Print this page
Sunday, 10 March 2019 00:00

ቃለ ምልልስ “ለችግሮቹ ተጠያቂዎች ኢህአዴግና መንግስት ናቸው”

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(11 votes)

                    “ህውሓት ብቻውን አገር አልመራም”

ካለፈው ሳምንት የቀጠለው ቃለ-ምልልስ ከዚህበታች ቀርቧል፡፡ ወደ ትግራይ ክልል ያመራሁት ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዩን ገ/ሚካኤል ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ ነበር፡፡ ጉዞዬን በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አድርጌ ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ ላይ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ገባሁ፡
፡ ከአየር ማረፈያው ጀምሮ ሆቴሌ ድረስ እንዲሁም በመቀሌ ቆይታዬ ሁሉ የትራንሰፖርት አገልግሎት የሰጡኝ ባለታክሲና ባለባጃጅ ፍፁም ትሁትና
አንግዳ አክባሪ ናቸው፡፡ ያለ ክፍያ እንግድነቴን አክብረው አስተናግደውኛል፡፡ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ቢሮ በቀጠሮዬ ሰዓት ደረስኩ፡፡ በር ላይ የነበሩት ጥበቃዎች የተቀበሉኝ በአክብሮት ነው፡፡ ቋንቋቸውን አለመቻሌ የፈጠረብኝ ችግር አልነበረም፡፡ አስተርጓሚ ተመድቦልኝ ወደ ቢሮአቸው ተላኩ፡
፡ ቢሮአቸው ስደርስ ዶ/ር ደብረፅዮን ከአሜሪካ ከጀርመን፣ ከኖርዌይና ከእስራኤል አምባሳደሮች ጋር ዉይይት ላይ ነበሩ፡፡ ተራዬ እስኪደርስ ግማሽ
ሰዓት ያህል ጠብቄ ገባሁ፡፡ዶ/ር ደብረፅዮን ከወንበራቸው ተነሰተው በአክብሮት ተቀበሉኝ፡፡ ለጥያቄዎቼ ሁሉ ምላሸ ለመስጠት ፍቃደኝነታቸውንም ገለፁልኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሰጡን ምላሾች የመጀመሪያው ክፍል እነሆ፡-


በየአካባቢው የሚፈጠረው ግጭትና የሰላም ዕጦት መንስኤው ምን ይመስልዎታል?
ህዝቡ እራሱ የሚበላሸው መሪ ስላጣ ነው፡፡ ህዝቡ የሚመራው ነው የሚፈልገው፡፡ የአመራር ጉድለት የዶ/ር ዐቢይ የግሉ ነው ብዬ አልወስደውም።  የጋራ ጉድለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ  ወደ እራሳችን የምንቀስር ባይሆንም የዶ/ር ዐቢይም ሆነ የሌላው ችግር፣ የእኛም ችግር አድርገን ነው የምንወስደው፤ ምክንያቱም እኛም ኢህአዴጐች ነን፡፡ ድርጅቱ መብሠል አለበት፤ በሚከሰቱ ችግሮች ላይ እኛም ድርሻ አለን፡፡ የግሉ ችግር ግን የግል ነው፡፡ እኔም የራሴ ድርሻ አለኝ፤ እንደዚህ አበላሽቻለሁ እላለሁ። በክልልም እኛም አበላሽተናል ብለናል፡፡ ሌላውም የድርሻውን ጥፋት አምኖ ወስዶ፣ ችግሩን በጋራ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በየአካባቢያችን የሚፈታ ከሆነ ደግሞ በአካባቢያችን መፍታት ነው፡፡ ህወሓት የራሱን የአካባቢውን እየፈታ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሠላም የሰፈነው፡፡
በየአካባቢው ብጥብጥ ነው፤ ሰው ሠላም እያገኘ አይደለም፤ ስለዚህ የጋራ ስራ በአግባቡ አልተሠራም፤ በተናጥልም ያለው እየፈረሰ ነው፡፡ ህዝባችን እየተበታተነ ነው፡፡  እኛ  ችግራችንን አውቀናል፤ ቢያንስ በክልላችን፡፡ ሠላምን የሚያደፈርስ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፤ በተረጋጋ መንፈስ በማስተዋል ስለምንራመድ ነው፡፡ ሌላው እንደዚህ አደረገኝ ብሎ መጓዝ ሁላችንንም የሚያጠፋ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡ እኛ ሰላም የሆንነው በትክክል መምራትና መደማመጥ ስለተቻለ ነው፡፡ ሌላው ግን መምራትና መደማመጥ አልቻለም፡፡
በዚህ የተጐዳው የትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም፤ ከትግራይ በላይ የተፈናቀለው የሌላው ክልል ህዝብ ነው፡፡ ሱማሌ፣ ኦሮሞ፣ ደቡብ፣ አማራ… ያልተጐዳ የለም፤ ሁሉም ተጐድቷል፡፡
የችግሩ ምንጭ ወደ አንድ ወገን ማነጣጠር ነው። ዋናው ችግር ሌላ ሆኖ እያለ፣ ማነጣጠሩ ግን በሌላ ይሆንና ብዙ ስራዎች ሳይሠሩ ይቀራሉ ማለት ነው፡፡ የአመራር ችግር ነው ያልነው ዝም ብለን አይደለም፡፡
እርስዎ በቅርቡ “ህገ-መንግስቱ ሲጣስ ዝም ብለን አናይም፤ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ ምን ዓይነት እርምጃ?
ህገ-መንግስቱ ከተጣሰ፣ አንድ ላይ ድምፃችንን ማሠማት አለብን፡፡ ከዛ አልፈን ደግሞ የተለያዩ መድረኮች አሉ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ማለት ነው። በመድረኮቹ ይሄንን ሃሳባችንን እናራምድበታለን። ምክንያቱም የፖለቲካ ችግር ስለሆነ በፖለቲካ መከላከል አለብን፡፡ ለምሳሌ ከትግራይ ተወክለው ፓርላማ ያሉ በአደባባይ ነው እየተቃወሙ ያሉት። እርምጃ እንወስዳለን ስንል በመተኮስ አይደለም። አቋማችንን እንገልፃለን፤ መድረኮች በስፋት እንፈጥራለን ማለታችን ነው፡፡ ዝም ብሎ በድርጅት ብቻ የታጠረ አይሆንም፤ መውጣት አለበት፤ ታፍኖ መቅረት የለበትም፡፡ የህግ ጥሰት አለ ብለን ዝም ብለን ልንቀመጥ አንችልም፤ በአደባባይ፣ በሚዲያ፣ በተወካዮች ም/ቤት፣ በፌዴሬሽን ም/ቤት መድረኮች፣ መፍጠርና ያለማቋረጥ መናገር፣ ህዝቡንም ማሳተፍ፣ ጉዳዩ ግልጽ እንዲሆንለት ማድረግ ማለት ነው፡፡ አንዱ ጉዳይ የድንበር ኮሚሽን ነው፤ ህገመንግስቱን የጣሰ ነው ብለናል፡፡ ፖለቲካዊ ትግል ነው የምናደርገው፡፡ የተቃዋሚ ድርጅቶችን እያመጣን አቋም እንዲወስዱ፣ እነሱም እንዲቃወሙ እያደረግን ነው፤ የእኛ ብቻ አይደለም፤ የትግራይ ብቻ የሚባል ህገመንግስት የለም፡፡ የአገሪቱ ነው፡፡ አንዳንዱ ድፍረት ስላጣ ነው እንጂ ህገመንግስቱ መጣሱን ያውቀዋል፡፡ መድፈር አለበት ነው የምንለው፤ እኛ የተለየ ነገር የለንም፤ አቋማችን ጠንካራ ሊሆን ይችላል፡፡ የትግራይ ህገመንግስት በትግራይ ነው ያለው፡፡ የፌደራል የሁሉም ገዢ ስለሆነ፣ ሲጣስ ዝም አንልም ያልነው፡፡
የድንበር ኮሚሽኑን ለምንድን ነው የተቃዋማችሁት?
አንዳንዱ የራያ እና የወልቃይት ጉዳይ ስለተነሳ፣ የድንበር ኮሚሽኑ፤ እኛን የሚጐዳ ይመስለዋል። እዛ ላይ ችግር የለብንም፤ በህዝቡ ውሳኔ መገመት እንችላለን፤ ህዝቡ ምን እንደሚወስን ብዙ የምንጠራጠረው ነገር የለም፡፡ እኛ ህገመንግስቱ ተጣሰ ያልነው፣ ስለ ራያ እና ወልቃይት ለመከላከል አይደለም፡፡ ድሮም በደርግ ጊዜ ትግሬ የሚባል ነበር፤ አፋር የሚባል ግን አልነበረም፤ ቤንሻንጉል የሚባል አልነበረም፣ ጋምቤላ አልነበረም፣ ኦሮሞም፣ አማራም አልነበረም፤ ወሎ፣ ጐጃም እየተባለ ተበታትኖ የነበረ ነው፡፡ ይሄ አንድ አስተሳሰብ፣ ቋንቋ ያለው ህብረተሰብ በአንድ የመደራጀት ውጤት ነው፡፡ እና ይሄ ወሰን የሚባለው ሁሉንም ነው የሚያፈራርሰው፤ የፌደራል ስርአቱን ያፈርሰዋል፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ በዚህ ጉዳይ እጁን ማስገባት የለበትም፡፡ ማፍረስ ካለበት ህዝቡ ነው ማፍረስ ያለበት፡፡ ማንም አዋቂ ነኝ የሚል፣ ማንም መሪ ነኝ የሚል መጥቶ፣ ተደራጅቶ ሊወስን አይችልም፡፡ “አንተ ማንነትህ ይሄ ነው” የሚል ሌላ ወገን መግባት የለበትም፡፡ ራሱ ህዝቡ ነው መወሰን ያለበት፤ ያንን ነው ከህገመንግስት ስርአት የወጣ ነው ያልነው፡፡
ይሄ ህገመንግስት፤ በማንንት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ስለዚህ ማንም ጥያቄ ያለው ስርአቱን ጠብቆ ይሂድ ነው፤ ያልነው፡፡ በህገመንግስቱ ስርአት ድንበር ይወሰን ቢባል፣ ራያ እና ወልቃይት ቢቀሩ ትግራይ ግን ትቀጥላለች፡፡ አፋር ይበተናል፡፡ ምክንያቱም የአፋር ድንበር ወደ አማራ የሚሄድ አለ፣ ወደ ኦሮሞ የሚገባ አለ፣ ወደ ትግራይ የሚገባ ብዙ ነው፤ ከትግራይ የሚቀርበት ትንሽ ነው፡፡ ቤንሻንጉል የሚባል አይኖርም፤ በአብዛኛው አማራ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ የተወሰነው ደግሞ ኦሮሚያ ነው የሚገባው፡፡ ጋምቤላም ኦሮሚያ ውስጥ ነው የሚገባው፤ ማንነቱ ተጠብቆ ካልሄደ ተውጦ ነው የሚቀረው፡፡ ይሄ ደሞ ወደ ድሮው አካሄድ ነው የሚያስገባን፡፡
እንደ ችግር ለምታነሷቸው ጉዳዮች ተጠያቂው ማነው ትላላችሁ?
ከፓርቲ አንፃር ኢህአዴግ ነው ኃላፊነት ያለበት፤ ህዝቡ የመረጠው እሱን ነው፡፡ በዋናነት እሱ ነው የሚጠየቀው፡፡ እንደ መንግስት ደግሞ የፌደራል መንግስት ነው፡፡ ተጠያቂው አንድ ግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ መንግስት ነው ተጠያቂ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ እና የፌደራል መንግስት ናቸው ተጠያቂዎች፡፡
በሚዲያ ከመወቃቀስና ቃላት ከመወራወር፣ ችግሮችን በውይይት  መፍታት አይሻልም?
በንግግር እናምናለን፤ የእኛም ፍላጐት ነው፤ ግን ከአንድ ወገን ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ሁሉም አምኖበት እስኪስተካከል ድረስ አሁን ባለንበት መንገድ እንቀጥላለን፡፡ ከሁሉም በፊት መተማመን ያስፈልጋል፤ ወደ መተማመን መመለስ የግድ ነው። ችግሮች የጋራ ናቸው፤ መፍትሔውም በጋራ ነው የሚመጣው የሚል አስተሳሰብ መኖር አለበት፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ካልተቀየረ ችግሮች ይቀጥላሉ፡፡ አንድ ቦታ ላይ ወይ ይፈታሉ ወይ የባሰ ነገር መምጣቱ አይቀርም፡፡ ተገናኝተን ስንወያይ እኮ እንጠይቃለን፤ ለምን ይሄ ይባላል ብለን እንጠይቃለን፡፡ ግለሰቦች እንኳን ትላንት እንደዚህ ተባብለን፣ ዛሬ ካድከኝ ይባባላሉ፡፡ ትዝብት ላይ ይጥላል፣ ትላንት የተግባባንበትን አፍርሶ ሌላ ሲባል፣ እንደ ፖለቲከኛ በጣም ጥፋት ነው፤እንደ ሰው አሳፋሪ ነው፡፡ አቋም መያዝ አለበት፡፡
ህወሓት የሚባል አንድ ፓርቲ ብቻ አገር አልመራም፡፡ እንደዚህ አይነት ስልጣንም አልነበረውም፡፡ ይሄ ነበር በስብሰባዎች ላይ ሲነገር የነበረው፤ አሁን ግን የቀድሞውን ስልጣን ሙሉ በሙሉ ህወሓት ይዞ ሲሠራ እንደነበር ነው ሲነገር የሚሰማው፡፡
የናንተ እሠጣ ገባ ህዝብ ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም?
በፖለቲካ መብሰል፣ መመካከር ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው የሚናገረውን ነገር መጠንቀቅ አለበት፡፡ ህዝብን የሚነካ ይቅርና ግለሰብን መንካት የለበትም። የጠፋ ነገር ካለ ይሄ ጠፍቷል ተብሎ መመካከር ነው የሚያስፈልገው፤ መካሰስ ከሆነ ሌላ ጉዳይ ነው። መመካከር ከሆነ ግን በመጐዳዳት አይደለም፡፡ “የቀን ጅብ” የተባለው ደቡብ ላይ ነበር፤ በመጀመሪያ ተነጋግረንበታል፤ በመጨረሻ ግን ለትግይ ህዝብ ነው የሆነው፡፡ “ፀጉረ ልውጥ” የሚለውም ፖለቲካዊ ጉዳት አለው፤ እኔን በግል ብትጠይቂኝ ግን ምንም አይሠማኝም፡፡ ይሄ በአጠቃላይ የአመራር ብቃት ችግር እንዳለ የሚያሳይ ነው፤ ችግር ካለ መድረኮች አሉ፤ እኛ ያንን ተከትሎ ሌላ ነገር ብንናገር ህዝቡን ነው የምናርቀው፡፡ አመራር ከህዝቡ ጋር አብሮ ተመካክሮ መሄድ ሲገባው፣ በራሱ ብቻ ሲሄድ ይሳሳታል፡፡ ሰው አይሳሳትም አይደለም፡፡ ግን ሲደጋገም ደግሞ፣ በተለያዩ መልኮች ሲገለፅ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ መሄዱ መቆም አለበት፡፡ ችግሩ ይቀጥላል ብለን አናምንም፡፡
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ ክልሉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም ብሏል፡፡ ፍቃደኛ ያልሆናችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?
እኛ ፍቃደኞች ነን፡፡ ጄኔራል ክንፈ እኮ ከእኛ ክልል ነው የሄደው - ተጠርጣሪ ነው፡፡ አስረክቡን አሉን አስረከብን፡፡ ሌሎችም ተጠርጣሪዎች አሉ፤ ስማቸው የተላከ፡፡ ግን በእሱ ነው የተጀመረው፡፡ ከተያዘ በኋላ በሚዲያ ሌላ ነገር እንደሆነ ነው የገባን፤ እኛ ነን በሠላም ያስረክብነው፡፡ በካቴና ማሠር፣ በአደባባይ በቴሌቪዥን ማሳየት፣ ዶክመንተሪ ማቅረብ ሲመጣ የተዘጋጀ ነገር እንዳለ ያሳያል፡፡ ይሄ ደግሞ በራሳቸው መፍረድ ጀመሩ ማለት ነው፡፡ ህግን ጠብቆ መስራት ሳይሆን የፖለቲካ አካሄድ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ተጠርጣሪማ ተይዞ ፍ/ቤት ነው መቅረብ ያለበት፡፡ የሆነው ግን ወደ ፍ/ቤት ሳይሆን ወደ ሚዲያ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ ፍትህ የለም ማለት ነው፡፡ ተጠርጣሪ በፌደራል ብቻ ሳይሆን በእኛም ክልል ቢፈለግ፣ አንለቅም፤ ግን ይሄኛው ፖለቲካዊ አካሄድ ነው፡፡ ዶክመንተሪውን አይተሽው ይሆናል፤ ሄዶ ሄዶ “ትግሬ እንዲህ አደረገ” እየተባለ፣ ጠቅላላ ትግሬ ነው የተጠላው፡፡ ይሄ ሙሉ በሙሉ ፖለቲካ ነው፡፡ “ትግሪኛ ተናጋሪ” እየተባለ ነው ሲነገር የነበረው፡፡ ይሄ ፖለቲካ ነው፡፡ ፖለቲካ ከሆነ ደግሞ መታገል ያለብን በፖለቲካ ነው፡፡ እኛም ዝም ብሎ እገሌ ተጠርጣሪ ነው ስለተባለ ብቻ የምናስረክብበት ሁኔታ የለም፡፡ ቀድሞም ጥርጣሬ አልነበረንም ማለት አይደለም፤ ለምን ከዚህ ክልል ብቻ ብለን ጠይቀን ነበር፡፡
ለአሁን የተጠናው በእነሱ ላይ ነው፤ እንቀጥላለን ነበር የተባለው፡፡ ተስማምተን ስንጀምረው ግን ዶክመንተሪ ማሳየት ነው የተጀመረው፡፡ ይሄ ደግሞ ተቀባይነት የለውም፡፡
ስለዚህ ተጠርጣሪ በቀጥታ ህግ ፊት ቀርቦ የሚጠየቅ ከሆነ እናስተላልፋለን፤ የፖለቲካው አየር ግን መቀየር አለበት፡፡ ትግርኛ ተናጋሪ ብቻ የሚያስተዳድረው አገር አልነበረም፡፡ ግን የተፈለገው አንድን ብሔር መቀጥቀጥ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሊሆን አይችልም፤ ለመብቱ የታገለ ህዝብ ነው፤ ከተፈለገ እንታገላለን እንጂ ትግሬ በመሆኑ ብቻ እየተጐተተ የሚሄድ የለም፡፡ ባለስልጣን በመሆኑ ካጠፋ ሊያዝ ይችላል፤ ትግርኛ ተናጋሪ በመሆኑ ግን ሊያዝ አይችልም፡፡
አቃቤ ህግ የሚፈልጋቸው አቶ ጌታቸው አሠፋ፤ በክልሉ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል ይባላል …
በክልሉ ምንም ስልጣን የለውም፡፡ የት እንዳለ አናውቅም፤ ተደብቋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸው ሰዎች ላይ የተሰራ ዶክመንተሪ ተላልፎ ነበር፡፡ አይተውታል?
የተወሰነውን ነው ያየሁት፤ ሁሉንም ግን ሰምቻለሁ፤ በግሌ ተፈጽሟል ብዬ አላስብም፡፡ አንዳንዱ እንደውም ውሸት እንደሆነ አይተናል፡፡ ለምሳሌ ፖለሲ ጣቢያ ላይ እግሩ ተቆረጠ የተባለው አቶ ከፍያለው፤ ፕ/ር መረራ እስር ቤት ሲያውቁት፣ እግሩ ተቆርጦ እንደመጣ ነው፡፡ ዶክመንተሪው ላይ ግን ጉዳቱ ፖሊስ ጣቢያ ገብቶ ምርመራ ላይ ያጋጠመ መሆኑ ነው የተናገረው፡፡ እውነቱ ግን ከራሱ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ነው ጉዳቱ የደረሰበት፡፡  እንደ ኢህአዴግ ነው እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ እንደዛ አልተፈፀመም። የጥፍር ነቀላ ሲባል ሰምቻለሁ፤ ይሄንን እኔ በፍፁም አልቀበልም፡፡ ይሄ ከተደረገም በግለሰብ ደረጃ ሊሆን ይችላል፤ እሱን መጠየቅ ይቻላል፡፡ እንደ ስርአት ግን ተወስዶ ሊታይ አይችልም፤ ይሄ ማለት በአገር አልነበርንም ማለት እኮ ነው፡፡ ይሄ ሆን ተብሎ ለማጥላላት የተደረገ ነው፡፡ ሁላችንም የታገልነው እንደዚህ አይነት ግፍ እንዳይፈፀም ነው፡፡ ስለዚህ በኢህአዴግ የሚመራ መንግስት ካጠፋ ሁሉም ይጠየቅ፡፡ ማንም ቢሆን መጠየቁ አይቀርም፤ ከፖለቲካ ጋር መገናኘቱን ብቻ ነው የማንቀበለው፡፡
አቶ ጌታቸው ከቅርበታችሁ አንፃር ምን አይነት ሰው ናቸው?
በስራ ተናዳጅ፣ ተናጋሪ ሊሆን ይችላል፤ ግን ስርአት ጠብቆ የሚሄድ ሰው ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ሊጠየቅ ይችላል፤ 27 አመት እንደዚህ ነበር ተብሎ የቀረበው ግን ፈጽሞ ውሸት ነው፡፡ የፌደራል ፖሊስንም ሆነ፤ ማዕከላዊን አውቀዋለሁ፡፡ ግን የትግራይ ምርመራ የሚባል የለም፤ ሁሉም ብሔር ነው እዛ ያለው፡፡
በወቅቱ የነበሩ መሪዎች እኮ ሌሎች ናቸው፤ እነሱ አልተነኩም፡፡ ጉዳዩን ወደ አንድ ክልል ብቻ ማድረግ ስለሚፈለግ፣ የሁሉም አዛዥ፣ የሁሉም ፈላጭ ቆራጭ አንድ ሰው ተደረገ፡፡ ጌታቸው እንደዚህ አይነት ስልጣን እንደሌለው አውቃለሁ፡፡ የሁሉም አዛዥ አይደለም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ካልፈቀዱ ጌታቸው ምንም ሊያደርግ አይቻልም፡፡  ጠ/ሚኒስትሩ ያልፈቀዱለትን ስራ ሲሰራ ከነበረ፣ ይጠየቅ፡፡ ያንን ካደረገ ፌደራል መንግስት ባይጠይቀውም እንኳን እኛም ቢሆን እንጠይቀዋለን፡፡ ለምን ቢባል.፣ የታገልንለት ስለሆነ፡፡
በቅርቡ በትግራይ ክልልና በአማራ ክልል መካከል የተካሄደው ሽምግልና ውጤታማ ነው ይላሉ?
ችግሩ የፖለቲካ ነው፤ ተገዳችሁ ነው የገባችሁበት ነው ያልኳቸው - ሽማግሌዎቹን፡፡ እኛ እራሳችን ችግራችንን ባለመፍታታችን ህብረተሰቡም እየተጐዳ ስለሆነ፣ በሀይማኖትም በሌሎች ሽምግልና መሪዎችም፣ በቃ ሠላም ማስፈን አለባችሁ በሚል ነው የተደረገው፡፡
ነገሩ የሁላችንም ችግር ነው፡፡ የህብረተሰቡ ጫና ይገባናል፡፡ ጫና እንዳለ እናውቃለን፤ መንገድ ይዘጋል፤ ሰው ይፈናቀላል፤ የእኛ የሚለየው ክልሉ ስላልተበጠበጠ ብቻ ነው፡፡ ለህብረተሰቡ ሠላም ሲባል ችግርም ካለ በአግባቡ ይፈታል እንጂ ወደ ግጭት ወይም ወደ ጦርነት ለመሄድ ሃሳብ ሊኖረን አይችልም፡፡ እኛ በጦርነት ነው ያደግነው፤ ስንት ዋጋ ተከፍሎ ነው እዚህ የተደረሰው፤ ያንን መድገም አንፈልግም፡፡ የቀድሞ ስርአት ችግሮችን በሠላም መፍታት ስለማያቅ ነው ወደ ጦርነት የተገባው፡፡ ነገሩ በሠላም እሚያልቅ ከሆነ ለምን ወደ ጦር መማዘዝ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ለጀግንነት ከሆነ እኛ ደጋግመን አሳይተናል፡፡ አሁን ምን እናሳያለን? ለማንስ ነው የምናሳየው? ሁኔታውም ወደዛ የሚጋብዝ አይደለም።
የአገር ሽማግሌዎቹ ተነሳስተው ስለመጡና “እናገናኛችሁ” ስላሉ ነው እንጂ እኛማ በስብሰባም በፖለቲካ ጉዳይም እንገናኛለን እኮ፡፡ በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል አመራሮች “ሠላም ነው የምንፈልገው” ብለዋል፡፡ እኛም ለሰላም ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡    







Read 11695 times