Saturday, 30 March 2019 13:06

ባለፉት 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


          • ኢትዮጵያ በ264 ሜዳልያዎች ከዓለም 2ኛ
          • አትሌት ቀነኒሣ በቀለ 27 ሜዳልያዎችን (16 ወርቅ፣ 7ብር ና 2 ነሐስ) ከዓለም አንደኛ
          • አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ በሴቶች ምድብ 21 ሜዳልያዎችን (11 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሐስ)
          • 174 አገራትን በመወከል 11,683 አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡


          43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ዛሬ በዴንማርኳ ከተማ አሩሁስ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡድን ባለፉት ሶስት ሻምፒዮናዎች በኬንያ የተወሰደውን ብልጫ እንደሚያጠብብ ተገምቷል፡፡ 67 አገራትን የሚወከሉ 582 አትሌቶች ተሳታፊ በሚሆኑበት ሻምፒዮናው በአዋቂዎች ምድብ 171 ወንዶች እና 139 ሴቶች እንዲሁም በሀ 20 የወጣቶች ምድብ  121 ወንዶች እና 111 ሴቶች ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ ሁለቱንም ፆታዎች በሚያሳትፈው የድብልቅ ውድድር ላይ  ደግሞ 10 ቡድኖች ተመዝግበዋል፡፡ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ  310ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት  ያቀረበ ሲሆን በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታዎች የሚያሸንፉት 30ሺ ዶላር እንደሚሸለሙና በድብልቅ ውድድር የሚያሸንፈው ቡድን ደግሞ ሽልማቱ 12ሺ ዶላር እንደሆነ ታውቋል፡፡
በአዋቂ ወንዶች የ10 ኪሎሜትር ውድድር አዲስ ሻምፒዮን እንደሚፈጠር ቢገመትም፤ ባለፉት ሁለት ሻምፒዮናዎች አከታትሎ ያሸነፈው የ26 ዓመቱ ኬንያዊ ጂዮፍሪ ኪምዎሪር ለሶስትኛ ጊዜ እንደሚያሸንፍ የጠበቁም አሉ፡፡  የዓለም ግማሽ ማራቶንን ለሶስት ተከታታይ ዓመታት አከታትሎ ያሸነፈው ኪምዎሪር፤ ወደ ሻምፒዮናው ለመግባት ኬንያ ውስጥ በተደረገ ማጣርያ አምስተኛ ደረጃ ነበረው፡፡ ከኪምዎሪር ሌላ የ19 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሰለሞን ባረጋም ልዩ ግምት አግኝቷል፡፡ በ5ሺ ሜትር የትራክ ውድድር ከምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች አንዱን ያስመዘገበውና እና በጎዳና ላይ ሩጫ የተወሰነ ልምድ ያለው አትሌት ሰለሞን  ፈጣን አሯሯጩን ከፈታኙ የአገር አቋራጭ ውድድር ጋር በማዋሃድ ያልተጠበቀ ድል ሊወስድ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በአዋቂ ወንዶች በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈችው በ2011 እኤአ ላይ በኢብራሂም ጄይላን አማካኝነት ነበር፡፡ ኬንያዊው ኪሩዊ  እና ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጊ ሌሎቹ ተፎካካሪዎቹ ሲሆኑ፤ በጃንሜዳ አገር አቋራጭ ያሸነፈው ሞገስ ጥኡማይ ጠንካራ ተሳትፎ ይኖረዋል፡፡
በአዋቂ ሴቶች ምድብ የኬንያ አትሌቶች ከ2 ዓመት በፊት ካምፓላ ላይ ከ1 እስከ 6ኛ ደረጃ በመግባት የወሰዱትን የበላይነት ለማስጠበቅ ቢያቅዱም፤ የዘንድሮ ተሳታፊዎች ባለፈው ውድድር ላይ ያልነበሩ አዳዲስ አትሌቶች መሆናቸው ስኬቱን አጠያያቂ አድርጎታል፡፡ በ2015 እና በ2017 እኤአ በወጣት ሴቶች ምድብ አከታትላ ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ ዘንድሮ በአዋቂዎች ምድብ ተሰልፋ  ለሜዳልያ የምትጠበቅ ሆናለች፡፡ ከ2 ዓመት በፊት በወጣት ሴቶች ምድብ ለተሰንበትን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳልያ የወሰደችው ሃዊ ፈይሳም ልዩ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ “AAHRUS 2019 Facts & Figures” በሚል ርዕስ ከ1981 እኤአ ጀምሮ  የተካሄዱትን 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች የውጤት እና የሜዳልያ ዝርዝር የያዘውን ባለ 147 ገፅ ሪፖርት ይፋ ያደረገው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ከመካሄዱ በፊት ነው፡፡ በሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተው ባለፉት 42  የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች 174 አገራትን በመወከል 11,683 አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡ በሁሉም የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ በመሳተፍ 5 አገራት የሚጠቀሱ ሲሆን እነሱም እንግሊዝ፣ ሰሜን አየርላንድ፣ ጣሊያን፣ ስፔንና አሜሪካ ናቸው፡፡ ከአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ አባል አገራት መካከል ደግሞ 51 በጭራሽ የዓለም አየር አቋራጭ ሻምፒዮናን ተሳትፈው አያውቁም፡፡
ባለፉት 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በሁሉም የውድድር መደቦች 316 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ የሆነችው ኬንያ ስትሆን ኢትዮጵያ በ264 ሜዳልያዎች እንዲሁም አሜሪካ በ63 ሜዳልያዎች በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ይከተላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የሜዳልያ ስብስብ በማግኘት ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ 27 ሜዳልያዎችን (16 ወርቅ፣ 7ብር ና 2 ነሐስ) በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ነው፡፡  በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ 21 ሜዳልያዎችን (11 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሐስ) በመሰብሰብ ዓለምን ትመራለች፡፡  ባለፉት 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ለቡድን ሽልማት ከቀረቡ 171 ሜዳልያዎች ኬንያና ኢትዮጵያ 132 ድሎችን የተከፋፈሉ ሲሆን ሁለቱ አገራት በ153 የቡድን ውድድሮች ተገናኝተው 83 ጊዜ ኢትዮጵያ ስትሸነፍ 50 ድል የኬንያ ሆኗል፡፡
በብዙ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ በመሳተፍ የሚጠቀሱት የኢትዮጵያ አትሌቶች ደግሞ 12 ሻምፒዮናዎችን የተሳተፈችው መሪማ ደንቦባ እና እያንዳንዳቸው 11 ሻምፒዮናዎችን የተሳተፉት ጌጤ ዋሚ እና ጌጤ ኡርጌ ናቸው፡፡
ባለፉት 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ  በወንዶች 21 እንዲሁም በሴቶች 21 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1 በላይ ሜዳልያዎችን ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን  ከዚህ በታች የቀረበው በሜዳልያ ስብስባቸው ከ1-10 ያላቸው ደረጃ ነው፡፡


______________________

                በወንዶች                                            ወርቅ        ብር         ነሐስ
ቀነኒሣ በቀለ - 27 ሜዳልያዎች                                    16          9            2
ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም -16 ሜዳልያዎች                 6          7            3
ሐይሉ መኮንን - 11 ሜዳልያዎች                                   2          6            5
አሰፋ መዝገቡ - 11 ሜዳልያዎች                                    1          8            2
በቀለ ደበሌ- 9 ሜዳልያዎች                                           5          2            2
ሚሊዮን ወልዴ- 8 ሜዳልያዎች                                      2         5             1
መለስ ፋይሣ- 8 ሜዳልያዎች                                          2         3             3
ስለሺ ስህን- 8 ሜዳልያዎች                                            1         5             2
ወዳጆ ቡልቲ- 7 ሜዳልያዎች                                          4         1             2
መሐመድ አወል- 7 ሜዳልያዎች                                      2         4              1



             በሴቶች                                               ወርቅ           ብር            ነሐስ
ወርቅነሽ ኪዳኔ- 21 ሜዳሊያዎች                            11               6                4
ጥሩነሽ ዲባባ -20 ሜዳልያዎች                                14              6                 -
ጌጤ ዋሚ -19 ሜዳልያዎች                                     9               8                2
መሰለች መልካሙ -18 ሜዳልያዎች                           9               4                 5
መሪማ ደንቦባ -15 ሜዳልያዎች                                6                7                 2
ደራርቱ ቱሉ -12 ሜዳልያዎች                                  6                5                 1
ገለቴ ቡርቃ -9 ሜዳልያዎች                                     6                2                 1
አየለች ወርቁ -9 ሜዳልያዎች                                    4                3                 2
ጌጤነሽ አርጌ- 9 ሜዳልያዎች                                   1                 7                 1
ብዙነሽ በቀለ - 8 ሜዳልያዎች                                  5                 3                  -

Read 1471 times