Saturday, 06 April 2019 15:07

እዚህም ሌላ መስኮት አለ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

    ወንድና ሴት ተቃራኒዎች ናቸው ይባላል፡፡ ከእሱ ይልቅ የሚበልጠው የማይሽረውና ዘለዓለምም ፀንቶ የሚኖረው ተፈላላጊነታቸው ነው፡፡ አለምን አለም ያደረጓትና፣ አለምን የተሸከሟት ሁለቱ ምሰሶዎች ወንዱና ሴቷ ናቸው፡፡ ዘመን እያዘመነ የመጣው፣ እንዲዘመነም የሚቀጥለው በሁለቱ መፈላለግ በሚተካው ትውልድ ነው፡፡ መፈላለጋቸው ግን ለሕግና ለሥርዓት የተገዛ ሊሆን ይገባል ግድ ያስፈልጋልም፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የተቀናጀ የሴቶችና ሕፃናት እንክብካቤና ፍትሕ ማዕከል ዋና ሥራ፣ የወሲብ ጥቃት ለደርሰባቸው ብዙ ጊዜ ለሴቶች አልፎ አልፎ ደግሞ ለሕፃናት ወንዶች እንክብካቤና የሕግ አገልግሎት ድጋፍ  መስጠት ነው፡፡
የማዕከሉ ዋና አስተባባሪ ሲስተር መሠረት ዲባባ፤ ማዕከሉ ከ ተቋቋሙ የአስር ወር እድሜ እንዳለው ገልጠዋል፡፡ የወሲብ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወደ ማዕከሉ የሚመጡት ሴቶች ወይም ወጣት ወንዶች ማዕከሉ ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሊቆዩ የሚችሉት ለሰባ ሁለት ሰዓት ወይም ለሶስት ቀን መሆኑን ነግረውኛል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም የኤችአይቪ ኤድስን ጨምሮ የጤና ምርመራ እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል፡፡
የእርግዝና ጉዳይ ከአጋጠመም እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች ፈጥነው ወደ ማዕከሉ ከመጡና ጽንስ የማቋረጡ ሂደት ሴትየዋ ላይ ችግር የማያስከትል ሆኖ ከተገኘ ነው፡፡
በንግዱ አለም የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚባል አለ፡፡ ነጋዴው ከመንግሥት የሚፈልገውን አገልግሎት ከአንደኛው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ወደ ሌላኛው የሚኒስቴር መ/ቤት ወይም መምሪያ ሳይንከራተት ሁሉንም አንድ ቦታ እንዲያገኝ የሚያደርግ እዚህም እንዲያ ነው፡፡ የወሲብ ጥቃት የተፈፀመባቸው ወገኖች የጤና ምርመራ የሚያደርግላቸውን ሐኪም፣ ወንጀሉን የሚያጣራውን ፖሊስ፣ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አደባባይ የሚያደርሰው አቃቤሕግ ብቻ ሳይሆን ከደረሰባቸው የሥነ አእምሮ ጉዳት ያገግሙ ዘንድ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችንም በማዕከሉ ያገኛሉ፡፡ አንድ መስኮት ማለት ይህ አይደል?
ይህ መሆኑ ደግሞ ተጐጂዎቹ በየቦታው በየደረሱበት ጉዳታቸውን ደጋግሞ በመተረክ የሚደርስባቸውን የመንፈስ ስብራት እንዲቀንስ ከማድረጉ በላይ ምን አልባትም በድግግሞሹ መባዛትና ሊከተል የሚችለውን ተስፋ መቁረጥም ያስቀራል ተብሎ ይታመናል፡፡
በቤተሰቡ ውስጥ እናትና አባት እህትና ወንድም ይገኛሉ፡፡ እህትና ወንድም በአባት አይገናኙም፡፡ ወንዱ ልጅ እህቱን ማለትም የእናቱን ልጅ ይደፍራል፡፡ ቤተሰብ ተጠራጥሮ ጉዳዩን ለፖሊስ ያደርሳል፡፡ ልጅ ይያዛል ሁለቱም ወደ ማዕከሉ መጥተው ልጅቷ ተገቢውን እንክብካቤ ማግኘቷን ሲስተር መሰረት ገልጠዋል፡፡ ልጅቷ በእድሜ 15 ዓመት ላይ እንደነበረች አስታውሰውም የእርግዝና ችግር እንዳልነበረም አሳውቀዋል፡፡
“መደፈር ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ በሽታ አይደለም” በማለት በምሬት የሚናገሩት ሲስተር መሠረት፤ በዚህ አስር ወር ውስጥ ከገጠማቸው የፆታ ጥቃቶች በአንድ የመንግሥት ሠራተኛ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ምን ጊዜም ከኅሊናቸው ሊጠፋ እንደማይችል ገልጠዋል፡፡ እሳቸው እየተጨነቁ በሀዘን ተውጠው የነገሩኝን እኔም ለመስማት እየከበደኝ ያደመጥሁትን ታሪክ እንደ አለ ማቅረብ ይከበዳል፡፡
ሴትዮዋ ከሥራ ወጥታ ወደ ቤቷ የሚወስዳትን የመ/ቤት መኪና እየጠበቀች ነው፡፡ አንድ ሰው ሰላምታ ሰጥቶ ያናግራታል፡፡ ወደ ቤቷ ለመሄድ ሰርቪስ እየጠበቀች መሆኑን ትነግረዋለች፡፡ ጩቤ አውጥቶ እጇን ይወጋታል፡፡ የሚሰጣትን ትእዛዝ በዝምታ እንድትቀበል እምቢ ብትል ሕይወቷን እንደሚያጠፋው ይዝታል፡፡ ለሕይወቷ በመስጋቷ ተከትለው ትሄዳለች፡፡ አንድ የመኝታ ክፍል ይዟት ይገባል፡፡
ከመደበኛው ፆታዊ ግንኙነት ባፈነገጠ መንገድ ለሊቱን ሙሉ ሲያሰቃያት ያድራል፡፡ ሰውዬ የግበረሰዶም ልምድ ያለው ሊሆን ይችላል ፈንጢጣዋ ተጉድቷል፡፡ በጣም የሚከፋው የሰውየው ተግባር ደግሞ እያንዳንዱን ድርጊቱን በፎቶግራፍና በቪዲዮ መቅረፁ ነው፡፡ የተለያት “ለፖሊስ ብታመለክች ፎቶውንና ቪዲዮውን ፌስቡክ ላይ እለጥፈዋለሁ” በማለት ነው እሷ ግን ይህ ማስፈራሪያ የሚበግራት ሴት አልነበረችም፡፡ ለፖሊስ ሪፖርት አድርጋ ሰውየው ከነስልኩ ለመያዝ በቅቷል፡፡ ስልኩ በተፋተሸ ጊዜም ተመሳሳይ ጥቃት የተፈፀመባት የሌላ ሴት ፎቶ መገኘቱም ታውቋል፡፡
በአማካይ በቀን አምስት ያህል ጥቃት የተፈፀመባቸው ሰዎች ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡ ሲስተር መሠረት ዲባባ ጠቅሰው፤ ይህ ቁጥር በብዙ ምክንያት እየተደበቀ ከሚቀረው የተረፈ ስለሆነ ዝቅ ተደርጐ መታየት እንደሌለበት በአጽንኦት አስግነዝበዋል፡፡
ማዕከሉ ከሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት የሚሠራ ሲሆን፤ ከቤተሰብ አባላት በአንዱ ጥቃት ተፈፅሞባቸው ተመልሰው ቢቀላቀሉ፣ ተጨማሪ ጥቃት ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ በሚታመንበት ጊዜ ድጋፍ ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኛቸው የሚኒስትር መ/ቤቱ መሆኑን ሲስተር መሠረት አመልክተዋል፡፡
በማዕከሉ በነበረው ቆይታዬ፣ ወደ ማዕከሉ ከሚመጡ ሰዎች ችግር ክፋት ሠራተኞች የራሳቸውን ልብስ ሳይቀር ሰጥተው የሚሸኙበት ጊዜ እንዳለ ተነግሮኛል፡፡ ሲስተር መሠረት ደግሞ “ማዕከሉ የራሱ መኪና የለውም የሚገለገለው የሆስፒታሉን ነው በተለይ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ተደፍረው በሚመጡበት ጊዜ ችግሩ ይብስብናል” ብለውኛል፡፡
በጋንዲ መታሰቢያ እና በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተመሳሳይ ማዕከሎች ያሉ ሲሆን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም በአዲስ አበባ አራተኛው ማዕከል በመቋቋም ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
በየአቅራቢያቸው የሰውና የድርጅት አቅም ባላቸው እንደ ጅማ፣ ጐንደር፣ ባሕርዳር ወዘተ ሪፈራል ሆስታሎች አገልግሎቱን ማስጀመር እንደሚቻል እናምናለ ፡፡
ችግሩ ግን ሰፊ ነው፡፡ ከቤተሰብና ከመንደር ጀምሮ በጠቅላላም በአገር አቀፍ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ኢንሸየቲቭ አፍሪካ በማንኛውም መልኩ በሴቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ሊወገዱ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን እያሳወቀ፣ ጥቃቶች የሚያስከትሉትን ተጓዳኝ ጉዳት የሚያስገነዝቡ ስራዎች እየሠራ ነው፡፡ ይህ የሌሎችንም ርብርብ ይጠይቃል - ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፡፡

Read 1139 times