Saturday, 23 March 2019 13:00

ቃለ ምልልስ “አዲሱ ትውልድ ፖለቲካውን ከ60ዎቹ መንጠቅ አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 ህዝብ ተደራጅቶ አክራሪ ሃይሉን መቅጨት ካልቻለ፣ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች

         የ1960ዎቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮተ አለማዊ አሠላለፍ በሚተነትነው “ይድረስ ለባለታሪኩ” የተሰኘ መጽሐፋቸው የሚታወቁትና የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም የቅርብ ረዳት የነበሩት አቶ ተስፋዬ መኮንን፤ ከሁለት አመት በፊት በአሜሪካ ከአጋሮቻቸው ጋር የመሠረቱት “የአማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት” ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በቅርቡ የተመሰረተው ከ45 በላይ ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት “የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ኮሚቴ” አመራርም ሆነው ይሰራሉ። ዕድሜያቸውን በሙሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሳለፉት አቶ ተስፋዬ፤ አሁን የገነነውን አክራሪ ብሄርተኝነት ያመጣው “የኔ ትውልድ ነው” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡ አዲሱ ትውልድ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ከ60ዎቹ ትውልድ ላይ መንጠቅ አለበት የሚል ጽኑ እምነት ያላቸው አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ ለዚህም ህዝቡ መደራጀት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ አገሪቱ ለምትገኝበት ፖለቲካዊ ችግር መፍትሄ ነው የሚሉትን የብሄራዊ መግባባት ጉባኤ በቅርቡ ለማካሄድ እየሰሩ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተለይም በጽንፈኛ ብሄርተኝነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር  ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-


          “የአማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት” እንዴት ተቋቋመ?
የተመሠረተው ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ከሁለት አመት በፊት ነው፡፡ በተለያዩ የአለም ክፍሎች አባላት አሉን፡፡ በኢትዮጵያም አሉን፡፡ ስንመሠረት 70 አባላት ከውጭ ሀገር፣ 30 ከሀገር ውስጥ ሆነን ነው። ይሄ ድርጅት አላማው አማራ የኢትዮጵያ ማንነት ያለው ህዝብ ነው ሌላ ማንነት የለውም፡፡ እንደ ሌሎቹ አክራሪ የነገድ አቀንቃኞች፣ የራሳችን ማንነት አለን አንልም፤ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን ብዙ መከራ እየገጠመው ያለውን አማራን ማዳን ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ አማራ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት ለመሆኑ ማስረጃዎች አሉን፡፡ ለአማራ መብትና ህልውና እየታገልን፣ ለኢትዮጵያዊ ማንነት እንቆማለን፤ ዘረኝነትና ጐሰኝነትን እንታገላለን፡፡ ይሄን ከሚታገሉ እንደኛ ያሉ ነገዳዊ ድርጅቶች ጋር ተባብረን እንሰራለን። እኛ አድማሳችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ከየአቅጣጫው በደልና መከራ የበዛበትን አማራን ለማዳን እንታገላለን፡፡ አማራን ማዳን፣ ሌላውን ነገድም ከጥፋት ማዳን ለኢትዮጵያ መዳን ወሳኝ ነው፡፡ እኛ ዘረኝነትን እንዋጋለን፤ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው። ጽንፈኛ አቋም የለንም፡፡ አማራ ስንል ህዝብን ከጥፋት የማዳን ጉዳይ ነው፡፡
አማራ ብሎ መደራጀት በራሱ ዘረኝነት ነው የሚሉ ወገኖች  አሉ?
የኛ አካሄድ ሠብአዊነትን ያዘለ፣ ዘረኝነትን የሚዋጋ ነው፡፡ አሁን በኛ እምነት፣ በአማራነት መደራጀት የዘረኝነት ጉዳይ ሳይሆን በህይወት የመኖርና ያለመኖር፣ የህልውና ጉዳይ ሆኖብን ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ማንነቱ ኢትዮጵያዊነቱ ነው፡፡ ማንነቱ አማራነት አይደለም፡፡ ለምሣሌ እነ ጃዋር፣ “የኔ ማንነት በመጀመሪያ ኦሮሞነት ነው” እንደሚሉት ሳይሆን የኔ ማንነት ኢትዮጵያዊነት ነው፤ የምታገለው ለኢትዮጵያ መዳን ነው፡፡ አማራን ደግሞ ከጥፋት የመታደግ ትግል ነው፡፡ ለአማራ ብቻ መታገል ከሆነ ግን ዘረኝነት ነው፡፡ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
ቀደም ሲል በአንድነት የፖለቲካ ጎራ ነበር የተሰለፉት፤ ያውም “አንድ ህዝብ አንድ ኢትዮጵያ” በሚለው ጎራ፡፡ አሁን ወደ ብሔር ፖለቲካ መግባትዎ ከቀደመ አቋምዎ  ጋር አይጋጭም?
ቀደም ሲል ፖለቲካ ነበረን፡፡ አሁን ፖለቲካ የለንም፡፡ ቀድሞ  የሚያለያየን የፖለቲካ ርዕዮተ አለም ነበር፤ አሁን የፖለቲካ ርዕዮተ አለም የለም። በርዕዮተ አለም የተደራጀ ፖለቲካ የለም፡፡ የአማራ መደራጀትም ርዕዮተ አለማዊ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የማዳንና ያለማዳን ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ እኔም ከቀደመ አቋሜ ያፈገፈግሁ ይመስላል፡፡ ነገር ግን በታሪክ ሳልፈልግ የተሠጠኝን ኃላፊነት ነው እየተወጣሁ ያለሁት፡፡ ሌላ ተልዕኮን የመወጣት ጉዳይ ነው እንጂ ከርዕዮተ አለም ፖለቲካ የማፈግፈግ አይደለም፡፡
አሁን በአገሪቱ ለተንሰራፋው የዘረኝነትና ጐጠኝነት ፖለቲካ ተጠያቂው ማን ነው?
ተጠያቂው የኔ ዘመን ትውልድ ነው፡፡ አሁን የሚታየው ችግር ከ60 አመት በፊት የተጀመረ ነው። ያኔ የነበረው ትግል ይዞ የተነሳው ጥያቄ፣ የመደብና የብሔር ጉዳይ ነው፤ ሁለቱን አጣምሮ ነበር የተነሳው፡፡ በኋላ ጉዳዩ አድጐ ወደ ዘር ማጥፋት ነው ያመራው፡፡ በመጀመሪያ የዘር ፖለቲካው ማኒፌስቶ ነው የወጣው፡፡ እነ ኦነግ በ1964 በዘር አሠላለፉ ላይ ማኒፌስቶ አወጡ፡፡ ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ ርዕዮተ አለማዊ ቅስቀሳ ማድረግ ነበር፤ ጠላት ማን ነው ሲባል፣ አማራ ነው ተባለ፡፡ ሶስተኛ የሄደው ወደ ጭፍጨፋ ነው፤ ይሄ ሁሉ ተፈጽሟል፡፡ ወያኔና ኦነግ ለተግባሩ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ለርዕዮተ አለሙ ድጋፍ ደግሞ ዋናው ድርሻ የኢህአፓ ነው፤ እነ ዋለልኝ መኮንን ናቸው “አማራ ጨቋኝ ነው” የመሳሰሉ ትርክቶችን ያመጡት፤ስለዚህ አሁን ግለሰብ ሳይሆን እንደ ትውልድ፣ የኔ ትውልድ ነው አሁን ለገባንበት ቀውስ ተጠያቂው፡፡ “እኛ እና እነሱ” የሚለውን ያመጣው የኔ ትውልድ ነው። የመደብ ትግል ተብሎ ነበር፣ እሱ ተመለሰ፡፡ የብሔር ጭቆና ተባለ፤ ከሶቪየት ህብረት የተቀዳ ስለሆነ አልሰመረም፡፡ እኛ ሀገር ያለው አንድ ብሔርና በርካታ ነገድ ነው። የተሳሳተ የነገድና የብሔር አረዳድ ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያን የገነቡ በርካታ ነገዶች አሉ፤ ግን አንድ ብሔር ነው ያለን፤ እሱም ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በደርግ ጊዜ በመደብ ፍጅት ተካሄደ፤ በወያኔ ጊዜ የብሔረሰብ ጥያቄ መጣ፡፡ የአሁኑ የብሔረሰብ ትርክት ደግሞ ወይ ኢትዮጵያን ሊያድን ወይ ይዞ ሊጠፋ የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ማዳን የሁላችንም ጥያቄ ነው። እኔ አሁን ያለሁበት ትግል፣ ታሪክ የሠጠኝ አጀንዳ ነው፤ ግን ጥያቄው ኢትዮጵያን የማዳን ነው፡፡ አሁን አክራሪ ብሔርተኞች የሚያደርጉት ፖለቲካ፣ የ60ዎቹ ትውልድን ይዞ የመጣና የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰ ነው፡፡
እነ ጃዋር እኮ ከአንድ አመት በፊት ለንደን ላይ ተሰብስበው፣ ኦሮሚያ የምትወጣው ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ስር ነው ብለዋል፡፡ ወደዚህ አቅጣጫ የመግፋት ትግል ነው የሚያደርጉት፡፡ ለዚህ ነው ይሄ ወቅት የመጨረሻው ምዕራፍ ነው የምለው። ይሄን ትግል በአሸናፊነት የሚደመድመው ሃይል፣ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል፡፡
ሀገሪቱን ለብሔርተኛ ሃይሎች ያጋለጠው የደርግ ስትራቴጂና አካሄድ ነው የሚሉ ፖለቲከኞች አሉ፤ በተለይ የአንድነት ሃይል የነበሩትን ኢህአፓና መኢሶንን በማጥፋት፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
ኢህአፓ ህብረ ብሔር ነው፤ ግን በወጣቶች የተሞላ ፋሽስታዊ ድርጅት ነው፡፡ ለሱ መጥፋት ደርግ ሳይሆን የራሱ አቋም ነው ተጠያቂ የሚሆነው። አንዴ ከሱማሊያ ወረራ ጋር፣ ሲያሻው ከሻዕቢያ ጋር እየቆመ ሲዋጋ ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ ለሱ መጥፋት ተጠያቂው ራሱ ነው፡፡ መኢሶን ደግሞ አሳሳች ድርጅት ነው። ኢትዮጵያ ይላል፤ነገር ግን በተግባር ለኦነግ መጠናከር ከፍተኛ ሚና የነበረው ድርጅት ነው፡፡ ሃይሌ ፊዳን በጣም አውቀዋለሁ፡፡ ዛሬ ቁቤ የሚባለውን ፊደል የቀረፀው እሱ ነው፡፡ ኦነግን ይደግፍ የነበረ ነው፡፡ ስለዚህ ለመኢሶን መጥፋት የራሱ አቋም ነው ተጠያቂው፡፡ ደርግን በብዙ መንገድ መውቀስ እንችላለን፤ ነገር ግን የአንድነት ሃይሎችን በማጥፋት ሊወቀስ አይችልም፡፡ ሃይሌ ፊዳ እኮ የኮሎኔል መንግስቱ ጥብቅ ወዳጅ ነበር። ደርግ መኢሶንን ያቀፈውን ያህል፣ በሩ ለማንም ክፍት አልነበረም፤ ግን አልተጠቀመበት፡፡
ወደ ኢትዮጵያ  ከተመለሳችሁ በኋላ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት አገኛችሁት?
የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በተለይ በዋነኛው ኦዴፓ በኩል ያለው ሁለት አካሄድ ሆኖብናል። በአጠቃላይ የኦሮሞ ድርጅቶች የኦነግ ፍልፈሎች ናቸው፡፡ ሁሉም የኦሮሞን የበላይነት ለማንገስ የሚንቀሳቀሱ ሆኖ፣ በአካሄድ ግን ይለያያሉ። የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ዶ/ር ዐቢይ፤ ኦሮሞ የቁጥር የበላይነቱን ይዞ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ መኖር ይችላል ነው የሚሉት፡፡ እነ ጃዋርና ኦነግ ደግሞ ኦሮሞ ነፃነቱን አግኝቶ፣ አንድ ግዛት መፍጠር አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ አዲስ አበባን፣ ወሎን ይዘን ታላቅ ሀገር ሆነን መኖር እንሻለን የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይሄ የኛ ግምገማ ነው። ለንደን ላይ “የኦሮሚያ ነፃነት የሚረጋገጠው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ነው” ማለታቸውን መዘንጋት የለብንም። አሁን የእነ ጃዋርና የጽንፈኞቹ ጉልበት እየበረታ ያለ ይመስላል፡፡ አሁን በጉጉት የሚጠበቀው እነ ዶ/ር ዐቢይ በእነዚህ ሃይሎች ይዋጣሉ ወይስ ተገዳድረው እነዚህን ሃይሎች ያሸንፋሉ የሚለው ነው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ  ከእኛ ጋር ቆመው እነዚህን አክራሪ ሃይሎች በማጋለጥ ከተንቀሳቀሱ አሸናፊ ይሆናሉ፤ ኢትዮጵያንም ያድናሉ፡፡ እኛ የኦሮሞን ኢትዮጵያዊነት አንጠራጠርም፤ ግን በጽንፈኞች ከመዋጥ ቢያድኑት የተሻለ ነው፡፡  
ሁሉም በብሔሩ ተካትቶ ግራና ቀኝ መጓተቱ፣ ሀገሪቱን ወዴት ያደርሳት  ይሆን?
በጽንፈኝነት አንፃር አሁን ጐልቶ የሚታየው የኦሮሞ ጽንፈኛ ሃይል ነው፡፡ ሌላው ላይ በዚህ ልክ አይንፀባረቅም፡፡ ይሄን ጽንፈኛ ሃይል በኢትዮጵያዊነት ስሜት መገዳደር ያስፈልጋል። የኢትዮጵያን አንድነት የሚጠብቅ እንቅስቃሴን ማጠናከር ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ያለውን የኦሮሞ ነገዳዊ ጽንፈኛ ሃይል በዚህ መልኩ መገዳደር ያስፈልጋል፡፡ በአማራ ውስጥ ጠንካራ ነገዳዊነት እስካሁን አልታየም፡፡ “አብን” የወጣቶች ድርጅት ነው፤ ወጣቶች ውስጥ ስሜት አለ። ጽንፈኝነት ካለ ግን የአማራ ህዝብ አይቀበለውም። የአማራ ጽንፈኝነትን የሚዋጋልን ራሱ ህዝቡ ነው። የአማራ ጽንፈኝነት ስር ሰዶ፣ አማራን ከኢትዮጵያ የመነጠል አቅም የለውም፤ አይኖረውም፡፡
ጽንፈኛ ብሔርተኛ ሃይሎች በገነኑበት ወቅት ያሰባችሁትን ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አያስቸግራችሁም?
የብሔራዊ መግባባቱ መድረክ ዋነኛ አላማው፣ ሲንከባለል የመጣውን የትርምስ ፖለቲካ ማጥራት ነው፡፡ የፖለቲካ ይዞታውን ከ60ዎቹ እጅ የማውጣት አላማ ነው፡፡ ይሄ ፖለቲካ ከእነሱ እጅ ካልወጣና አሁንም ህዝቡ ፖለቲካውን በእነሱ እጅ ብቻ እያየ የሚቆይ ከሆነ አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ብሔራዊ መግባባት ቢሳተፍ፣ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን የመጀመሪያው ምዕራፍ ይሆናል። የ60ዎቹን ፖለቲካ ከእጃቸው መንጠቅና የራሱን መሠረት መጣል አለበት። የብሔራዊ መግባባት ጉባኤ ማድረጉ አንዱ ጥቅም ይሄ ነው፡፡ አግላይ ፖለቲካን በዚህ ጉባኤ መስበር ያስፈልጋል። እኛ ጠ/ሚኒስትሩንም ጠርተናል፡፡ 47 የፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳዩን ደግፈውታል፡፡  
የሽግግር መንግስት ማቋቋም የሚል ሃሳብም አላችሁ -- ?
ሦስት አጀንዳዎች አሉት፡፡ አንደኛው፤ የሽግግር ሂደቱን ማን ይምራው? የሚል ነው። ይሄ ሰነድ ተዘጋጅቶለታል፡፡ ሁለተኛ፤ የህገ መንግስቱ መሻሻል ጉዳይ ነው፣ ገለልተኛ የሆኑ ምሁራን የሚያቀርቡት ይሆናል፡፡
ሶስተኛው እርቅ ነው፡፡ እርቅ ስንል ምን ማለታችን ነው? ማንና ማን ነው የሚታረቀው? በሚለው ላይ ጉባኤው ተወያይቶ፣ ውሣኔ ያሳልፋል፤ ውሳኔውን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ይቋቋማል። ያ ኮሚቴ ከመንግስት ጋር ይደራደራል፡፡ በመጨረሻም የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው፡፡ ይሄን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ፣ በተለያዩ ሃይሎች አጣብቂኝ ውስጥ የገቡና ጫና የበረታባቸው ይመስላሉ የሚሉ ወገኖች አሉ፤ በዚህ ይስማማሉ?
እሳቸው አንድ የሠሩት ስህተት ህዝቡ የሠጣቸውን ድጋፍ አለመጠቀማቸው ነው። ህዝቡ የሰጣቸውን ድጋፍ ተጠቅመው ፖለቲካውን ወደ መሀል ማምጣትና የሚፈልጓቸውን ሰዎች በማካተት መሠረተ መንግስታቸውን ማስፋት አለመቻላቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ኢህአዴጋዊ መስመርን ላለመልቀቅ መፈለግ አለ፡፡ ኦዴፓን ከኢህአዴግ ነጥለው በማውጣት ከሌሎች ጋር ተሠናስለው ለመስራት ቁርጠኛ መሆን አልቻሉም፡፡ ህዝቡ የበለጠ ኢትዮጵያዊነትን ያጐላሉ የሚል ተስፋ ነበረው፤ ነገር ግን የህዝብ ድጋፍን መነሻ አድርገው የመንግስታቸውን ኢትዮጵያዊ መሠረት ማስፋት አልቻሉም፡፡ ባንክ የዘረፈ የመንግስት መዋቅር ያፈረሰ አካልን ምንም ለማድረግ አልደፈሩም። ለዚህ ነው በሳቸው ላይ ተስፋ አድርጐ የነበረ ህዝብ፣ ተስፋ ወደማጣት የተሸጋገረው፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ቢፈርስ ምንድን ነው የሚሆነው የሚለው አስጊ ነው፡፡ ጽንፈኛ ሀይሎች ናቸው ሥልጣኑን  የሚቆጣጠሩት፡፡ ያ ደግሞ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ነው የሚያመራው፡፡ ይሄ ሁሉ የእሣቸው ጥፋት ነው፡፡
ከዚህ የፖለቲካ አጣብቂኝ እንዴት መውጣት ይቻላል?
ትልቁ አሁንም ያለው እድል፣ የህዝብ መደራጀትና በትንቅንቁ መሃል መግባት ነው። ህዝብ ተደራጅቶ የአክራሪ ሃይሉን መቅጨት ካልቻለ፣ ምንም ጥርጥር የለውም ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፡፡ አሁን እኛ ብሔራዊ መግባባት ብለን የምንሞክረው የመጨረሻው አማራጭ ነው፡፡ ይሄ ከተሳካ ጥሩ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፤ ህዝብ ጉባኤውን ከደገፈ ውጤቱ ጥሩ ይሆናል። ከተደናቀፈ ግን ያለጥርጥር የሀገሪቱ ሁኔታ ወደማይፈለግ አቅጣጫ ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ የህዝብ ሃይል ተደራጅቶ መሃል መግባት አለበት፡፡
እንዴት? እስቲ ያብራሩት?
ለምሣሌ ወጣቶች በኢትዮጵያዊነት፣ በተማሪነት በሌላውም መደራጀት ይችላሉ፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ህዝቡ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መደራጀት አለበት፡፡ በዚህ መልኩ ከተደራጀ በአካባቢው ያሉ ጽንፈኞችን በቀላሉ መለየት ይችላል፤ ጽንፈኛው ሃይልም በዚህ መልኩ ተንገዋሎ ማረፊያ ያጣል። ጽንፈኞች  እኮ ብዙ አይደሉም፤ ግን ድምጽ አላቸው፤ የተግባር ሰዎች ናቸው፡፡
አዲሲቷን ኢትዮጵያ፣ አዲሱ ትውልድ፣ ከኔ ትውልድ መንጠቅ አለበት፡፡ የኔ ትውልድ፣ የሃሳብ ልዩነትን የሚያስተናግደው በትዕዛዝ ነው፡፡ ምታ ይላል፣ ይመታል፤ አዲሱ ትውልድ ግን በውይይት፣ በሃሳብ ፍኖት ያምናል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከዚያ ትውልድ ወደ አዲሱ ትውልድ መሸጋገር አለባት። የኛ የተሳሳተው ያ እዝ ትውልድ ነው ኢትዮጵያን ሲያምስ የኖረው፤ አሁን ግን ወጣቱ ሃገሩን ከዚህ ሃይል መንጠቅ አለበት፡፡

Read 7703 times