Sunday, 10 March 2019 00:00

“ኤርትራ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ ይታያል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

የኢሳት ጋዜጠኞች የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ያመጣውን አዲስ የለውጥ ምዕራፍ በመጠቀም የ“ኢሳትን ቀን” በኢትዮጵያ ለማክበር በቅርቡ ወደ አገር ቤት መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሳምንት ከሦስቱ የኢሳት ጋዜጠኖች ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ ለንባብ በቅቷል፡፡ ዛሬ ደግሞ የአዲ አድማሷ ናፍቆት ዮሴፍ ከጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ጋር ያደረገችውን ቆይታ እነሆ፡-

        በምን አጋጣሚ ነበር ከአገር የወጣኸው?
የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ከሀዋሳ አንድ ዘጋቢ ይፈልግ ነበር፤ በዚያን ጊዜ እኔን መርጠውኝ ከሃዋሳ ዜና ለማስተላለፍ የሙያ ፈቃድ ያስፈልገኝ ነበርና፣ ያንን ፈቃድ ስጠይቅ ከለከሉኝ፡፡ ይህን ፈቃድ የከለከለኝ በወቅቱ በአቶ በረከት ስምኦን የሚመራ አንድ መስሪያ ቤት ነው፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ይሆን?
አዎ፤ ይሄ መስሪያ ቤት የሙያ ፈቃድ ከለከለኝ። የጀርመኑ ኃላፊ ለአቶ በረከት የፃፉትን ደብዳቤ አይቻለሁ፡፡ ሆኖም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
ምክንያታቸው ምን ነበር?
ያው እኔ ተወልጄ ያደግኩት፣ የተማርኩትም፣ የተዳርኩትም ሀዋሳ ከተማ ነው፡፡ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄ አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ አዲስ አበባ የገባሁት በጋዜጠኝነት ሙያ ለመቀጠል የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ይህንን ዕድል የሚሰጥ ተቋም አልነበረም፤ እናም የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ቡድን ወደ ብሩንዲ ሲሄድ አብረው ከተጓዙት 18 አስተርጓሚዎች ጋር ተወዳድሬ አልፌ ከሰላም አስከባሪ ቡድኑ ጋር ብሩንዲ ሄድኩኝ፡፡ ከዚያ በአብዛኛው በትርጉም የኢትዮጵያን ሰራዊት ከሌላው አለም ሰራዊት ጋር በማገናኘትና በማግባባት ድልድይ ሆነን እንሰራ ነበር፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በመከላከያ ሰራዊት ስር ነበር የምንሰራው፡፡
ከብሩንዲ እንደተመለስኩ ወደ ሃዋሳ ተመልሼ፣ በደቡብ ኤፍኤም ለአምስት አመታት ከምስረታው ጀምሮ ሰራሁ፡፡ በጣም ተቀባይነትን አግኝቼ ነበር፡፡ በጣቢያው በርካታ ፕሮግራሞችን ነበር የምሰራው፡፡ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ጥያቄና መልስ፣ የዓለም ትኩረት፣ እና በርካታ ስራዎችን እሰራ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በእናንተ ጋዜጣም “አዲስ አድማስ” ላይ ብሩንዲ እያለሁ የምፅፈው ታሪክ ነበር፡፡ “ደቡብ አፍሪካ የተስፋይቱ ምድር” የሚል ለተከታታይ 13 ሳምንታት ወጥቶ አንባቢ ወዶት ነበር፡፡ እንግዲህ ለምን የሙያ ፈቃድ ከለከሉህ ላልሺኝ፣ በደቡብ አፍኤም ውስጥ ስሰራ፣ “የአፍሪካ ትንሳኤ” የሚባለውን ፕሮግራም ወደ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ” በፈቃዳቸው ቀየሩት። ይሁን ብለን በዚህም መስራት ቀጠልን፡፡ ብዙም አላስከፋንም፡፡
ወቅቱ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ነበርና “የሚሊኒየሙን ምርጥ ኢትዮጵያዊ ምረጡ” የሚል አንድ ዝግጅት ነበረን፡፡ በዚህ ፕሮግራም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ አፄ ቴዎድሮስን መረጡ፡፡ ይህንን የወቅቱ የክልሉ ባለስልጣናት ስላልወደዱት፣ ፕሮግራሙ ከ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ” ወደ “የደቡብ ትንሳኤ” ይቀየር አሉ፡፡ ይህን ልቀበለው አልቻልኩም፡፡ በገዛ ፈቃዴ ስራዬን ለቅቄ ወጣሁ፡፡ ከዚያ የራሴን የማስታወቂያ ድርጅት ከፍቼ ለመስራት ሞከርኩ፡፡ የፖለቲካው ኩርኩም ብቻ ብዙ እንቅፋት ነበር፤ አልሆነም፡፡ የሙያ ፈቃዱንም የከለከሉኝ ደቡብ ኤፍኤም ውስጥ ስሰራ፣ እነሱ የማይፈልጉትን ግን ትክክል ነው ብዬ ያመንኩበትን በመስራቴ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያ ለኢንተርንሺፕ ጀርመን መምጣት አለብህ ብለው፣ ከ2002 ምርጫ ቀደም ብዬ ጀርመን ወሰዱኝ። በዚህ መልኩ ነው ከአገር የወጣሁት፡፡ በዶቼ ቬሌ ባደረኩት የ3 ወር ቆይታ ተገምግሜ፣ ጊዜው ይራዘም ተባለ፤ ምክንያቱም ከዚህ ስሄድ አዲስ ጉልበት፣ ፍላጎትና ስሜት ይዤ ስለነበር፣ ጣቢያውን በማነቃቃት በኩል ጥሩ በመስራቴ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ በጀርመን ራዲዮ ቆይታዬ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡
በምን ምክንያት?
ኢትዮጵያ ውስጥ አፈና አለ፤ ጭቆና አለ፤ ይሄንን ማጋለጥ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ አክቲቪዝም ያስፈልጋል ብዬ አመንኩ ግን ይህንን ጀርመን ድምፅ ራዲዮ ውስጥ ሆኜ ማሳካት አልችልም፡፡ አንደኛ ውስን አየር ሰዓት ነው ያለው፡፡ ሁለተኛ ከጀርመን መንግስት ፍላጎት አንፃር የተሰሉ ፕሮግራሞችና የዜና አቀራረቦች ነበሩ፡፡ ብዙ ጥያቄና ቅሬታ ከኢትዮጵያ እየመጣ አይተው እንዳላዩ ሲያልፉት አያለሁ፡፡ በኢህአዴግ አገዛዝ ላይ የሰላ ትችት ያላቸው ምሁራን እንዳይቀርቡና ሀሳብ እንዳያስተላልፉ ሲከለከሉ እመለከታለሁ፡፡ ይሄ በፍፁም ሊያስደስተኝ አልቻለም፡፡ በዚህ መከፋት ውስጥ እያለሁ ነው “ኢሳት” የተቋቋመው፡፡
ከ“ኢሳት” ግብዣ ቀርቦልህ ነው ወይስ አንተ አመልክተህ ነው የተቀላቀልከው?
“ኢሳት” ሲቋቋም፣ የኔ ቤት መሆን ያለበት፣ ያ ቤት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ፡፡ በእርግጥ ገንዘብ፣ ስኬትና ምቾት የማስቀድም ከሆነ፣ የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ጥሩ ክፍያ ስለሚከፍለኝ ግድ አይኖረኝም ነበር፤ ነገር ግን በአካልና በገንዘብ እየወፈሩ በሙያ መኮሰስ ስላልፈለግኩኝ፣ “ኢሳት”ን መረጥኩኝ። የሚገርምሽ ከኢትዮጵያ ብዙ አቤቱታዎች ወደ ዶቼቬሌ ሲመጡና ሲታፈኑ፣ “ኢሳት” አምስተርዳም ተከፍቶ ስለነበር፣ ወደዛ አስተላልፍና እንዲዘገብ አደርግ ነበር፡፡ ብቻ በጀርመን ድምፅ ራዲዮ የነበረኝ እድሜ እንደሚያጥር እርግጠኛ ነበርኩኝ፡፡ “ኢሳት” በአሜሪካ እንደተቋቋመ አቅም አልነበረውም፤ ግን እኔ ግዴለም በነፃነት የህዝብ ጉዳይ ማሰማት አለብኝ ብዬ ነአምንን ልምጣ አልኩት፡፡ ትጎዳለህ ቢለኝም፣ ግዴለም ብዬ በአሜሪካ ከተቋቋመ ከ6 ወይም ከሰባት ወር በኋላ አሜሪካ ሄጄ “ኢሳት”ን ተቀላቀልኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ስምንት ዓመታት ከባልደረቦቼ ጋር ሆኜ ስታገል ቆይቼ፣ በመጨረሻም በመጣው ለውጥ አገሬ ለመግባት ችያለሁ፡፡
አንተ አሜሪካ ስትገባ ኢሳት ቴሌቪቪን ብቻ ነበር፤ ሬዲዮውን ያቋቋምከው አንተ ነህ …
ትክክል ነሽ፤ ሬዲዮውን እኔና አበበ ገላው ነን ያቋቋምነው በተለይ እኔ ፕሮግራሙን ከመቅረፅ አንስቶ በብዙ ነገር ተሳታፊ ነበርኩኝ፡፡ ጥሩ ተቀባይነትና ብዙ አድማጭ ያለው ነው ኢሳት ሬዲዮ፡፡
ወደ ኤርትራ ያቀናህበት ዋና ምክንያት ምን ነበር?
ወደ ኤርትራ የሄድኩት በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያቴ የነፃነት ታጋዩ የአንዳርጋቸው ፅጌ መያዝ ነው፡፡ የመን ላይ እሱ ሲያዝ፣ በግሌ የተሰማኝ ስሜት ነበር፤ እርሱ እዚያ በረሃ ለበረሃ ሲንከባለል የነበረው ስለ ኢትዮጵያ ሲል ነው፤ ሌላ ምንም ፈልጎ አይደለም። እሱ የተንከራተተበትን ቦታ ማየት አለብኝ በሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ እውነት የኢትዮጵያ ሰራዊት ኤርትራ ውስጥ አለ ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ የህዝብም ጥያቄ ነበር፡፡ እዛ ሰራዊት የለም፤ የኤርትራ መንግስት ያቋቋማቸው ተራ ፍየል ጠባቂዎች ናቸው ይባላል፡፡ ይሄን ማየት ነበረብኝ፤ ሄድኩኝ፡፡ ከመላው ኢትዮጵያ የሄዱ፣ ከአርባ ምንጭ፣ ከጎንደር፣ ከአፋር … ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ከደቡብ አፍሪካና ከተለያዩ ዓለማት ምቹ ኑሯቸውን ትተው የመጡ፣ እዛ የቀበሮ ጉድጓድ በሚመስል ቦታ ሆነው፣ ለአገር ነፃነት ቁርጥ አላማ የያዙ ያገሬ ልጆችን አግኝቼ፣ እነሱ ከሚከፍሉት መስዋዕትነት አንፃር እኔ ምንም እየሰራሁ እንዳልሆነ እንዲሰማኝ ነው ያደረጉኝ፡፡ ሶስተኛው የኤርትራ መንግስት በምን ምክንያት ነው የኢትዮጵያን ሰራዊት የሚደግፉት? ይህን ሰራዊት የሚያስጥጠልሉበት ምክንያት ምንድነው? የሚለውን ለማወቅ ነበር፡፡ በጥሩ ሁኔታ አላማዎቼን አሳክቼ ነው የመጣሁት፡፡
የኤርትራ መንግስት እነዚያን ታጋዮች የሚደግፉበት ምክንያት ምን ሆኖ አገኘኸው?
አየሽ … የኤርትራ ጉዳይ በጣም ሴንሴቲቭ ጉዳይ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ባለን የጉርብትናና አጠቃላይ ቅርበት አንፃር ከ70 ሺህ በላይ ወገኖቻችንን ህይወት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከገበርን በኋላ አጠቃላይ ስለ ኤርትራ ጥሩ ነገር እንዳይሰማን ተደርገን ነው የኖርነው፡፡ በአንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን “ከኢትዮጵያዊነት አቶ ኢሳያስ ይበልጥብኛል” ብለው የተናገሩትን አስታውሳለሁ፡፡ የጄነራል ደምሴ ቡልቶ ልጅ ዶ/ር ደረጀ ደምሴ በ“አባቴ ያቺን ሰዓት” የሚለውን መፅሀፉን አንብቤው ነበር፡፡  በተለይ የደርግን የ1981 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ስመለከት በሌላ በኩል ስብሃት ነጋ በድምፀ ወያኔ ላይ የተናገሩትን “በተደጋጋሚ የኤርትራን ነፃነት ለሻዕቢያ አሳልፈው ሊሰጡ ሲሉ እኛ ነበርን የምንታደገው” ያሉትን ሳስታውስ፣ ከሻዕቢያ በላይ ህውሃቶች ነበሩ ለኤርትራ መገንጠል ሰፊ ስራ ይሰሩ የነበሩት፡፡
በኤርትራ ቆይታዬ እዛ ያሉትን የኢትዮጵያ አርበኞችን ሀውልት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ መፅሀፍት የተሞላውን የአስመራን ወመዘክር ስጎበኝ፣ የቤተ ክርስቲያን ስነ ስርዓቱን፣ ምፅዋ የሚገኘውን የአፄ ኃይለስላሴን ቤተ መንግስት በቅርስነት ስመለከት፣ ከዚህ ይልቅ ኤርትራ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ ይታያል፡፡ በአሻራ ደረጃ ኢትዮጵያዊነት አስመራ ይታያል፡፡ የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ሰራዊት ለምን ይደግፋሉ? የሚለውም የኢትዮጵያ ሰላም የኤርትራ ሰላም ነው ብለው የኤርትራ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በተለይ ለምስራቅ አፍሪካ ልብ ለሁሉም የሰውነት ክፍል ደሞ እየረጨ እንደሚያደርስ ኢትዮጵያም ለሀገራቱ የደም ስር ነች ብለው ያምናሉ፡፡ እናም በኢትዮጵያ የጭቆናና የአፈና ስርዓትን ለመታገል፣ ከአስመራ በ400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኙትን የተለያዩ የነፃ አውጭ ድርጅቶች፣ አርበኞች እንደሚደግፉ ለማወቅ ችያለሁ፡፡
ወደ “ኢሳት” ልመልስህና … በኢሳት በዚህ አገር ውስጥ ካለው ጋዜጠኛ በተሻለ መረጃዎች ታገኛላችሁ እስኪ ስለምንጮቻችሁ ንገረኝ?
እኛ በአብዛኛው መረጃ ይደርሰን የነበረው ከኢህአዴግ ሰዎች ነው፡፡ እርግጥ ተደርሶባቸው የታሰሩ፣ የተዋከቡ፣ ከስራ የተባረሩ፣ ባለስልጣን ያልሆኑ፣ አገር ወዳድ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ በጣም መመስገን አለባቸው፡፡ ለውጡም ያለእነርሱ ምንም አልነበረም፡፡ እንዳልኩሽ ዋና ዋና መረጃዎቹ፤ ከኢህአዴግ ሰዎች ሲደርሱን፣ ዝም ብለን አንለቅም፤ በሌላ መልኩ ማረጋገጫ ለማግኘት እንጥራለን፡፡
በምን መልኩ ታረጋግጡ ነበር?
ለምሳሌ መረጃው የመጣው ከኦህዴድ ሰው ከሆነ፣ እኛ  ለብአዴን ሰው ደውለን እንዲህ ያለው ነገር እንዴት ነው እንላለን፡፡ ብቻ በመረጃ በኩል መቶ በመቶ እርግጠኛ ሳንሆን ያስተላለፍናቸውም አሉ፤ ስህተት ሰርተናል፡፡ ይቅርታ የጠየቅንባቸውም በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአቶ መለስን ሞት ያረጋገጥነው ከኢህአዴግ ሰዎች ነው፤ አሁን ስም መጥራት አያስፈልግም፤ ሞታቸው ለቤተ መንግስትም ተደብቆ ነበር፡፡ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ በሚባል የአሜሪካ የደህንነት ተቋም በትርጉም አገልግሎት የሚሰራ ኢትዮጵያዊ ሰው ነበር፡፡ ልክ አቶ መለስ በሞቱ ዕለት ሰዓቷ ሳትቀር ተፅፋ፣ ነገር ግን ሞታቸው የሚገለፀው መንግስት ይፋ ሲያደርግ እንደሆነ የሚገልፅ ሪፖርት ተዘጋጅቶ ነበር። ያ መረጃ በጣም ምስጢራዊ ነው፤ ነገር ግን ወደ አማርኛ መተርጎም ነበረበት፡፡ ያ ኢትዮጵያዊ ላከልን፤ እንደላከልን ወዲያው መረጃውን አለቀቅነውም። እኛ ራሱ እስክንለቀው የሁለት ሳምንት ጊዜ ወስዶብናል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ኢትዮጵያዊያን አሉ። “ኢሳት” ኢትዮጵያዊ ተቋም ነው፤ አገርና ህዝብ የሚያገለግል ነው” ብለው የሚያምኑ፡፡ ስንቋቋም እንደ ግለሰብ ብሄር ሊኖረን ይችላል፤ እንደ ኢሳት ግን ብሔር የለንም፡፡ ይህን በወጉ የተረዱ በመላው አገሪቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን በመረጃ ሲደግፉን፣ ራሳቸውን አሳልፈው ለችግር እየሰጡ ወገናቸው ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ ሲያጋልጡ ኖረዋል፤ የለውጡም ትልቅ ሞተር ናቸው፤ እናመሰግናቸዋለን፤ ክብር ይገባቸዋል፡፡
በሚዲያ ተላልፈው ጉዳት አድርሰዋል የምትላቸውና የተፀፀትክባቸው መረጃዎች አሉ?
አንዱን ልንገርሽ፡፡ አንድ ጊዜ የቀትር ዜና ላይ አንዱ ዜና እየነገረኝ፣ ለካ በጥይት ተመትቷል፡፡ የሚነግረኝ አንድ አካባቢ በተነሳ ግርግር ላይ ነው፡፡ ከዚያ ስልኩ ተቋረጠና ሁሉም ነገር ጭለማ ሆነ፡፡ ለካስ ባህር ዳር ቀውጢ ሆናለች፤ ጨካኙ የህወሓት በትር አርፎባት 58 ሰው ተቀጥፏል፡፡ ጓደኞቹም “በቃ ደግመህ አትደውልለት” አሉኝ፡፡ በጣም ደነገጥኩ፤ አስቢው ከደቂቃዎች በፊት በስልክ ድምፁን ስሰማው የነበረ ልጅ፣ አጫጭር ቪዲዮዎችን ሲልክልኝ የነበረ ሰው፣ ወዲያው ተመትቶ ሲወድቅ … እስከ ዛሬ ይሄ ነገር ከውስጤ አልወጣም፡፡ ልጁ ህይወቱ አልፏል፡፡
የዶ/ር ዐቢይ መንግስትን አካሄድ እንዴት ታየዋለህ?
የዶ/ር ዐቢይ አህመድ አካሄድ እንግዲህ ፍፁም እንከን የለሽ ባይባልም፣ አገሪቷንና ህዝቦቿን ግን 27 ዓመት ከነገሰባት ጨለማ አላቆ፣ የተስፋ ብርሃን እንድናይ አድርጓል፡፡ ኢሳት ሶስት አላማዎችን አንግቦ ነበር ሲታገል የነበረው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ኢትዮጵያን የሚያነግስ ሥርዓትና መሪ ማምጣት ናቸው … ሶስቱ ዓላማዎቹ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማንገስ ቃል የገባ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያነግስ፣ ህዝቡን የሚያወድስ መሪ… ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ ንግግሮች የተነሳ ስሜት ውስጥ ገብተን ብዙ ነገር ሆነናል፡፡ በዚያ ላይ ከሚያበሻቅጠን መሪ ወጥተን ነው ይህን ሰው ያገኘነው፡፡ ከልቡ ኢትዮጵያዊነትን የሚወድ፣ ህዝብ ለማቀራረብ የሚሰራ ነው - ዶ/ር ዐቢይ፡፡ በዚህ ዓይነት መሪ የሚመራ መንግስት፤ ምንም ፈተና ቢገጥመውም፣ ህዝቡን ከጎኑ አሳልፎ ወደፊት መቀጠል ይችላል፡፡ ስህተቶች አሉ፤ ችግሮች አሉ ግን ከታገዘና ከተደገፈ ተስፋ ያለው መሪ ነው፡፡

Read 7059 times