Sunday, 10 March 2019 00:00

አምባገነኖች እንዴት ይፈጠራሉ?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)


          ለመሆኑ አምባገነን፣ ፈላጭ ቆራጭ (Dictator) መሪዎች እንዴት ነው የሚፈጠሩት? ማን ነው የሚፈጥራቸው? የአምባገነንነት መመዘኛው ምንድነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከማቅረቤ በፊት ለመንደርደሪያ የሚሆኑ አጠቃላይ ነገሮችን ለማቅረብ ወደድሁ፡፡
አንዳንድ ሰዎች “ህዝባችን ሲወድህም ልክ የለውም፡፡ ሲጠላህም መጠን የለውም፡፡ ግን እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚገርም አይደለም፣ ምክንያቱም የሰው ባህሪ ነውና!” ሲሉ እሰማለሁ፡፡ “የሰው ባህሪ ነውና!” የሚለውን አባባል እንዳለ መውሰድ ይከብደኛል። እናም “ያልተገራ፣ ስነ-ምግባር የሌለው፣ ግብረ-ገብነት የጎደለው፣… ሰው ባህሪ ነውና” ብዬ ማሻሻል ፈለግሁ፡፡
ያልተገራ ባህሪ ያለው ሰው ይቸኩላል፡፡ ያልተገራ ባህሪ ያለው ሰው ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ያልተገራ ባህሪ ያለው ሰው አንዳች ነገር መወርወሩን እንጂ የወረወረው ነገር ምን ላይ እንደሚያርፍ ግድ የለውም። ያልተገራ ባህሪ ያለው ሰው ይሉኝታ የለውም፡፡ ያልተገራ ባህሪ ያለው ሰው ለመንግስት ህግም፣ ለሞራል ህግም ተገዢ የመሆን ፍላጎት የለውም፡፡ እነዚህ ህግጋት መኖራቸውም ስሜት አይሰጠውም፡፡
የስነ-ምግባርንና የግብረ-ገብነትን ጉዳይ የጽሁፌ መንደርደሪያ ማድረጌ ስለነዚህ ጽንሰ-ሃሳቦች ማብራሪያ ለመስጠት አይደለም፡፡ ስለ ሰው ባህሪ ለመተንተንም አይደለም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሜዲያና በእለት ከእለት እንቅስቃሴዬ የማያቸውና የምሰማቸው ሁኔታዎች ናቸው በመንደርደሪያነት የጠቀስኳቸውን ሃሳቦች እንዳነሳ ግድ ያሉኝ፡፡
አንዳንድ ሰዎች እነሱ የሚወዱትን እንድትወዱ፣ እነሱ የሚጠሉትን እንድትጠሉ ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ለምን እንደሚጠሉ ወይም ለምን እንደሚወዱ ብትጠይቋቸው የሚሰጧችሁ ምክንያት የለም። ምክንያቱን በማያውቁት “ምክንያት” የወደዱትን ወይም የጠሉትን እነሱን መስላችሁ በደፈናው እንድትወዱ ወይም እንድትጠሉ ነው የሚፈልጉት። እነዚህ “ምክንያት አልባ” ሰዎች ከሳምንታት ወይም ከወራት በኋላ ብታገኟቸው የወደዱትን ዓንህን ለአፈር ብለው፣ የጠሉትን ማሬ ወለላዬ ሲሉ ልትሰሙ ትችላላችሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ የምክንያት አልባነት፣ የመርህ የለሽነትና የአድርባይነት ድምር ውጤት ነው፡፡ ምክንያት አልባነት፣ መርህ የለሽነትና አድርባይነት ደግሞ ያልተገራ ባህሪ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ምክንያት አልባነት፣ መርህ የለሽነትና አድርባይነት የሚወልደው ‘ጭፍን ድጋፍ’ ደግሞ ውጤቱ አምባገነን መሪን መፍጠር ነው፡፡
ርዕሱ እንደሚያመለክተው የዚህ ጽሁፌ ትኩረት በአምባገነንነት ዙሪያ በመሆኑ ወደዚያው እናምራ፡፡ በቅድሚያ “Dictator” የሚለው ቃል  በእንግሊዝኛ የተሰጠውን ትርጉም እንይ፡፡ “A dictator is a political leader who possesses absolute power” ይላል፡፡ ይህም ማለት “ዲክታተር ማለት ስልጣንን ጠቅልሎ የያዘ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ማለት ነው” የሚል ትርጉም ይሰጠናል፡፡ በአጭር አማርኛ “Dictator” ማለት “አምባገነን” ወይም “ፈላጭ ቆራጭ” የሚል ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን። የሚገርመው ነገር በእንግሊዝኛ “Dictator” የሚለው ቃል ጥንት የነበረው ትርጉም አሁን ከተሰጠው ትርጉም ጋር ፍጹም የተለየ መሆኑ ነው። ያኔ የነበረው ትርጉም የመሪዎችን መጥፎነት ማሳያ አልነበረም፡፡ ይህንን ሃሳብ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ታሪካዊ አመጣጡን የሚያሳይ በእንግሊዝኛ የተጻፈ ማብራሪያ ላቅርብ፡፡
“A dictator is a political leader who possesses absolute power... The word originated as the title of a magistrate in the Roman Republic appointed by the Senate to rule the republic in times of emergency… the word “dictator” came to be used almost exclusively as a non-titular term for oppressive, even abusive rule.”
ይህንን ወደ አማርኛ ስንመልሰው ደግሞ “ዲክታተር ማለት ስልጣንን ጠቅልሎ የያዘ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ማለት ነው፡፡ የቃሉ መነሻ በጥንት የሮማ ሪፑብሊክ ድንገተኛ ችግር ሲገጥም ሙሉ ስልጣን ተሰጥቶት ሪፑብሊኩን የሚመራ ሹም ማዕረግ ነው፡፡ … በኋላ ላይ ግን ቃሉ የሹመት ማዕረግ መሆኑ ቀረና ዋነኛ የጭቆና አገዛዝን የሚያሳይ ትርጉም ተሰጠው” እንደማለት ነው፡፡
ቃሉ ጥንታዊ የሹመት ማዕረግነቱን እያጣ የመጣው ሙሉ ስልጣን ተሰጥቷቸው የተሾሙ ባለስልጣኖች የስልጣን ዘመናቸው ቢያልፍም እዚያው ስልጣን ላይ ተቀምጠው አንወርድም ብለው በማስቸገራቸው ብቻ ሳይሆን፤ በስልጣን ዘመናቸው እነሱ ያሉት ብቻ እንዲፈጸም በማድረግ የሚያስተዳድሩት ህዝብ ውልፍት እንዳይል ወጥረው በመያዛቸው ጭምር ነው፡፡ አምባገነን የሚለው ቃል ትርጉም ይህ ከሆነ ለመሆኑ አምባገነኖች የሚፈጠሩት እንዴት ነው? ባህሪያቸውስ ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ተጨባጭ ምሳሌዎችን በማንሳት ለማብራራት እንሞክር፡፡
አምባገነኖች የሚፈጠሩት እንዴትና በነማን ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ ከአንድ የታሪክ ምሁር ወንድሜ ጋር ባደረግነው የሃሳብ ልውውጥ “ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ አምባገነን መሪዎች የሚፈጠሩት በዋናነት በህዝብ በራሱ ነው፡፡ ‘ሰማይ አይታረስ፣ ንጉስ አይከሰስ’ እያለ ትከሻውን ለጭቆና የሚሰጥ ህዝብ አምባገነኖችን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለአገዛዛቸውም ምቹ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አምባገነኖችን የሚፈጥሩት በስርዓቱ ውስጥ ያሉ በአምባገነኑ መሪ ዙሪያ የተኮለኮሉ የስልጣን ተስፈኛ የሆኑ ግለሰቦች ናቸው” ይላል ምሁሩ፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለአምባገነኖች መፈጠር ምክንያት ሆኖ በሦስተኛነት የሚጠቀሰው ግለሰባዊ ሰብእና ግንባታ (cult of personality) ነው። በዚህ ረገድ አምባገነኖች ለሰብዕና መገንቢያነት የሚጠቀሙባቸው ቴክኒኮች አሏቸው፡፡ መገናኛ ብዙሃን፣ ፕሮፓጋንዳ፣ የተጋነኑ ውሸቶች፣ የኪነ ጥበብ ትርዒቶች፣ ስነ-ጥበባት፣ ስሜትን የሚቀሰቅሱ የአርበኝነት ንግግሮች፣ ሰላማዊ ሰልፎች፣ ስብሰባዎች፣ የጀግንነት ድል ታሪኮች ትርክት፣ የመሪዎች ምኞችና ህልም የመሳሰሉት ተጠቃሽ ቴክኒኮች ናቸው፡፡ እነዚህን ነጥቦች በልባችን ይዘን ዓለም የሚያውቃቸውን አምባገነኖች ታሪክ እንይ፡፡
የቀድሞዋ ዛየር የአሁኗ ዴሞክራቲክ ኮንጎ መሪ የነበረው ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ከአፍሪካ አምባገነን መሪዎች አንዱ ነው፡፡ ዛየርን ለ32 ዓመታት ገደማ ያስተዳደረው ሞቡቱ ወደ ስልጣን የወጣው ታዋቂውን የነጻነት ታጋይ ፓትሪስ ሉሙምባን በወታደራ መፈንቅለ መንግስት ገልብጦ ነበር፡፡ አምባገነኖች ለራሳቸው ስም በማውጣት ይታወቃሉ። ሞቡቱ የሀገሩን ስም ከኮንጎ ወደ ዛየር ብቻ አይደለም የቀየረው፡፡ የራሱንም ስም “ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ፣ ጽናት ያለው፣ አይበገሬው፣ ከድል ወደ ድል የሚሸጋገረው፣ ኃይለኛው ጦረኛ” በማለት አስረዝሞት ነበር፡፡
የታሪክ ምሁራን ስለ አምባገነኖች ሲያስተምሩ የሚጠቅሷትን የአንድ ሚንስትር ንግግር እዚህ ላይ  ላንሳ፡፡ የዛየር የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር የነበረው ኢንጉሉ ባንጋ ፖንጎ፣ በ1970 እንዲህ ብሎ ነበር “እግዚአብሔር ታላቅ ነቢይ የሆነውን፣ ታላቁ መሪያችንን ሞቡቱን ልኮልናል። ይህ ነብይ የእኛ ነፃ አውጪ፣ መሲህ ነው። ቤተክርስቲያናችን MPR (ፓርቲው Popular Movement of the Revolution - MPR) ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችን ዋና መሪ ሞቡቱ ነው፡፡ አማኞች ጳጳሳቸውን እንደሚያከብሩት ሁሉ እኛም ሞቡቱን እናከብረዋለን፡፡ ወንጌላችንም ሞቢቱዝም ነው፡፡ መስቀሉ በእርሱ ፎቶ መተካት ያለበት ለዚህ ነው” በማለት ተናግሮ ነበር፡፡
አምባገነን መሪዎችን አምባገነን ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያደርጓቸው እንዲህ እንደ ዛየሩ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ያሉ የስልጣን ጥመኞች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ ጥሩ አሽከር ያለው መሆኑን ያረጋገጠው ሞቡቱ ለራሱ “የማርሻል” ማዕረግ ከመስጠቱም በላይ አልተሳካለትም እንጂ የእድሜ ልክ ፕሬዝዳንት ለመባል ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡
ማላዊን ለ31 ዓመታት የገዛው ታዋቂው አምባገነን መሪ ካሙዙ ባንዳ ተቃዋሚዎቹን በማሰርና በመግደል ይታወቃል፡፡ ካሙዙ ራሱን የማላዊ የእድሜ ልክ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰይሞ ነበር፡፡ “ሁሉም ነገር የኔ ኃላፊነት ነው፣ እኔ አልኩ ማለት ህግ ሆነ ማለት ነው” የሚለው ካሙዙ ባንዳ ራሱን “የበላዮች የበላይ፣ ታላቁ አንበሳ፣ የማላዊ የእድሜ ልክ ፕሬዝዳንት፣ ዶክተር ካሙዙ ባንዳ” ብሎ ይጠራ ነበር፡፡
(የአሜሪካ መሪዎች በዓለም ላይ ያሉ “ክፉ አምባገነኖችን” ለመቅጣት ጦርነት ውስጥ እንደሚገቡ ለአሜሪካ ህዝብ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ በህዝብ ሀብት የተቋቋሙ ሜዲያዎቻቸውም ይህንኑ ያስተጋባሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 በተደረገ ጥናት በዓለም ላይ 49 ሀገሮች በአምባገነንነት የተፈረጁ ሲሆን፤ የሚገርመው ነገር አሜሪካ “በዓለም ላይ ካሉት አምባገነኖች ውስጥ ሰባ ሦስት በመቶ የሚሆኑት ከአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ያገኛሉ” ይላል ሪክ ዊትኒ የተባለ ጸሐፊ)
ለግንዛቤ ያህል ከላይ የቀረቡትን ሁለት “ታዋቂ አምባገነኖች” ካየን ወደ ሀገራችን እንመለስ፡፡ ህዝባዊ አመጽን በወታደራ መፈንቅለ መንግስት አጅቦ ወደ ስልጣን የወጣው ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ስሙ ከአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ኮ/ል መንግስቱ የሀገሪቱ ስልጣን ሁሉ በእጁ ነበር፡፡ እንደነ ካሙዙ ባንዳ የመንግስቱም ስም በብዙ ቅጽሎች የታጀበ ነበር፡፡ “ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ የኢሠፓ ዋና ጸሐፊ፣ የኢህዲሪ ፕሬዝዳንት፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የብሔራዊ ሸንጎ ሰብሳቢ፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ የብሔራዊ የሰርቶ አደሮች ቁጥጥር ኮሚቴ ሰብሳቢ፣… ” ይባል ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኮ/ል መንግስቱ “ቆራጡ መሪያችን” እየተባለ ይሞካሽ ነበር፡፡
በታዳጊነት ዕድሜየ የሰማሁትን “ከቆራጡ አብዮታዊ መሪያችን ከጓድ ሊቀ መንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም አመራር ጋር ወደፊት” የሚለውን መፈክር ምንጊዜም አልረሳውም፡፡ ይህንን መፈክር ልክ እንደ ዛየሩ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር አንዱ የኮ/ል መንግስቱ እወደድ ባይ ሚንስትር የቀረጸው እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ “ቆራጡ፣ አብዮታዊው መሪያችን፣ አንድ ለእናቱ፣ ጥቁር እንቁ…” የሚሉት ቅጽሎች ኮ/ል መንግስቱን የልብ ልብ አልሰጡትም ብሎ ለማሰብ ያስቸግራል፡፡
አምባገነኖች የሚታወቁት በስልጣን ዘመናቸው ተቃዋሚያቸውን በማሰር፣ በማንገላታትና በመግደል ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ መፈክራቸው “አንድ ሀገር፣ አንድ መሪ፣ አንድ ፓርቲ፣…” የሚል ነው፡፡ አምባገነኖች (እነርሱን የሚደግፍ ካልሆነ) የመናገር ነፃነት፣ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የመደራጀት ነፃነት፣… ብሎ ነገር አያውቁም፡፡
ማንም ሰው ሲፈጠር አምባገነን ሆኖ አይፈጠርም፡፡ ስለ አምባገነኖች ባህሪ ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት ብዙዎቹ አምባገነኖች እንዲያውም ዝምተኛ፣ ዓይን አፋር፣ ሩህሩህነት የሚስተዋልበት ባህሪ አላቸው። የሌላቸውን ሰብዕና እየደረደሩ ወደ አምባገነንነት የሚለውጧቸው በዙሪያቸው የተኮለኮሉ ስልጣን ናፋቂዎችና ጭፍን ደጋፊዎቻቸው ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ የእኛ የኢትዮጵያውያን ባህሪ አምባገነኖችን ለመፍጠር ምቹ መሆኑ ይታየኛል። ኮ/ል መንግስቱን ብቻ ሳይሆን አቶ መለስንና ህወሓት መራሹን ኢህአዴግ “ባለ ራዕዩ መሪ” እያልን የአውራ ፓርቲ ስርዓት እንዲፈጠር አድርገናል፡፡ “እሱ ከሌለ የሀገሪቱ ደህንነት አደጋ ላይ ይወድቃል” እያልን የሰብአዊ መብት ገፋፊ ግልገል አምባገነኖችን ተሸክመናል፡፡ “ጓዶችን አትንኳቸው” እያልን ሙሰኞችንና ኮንትሮባንዲስቶችን አንግሰናል፡፡ ቁም ነገር “ዛሬስ ከዚህ ተምረናል?” ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ዓሊ ስም ደጋግሞ መነሳትና የማህበራዊ ሜዲያ መነጋገሪያ መሆን የጀመረው የዛሬ ዓመት፣ በዚህ ወቅት መሆኑን እናስታውሳለን፡፡ ዶ/ር ዓብይ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙ ዕለት (መጋቢት 24 ቀን 2010) ከተለመደው የኢህአዴግ መሪዎች እንጨት እንጨት የሚል ደረቅ ንግግር ወጣ ያለ አነቃቂ ንግግር ካደረጉ በኋላ ሰማይ ምድሩ “ዓብይ፣ ዓብይ” አለ፡፡ ህፃኑም አዋቂውም “ዓብይ፣ ዓብይ” አለ፡፡
ከሹመታቸው በኋላ በተለያዩ ክልሎች በመገኘት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማነጋገር በጀመሩበት ወቅት “አንተ ዓብይ ሳትሆን ነብይ ነህ” የሚሉ አስተያየቶች ተደምጠዋል፡፡ ጋዜጦችና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር (በፈርዖን ቤት ይመለኩ የነበሩ ትንንሽ ፈርዖኖች መኖራቸው ተዘንግቶ) “ከፈርዖን ቤት የወጣ ሙሴ…” በማለት አሞገሷቸው። የማህበራዊ ሜዲያ አውታሮችም ይህንኑ እየተቀባበሉ አስተጋቡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ ላይ ሂስ ቀርቶ ተራ አስተያየት እሰጣለሁ ማለት በአንገት ላይ መጅ አስሮ ወደ ገደል ከመወርወር የተለየ አልነበረም፡፡
በእንደዚህ ያለ የሽግግር ወቅት ሁላችንም እንደ ጉንዳን በአንድ መስመር ተሰልፈን መጓዝ ተገቢ ሆኖ አይታየኝም፡፡ “ዶ/ር ዓብይ እየሄዱበት ያለው መንገድ እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደትን የተከተለ ነው ወይስ ዴሞክራሲያዊ ማጭበርበር? (are we really in a kind of democratic transition or democratic deception?) ብሎ መጠየቅና ትንሽ ጥርጣሬን መጫር ካለፉ ስህተቶች መማር እንጂ ዶ/ር ዓብይን መጥላት ወይም ስልጣን ይልቀቁ ማለት አይደለም፡፡
ዓይናቸውን ጨፍነው፣ ልባቸውን ደፍነው፣ አእምሯቸውን ዘግተው ዶ/ር ዓብይን በ“ጭፍን የሚወዱ” ሰዎች መስሏቸው ነው እንጂ ዶ/ር ዓብይን አይወዷቸውም፡፡ እንደኔ እንደኔ ዶ/ር ዓብይን የሚወዱ ሰዎች በምክንያት ላይ የተመሰረተ የሰላ ሂስ በማቅረብ ዶ/ር ዓብይ የሚሄዱበትን ጎዳና ከአሜኬላ በማጽዳት የዶ/ር ዓብይ ራዕይና ዓላማ እንዲሳካ ያደርጋሉ፡፡ ዶ/ር ዓብይን የሚወዱ ሰዎች ሰውየው የተዋጣለት፣ ጥሩ መሪ እንዲሆኑ ስህተቶቻቸውን ነቅሰው በማውጣት ይተቻሉ፤ የተሻለ የሚሉትን አቅጣጫ ያመላክታሉ፡፡
አሁን አሁን የምናያቸው የዶ/ር ዓብይ ደጋፊ ነን የሚሉ ሰዎች ግን ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት የነበሩ “ታጋዳላይ” ያሳዩት የነበረው ዓይነት ባህሪ ሲያንጸባርቁ ይስተዋላሉ። እነዚህ “ጭቆና በኛ ያምራል” የሚል አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ጭፍን ደጋፊዎች “ጭቆናን” ሳይሆን “ጨቋኝን” የመታገል መንፈስ ይታይባቸዋል። እንዲህ ያለው አካሄድ ዶ/ር ዓብይንም፣ ብሔርተኛ ካድሬዎቹንም፣ የፌስቡክ አርበኞችንም፣… በጥቅሉ ሀገሪቱንና ህዝቡን ወደተለመደው የጥፋት አዙሪት ውስጥ መክተት እንጂ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም፡፡
በመሆኑም፤ ዶ/ር ዓብይንና መንግስታቸውን በምክንያትና በመረጃ ላይ ተመርኩዘን በሰላ ሂስ ማጥረግረጋችን ይቀጥላል፡፡ ይህም ለዶ/ር ዓብይና ለመንግስታቸው ያለንን በጎነት እንጂ ክፋት የሚያሳይ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ ከነ ተረቱ “መካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግስ” አይደል የሚባል! - ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ በ“ዴሞክራሲያዊ አግባብ” ከአንድ ዓመት በላይ እንዲያስተዳድሩን እንመክራለን፡፡
    ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1474 times