Sunday, 10 March 2019 00:00

የካራማራው ጀግና - ባሻ ሁሴን ጐበና

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

(የ1ኛ ደረጃ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳሊያ ተሸላሚ)


*ከደርግ ውድቀት በኋላ ማንም ያስታወሰኝ የለም፤ ዘበኛ ሆኜ እየሰራሁ ነው
*67 ዓመቴ ነው፤ ጠላት ከመጣ ግን ለሀገሬ ከመሠለፍ ወደ ኋላ አልልም
*አሁን ህዝብን እርስ በእርስ ማባላቱ ይቁም፤ ሀገራችንን እናስከብር

የተወለዱት ባሌ ጐባ ነው፡፡ የ67 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ በሀረር ከተማ ይኖራሉ፡፡ ባሻ ሁሴን ጐበና ጣለም፡፡ የዚያድ ባሬ የሶማሌ ወራሪ ሃይል በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በከፈተበት ወቅት ከፍተኛ ጀብዱ ከፈፀሙ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አንዱ ናቸው፡፡ ለዚህም ጀግንነታቸውና የጦር ሜዳ ተጋድሏቸውም የ1ኛ ደረጃ የጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበሩ፡፡ የጠላት ጦር ታንኮችን ለብቻቸው በቦንብ አገላብጠዋል፤አጋይተዋል፤ የጦር መሪዎችን ለብቻቸው ማርከዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩትን
ገድለዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ተጋድሎዎች ሦስት ጊዜ ቆስለዋል፡፡ የደርግ ውድቀትን ተከትሎ፣ከወታደር ቤት ያለ ጡረታ የተባረሩት እኚህ ጀግና፤ ዛሬ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደተለመደው፣ ዛሬም ባለ ውለታዋን ዘንግታለች፡፡ ለነጻነቷ የተዋደቀላትን ጀግና ልጇን የሚገባውን ክብር ነፍጋለች፡፡እኚህን የሀገር ባለውለታ፣ ሰሞኑን ታስቦ የዋለውን 41ኛ ዓመት የካራማራ ድልን ምክንያት በማድረግ፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከሚኖሩበት ሀረር ከተማ በስልክ አነጋግሯቸዋል፡፡ አስደማሚ የጦር ሜዳ ገድላቸውን፣ በአስደናቂ አተራረክ ይገልጹታል፡፡ እነሆ፡-
 
የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሰራዊትን መቼ እና እንዴት ነበር የተቀላቀሉት?
ከሃገሬ በ1967 በወታደርነት ተመልምዬ ቀጥታ ወደ ሃረር ሄድኩ፡፡ ሃረር ጦር አካዳሚ፣ ኮማንዶ ለ1 ዓመት ከ6 ወር በሚገባ ሰለጠንኩ፡፡ የስልጠና ውጤቴ ጥሩ ስለነበር፣ እዚያው በአሰልጣኝነት መስራት ጀመርኩ፡፡ በርካታ የኮማንዶ ተዋጊዎችንም በወቅቱ አሰልጥኛለሁ፡፡
እርስዎ በየትኞቹ ጦርነቶች ላይ ነው በዋናነት የተሳተፉት?
በዋናነት በደጋሃቡር በተደረገው ላይ ነው፤ ለሽልማት ያበቃኝን ተጋድሎ ያደረግሁትም በዚሁ አካባቢ በተደረገው ጦርነት ላይ ነው፡፡ ኤርትራ ናቅፋ ላይም ተሳትፌያለሁ፡፡
ለ1ኛ ደረጃ የጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚነት የበቁት ምን ገድል ፈጽመው ነው?
አሰልጣኝ ሆኜ እየሰራሁ በነበረበት በ1969 ዓ.ም አንድ የኛ ፖሊስ ሻለቃ ጦር፣ በዚያድ ባሬ ጦር ይከበባል፡፡ ሰደድ ጦር ትባላለች የፖሊስ ጦር ኃይሏ፡፡ እሷን ከከበባ ለማውጣት ተላክን፡፡ እኛም ተልዕኮውን ይዘን ሄድን፡፡ ወዲያው ሶማሌዎቹ ላይ የተቀናጀ ጦር ከፈትን፡፡ ግማሹ ሞተ፣ ግማሹ ሸሸ፡፡ እኔም ጦሩን ይዤ ወደ ደጋሃቡር ሄድኩ፤ እየተከታተልኳቸው። በዚያ ቦታ ላይ የደፈጣ ውጊያ ተጀመረ፡፡ አራት ሰዎች ነበርን፤ እነሱን የገጠምናቸው፡፡ አንዱ ጓድ ወዲያው ተመቶ ሞተ፡፡ አንደኛው ደግሞ ያለውን ሁኔታ ከኋላ ላለው ደጀን ጦር እነግራለሁ ብሎ ሄደ። ብቻዬን ቀረሁ፡፡ ከሌሊቱ 10 ሰዓት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ በቦታው ብቻዬን ነበርኩ፡፡ ጥሩ ምሽግ ይዤ ነበር፡፡ የመጣው ይምጣ እነዚህን ወራሪዎች አጥፍቼ መጥፋት አለብኝ፣ እኔ ሳልሞት ወደፊት አይገሰግሱም፤ ሃገሬን አይወሩም ብዬ፣ ብቻዬን ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ውጊያ ገጠምኳቸው፤ እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ጥሩ ጥሩ ኢላማ ተኩስ እየተኮስኩ፣ 75 የሶማሌ ተዋጊዎችን ገድዬ፣ አንድ ሃኪምና አንድ  ጋዜጠኛ ማረኩ፡፡
ብቻዎትን ነው 75ቱን ገድለው፣ ሌሎቹን የማረኩት?
አዎ! በወቅቱ በውጭ አገር ጋዜጠኞች ሁሉ ቃለ ምልልስ ተደርጎልኝ ተዘግቧል፤ በፅናት ነበር የተዋጋሁት፡፡
ከዚያስ ጦርነቱ ቀጠለ?
ስጠብቀው የነበረ 130 አባላት ያሉት አጋዥ ጦር ከመጣ በኋላ፣ ሌላ የማጥቃት ጦርነት በሱማሌዎቹ ላይ ከፈትን፡፡ ጦርነቱን ለ3 ተከታታይ ቀናት ነበር ያደረግነው፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ለብቻዬ፣ አንድ ታንክ፣ በድምሩ 3 ታንኮች ነበር ሙሉ ለሙሉ በቦንብ ያጋየሁት፡፡ በዚህ ውጊያ 40 ታንኮችን በሶስት ቀን ውስጥ ማርከናል፡፡ እና ሶማሌዎቹን እያሯሯጥን ደምስሰን፣ ወደ ካራማራ ነበር የሄድነው፡፡ በዚህ ዘመቻችን በጥቂት ቀናት ውስጥ እኛ 130 ብቻ ሆነን፣ 500 ያህል ሶማሌዎችን ገድለን፣ በርካቶችን ማርከናል፡፡ ከኛ ውስጥ በኋላ ላይ በተደረጉ ከባድ ውጊያዎች በርካቶች ሞተው፣ የተረፍነው 70 ያህል ነበርን፡፡ መራር ጦርነትና ተጋድሎ ነበር ያካሄድነው፡፡ ሌሊት ከቀን ነበር ጦርነቱን ያለማቋረጥ ያደረግነው፡፡
እርስዎ ታንኮችን ያጋዩ የነበረው በምን መሳሪያ ነው?
ሁሉንም ያጋየሁት በእጅ ቦንብና በ50 ካሊበር መሳሪያ ነበር፡፡ 12 የእጅ ቦንብ ይዤ ነበር የወጣሁት፡፡ እነሱን ነው በአግባቡ የተጠቀምኩት። የማረኳቸውም ወታደሮች በአብዛኛው ከኔ ቦንብ ጥቃት የተረፉ ነበሩ፡፡ እኔ በወቅቱ ትልቅ ወኔ የሆነኝ የሃገር ፍቅር ነው፡፡ እስራኤሎች ናቸው እኔን ያሰለጠኑኝ፤ ለአላማ አጥፍቶ መጥፋት ምን እንደሆነ በሚገባ አሰልጥነውናል፡፡ ስለዚህ በጀግንነት ተዋግቼ፣ አጥፍቼ ብጠፋ፣ ሃገሬ ባለውለታዋን አትረሳም የሚል ህልም ይዤ ነበር፣ በቆራጥነት የተዋጋሁት፡፡
በዚህ ጦርነት የተከበቡትን ፖሊሶች ማስጣል ችላችኋል?
አዎ! በወቅቱ ውጊያው ከባድ የነበረ ሲሆን 20 ያህል ተገድለውብናል፡፡ እኛ የገደልናቸው የጠላት ወታደሮች ግን ከ600 በላይ ናቸው፡፡ ደፈጣ ይዘው በጠበቁን ሰዓት ነው፣ 20ዎቹን የገደሉብን እንጂ በመጀመሪያ ሁሉንም አስለቅቀን ነበር፡፡ የእነሱን ሶስት ታንኮች ሳጋይ ቢያንስ በአንድ ታንክ ውስጥ 6 ተዋጊ ይኖራል፡፡ 18 ያህል ከታንኮቹ ጋር ሞተዋል ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ስዋጋ መሳሪያ (ጥይት) ሲያልቅብኝ፣ ከሞቱ የጠላት አባላት ላይ እየወሰድኩ ነበር የምዋጋው፡፡ ከሬሳቸው ላይ እየወሰድኩ ነው፣ በመትረየስ ሁሉ የፈጀኋቸው፡፡ መሬት ላይ እየተንከባለልኩ፣ ቦታ እየቀያየርኩ ነው 75 ያህሉን የፈጀኋቸው፡፡ ይሄ ጋዜጠኞች በወቅቱ የዘገቡት ሃቅ ነው፡፡ ታንኮቹን፣ ነዳጃቸውን እያለምኩ ነበር ቦንቡን በትክክል የምወረውረው፡፡
በወቅቱ ምን ተሸለሙ?
ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም እጅ፣ የ1ኛ ደረጃ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳሊያ ተሸልሜያለሁ፤ ይህ የተጋድሎ ታሪኬ በወቅቱም በጋዜጣ ላይ ወጥቷል። አሁንም ጋዜጣው በእጄ አለ፡፡ የባሻ ማዕረግም ተሰጥቶኛል፡፡ የፕሬዚዲየም አባልም ልደረግ ነበር፡፡ በኋላ ኢህአዴግ መጣና ሁሉም ነገር ቀረ፡፡
ኮሎኔል መንግስቱ ምን አሉዎት?
ምን አለኝ መሰለህ? ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ? አለኝ፡፡ እኔም ሃገሬ ሰላም ከሆነች ሌላ የምፈልገው ነገር የለም አልኩ፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ፣ ከፈለክ ወደ ሲቪል አስተዳደር መመደብ ትችላለህ ብሎኝ ነበር፡፡ ግን እኔ ብዙም አልፈለግሁም፡፡
ከወታደር ቤት መቼ ነው የወጡት?
ያው ደርግ ሲለወጥ ነው፡፡ በወቅቱ ለሃገር እንዳልሞትን ልክ እንደ ሌባ ያሳድዱን ነበር፡፡ እኔም ስንት ለሃገሬ ከተዋደቅሁለትና በርካታ ተዋጊዎችን ካፈራሁበት ወታደር ቤት ተባርሬ፣ ያለ ጡረታ ነው የኖርኩት፡፡
ቤተሰብስ መስርተዋል?
አዎ፤ አራት ልጆችን አፍርቻለሁ፡፡ ተምረው የየራሳቸውን ስራ ይዘዋል፡፡ አንዷ አስተማሪ ነች፣ አንዷ ኮሌጅ ትማራለች፣ ሌላኛው ፋብሪካ ውስጥ ይሰራል፣ ሌላኛዋ ተማሪ ነች፡፡
አሁን በምን ይተዳደራሉ?  የት ይኖራሉ?
እዚያው ሃረር ነው የምኖረው፡፡ ልጆቼን ያሳደግሁት ኩሊ እየተሸከምኩ፣ ዘበኝነት እየሰራሁ ነው፡፡ አሁን በአንድ የግል ተቋም ዘበኛ ሆኜ እየሰራሁ ነው፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ማንም ያስታወሰኝ የለም፤ ለሃገሬ ተዋድቄ፣ ቆስዬ ግን ተገቢ ህክምና እንኳ አላገኘሁም፡፡ ውለታዬ የተረሳ እየመሰለኝ፣ ሁሌ አዝናለሁ፤ እከፋለሁ፡፡
በጦርነቱ ወቅት ቆስለዋል?
አዎ ሶስት ቦታ ላይ ቆስያለሁ፡፡ ውጭ ድረስ ሄዶ ይታከም ተብሎ ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ ዛሬም ቁስሌን ይዤ እኖራለሁ፤ የቦንብ ፍንጣሬ በሰውነቴ ውስጥ አለ፡፡ ጥይቶች እንኳ ከውስጤ ወጥተዋል፡፡ ሀገር እንኳን ውለታዬን ሊቆጥር፣ ኢህአዴግ እኮ ዝም ብሎ ለ6 ወር አስሮኛል፡፡ በኋላ ምንም ወንጀል ሲያጡብኝ ለቀውኛል፡፡
አሁን ስለ ሀገርዎ ምን ያስባሉ?
ሀገር ከሌለ ማንም ሰው አይኖርም፡፡ አሁን 67 አመቴ ነው፡፡ ነገር ግን ጠላት ከመጣ ለሀገሬ ከመሠለፍ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ሀገር ካልኖረ እኔ መኖር አልችልም፡፡ የኔ ህይወት እስካለ ጠላት ድንበር ጥሶ ገብቶ አያንበረክከንም፤ አሁን ህዝብን እርስ በእርስ ማባላቱ ይቁም፤ ሀገራችንን እናስከብር፡፡



Read 2379 times