Sunday, 03 March 2019 00:00

የአድዋ ድልና የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


   የአድዋ ድልና ኢትዮጵያዊነት፣ ታሪክና ብሔራዊ መግባባት፣ የዘርና የብሔር ፖለቲካ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም ሰፊ ትንታኔ ሰጥተውናል፡፡ የክፍፍልና ብሄር ፖለቲካ ምንጩን ይነግሩናል፡፡ ምሁሩ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እነሆ፡-

አድዋና ኢትዮጵያዊነት ምንና ምን ናቸው?
ኢትዮጵያ፤ ከአድዋ በፊት 3ሺህ ዓመታት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ሃገር ናት፡፡ ነገር ግን አድዋን ልዩ የሚያደርገው፣ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ አፍሪካን ለመቀራመት፣ የአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም አፍሪካን በእጁ ያስገባበት ወቅት ነው፡፡ ትንሽ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብናይ ደግሞ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ከግብፅ፣ ከእንግሊዝ፣ ከጣሊያን ጋር በርካታ ሉአላዊነትን ያለማስደፈር ጦርነቶች የተደረጉበት ወቅት ነበር፡፡ አደዋ የእነዚህ ሁሉ ሙከራዎች መደምደሚያ ነው፡፡ ወቅቱ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ በአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት የተከበበችበት ነበር፡፡ አድዋ ይሄን የከበባትን ስጋት ሁሉ የናደ ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ እስካሁንም የአድዋ ጦርነት ብቸኛ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ነው፡፡ አድዋ የኢትዮጵያ የነፃነት አክሊል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህልውና እና ሉአላዊነት ውስጥ አድዋ ያለው ትርጉም ከፍተኛ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አልፎም በጥቁር ህዝቦችና በዓለም ላይ ለተጨቆኑ ህዝቦች ያለው ትርጉም ልዩ ነው፡፡ አድዋና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ አድዋ ባይኖር ዛሬ ያለው ኢትዮጵያዊነት አይኖርም ነበር፡፡
በአድዋ ድል ታሪክ ላይ የሚነሱ ውዝግቦች መነሻቸው ምንድን ነው?
የአደዋ ድል የማን ነው የሚሉ ክርክሮች ናቸው አሁን ችግር የሚፈጥሩት፡፡ እንዲህ ያሉ ክርክሮች የመጡት ደግሞ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ ነው፡፡ በተለይ የተጠናከሩት ከአብዮቱ ዘመን በኋላ፣ ያውም በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ነው እንጂ ስለ አድዋ ከዚያ በፊት ክርክርም ብዥታም አልነበረም። የመጡት አስተሳሰቦች ሁለት ናቸው። አንደኛው ዘውጋዊ የሆነው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይሄ ኢትዮጵያን በአጠቃላይ የሚተረጉመው በዘውጋዊ መልክ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያን የሚተረጎመው ስር ነቀል አብዮታዊ በሆነ መልክ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ትርጓሜዎች የመጡት በአብዮቱ ጊዜ ከማርክስና ሌኒን አስተሳሰብ ጋር ተያይዘው ነው። እነዚህ ናቸው የአድዋን ትርጉም ያዛባ አስተሳሰብ ያመጡት፡፡ ደርግን ጨምሮ በሶሻሊስት አስተሳሰብ ስር የነበሩ ኃይሎች በሙሉ፣ አድዋን አስመልክቶ ያስቀምጡት የነበረው ትንታኔ፤ ከድሉ ጋር ተያይዞ መነገር ያለበት የነገስታቱ ገድል ሳይሆን የሰፊው ጭቁን ህዝብ የነፃነት ተጋድሎ ነው የሚል ነበር፡፡ የተዋጉት ነገስታቱ መኳንንቱ ብቻ ሳይሆን ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፤ ስለዚህ አድዋ ይበልጥ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚወክል እናድርገው የሚል ሀሳብ ነበር የተራመደው፡፡
በእርግጥ ይህ የመጀመሪያው አስተሳሰብ አዎንታዊ መልክ ያለው ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በጣሊያን ድጋሚ ወረራ ወቅት እንኳ በጦርነቱ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሙ የነበረው ባንዲራ ሁለት ዓይነት መልክ ያለው እንደሆነ ተደርጎ በደርግ በኩል ይቀርብ ነበር፡፡ በዋናነት በወቅቱ የነበረው ክርክር፤ ነገስታት ብቻ ለምን ይወደሳሉ፤ ሰፊው ጭቁን ህዝብስ ለምን በጉልህ ስሙ አይነሳም የሚል አዎንታዊ መልክ ያለው ሃሳብ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን ሃሳብ በታሪክ ሚዛን ስናስቀምጠው፣ ብዙም አያስኬድም፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም የዓለም የጦርነት ታሪክ የሚዘገበው ጦርነቱን የመሩ የጦር አዛዦች፤ የጦርነቱ ወኪል ተደርገው ነው፡፡ የሰው ልጅ መረዳቱም በውክልና በመሆኑ፣ የጦር አዛዦችና መሪዎች ናቸው በውክልና በጉልህ የሚነሱት፡፡ ይሄ በኛ ሃገር ብቻ አይደለም፤ በሁሉም የዓለም የጦርነት ታሪክ ውስጥ ያለ ሃቅ ነው፡፡ እያንዳንዱን ተዋጊ ስም ጠርቶ የሚዘለቅ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ለአድዋ አረዳድ ውዝግብ መነሻ የሆነው ደግሞ የዘውገኝነት መግነን ነው፡፡ የዘውገኝነት መግነን አፄ ምኒሊክን ከአማራው ጋር፣ አፄ ቴዎድሮስን ከአማራው ጋር አድርጎ በአጠቃላይ ስራቸውን የመቃወም ነገር ነው የተፈጠረው፡፡ ይሄ ከየት መጣ? ከተባለ፣ የቅኝ ገዥዎች የተከሉትን ርዕዮተ ዓለም መለስ ብሎ ማየቱ ምላሽ ይሰጠናል፡፡ በአመዛኙ ይሄ ዘውገኝነት ዝም ብሎ የመጣ ወይም በልሂቃን ምርምር የተፈጠረ አይደለም፡፡ ቅኝ ገዥዎች የተከተሉት አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጣሊያንና ሌሎች ቅኝ ገዥዎች የተከሉት አደገኛ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ለምሳሌ ጣሊያን የምስራቅ አፍሪካ ኮሎኒ (ቅኝ ግዛቱን) ሲያደላድል፡- ታላቋ ሶማሊያ፣ ታላቋ ትግራይ፣ ታላቋ ኦሮሚያ… እያለ ነው፡፡ እንግሊዞችም ይሄን ስልት ይከተሉ ነበር፡፡ በተወሰነ መልኩ ግብፆችም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ካላቸው ጥቅም በመነሳት፣ ዘውገኝነትን እንደ ርዕዮተ አለም አስፋፍተዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ግብፆች አማራውን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ፈርጀው ለመምታት ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ጣሊያንም ተመሳሳይ አቋም ነበረው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለመምታት የሚፈልጉ በሙሉ ጉዳዩን ከአማራው ጋር አጣብቀው ነው የሚተረጉሙት፡፡ ጎሰኛ ልሂቃን የመጡት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ቅኝ ተገዥነት የሚናፍቃቸው፣ ተገዝተናል የሚሉ ኃይሎች፤ የአውሮፓ ቅኝ ተገዥነትን የማያውቁ ሰዎች የተፈጠሩት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ፀረ ኢትዮጵያዊነትና የተገዥነት ስሜት በጎሰኛ ልሂቃን መቀንቀን የጀመረው፣ በጣሊያን የከፋፍለህ ግዛ አስተምህሮ ነው፡፡ በተለይ አፄ ምኒሊክን ማዕከል አድርጎ፣ አፄው ራሳቸው ቅኝ ገዥ እንደነበሩ አድርጎ ማቅረብ፣ እስከዛሬ ያሉትን ቁስሎች በሙሉ አፄ ምኒልክ ላይ ማላከክ የመጣው፣ ቅኝ ተገዥነትን በተግባር ካለማወቅ ነው፡፡ የራሳቸው ልሂቅ ላጠፋው እንኳ አፄ ምኒልክን ተጠያቂ የሚያደርጉ ልሂቃን ናቸው በዚህ መንፈስ የተፈጠሩት፡፡ አፄ ምኒልክ ካለፉ ከ100 ዓመታት በላይ ቢሆናቸውም አራት ትውልድ ያህል ዛሬም እየተወቀሱ ነው፡፡ አራት ትወልድ በሙሉ አፄ ምኒልክን እየወቀሰ፣ ኢትዮጵያዊነትን ለአማራው ሰጥቶ፣ ከኢትዮጵያዊነት በተቃራኒው እየቆመ ነው ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ አድዋንም ከዚህ ጋር አስተሳስረው የማጠልሸትን መንገድ ነው ሲከተሉ የኖሩት፡፡ ኢትዮጵያን የሚያስከብረውን፣ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርገውን በሙሉ እግር በእግር እየተከታተሉ የሚፃረሩ ርዕዮተ ዓለሞች በመንገሳቸው የተነሳ ነው እንጂ አድዋ ለሰከንድ እንኳ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አልነበረም፡፡ ለምን ወራሪን ወግተን አሸነፍን? ለምን ነፃነታችንን አስከበርን? ብሎ ማልቀስ ከበታችነት ስሜት የሚመጣ ነው። ታሪክ እየተዛባ፣ ትውልድም የበታችነት ስሜት ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ የሚቀረፁ አስተሳሰቦች በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት የገነኑ ስለሆኑ በቀላሉ የሚስተካከሉ አይሆኑም፡፡
ዛሬ ትልቁ የልዩነት ምንጭ የሆነው የዘር፣ የጎሳ፣ የብሔር… ጉዳይ ነው፡፡ በአድዋ ጦርነት የብሄር ጉዳይ ምን ቦታ ነበረው? ከዚያ በኋላስ ባሉት አመታት…?
በአድዋ ጦርነት ጊዜ ሃገሪቱ አንድነቷ የተጠናከረ ነው፡፡ ህዝብ በወንዝ ነው እንጂ የሚለየው ጎጃሜው በጎጃሜነቱ፣ ሸዋው በሸዋነቱ፣ ሃማሴኑ በሃማሴንነቱ የሚኖረው እንጂ ብሔሩ ርዕዮተ ዓለሙ አልነበረም። በወቅቱ የሃገሬው ርዕዮተ ዓለም ሃይማኖቱ ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ “ማርያምን አልምርህም” ነው ያሉት። ብሔርተኝነቱም ያለው ሃይማኖቱ ውስጥ ነው። “እናት ሃገሩ ሚስቱ፣ እናቱ ናት” የሚል ርዕዮተ ዓለም ነው ህዝቡ የነበረው፡፡ ምኒልክ በዚህ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ያለን ሃገር እየመሩ ስለነበር፣ ህዝቡን በአንድ ቃል አስተባብሮ፣ ጦርነቱን ለማሸነፍ አልከበዳቸውም፡፡ አድዋ የኢትዮጵያ አንድነት ፅኑ ማሳያ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ዘርና ብሄር የልዩነት መነሻ መሆን የጀመረበት ትክክለኛ ወቅት መቼ ነው?
ችግር መፈጠር የጀመረው ከአድዋ በኋላ ነው። በተለይ የአደዋን ድል ተከትሎ፣ ወደ ሃገሪቱ የሚመላለሱ አውሮፓውያን ዘጋቢዎች ነበሩ። በተለይ በሃገሪቱ የነበረውን የአንድነት መንፈስ በወቅቱ ይታዘቡ ነበር፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ የብሔራዊ ፍፁም አንድነቷን ያፀናችበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ እና ጣሊያን ወይም ነጭ በመሸነፉ መላ አውሮፓ በእጅጉ ተናደው ነበር፡፡ የሃገሪቱ አንድነትም ያበሳጫቸው ነበር። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ስልቶችን ነድፈው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የማያዳግም ቅጣት ለመቅጣት ያልሙ ነበር፡፡ ለዚህ ቀላል ሆኖ ያገኙት ደግሞ ሃገሪቱን በዘውግ - በጎሳ መከፋፈል ነው፡፡ ከአድዋ በኋላ ጣሊያኖች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የቆንፅላ ፅ/ቤቶችን አቋቁመው ነበር፡፡ ያቋቋሙትም ለዚህ ተግባር ነበር፡፡ በቆንፅላዎቻቸው አማካይነት የህዝቡን ስነ ልቦናና አንድነት እያጠኑ፣ እየሰለሉ፣ ባላባቶቹን በድለላ እየከፋፈሉ፣ የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊ ክፍተቶች - ሃይማኖትን ጨምሮ ጎሳ፣ ዘርን፣ መደብን ያጠኑ ነበር፡፡ ደቡብ፣ ሰሜን የሚባለውን፣ ኩሸቲክ ሰሜቲክ፤ አቢሲኒያ ኢትዮጵያ የሚባለውን ክፍፍሎች በሙሉ እያጠኑ፣ እየከፋፈሉ፣ ለ40 ዓመት መርዛቸውን ሲረጩ ነው የኖሩት፡፡ አንድ ትውልድ መርዝ ሲረጩ ኖረዋል፡፡
እንደሚታወቀው፤ በማይጨው ጦርነት ዋዜማ ላይ ትላልቆቹ ደጃዝማች፣ ራሶች ናቸው ሸፍተው ከጣሊያን ጎን የተሰለፉት፡፡ በአንድ ጊዜ ተንደው ነው ባንዳ የሆኑት፡፡ ጦርነቱ ማይጨው ላይ ሳይደረግ ነው ኢትዮጵያ የተሸነፈችው፡፡ ይሄን ያመጣው ትልቁ ነገር የጣሊያኖች የ40 ዓመት የመከፋፈል ስራ ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመናዊነትን አፋጥናለሁ በሚል ስልጣንን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ራሳቸው ማሰባሰባቸውና ሌሎችን የየአውራጃ ገዥዎች መብቶችን መሸርሸራቸው እንዲሁም ዘውዱን አንድ ቤተሰብ ብቻ የሚይዘው አድርገው በአዋጅ ማውጣታቸው፤ ነገ ዘውዱን አግኝቼ ሃገር እመራለሁ የሚለውን የየአካባቢው ገዥ ቅሬታ ውስጥ መክተቱ ደግሞ ታማኝ ለማጣታቸው ሌላኛው ምክንያት ነበር፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ዓለም ያወቃቸው ጥበበኛ ዲፕሎማት ቢሆኑም ኢትዮጵያን በወታደር ኃይል ባለማጎልበታቸው የተነሳ ሽንፈቱ እንዳጋጠመም መረዳት ይቻላል፡፡ እሳቸው የተማመኑበት ዲፕሎማሲ ሲከሽፍ፣ አስቀድመው በዲፕሎማሲ የሰሩትን ያህል ወታደራዊ አቅም በመገንባት ላይ አለመስራታቸው ዋጋ ካስከፈሉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ እሳቸው የተማመኑበት የዓለም መንግስታት ድርጅት፣ ተስማምቶ ነው ኢትዮጵያን ለጣሊያን የሸጣት፡፡ ከምንም በላይ ግን ጣሊያን በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ የሰራው የመከፋፈል ሴራ፤ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ስልጣንን ወደ ራሳቸው ከማሰባሰብ ጋር ተደማምሮ፣ በሁለተኛው ጦርነት እንድንሸነፍ አድርጎናል፡፡
ወያኔም የአናሳዎች መንግስት ስለነበረ፣ ለከፋፍለህ ግዛው መርህ እንዲጠቅመው የኮረጀው የአስተዳደር መዋቅር ነው፡፡ ጣሊያን ያቀደውንና በ5 ዓመቱ ወረራ በተግባር ያዋለውን ወያኔ አጠናክሮ፣ ላለፉት 27 ዓመታት በተግባር አውሎታል፡፡ አሁን የምንከተለው የፌደራል ስርአት፤ ጣሊያን ለቅኝ ግዛት ስልት ሲጠቀምበት የነበረው አይነት ነው፡፡
የአደዋ ድል በኢትዮጵያዊያንና በሌላው ዓለም ባሉ አፍቃሬ ኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለው አተያይ እንዴት ይገለፃል?
ከኢትዮጵያ ውስጥ ለኢትዮጵያዊነት ግምት የማይሰጥ የተወሰነ አካል ለዚህ ድል ብዙም ግምት አይሰጠውም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነን ለምንል ግን አደዋ አሁንም የአልማዝ አክሊላችን ነው፡፡ የነፃነታችን አክሊል ነው፤ እንኮራበታለን፣ ለወደፊትም ልጆቻችን እንዲኮሩበት የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ በአክራሪ ዘውገኞችና በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አራማጆችና መካከል ያለው አተያይ ነው የተራራቀው እንጂ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አራማጆች በሌሎች ሃገራት በሚገኙ አፍቃሬ ኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ለአድዋ ያለው ስሜት ተመሳሳይ ነው። አትዮጵያውያን አድዋን አልካድንም፤ የካዱት በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የማይሰማቸው ናቸው፡፡ አሁንም አደዋ በዓለም ላይ ለጥቁር ህዝቦችና ጭቁኖች አንፀባራቂ ድል ነው፡፡ ለየትኛውም የጭቁን ህዝቦች አደዋ የተስፋ አርማ ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከምንም በላይ የህልውናችን መሰረት ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ርዕዮተ ዓለሙ አድዋን ማዕከል ሳያደርግ ሊመሰረት አይችልም፡፡
አባቶቻችን አጥንታቸውን የከሰከሱበት፣ ደማቸውን ያፈሰሱበት፣ ለ3 ሺህ ዓመታት ጠብቀው ያቆዩትን ሃገር፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊገድላት የመጣን ቅኝ ገዥ ኃይል ድል የመቱበት ነው፡፡ ይሄ ልንኮራበት ይገባል፡፡ ለሃገራችን ማንኛውንም መስዋዕትነት እንደምንከፍል ቋሚ ማስረጃችን ነው - አድዋ፡፡ ነገር ግን ስልጣን ይዘው፣ የኢትዮጵያን ሚዲያዎች ተቆጣጥረው የነበሩ ኃይሎች፣ አድዋን በማጥላላት ዘመቻ ላይ በግልፅ ተሰማርተው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ናቸው፣ በአድዋ ላይ መርዝ የረጩት፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ እንኳ አድዋ ድረስ ያለ ስጋት መሄድ ያልተቻለው ለዚህ ነው፡፡ ይሄ ለወደፊት ልጆቻቸው የሚሸማቀቁበት አሳፋሪ ታሪክ ነው፡፡
በታሪክ የሚያግባባን ብሔራዊ ጀግና ማጣታችን፣ ለብሔዊና አለመግባባቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ የእርስዎ አተያይ ምንድን ነው?
እኔ በተገላቢጦሽ ነው የማየው፡፡ ብሔራዊ መግባባት አለመቻላችን ነው ብሔራዊ ጀግና ለማጣታችን መሰረት የሆነው፡፡ ያለመግባባታችን ነው ጀግኖቻችንን እንድንቆጥራቸው ያስገደደን፡፡ ዛሬ ለኢትዮጵያዊነት የተዋደቁ ጀግኖቻችንን ባልዋሉበት፣ ባልሰሙበት፣ በሌሉበት አጥንት ቆጥረን፣ ዘር ሰጥተናቸው ነው ወደ የራሳችን የምንጎትተው። እገሌ የአማራ ጀግና ነው፣ እገሌ የትግሬ ጀግና ነው፣ እገሌ የኦሮሞ ጀግና ነው እያልን፣ ሰዎቹ በነበሩበት ጊዜ ያላሰቡትን ነገር ነው የምንሰጣቸው፡፡ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ አድዋ ላይ የተዋጉት የኦሮሞ ጀግና ነኝ ብለው አይደለም፤ የኢትዮጵያ ጀግና ነኝ ብለው ነው፡፡ ራስ አሉላ አባነጋ አደዋም ዶጋሊም ሲዋጉ ሃገሬ ኢትዮጵያ ወራሪ አይደፍራትም ብለው ነው፡፡ የኢትዮጵያን አፈር አትነካም ብለው ነው የተዋደቁት እንጂ የትግሬ ጀግና ነኝ ብለው አይደለም፡፡ እኛ ነን አጥንትና ደም እየቆጠርንላቸው ይሄ ትግሬ፣ ያኛው አማራ፣ ሌላው የኦሮሞ ጀግና ነው እያልን የከፋፈልናቸው፡፡ ስለዚህ በብሔራዊ ጉዳይ አለመግባባታችን ነው ሁላችንም የምንቀበለው ጀግና  ያሳጣን፡፡ በእርግጥ በየትኛውም አለም መቶ በመቶ ሃገርን ሙሉ ለሙሉ ያስማሙ ጀግኖች አይገኙም። ለምሳሌ የአሜሪካ መስራች አባቶች የሚባሉት እነ ጆርጅ ዋሽንግተን፣ ጀፈርሰን ዛሬ ጥቁሮች ቅሬታ የሚያቀርቡባቸው ናቸው፤ ይሁን እንጂ በኛ ሃገር እንዳለው ዘመንን ባልዋጀ ጥላቻ አይታወሩም፡፡ ባርነትን ይደግፋሉ ብለው ይቃወሟቸዋል፡፡ የጋራ ብሔራዊ ጀግና ማለት፣ መቶ በመቶ የሚያስማማ ነው ብሎ መጠበቅ አይቻልም፤ ነገር ግን መሰረታዊ በሆኑት ጉዳዮች፣ የታሪክ አንጓዎች ከተግባባን በቂ ነው፡፡
በታሪክ ወደኋላ እየተጓዝን ከመናቆርና ከጥላቻ እንድንወጣ መፍትሄው ምንድን ነው?
እንዲህ አብዮቱ ሁሉን ነገር ካፈነዳው በኋላ እስካሁን የሰከነ ነገር የለም፡፡ የሰከነ ትውልድ አልተፈጠረም፡፡ በደርግም በኢህአዴግም የታፈነ ትውልድ ነው የተፈጠረው፡፡ ሁለት ተከታታይ ትውልድ የታፈነና ለአንድ ቦይ ፕሮፓጋንዳ የተጋለጠ ነው፡፡ የኛ ቀጣይ ልጆች ከዚህ አፈና ይላቀቁ ይሆን የሚለውን በቀጣይ የምናይ ነው፡፡ እስከዚያው ግን ኢትዮጵያውያን ለታሪካችን ለመግባባት በመጀመሪያ አሁን ባለው የፖለቲካ ስርአታችን ልንግባባ ይገባል። ሁሉንም በእኩልነት የሚያያይዘው ከአክራሪነት የወጣ ፍትሃዊ የፖለቲካ ስርአት ሊገነባ ይገባዋል። ያ እስካልተገነባ ድረስ ስለታሪካችን ሰከን ብለን የምንነጋገርበት እድል ሊመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ማስተካከል ያለብን የፖለቲካ ስርአታችንን ነው፡፡ የፖለቲካ ስርአቱን ስናስተካክል ነው በታሪክ ጉዳይ ሰከን ብለን ተነጋግረን መግባባት የምንችለው። ሁላችንንም በእኩልነት የሚያይ ስርአት ሲፈጠር፣ ምንድን ነው ብለን የጋራ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትን ማስፋፋት እንችላለን፡፡ ይሄን ማድረግ አይቸግረንም። ትልቁ የፖለቲካ ነቀርሳ ከተስተካከለ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ስርአቱን ከተራ የውረፋ ስርአት ማላቀቅ ወሳኝ ነው፡፡ የትግሬ ተራ ነው፣ የአማራ ተራ ነው፣ የኦሮሞ ተራ ነው፣ የሶማሌ ተራ ነው … እየተባለ መቀለጃ የማይሆን ስርአት መመስረት ግዴታችን ነው፡፡ አሁን የሰሜን ተራ አብቅቷል፤ አሁን የደቡብ ተራ ነው የሚል ልሂቅ ባለበት ሃገር ግን እንዴት አድርገን ነው በታሪክ የምንግባባው? ሃገርን የከፋፈለው የዘውግ አስተሳሰብ ነው በመጀመሪያ መፍትሄ ማግኘት ያለበት፡፡   Read 649 times