ተከተላቸው በአመቱ በከፍተኛ ሁኔታ በምግብ እጥረትና በረሃብ የተጠቁት አገራት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢትዮጵያ፣ ሶርያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ናይጀሪያ እንደሆኑ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአለማችን የችግሩ ሰለባ ከሆኑት 110 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 72 ሚሊዮን ያህሉ በእነዚህ ስምንት አገራት ውስጥ እንደሚገኙም አስረድቷል፡፡
በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት የምግብ እጥረትና ርሃብ እንዲከሰት ዋነኛ ምክንያት ናቸው ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱት ጉዳዮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ የተፈጥሮ አደጋዎችና የእርስ በእርስ ግጭቶች ናቸው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ በአለማችን በየአመቱ ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 20 በመቶ ያህሉ የ11 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ከአመጋገብ ችግር ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ላሰንት ሜዲካል ጆርናል ያወጣውን አለማቀፍ ጥናት ጠቅሶ ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከአመጋገብ ችግር ጋር ተያይዞ በአለማችን በየአመቱ ለሞት ከሚዳረጉ ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በቂ ጥራጥሬዎችንና ፍራፍሬዎችን በበቂ መጠን ካለመመገብና ከፍተኛ መጠን ያለው ጨው ከመመገብ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ በሽታዎች ሳቢያ የሚሞቱ ናቸው ያለው ጥናቱ፤ የተቀሩት ደግሞ ጥሬ ስጋና የተቀነባበረ ስጋና ስኳር ያለባቸው ጣፋጭ መጠጦችን በመጠቀምና ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን በመመገብ ለሞት እንደሚዳረጉ አመልክቷል፡፡

Read 1158 times