Saturday, 23 March 2019 13:48

የ”ኬኛ” ፖለቲካ እንዴት ያሰልፋል?

Written by  መስከረም አበራ
Rate this item
(6 votes)

“--በዚህ ሁሉ ውስጥ ሚናውን ያልለየው፣ ድምፁን ያጠፋው የተቃውሞ ጎራ አሰላለፉ ከወዴት እንደሆነ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ የተቃውሞ ጎራው ሃገሪቱ እንዲህ አቅጣጫ በጠፋት ጊዜ ብቅ ብሎ ህዝቡን ካላረጋጋ፣ ህልውናው ለመቼ እንደሚያስፈልግ ግልፅ አይደለም፡፡ --”
                       
           ኦህዴድ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት የሚያደርጋቸው ድርጊቶች፣ “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው” ያስባለው የስልጣን ጥም አላማው፣ የኦሮሞ የበላይነትን ማስፈን እንደሆነ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ የኦሮሞ የበላይነት ፖለቲካ ደግሞ ሊያሳካቸው ከሚፈልጋቸው ዋና ነገሮች አንዱ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛትና የጨፌ ኦሮሚያ ተገዥ ማድረግ ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ የኦሮሚያ ግዛት አካልም ሆነ የጨፌ ኦሮሚያ ተዳዳሪ ያልሆነችውን አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት የማድረጉ የኦነግ/ኦዴፓ ህልም የሚታለመው፣ ህገ-መንግስቱ አንድም ዓረፍተ-ነገሩ እንዳይነካ በሜንጫ በሚያስፈራሩ ወገኖች መሆኑ ነገሩን ግራ ያደርገዋል፡፡
የህገ-መንግስቱ አንድም መስመር ሳይነካ፣ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት፣ የጨፌ ኦሮሚያ ተገዥ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ለሚለው ወሳኝ  ጥያቄ፣ ኦዴፓ/ኦህዴድ አስቻይ አድርጎ የያዘው መንገድ፣ የፌደራል ስልጣን የመጨበጡን መልካም እድል፣ የቆየውን የተበድዬ ተረክ፣ የኢህአዴግን የፓርቲ አወቃቀርና አሰራር (የአጋር/አባል ፓርቲ ነገር) ሊሆን ይችላል፡፡ ህወሃት ሊወድቅ ሲንገዳገድ፣ ኦህዴድን አባይ ማዶ ድረስ ያበረረው የስልጣን አምሮት ምንጩ፣ ስልጣን መያዝ የልብን ለመስራት ቁልፍ ነገር እንደሆነ በአቶ መለስ  ህወሓት ስለተማረ ሳይሆን አልቀረም፡፡
አቶ መለስ ስልጣን ላይ መቀመጣቸው በዘረፋ ሳይቀር የወገንን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዳስቻላቸው ኦህዴድ በደንብ ተገንዝቧል። ስለዚህ አይገቡ ገብቶ፣ አያወሩ አውርቶ፣ የማይከበር ቃል ገብቶ ስልጣን ላይ ተሰየመ፡፡ ከዚያ በኋላ ኦነግ ሲያምረው የቀረውን ነገር ሁሉ በአንድ ጀምበር ለማከናወን በከፍተኛ መራወጥ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ነገር ይሰምራል ወይ? የዛሬዋ ኢትዮጵያም ሆነች የዛሬው ኢህአዴግ አቶ መለስ እንደነበሩባቸው ዘመናት ያሉ ናቸው ወይ? የሚለውን ነገር ኦህዴድ በቅጡ የመረመረ አልመሰለኝም፡፡ የሆነ ሆኖ ኦዴፓ/ኦህዴድ “የኬኛ ፖለቲካውን ለማሳካት ሲንቀሳቀስ የሚያግዙትም ሆኑ የሚያደናቅፉት እውነታዎች አይጠፉም፡፡ እነዚህን እውነታዎች  መመርመሩ አስፈላጊ ነውና፣ ለ”የኬኛ” ፖለቲካ  አስቻይ መሰረቶችን በማየቱ እንጀምር፡፡
የተበድዬ ተረክ
በሃገራችን የተንሰራፋው የዘውግ ፖለቲካ፣ የትግሉ መነሻ በደልን መተረክ ሲሆን መዳረሻው ደግሞ አይኑ የወደደውን ሁሉ “የእኔ ነው” የማለት አካሄድ ነው፡፡ አይን የወደደውን የራስ ለማድረግ ደግሞ የተበድዬ ፖለቲካን መተረክ ዋነኛው የስኬት መንገድ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ እያጋነኑም እየፈጠሩም በደልን ማውራት ሁለት ጥቅም አለው፡፡ አንደኛ የዘውግ መሰሎችን በቁጭት ለማነሳሳት ይረዳል፡፡ በዘውጉ ምክንያት ብቻ እንደተጨቆነ የሚተርክ የበደል ተረክ የተጋተ ወጣት ቀርቶ፣ ማንኛውም ሰው ግራ ቀኝ ሳያይ በቀላሉ ወደ መሩት ይሄዳል፡፡ ሁለተኛው ጥቅም፣ በበዳይነት የሚነሳው አካል አንገቱን እንዲደፋና ነገሮች ሁሉ ተበዳይ ነን ባዮች እንደፈለጉ እንዲሆን ይረዳል፡፡
በእኛ ሃገር ሁኔታ የተበድዬ ፖለቲካን በማቀንቀን የኦሮሞና የትግሬ ልሂቃንን የሚወዳደር የለም፡፡ እነዚህ ልሂቃን በደለን የሚሉት ደግሞ የአማራ ብሄርን ነው፡፡ ይህ ምስስሎሽ የትግሬንና የኦሮሞ ልሂቃንን ከልብ የሚያስተሳስር እውነተኛ እምነታቸው ነው፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን የራባቸውን ስልጣን ለማግኘት፣ በለማ ቡድን በኩል፣ ከአማራው ብአዴን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ይህን ተረክ ቀየር አድርገውት የነበረ ቢሆንም፣ ነገሩ ከልብ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ አማራን በዳይ አድርጎ የሚያቀርበው የሁለቱ ልሂቃን፣ አማራ ወደ ስልጣን እንዳይመጣ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ይጠብቃሉ፡፡ አማራው ተጠናክሮ ወደ ስልጣን የመጣ ከመሰላቸው፣ የተጣሉ የሚመስሉት የትግሬና የኦሮሞ ልሂቃን ተመልሰው ግንባር ፈጥረው፣ አማራውን ወደ ከረመበት ድብታ ለመክተት እንደሚተባበሩ ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የአማራን ጭራቅነት ሲሰብኳቸው የኖሩትን የሌሎችን ብሔረሰቦች ካድሬዎች በተከታይነት መጥራታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡
ህወሓት ሲመራው በኖረው የ27 ዓመታት አስተዳደር፣ አማራው አንገቱን ደፍቶ የኖረው፣ ሲተረክ በኖረው የተበድዬ ተረክ ነው፡፡ ይህን ተረክ የብአዴን አመራሮችም ተቀብለውት ኖረዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ አማራው ጊዜው ያለፈበት በዳይ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበረ፣ የብአዴን መኳንንትም ሆኑ ተራው አማራ በበዳይነት ሃፍረት ተሸማቀው ኖረዋል። ይህ ተረክ አማራውን ወክለናል የሚሉት የብአዴን ባለስልጣናት፣ የህዝባቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሙግት አንስተው እንዳይከራከሩ ከልክሏል፡፡
በሃሰት የበዳይነት ተረክ ጨቋኝ ተደርጎ ፕሮፖጋንዳ ሲደለቅበት የኖረው የአማራ ህዝብን በህይወት የመኖር መብትን ጨምሮ ሌሎች መብትን የማስከበር ጥያቄ ሲያነሳ፤ ድሮ በለመደው ጨቋኝነት፣ ጨፍላቂነት፣ አሃዳዊነት ለመግዛት ፈልጎ የሚንቀሳቀስ እንጂ የእውነት ተቸግሮ መብቱን/ህልውናውን ለማስከበር ያነሳው ጥያቄ ተደርጎ አይወሰድም፡፡ ይህ ነገር አሁንም እንዳልቀረ ሰሞኑን ኦዴፓ/ኦህዴድ የአዲስ አበባ ባለቤትነቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ “ድሮ በለመዱት አካሄድ ....” በሚለው ሃረግ ላይ በግልፅ ይታያል፡፡
ይህ መግለጫ የተፃፈው አዴፓ/ብአዴን ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አዲስ አበባን አስመልክቶ፣ “አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች” ሲል ላወጣው መግለጫ መልስ እንደሆነ ከመንፈሱ መረዳት ይቻላል፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች ያወጡት መግለጫ፣ በፓርቲዎቹ መካከል ያለው መደማመጥ ነፋስ እየገባው እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ እነዚህ ፓርቲዎች ህወኃትን ለመጣል ዳርዳር ሲሉ ለሁሉም ዜጋ የምትበቃ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደቆረጡ ሲቀላምዱ የነበረው ቅጥፈት እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ለቃልኪዳኑ መፍረስ ሰበቡ ደግሞ ገበያ እንደወጣ ህፃን፣ ሁሉን ለእኔ የሚለው ኦዴፓ/ኦህዴድ ነው፡፡
በኦነግ አስተምህሮ ተፀንሶ ያደገው ኦዴፓ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሃገር ሆኖ መቆምና በዲሞክራሲ መራመድ ግድ ይለኛል ሲል የባጀው ክፉኛ የተጠማውን ስልጣን በእጁ አድርጎ፣ በአቶ መለስ ክርን ሲደሰቅ የኖረውን ገደብ አልባ ኦነጋዊ አምሮቱን ለማርካት ነበር፡፡ ይህን በወቅቱ መጠርጠሩ አስቸጋሪ ስላልነበረ፣ ብዙዎች በዚህ ዙሪያ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያስጠነቅቁ ነበር። ሆኖም የለማ ቡድን “ጤፍ የሚቆላ” ምላስ አዋቂ፣ ጠርጣራውን ሁሉ አደንዝዞት ከረመ፡፡ ይህ አፈ ቂቤ ቡድን፣ በመረጃ ዘመን፣ ህዝቡን በምላሱ አደንዝዞ፣ በሆዱ የያዘውን ጬቤ አውጥቶ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ማሰቡ ትልቁ ሞኝነቱ ነው፡፡ ሆኖም የለማ ቡድን ይህን ያሳሰበው ሌሎችን ጅል አድርጎ የማሰቡ ኢህአዴጋዊ ዝንባሌ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ ይህን ለማድረግ ያስችለኛል ብሎ እንዲያስብ ያደረገውና ያስተማመነው አንደኛው ምክንያት፣ በኦነግ እና ህወኃ ተደርሶ፣ በሁሉም የዘውግ ፖለቲከኛ ሲቀነቀን የኖረው የተበድዬ ተረክ ነው፡፡
የተበድዬው ተረክ አማራ ያልሆነውን የኢህአዴግ ካድሬ፣ አማራውን ሊፈራ እንደሚገባው ጭራቅ እንዲያይ አድርጎታል። ዛሬ ግንባር ፈጥረው ሃገር እንምራ ሊሉ የሞከራቸው ብአዴን እና ኦህዴድም፣ በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር ነን እያሉም፣ ለዘመናት የጎሪጥ ሲተያዩ የኖሩ እንደሆኑ በውስጣቸው የኖሩ ሰዎች የሚናገሩት ነው፡፡ የኢህአዴግ ፓርቲዎች አማራውን እንዲጠሉ በመለስ ዜናዊ ሲጋቱ የኖሩት የጥላቻ መጠጥ በአማራው ላይ ብቻ አይወሰንም። ተረኩ የኢትዮጵያን አመሰራረት ጭምር ከፈጠራው የአማራ ጨቋኝነት ጋር የሚፈተል ነው፡፡ ስለዚህም እነዚህ ካድሬዎች የአማራ ጥላቻ ኢትዮጵያን ጭምር ወደ ማፍረስ ጥፋት ለመንጎድ እንዳያመነቱ አድርጓቸዋል፡፡ ህወኃት ከስልጣን ሲነሳ፣ የአዴፓ/ብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ስልጣን ለመምጣት የአቶ ለማን ያህል ጉብ ቂጥ ያላሉት፣ አማራው ወደ ስልጣን ከመጣ፣ ቀሪው የኢህአዴግ ካድሬ ሀገር እስከ ማፍረስ የሚደርስ መሆኑን፣ ከኖሩበት ሃቅ ስለተረዱ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ኦህዴድ ወደ ስልጣን መጥቶ ሃገር ብትተርፍ የተሻለ እንደሆነ ብአዴን ራቅ አድርጎ በማሰቡ የሆነው ሆነ፡፡
ነባሩ የኢህአዴግ የሃይል አሰላለፍ  
እንደዚህ ባለ መንገድ በብዙ እልልታ ወደ ስልጣን የመጣው ኦዴፓ/ኦህዴድ፣ በተግባር ሲፈተሽ የሆነው ሌላ ነው፡፡ ኦዴፓ/ኦህዴድ ስላወራው ቃል ግድ ሳይለው፣ ካወራው በተቃራኒ የኦሮሙማን አላማ ይዞ የነጎደበት ሁለተኛው ምክንያት፣ በኢህአዴግ ውስጥ በአቶ መለስ የተበጃጀው የፖለቲካ አሰላለፍ፣ ስልጣን ለያዘ አካል የፈለገውን ለማድረግ የሚመች መሆኑን ስለሚረዳ ነው፡፡ ይህ የሃይል አሰላለፍ በሃገሪቱ ያሉ ዜጎችን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ “አባል” እና “አጋር” በሚል፣ መስፈሪያው በማይታወቅ አካሄድ፣ የአንድ ሃገር ሰዎችን አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ የሚደርግ አካሄድ ነው። አባል የተባሉት አራቱ ፓርቲዎች፣ በህወሃት አዛዥነት የሃገሪቱን ፖለቲካ ሲያሾሩ፣ ሌሎቹ አጋር ተብለው ከዋና የስልጣን ቦታዎችም ሆነ የሃገራቸውን ህልውና ከሚወስኑ ፖለቲካዊ ምክክሮች ተገልለው ኖረዋል፡፡
በእኛ ሃገር፣ ፓርቲ መንግስትን ይመራል፡፡ ፓርቲ ደግሞ በአራት አባል ፓርቲ ካድሬዎች ስራ አስፈፃሚ ውሳኔ ይዘወራል፡፡ የአራቱ ፓርቲ ካድሬዎች ደግሞ ለወትሮው በአቶ መለስ ቀጭን ትዕዛዝ ያድራሉ፡፡ በዚህ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ አጋር ፓርቲ ተብለው በየክልላቸው የኢህአዴግን ፍላጎት የሚያስፈፅሙ፡- ሶማሌን፣ ጋምቤላን፣ ቤኒሻንጉልን፣ ሃራሪን፣ አፋርን የሚመሩ ፓርቲዎች አይሳተፉም፡፡ ይህን ድልድል ያመጣው “ብሔረሰቦችን ከአማራ እስር ቤት ፈትቼ ለቀቅኩ” የሚለው የአቶ መለስ ህወኃት መራሽ አስተዳደር ነው፡፡ ይህ አካሄድ ለውጥ መጣ በተባለ ማግስት የሚቀየር ነገር መስሎኝ ነበር፤ተቀጥሎበታል፡፡
የለውጥ መሪ ነኝ ባዩ፣ ብልጣብልጥነት እየሞከራቸው ያለው ጠ/ሚ ዐቢይ ያደረጉት ነገር ቢኖር፣ በቅርቡ በተደረገ አንድ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የአጋር ፓርቲዎች ሊቀመናብርት ብቻ እንዲገኙ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ትርጉሙ ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ የተገኙት ሊቀመናብርትም በገዛ ሃገራቸው ጉዳይ ላይ ታዛቢ ብቻ ሆነው እንዲቀመጡ ለብቻቸው ወደተጠሩበት ስብሰባ ምን ሊሆኑ እንደሄዱ አይገባኝም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ሁለተኝነታቸውን ተቀብለው፣ በሃገራቸው አንኳር የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ሳይሳተፉ፣ ሰው በወሰነላቸው የኖሩ የአጋር ድርጅቶች ካድሬዎችም ሁሌ የሚደንቁኝ ጉዶች ናቸው፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ እነዚህን የአጋር ፓርቲዎች ሊቀመናብርት ብቻ ወደ ስራ አስፈፃሚ የጋበዙበት ምክንያት “ይህንንም ያደረግኩላችሁ እኔ ነኝ” የሚል ውለታ ለማስቆጠር ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃው ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ወደ አፋርና ሶማሌ ክልል ባመሩበት ወቅት ስንት ሚኒስትር ከአፋርና ሱማሌ እንደሾሙ እየቆጠሩ፣ “ተመስገን በሉ” አይነት ነገር ማውራታቸው ነው፡፡ ይህስ ለምን አስገለገ ከተባለ፣ አጭሩ መልስ፣ በውለታ ተይዘው ለኦዴፓ/ኦነግ፣ የኬኛ ፖለቲካ ስምረት የሚሰሩ አዳዲስ ሰራዊቶች ለመሰብሰብ ነው። በአሁኑ ወቅት በኬኛ ፖለቲካ ሳቢያ ኦዴፓ/ኦህዴድ፣ ከአዴፓ/ብአዴን ጋር የገባበት ፍጥጫ የሚካረር ከሆነ፣ እነዚህን አጋር ድርጅቶች ለኦሮሙማ ጥቅም በኦዴፓ/ኦህዴድ ሰልፍ ለማሰለፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ወደ አጋር ድርጅቶች መሄድ ለምን አስፈለገ? የሚለውን ተገቢ ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። አጋር ድርጅቶች ያስፈለጉበት ምክንያት ለወትሮው ግንባር ፈጥረው፣ አጋር ድርጅቶችን እንምራ ሲሉ የኖሩት አራቱ አባል ድርጅቶች ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ የተወናከረ፣ የድሮው አዛዥ ታዛዥ ድራማ የጠፋበትና ግንባሩ ራሱ አለ ወይ በሚያስብል ሁኔታ ውስጥ  መሆኑ ነው፡፡
ኢህአዴግ የወትሮው ነው?
የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ህወኃት፣ ደኢህዴን፣ አዴፓ እና ኦዴፓ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ህወኃት በስልጣን መነጠቁ ሳቢያ ያኮረፈና ከሚወደው ስልጣኑ የመገፍተሩ ዋነኛ ምክንያት ወትሮም የማይወደው የአማራ ልሂቃን መራሹ ብአዴን እንደሆነ ያስባል፡፡ በዚህ ምክንያት ከአዴፓ/ኦዴፓ ጋር ለተቃረነ ሁሉ አላማውን ሳይጠይቅ ጭምር መወገኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ አሁን ከአዴፓ ጋር ሽርክናውን ጨርሶ ወደ መሸካከር የሄደው ኦዴፓ/ኦህዴድ፣ ያየውን ሁሉ የእኔ ለሚለው የልጅ አካሄዱ ጭምር፣ ከህወኃት ጊዜያዊም ቢሆን ድጋፍ ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ሆኖም ከህወኃት ጋር አጋርነት መፍጠር በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በህወኃት ዓይን የመታየት አደገኛ ውጤት ይዞ የሚመጣ መሆኑ ለኦዴፓ አይጠፋውም፡፡ በዚህ ላይ የበላይ ካልሆነ የኖረ ከማይመስለው ህወሃት ጋር የሚደረግ ህብረት መጨረሻው ለኦሮሙማ የሚበጅ ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ከዚህ በፊት በኦሮሙማ ጉዳይ ላይ የነበረው የህወኃት እና የኦህዴድ ግንኙነት የሚያሳየው ነገሩ እንደማይበጅ ነው፡፡
በመቀጠል የሚመጣው የደኢህዴን ጉዳይ ነው፡፡ ኦዴፓ ለሚያሳየው የኬኛ ፖለቲካ፣ ደኢህዴን ሊመልሰው የሚችለውን መልስ መገመት አስቸጋሪ የሚያደርገው ደኢህዴን የሚመራው የደቡብ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለበት ቀውስ ነው፡፡ ደኢህዴን፣ የኦዴፓን የኬኛ ፖለቲካ ደግፎ አዲስ አበባን በጨፌ ኦሮሚያ ስር ለማድረግ ለሚያደርገው ሩጫ አጋርነቱን ካሳየ፣ በክልሉ አዋሳ የእኔ ናት ለሚሉት የሲዳማ ፖለቲከኞች ተመሳሳዩን ማድረግ አለበት። በተመሳሳይ አዲስ አበባ የእኔ ነች እያሉ መግለጫ የሚያግተለትሉት ባለ ጊዜ ነን ባዮቹ ኦዴፓዎች፤ የሲዳማ ፖለቲከኞች የሚያነሱትን የአዋሳ ባለቤትነት ጥያቄ መግፋት አይችሉም፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚለው ልክ ነው ብሎ መግለጫ የሚያወጣ አካል፣ አዋሳም የሲዳማ ነች የሚለውን የሲዳማ ልሂቃን ጥያቄ የሚገፋበት አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ አይችልም፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች፣ የሲዳማ ልሂቃንን የአዋሳ ባለቤትነት ጥያቄ አምርረው የሚደግፉት በዚሁ ተመሳሳይነት ሳቢያ ነው፡፡ አዋሳን የራሳቸው ለማድረግ አጥብቀው የሚሹት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስንና አቶ ደሴ ዳልኬን የመሰሉ የሲዳማ ልሂቃን የአድራጊ ፈጣሪው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስራ አስፈፃሚ አባላት ናቸው። በሌላ በኩል፣ ደኢህዴንን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት፤ በጠ/ሚኒስትሩ ዘንድ ሞገስ ከማግኘታቸው የተነሳ፣ የዶ/ር ዐቢይን መንግስት 2/3ኛ ስልጣንና ሃላፊነት የተሸከሙ ሴት ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የኦዴፓ/ኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካ፣ ከወደ ደቡብ  በሶስቱ ሰዎች ሊደገፍ ይችላል፡፡ ሌሎቹ የደኢህዴን ካድሬዎች በጉዳዩ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው አቋም እምብዛም ወደ ኦዴፓ ያጋደለ ላይሆን ይችላል፡፡
ቀጥሎ የሚመጣው በኦዴፓ የኬኛ ፖለቲካ ላይ ጋሬጣ መሆኑን በግልፅ መግለጫ ያስታወቀው አዴፓ/ብአዴን ነው፡፡ አዴፓ/ብአዴን ከሌሎች አባልም ሆነ አጋር ፓርቲዎች በተለየ የአዲስ አበባን ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ ያወጣውም ሆነ የኦዴፓን የኬኛ ፖለቲካ በአንክሮ የሚከታተለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ዋነኛው ምክንያት ኦዴፓ መራሹ የለውጥ መንገድ ሲጀመር፣ ከኦዴፓ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የማድረጉን ሃላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ ቃል መግባቱ ነው፡፡ በዚህ ቃል ሳቢያ የህዝብ ተስፋ አብቦ ነበር፡፡ ይህን ያበበ ተስፋ ኦዴፓ የፈለገው ፈልጎ፣ የበለጠው በልጦበት ገደል ስለከተተው፣ አዴፓም ተከትሎ የህዝብን ተስፋ ማጨለም የለበትም፡፡ ኦዴፓን እና አዴፓን ሁለት እግር አድርጎ የቆመው ኢትየጵያዊ፤ በእኩል የመኖር ተስፋ፣ በኦዴፓ መንሸራተት ምክንያት አንድ እግሩ ተሰብሮ ያነክስ ይዟል፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት አዴፓ/ብአዴን ቃሉን ጠብቆ፣ የህዝብን ተስፋ ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን የተሰበረውን አንድ እግር በበርካታ ጠንካራ እግሮች ተክቶ፣ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ የማደስ ታሪካዊ ሃላፊነት አለበት፡፡
ይህ ከባድ ሃላፊነት እንዳለበት ኦዴፓም እንደተረዳ፣ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያዊ እርስትና የፌደራሉ መንግስት መዲና እንጂ የአንድ ወገን ንብረት እንዳልሆነች ከገለፀበት መግለጫው ያስታውቃል፡፡ ይህ አባባል ደግሞ ከህገ-መንግስቱ ድንጋጌም፣ ከአዲስ አበባ ህዝብ ፍላጎት ጋርም፣ ከኦህዴድ/አነግ በቀር ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋርም አዴፓን የሚያስማማው አቋም ነው፡፡ የኬኛ ፖለቲካ በአሁኗ ቅፅበት እንኳ  በጌዲኦ፣ በወለጋ፣ በለገጣፎ፣ በሱሉልታና ሰበታ እያመረተ ያለውን የህዝብ ሰቆቃና እንግልት ያየ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣  አዲስ አበባን ለኦዴፓ አስረክቦ፣ የኢትዮጵያዊነቱን ምልክት ማጣትን የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡
የኬኛ ፖለቲካ ወዳጅ አለው?
አቶ መለስ በስልጣናቸው ላይ ዘመናቸው የፈቀደላቸውን የመርገጥ እድል ተጠቅመው፣ የዘውጋቸውን ልሂቃን ሁለንተናዊ የበላይነት እውን አድርገው ኖረዋል፡፡ ይህን እያየ ተመሳሳዩን ለመድገም ሲጎመዥ የኖረው አዴፓ፤ የአሳዳጊውን አካሄድ እየተከተለ ነው። ይህን ሲያደርግ የረሳው ነገር ግን ትናንት ዛሬ እንዳልሆነ ነው፡፡ ትናንት ዛሬ አለመሆኑ ኢህአዴግን ጭምር ቀይሮታል፡፡ ትናንት ለአቶ መለስ ሲያደገድግ የኖረው የአባል ፓርቲ ካድሬ፤ ዛሬ አለቃ ላወጣው መግለጫ ሌላ መግለጫ በሚሰጡ ሰዎች ተቀይሯል፡፡ የአማራን ጭራቅነት አንስቶ ማስፈራራቱም ቢሆን ብዙም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን ስልጣን መያዝም ለሌላው ኢትዮጵያዊ ምን  እንዳመጣ በአጭር ጊዜ ብዙ ትምህርት እየተገኘ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው አስፈሪ ቡድን ስልጣን ላይ ተቀምጦ፣ ስለ አሮጌው ጭራቅ ማውራቱ ሞኝ ሊያስመስል ይችላል፡፡
ኦዴፓ በፍጥነት እውነተኛ ምግባሩን መግለፁ በኢትዮጵያዊነቱ፣ በኢትዮጵያ ምድር እኩል ሆኖ የመኖር አምሮት ያለው ዜጋ ሁሉ ፊቱን እንዲያዞርበት አድርጓል። ይህ ከኦዴፓ በቀር በሃገሪቱ ብቅ እያሉ የመጡ አዳዲስ አመራሮችን ሁሉ የሚጨምር ይመስላል። ኦዴፓ በኬኛ ፖለቲካ በኩል የኦነግ አምሮት ወደሆነው  ኦሮሙማ በፍጥነት በሚምዘገዘግበት ወቅት፣ በሃገሪቱ አዲስ የሆነ የዲሞክራሲና የእኩልነት ፖለቲካን የመሻቱ ነገር እያየለ መጥቷል፡፡ የህወኃትን የበላይነት አዝሎ ጀርባው የዛለው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የማንንም የበላይነት የሚያስተናግድበት የጠጠር መጣያ ቦታ አልቀረለትም፡፡ ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካ በተቃራኒው ያቆመዋል፣ ኦህዴድን ጠላተ ብዙ አድርጎ መሞቻውን ጊዜ ያፋጥናል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሚናውን ያልለየው፣ ድምፁን ያጠፋው የተቃውሞ ጎራ አሰላለፉ ከወዴት እንደሆነ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ የተቃውሞ ጎራው ሃገሪቱ እንዲህ አቅጣጫ በጠፋት ጊዜ ብቅ ብሎ ህዝቡን ካላረጋጋ፣ ህልውናው ለመቼ እንደሚያስፈልግ ግልፅ አይደለም፡፡  
ኦህዴድ አሁን የያዘው መንገድ በሃገር ቤት ብቅ ካሉ አዲስ የለውጥ አመራሮች እስከ አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ፣ ከተራው ዜጋ እስከ ሲቪክ ማህበራት ድረስ ወዳጅ የሚያሳጣው ነው፡፡ የምዕራቡ ሚዲያ የሚቀባበለው የጌድኦ ስደተኞች ጉዳይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ እናት ፓርቲያቸውን አይንህ ላፈር የሚያስብል እንጂ አበጀህ የሚያስብላቸው ነገር አይደለም። ሰሞኑን በወለጋ ነጆ አካባቢ ሰብዓዊ ፍጡራንን መግደሉ ሳያንስ፣ በላያቸው ላይ እሳት መልቀቁ የኬኛ ፖለቲካ ትሩፋት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይን በሁለት እጃቸው የጨበጧቸው የምዕራብ ሃገራት ባለስልጣናት፣ ፊታቸውን እንዲያዞሩባቸው የሚያደርግ ነው፡፡ የምዕራቡ ሃገራት የወደዷቸውም የኢትዮጵያን ህዝብ ተከትለው ነውና፣ ህዝቡ ፊቱን ሲያዞርባቸው እነሱም ሙገሳውን እንደሚተው ግልፅ ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኦህዴድ መራሹን መንግስት ክፉኛ ማዳከሙ አይቀርም፡፡
ስለዚህ ኦህዴድ አዝማሚያውን ተረድቶ፣ የኬኛ ፖለቲካውን ልጓም ሊያበጅለት ይገባል፡፡ የኬኛ ፖለቲካ ልጓም ካልተበጀለት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳትና ጉዳቱን ለመቀነስ ሌላው ኢትየጵያዊ ምን ማድረግ አለበት የሚለውን ለማየት ለሳምንት ላሳድረው፡፡     
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሃፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡


Read 1695 times