Print this page
Sunday, 10 March 2019 00:00

እቺ ጐንበስ ጐንበስ ሣር ፍለጋ ሳይሆን ዱባ ለመስረቅ ነው

Written by 
Rate this item
(10 votes)


  ከዕለታት አንድ ቀን ባልና ሚስት ማሳቸውን ሊያፀዱ እሳት ጫሩበት፡፡ ማሳው እንደ ሰደድ እሳት ተያያዘ፡፡ ለካ አንድ እንስሳ እንዳጋጣሚ ማሳው ውስጥ ኖሮ፣ ሰደድ እሳቱ ያዘው፡፡ ተቃጠለ፡፡ ራሱን ለማዳን ካለመቻሉ የተነሳ፣ ደህና ኦሮስቶ ጥብስ መስሎ ቁጭ አለ፡፡ ባልና ሚስት ደግሞ ርቧቸዋል፡፡
ባል ለሚስት - መቼም እንደዚህ ተርበን ይሄን የመሰለ አሮስቶ አንምርም
ሚስት - እኔማ እንደ ጉድ ነው የሞረሞረኝ
ባል - በይ እናወራርደዋ! ትሪም ቢላም አቀራርቢያ፡፡
ሚስት  ስትበር ሄደች፡፡
ሁሉም ነገር ቀራረበና እስኪጠግቡ ኮመኮሙት፡፡
ከዚያም ባል፤
እንግዲህ ስለዚህ ነገር ትንፍሽ ትይና ወየውልሽ
ሚስት - ኧረ እኔ ምን ቆርጦኝ!
በነጋታው ግን፤
ሚስት አላስቻላትምና በቀጣዩ ቀን፤ (በዜማ)
“ትላንትና ማታ የበላነው ሲሳይ” ብላ ጀመረች
ባል፤
አባይ!
ሚስት
ሸሆናው ድፍን አይደለም ወይ?
ባል፤
አባይ!
ሚስት
አንቱ ወላዋይ፤ ሊክዱኝ ነወይ?
ባል
አሁን ምን አስለፈለፈሽ
ሆድሽን ረገጡሽ ወይ
ሚስት
ዕውነቱን መናገር ነውር ሆነ ወይ
ባል
ይልቅ ተመከሪ
ሚስት
ምን ላድርግ እሺ?
ባል
ሰው ሳይሰማ ሰው ሳያይ
እብስ ጥርግ አርገሽ ወዲያ ጣይ!
***
ከቶም በምሥጢር የሠሩትን በአደባባይ ማውጣት የሚያጣላና የሚያቆራርጥ ጉዳይ ነው፡፡ ወይ ከናካቴው አለመመሳጠር፡፡ ወይ ኃላፊነቱን ማሰብ፡፡ ወይ በግልጽ “መናገሬ ነው” ብሎ ለተዋዋይ ወገኖች ማሳወቅ፡፡ እንጂ ቀን አመቸኝ ብሎ በሌላው ወገን ላይ ጥቅም ማካበት እጅግ ጐጂ ነው፡፡
የጥንቱ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ በነበረው የግጥም መድብል፤
“…ቅንዝንዝንና የቀን ጐባጣን
ስቀህ አሳልፈው ቢያምርህ ሰው መሆን”
ይለናል፡፡
“እላይ አንዳንድ ነገር
አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር..” የሚሉን ደግሞ ገጣሚና ደራሲ ከበደ ሚካኤል ናቸው፡፡
ከሁሉም እንማራለን፡፡ የሁሉንም ትምህርት ሥራ ላይ ለማዋል መሞከር መልካም መሆኑን እናውቃለን!
መንገዳችን ዛሬም ረዥም ነው፡፡ የበለጠ ረዥም የሚያደርገው ደግሞ ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነታችንን በቅጡ ባለመወጣታችንም ጭምር ነው፡፡ በትምህርት ያልታገዘ ትውልድ፣ ነገውን በሚገባ ስለማያስተውል ይደነጋገራል፡፡ ተስፋውን አያነብም፡፡ አገሩን ወደ ውስጥ ከማየት ይልቅ ውጪ ውጪውን ብቻ ያያል፡፡ በትምህርቱ ደካማ ይሆናል፡፡ ውጪ አገር ወርቅ ይታፈሳል ብሎ ያልማል!
ታላቁ ኢኮኖሚስት ካርል ማርክስ፤ (ፍትጉ እንደተረጐመው)
“እኔ መች ፈልጌ ህይወት ያለችግር
መንፈሴስ መች ሸቷት እራሷ ግርግር
አንፈልግም እኛ አሳረኛ ህይወት
የተሞነጨረች ባሣረኛ ብዕር
ይኑር እልህ ቁጭት ንዴትና በቀል
ህይወቴ ትሞላ ትሁን የትግል ድል” ይላል፡፡
ባሁኑ ጊዜ ስለ ሌሎች ክፉ ክፉውን በማውራት፣ ንፁህ ለመምሰል የሚሞክሩ በርካቶች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡
ራስን መልካም አድርጐ የመቅረፅ ክህሎትን መቀዳጀት እንጂ ሌሎችን ማንቋሸሽን እንደ ሥራ በመያዝ ፍሬ ማፍራት አይቻልም፡፡ ይልቁንም “ይች ጐንበስ ጐንበስ፣ ሳር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነው” የሚለው ተረት ሰለባ መሆናችንን በቅጡ የሚያረጋግጥ ነው!!
ከዚህ ይሰውረን!

Read 9063 times
Administrator

Latest from Administrator