Sunday, 17 March 2019 00:00

“ጃርት እሾክ ያላቸው ልጆች ወለደች” ቢለው፤ “ተዋት አስተቃቀፉን ራሷ ታቃለች” አለው

Written by 
Rate this item
(10 votes)

 ሁለት ገበሬዎች በአንድ መንደር ይኖሩ ነበር፡፡ ሁለቱም ሣር ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡
አንድ ቀን የአንደኛው ገበሬ ሣር ክዳኑ ተቀየረና ቆርቆሮ ቤት ሆነ፡፡ አጥሩም ዙሪያውን በአጠና ታጠረ፡፡
የጐረቤቱ ገበሬ ግራ ገብቶት፤
“ይሄን ሁሉ ገንዘብ ከየት አመጣህ?” አለና ጠየቀው፡፡
ያም ቤት የቀየረ ገበሬ፤
“እዚህ ደጋ ውስጥ እህል ሁሉ ታች ቆላ ወስጄ ሸጥኩት፡፡ ከዚያ ከታች ቆላ ደግሞ ማጭድ፣ ዶማ፣ አካፋ፣ ማረሻ፣ ድጅኖ፣ ማጭድ ሳይቀረኝ ወዲህ ወደ ደጋ አምጥቼ ቸበቸብኩት”
“አሃ! ለካ ይሄም ዘዴ ኖሯል፡፡ እኔም ነገ እንደዚህ አደርጋለሁ!” አለ፡፡
እንዳለውም ቆላ ወርዶ ያለ የሌለውን ብረታ ብረት ተሸክሞ ደጋ ሲወጣ እዳገቱ መሀከል ላይ ወገቡ ቅንጥስ አለና ወደቀ፡፡
መንገደኞች ሁሉ ጉድ አሉ፡፡
ከመንገደኞቹ መካከል አንደኛው፤
“ወንድሜ ምን ሆነህ ነው እንዲህ የተጐዳኸው?” አለና ጠየቀው፡፡
“ኧረ ተወኝ ወንድሜ፤ ጐረቤቴ ነው ጉድ የሠራኝ”
“ምን አድርጐ ነው ጉድ የሠራህ?”
“ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ!”
***
አቶ ከበደ ሚካኤል፤ በትንቢት ቀጠሮ መጽሐፋቸው ላይ፤
“ቀን ሲሠራ ውሎ፤ ህዝቡ ሠራዊቱ
ተቀምጦ ባለበት፣ ሁሉም በየቤቱ
እንስሳ አራዊቱን፣ እንዲህ ሳስተውለው
በአሁኑ ሰዓት ነው፣ ልቤን ደስ የሚለው!”
ብለው በንጉሡ አንደበት ይነግሩናል፡፡
ሰላም በሁሉም አቅጣጫ የምንመኘው ነው፡፡ ህዝቡም፣ ሠራዊቱም፣ አራዊቱም ሰላም ውለው ማደራቸውን ሁሌም የምንመኘው ነውና! ምኞታችን ይፋፋ ዘንድ በቅርብ እየተገናኘን እንወያይ፡፡ እንመካከር፡፡ ከዳተኝነት ሁሉ ክፉ የሃሳብ ዳተኝነት ነው፡፡ የአዕምሮን ኬላ መዝጋት፡፡ የማስተዋልን በር መቀርቀር፡፡ ከትላንትና አለመማር፡፡ ዐይንን ከፍቶ ነገ ላይ አለማተኮር፡፡
ብዙ ጊዜ አንዲት ጠብታ ለውጥ ባየን ቁጥር አገር የሚያናውጥ ሽግግር አመጣን ብለን አገር ይያዝልን ማለት ለምዶብናል፡፡ የመሠረታዊ - መዋቅር ለውጥ (Infrastructural transition) የት አደረግን? በሰው ኃይል ላይ ምን ዓይነት ለውጥ አመጣን? ምን ያህሉ ህዝብ ተቀበለን? የህዝቡስ አቀባበል የዕውን ነው የለበጣ? ሐሳዊ ዲሞክራሲ ነው እሙናዊ ዲሞክራሲ? ዲሞክራሲ ስለተባለ ብቻስ አካኪ - ዘራፍ የሚያሰኘን ሥርዓት ዋና መፍትሔ ተገኘ በማለት “እልል-በቅምጤ” ያሰኛል ወይ? ኢ-ዲሞክራሲያዊነትና ኢ-ፍትሐዊነት ነጋ -ጠባ በሚዲያዎቻችን የሚለፈፉ ቃላትና ሐረጋት ባሉበት ዜና ጣቢያ ሁሉ የተዘበራረቁ የፖለቲካ መረጃዎች/መልዕክቶች በሚሰጡበት አገር፤ “እኔ ነኝ ሀቀኛ” ማለት እንደመርገምት የሚቆጠር ነው! በተለይ በአሁኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ!
አብዛኞቹ፤
አብዛኛውን ጊዜ አንዳች የግንኙነት ችግር በገጠመን ቁጥር የሂሳብ ስልቱ ያው የአካውንቲንግ ሕግን የተከተለ መሆኑን እንጂ ማህበራዊ ገጽታውን የማጤን ወይም የመተንተን ብቃት አይታይብንም፡፡ ያም ሆኖ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ማህበራዊው ምንጊዜም የተሠናሠሉ ናቸው፡፡ ዛሬ የመድብለ - ፓርቲ ሥርዐት የማቋቋም ልዩ ጊዜ ነው እየተባለ ነው፡፡ ምነው በተግባር በተሳካ ማለታችን አልቀረም፡፡ ብዙ ያመለጡ እድሎች እንደነበሩ እናውቃለንና በዚህኛውም የምርጫ ዘመን ያው እንዳይደገም እንጠንቀቅ እንላለን፡፡ የተፈጠረውን ብሩህ ተስፋ ዕውን እናድርገው፡፡
ፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህን ሁሉ ፓርቲዎች ምን ዓይነት መድረክ ትሰጣቸው ይሆን ተብሎ ቢጠየቅ፤
“ጃርት እሾክ ያላቸው ልጆች ወለደች” ቢለው፤
“ተዋት አስተቃቀፉን ራሷ ታቃለች” አለው፤ የሚለውን ተረት መተረት ነው፡፡

Read 7407 times