Saturday, 06 April 2019 15:05

አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይነቃም

Written by 
Rate this item
(12 votes)


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ነገር የገባው ሰው አዳማ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡
ታሪኩ ሲጠቀስ ከንጉሳውያን ቤተሰብ አፈንግጦ፤ መጀመሪያ ወደ አርሲ፣ ቆይቶ ወደ ናዝሬት (አዳማ) የመጣ ሰው ነው!
ይሄው ሰው ምንም እንኳ በልጅነቱ ከንጉሳውያኑ አፈንግጦ፣ በአርሲ የአህያ ሌንጬጭ እየሳበ ሸክሙን ወደ ዚታዎው (መኪና) የማድረስ ሥራ ይሰራል፡፡ ለዚህ ልፋቱ ዋጋው አስር የኢትዮጵያ ሳንቲም ብቻ ነው!
ሆኖም፤ አስር ሳንቲሞቹ ተጠራቅመው የዛሬውን ባለ ዚታዎና፣ ባለ ጎተራ ሰው ፈጠሩ! ያገሩ ሀብታም፣ ያገሩ ዲታ እሱ ሆነ! በአዳማ!
ስለዚህ ስለ ዲታ ሰው ስንፅፍ በኩራት ነው፡፡ ምክንያቱም ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ቦታ መድረስ ዋና ጉዳይ ነው፡-
ከአዝራር መሸጥ ተነስተው “ባንኩ ደህና አደረ?” እስከ ማለት የደረሱት ኢንተረፕሩነር ታላቅ አስተማሪያችን የመርካቶ ሰው ናቸው! ብርን ከትራስ አውጥቶ ወደ ባንክ ማህደር ማስገባት ትልቅ የአዕምሮ ስልጣኔ ነው፡፡ የብሔራዊ ከበርቴውን ሚና ዛሬም ከ45 ዓመታት በኋላ እንጠቅሰዋለን፡፡ ባይሰማ፤ አውቆ - የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም ብለን እንተወዋለን!
***
ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያን ነባር የኢኮኖሚ መሰረቶች መርሳት ከቶም በሀገራችን ላይ ትልቅ ጥፋት ማድረስ ብቻ ሳይሆን፤ መሰረታችንን እየናድን ወዴት እንደርሳለን የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ፊታችን ላይ ድቅን እንዲል ማድረጉ አይቀሬ ከመሆን እንዳይዘለል ያደርጋል! ከቶውንም እኔ ተጎድቻለሁና የአገር ኢኮኖሚ ኖረም አልኖረም፤ ፈፅሞ አያገባኝም፤ (ለሚሉ ወገኖች) ብዙ የችግሮች መዳረሻዎች፣ የብዙ ፈተናዎችና እንቅፋቶች መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢረዱ መልካም ነው፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ዲታ ሰውዬ ይህን ይላሉ፡- በጥንት በጃንሆይ ዘመን አዳማም ቤተ መንግስት ነበር፡፡ በኋላ ቤተ መንግስቱ ቀረና ወባ ማጥፊያ ሆነ፡፡ ቀጥሎ ወባ ማጥፊያው ቀረና የፖለቲካ ድርጅት ማጥፊያ ሆነ (ኢህአፓ፣ መኢሶን ወዘተ) ደሞ ቀጠለና የዘር ማጥፊያ ሆነ፡፡ ነገ ከናካቴው የትውልድ ማጥፊያ እንደማይሆን ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ጉዞው ከጥፋት ወደ ጥፋት ነው - ሁሌ ከድጡ ወደ ማጡ! አሊያም ዱሮ እንደተፃፈው ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ!
በተደጋጋሚ እንደገለፅነው ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ የተሳቱ አጋጣሚዎች መናኸሪያ ናት፡፡ 1966 ዓ.ም፣ 1969 ዓ.ም፣ 1997 ዓ.ም እንዲሁም ዛሬ፡፡ ዛሬን ሙሉ ለሙሉ አልሳትነውም፤ ለማለት ቢቻልም የዛኑ ያህል የህዝብ ንቃት ካልተጨመረበትና መሪዎቻችን ካልነቁ፣ የመቀልበስ አደጋ አለ፡፡ አልነቃንም ካሉ፤ “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይነቃም”ን እንተርታለን!!

Read 12170 times