Sunday, 10 March 2019 00:00

የልብ ቀስት

Written by  ደረጀ በ.
Rate this item
(11 votes)

  ሰውነቱ ላይ የሚፈስሰው ትኩስ ነገር እንደ ህልም ይታየዋል፡፡ የሆነ ሰመመን ውስጥ ገብቷል፡፡ በፊት የነበረበት የደመና ላይ እስክስታ የሚመስል ደስታ፣ የሚፈለቅቅ ሳቅ የለም፡፡ ከፊል እንባ፣ ከፊል ሳቅ ውስጥ የሚዋኝ ያህል ይሰማዋል፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ አንዳች ቁንጥጫ ነገር አጥንቱ ውስጥ ይሮጣል፡፡
አጠገቡ የተከማቸው የሰው ብዛት፣ ብቸኝነት ብብት ውስጥ ፈልቅቆ ሊያወጣው አልተቻለም፡፡ ልቡ ከበሮ ትደበድባለች፣ የደም ስሮቹ ውስጥ የነበሩት ዘፈኖች ከእነግጥማቸው የት እንዳሉ አያውቅም! ብቻ እንደ ህልም እጆቹ የነበሩበት ነዶ ውስጥ ይቆፍሩ የነበሩ ጣቶቹ ጠፍተዋል፤ ትንሽ ትንሽ ህይወት ህይወት የሚሸትተው የሳምራዊት ሽቶ ብቻ አሁንም ነፍሱ እልፍኝ ውስጥ ያካፋል፡፡
የህይወት ቋንቋ፣ የህይወት ድምፅ፣ ጨው የሌለው ጣዕም ፈጥሮበታል፡፡
“በፍጥነት ውሰዱት! … ስልኩን ክፈቱና … ለቤተሰቦቹ ደውሉ!” እያሉ ዙሪያውን የከበቡ ሰዎች ይንጫጫሉ፡፡
“በህይወት አሉ?”
“ሞተዋል!”
“እኔን ይድፋኝ!”
“ያ ነው ጥፋተኛ!”
“አምቡላንስ ጥሩ!”
ሰዎቹ ራሳቸው አይደማመጡም፡፡ በዓሉ ግን ራሱን ያዳምጣል፤ ራሱን የሰማል፡፡ ትንሽ ከውጭ፣ ጥቂት ከውስጥ ይሰማዋል፡፡ የት እንዳለ ማወቅ ግን አልቻለም፡፡ ገነት ይሁን ሲዖል ለጊዜው አልተገለጠለትም፡፡ የህይወት መዝገቡን ገፆች በትዝታ ሊገልጥ ቢሞክርም አድፈውና ቆሽሸው ሲኮረፏት ተዋቸው፡፡
እናቱን አስታወሰ፣ ከሞቱ ሰባት ዓመት አልፏቸዋል፡፡ አባቱም የለም፡፡ ሰናይትን ከሁሉ ይልቅ ያስታውሳል፡፡ ከሰናይት ጋር የልጅነት ህይወቱ ትዝታ ተሳስሯል። ህፃን እያለ ጀምሮ፣ ቤተሰቦቹ በሌሉበት እያቀፈች፣ እየሳመች በኋላም የማይፈቀደውን እያቀመሰች አሳድጋዋለች፡፡ ስራ ልትሰራ እንኳ ድክ ድክ ስትል እየተከተለ፣ እግር እግሯ ስር ይል ነበር፡፡ ብዙ ነገር አስለምዳዋለች፡፡ ጠረኗ እንዲጣፍጠው፣ ሰውነቷ እንዲናፍቀው አድርጋ አሳድጋዋለች፡፡ ከእናቱ ይልቅ እርሷን እንዲወድ አድርጋው ነበር፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ እንኳ ስቅስቅ ብሎ ያለቀሰው እሷን ወድዶ እንጂ የእናቱ ነገር ግድ ብሎት አልነበረም፡፡ ከፍ ሲል ግን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትርሲትን ሲያገኝ ሰናይት ቀለለችበት። የትርሲትን ያህል አልጣመችውም፡፡ በተለይ የሳይኮሎጂ ትምህርት ሲማር በህይወቱ ውስጥ ያስቀመጠችው አሻራ ሀዘን እያጨረበት መጣ። ቢሆንም ሊመልሰው አልቻለም፡፡ እያዘነ፣ እየመረረው ቀጠለ፡፡
መጠጥ ለመደ፡፡ ሴት ማዘውተር ያዘ። ከአንድ ሰው ስዕል ለመሸሽ፣ ከአንድ ገመድ ለመላቀቅ፣ ትዝታን ለመሰረዝ ወዲያ ወዲህ ማለት ቀጠለ፡፡ ቢሆንም ዕድለኛ ነው፡፡ ጥሩ መስሪያ ቤት ተቀጠረ፡፡ በተለይ ከአራት ዓመታት በኋላ የገባበት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኘው ሆነ፡፡
ከዚያ እናቱ ከመሞታቸው በፊት ድል ባለ ድግስ ተዳረ፡፡ “ሙሽራዬ፣ የወይን አበባየየ!” እያሉ እናቱ ብቸኛ ልጃቸውን ሞሸሩት። እልልታውን አቅልጦ ጎጆ አስቀለሱት፡፡ አሁንም የሰናይት ጠባሳ ጥሎት አልሄደም። የልጅነት ስዕሎች ይረብሹታል፡፡ ትዝ የሚለው ጠረን አለን፡፡ የማዕድ ቤት ጠረን ይናፍቀዋል። ይሄኔ ያልሆነ ቦታ ራሱን ያገኘዋል፡፡ “ተውኩት” ሲል ያሳድደዋል፡፡ “አመለጥኩ” ሲል ይጨብጠዋል።
ቪትዝ መኪና ከገዛ በኋላ ታክሲ መሰለፍ ተገላግሏል፡፡ አሁን ያቃተው፣ ከመጠጥ መገላገሉን ነው፡፡ የሚጠጣው ወድዶ አይደለም፤ እየተበሳጨ ነው፡፡ “ምናለ እናቴ ለሰራተኛ ጥላኝ ባትሄድ ኖሮ!” ይልና ይማረራል፡፡ በልጅነቱ ሰናይት የከተበችው ክትባት፣ አሁን እንደ ዐውሎ ነፋስ ነፍሱን ያመሳቅላታል፡፡
አንዳንዴ እንዲያውም ከአፉ ያመልጠውና “ወይኔ ዕድሌ!” ይላል፡፡ ጓደኞቹ “እንዲህማ አትቀልድ! ያንተ ዕድልማ ምርጥ ዕድል ነው!” ይሉታል፡፡ መልስ የለውም፤ ብቻ ደስተኛ አይደለም፡፡
ሚስቱ ትዝታ፤ ጥሩ ሰው ናት፡፡ ለስላሳ፣ አፍቃሪ፣ ሩቅ አሳቢ፡፡ “ለኔ የምትገባ ሰው አልነበረችም!  የተሻለ ሰው ማግባት ነበረባት!” ይላል፡፡
እርሷ ግን ሁሌ ለቤቷ ደፋ ቀና እንዳለች ነው፡፡ ከራሷ ይልቅ እርሱን ታስቀድማለች። የርሷ ቤተሰቦች የተማሩ ናቸው፡፡ በተለይ አባቷ እንደ ጓደኛ ቀርበው በግልፅነት ስላሳደጓት በመነጋገርና በውይይት እንድታምን አላደረጓትም ህይወትን በቀላሉ መኖር የምትችል ዓይነት ናት፡፡
እንደ ህልም እንደ ሰመመን፣ እንደ ሳቅ፣ እንደ ልቅሶ እያደረገው ሳለ የመኪናውን መስታወት ሰብረው፣ ሲያወጡት ዓይኑን ሊገልጥ ሞከረ፡፡
“አሁንም ጫጫታ አለ፡፡
“እየተሳሳመ ሲያሽከረክር ነው!”
“አይመስለኝም፣ መኪናው ፊት ለፊት መጥቶ ነው የወጣበት”
“ከሴትየዋ ጋር ሙድ ይዞ ይሆናል”
ትራፊኩ “እባካችሁ አትለፍልፊ! መጀመሪያ ህይወቱ መዳን አለበት፡፡ ደግሞስ ሴት የማይስም አለ እንዴ?” …
ድንገት አንድ ድምፅ አካባቢውን ቀወጠው፡
“ኡኡኡ … ኤፍሬምዬ….ኤፍሬምዬ…”
ሰው ሁሉ ገለል አለ፡፡ ሁሉም ሰው ፊት ፊቷን አየ፡፡
“አሳልፉኝ! አሳልፉ!”
ተወርውራ ስትሄድ ኤፍሬምና የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ ሳምራዊት ተዘርረዋል፡፡
“አምቡላንስ አስጠሩ!”
“በመኪና ሊወሰድ ነው… ተረጋጊ!”
ወደ መኪና ሊጭኑዋቸው ሲሉ፣ ዐይኑን በቀስታ ከፈተው፡፡
ትዝታን አያት፡፡
“ትዙ”
“ደህና ነው፤ ደህና ነው!” አለ ትራፊኩ፡፡
ሳምራዊትም ዐይኗን ቀስ ብላ ገለጠች። ከትዝታ ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ ዙሪያውን ከተገጠገጡት ሰዎች መካከል አንዷ፤ “ሚስቱ የትኛዋ ናት?” ስትል ጠየቀች፡፡
“ይህቺ የምትጮኸው መሆን አለባት!”
“አይደለም፣ ያቺ መኪና ውስጥ የነበረቺው ናት! እንደ ሎሚ ሲመጣት ነበርኮ!”
የትዝታ ጆሮ ውስጥ የገባው ድምፅ ልቧን ቆነጠጣት፡፡
“ሳምራዊት ባሌን ጠለፈችው ማለት ነው? … አይ ፈጣሪ!”
“ትዙ ይቅርታ! … ትዙዬ ይቅርታ!”
እምባው ኮለል ብሎ ወረደ፡፡ መኪናውም ወደ ሆስፒታል ሸመጠጠ፡፡ ደሙ እየፈሰሰ ነበር፡፡ “ደሜ የሀጢአት ዋጋ ነው?” ብሎ አሰበ።

Read 2544 times