Sunday, 03 March 2019 00:00

የማፍረስ አባዜ እስከ መቼ?

Written by  ኩርኩራ ዋፎ - ከለገጣፎ
Rate this item
(1 Vote)


ሰሞኑን ግንባር ቀደም አጀንዳ ሆኖ ሶሻል ሚዲያውን አጨናንቆ የከረመው የለገጣፎ ቤት ፈረሳ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የለገጣፎ ከተማ ነዋሪ በመሆኔ በዚያ አካባቢ የተፈጸመውንና እየሆነ ያለውን ሁኔታ በቅርብ ርቀት ተከታትየዋለሁ፡፡ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝም በዓይኔ በብረቱ ያየሁት በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከተማ ማደስ ማለት ምን ማለት ነው? ከተማን በማደስ ረገድ ዓለም አቀፍ ተሞክሮው ምን ይመስላል? መጠለያን በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድንጋጌዎች ምን ይላሉ? የመሳሰሉት ጥያቄዎች በጽሁፉ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመጨረሻም፤ ቤት የማፍረስን ጉዳይ በተመለከተ ምን ቢደረግ ይሻላል? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመላከት እሞክራለሁ፡፡
ከተማ ማደስ
በአሜሪካ ቺካጎ ተደጋጋሚ የከተማ እድሳት (Urban Renewal) መደረጉን የታሪክ ሰነዶች ይነግሩናል፡፡ እ.ኤ.አ በ1940ዎቹ እና በ1950ዎቹ ከሐይዴ ፓርክ ምንዱባንን የመጠራረግ እርምጃ ተወስዷል፡፡ በ1960ዎቹ ደግሞ ረዣዥም ፎቆችን በመስራት ተነሺዎች መጠለያ እንዲያገኙ ተደርጓል። የሚገርመው ነገር በዚያ ሂደት ቅድሚያ ይሰጥ የነበረው ለአናሳዎቹ ድሃ ጥቁሮች እንጂ ለድሃ ነጮች አልነበረም፡፡ ነጮቹ ከከተማ ውጪ ወዳሉ የገጠር መንደሮች እንዲሄዱ ነበር የሚገፉት፡፡ ይሄ አካሄድ ለጥቁሮች ያደላ ቢመስልም ነጮችና ጥቁሮችን ለያይቶ ለማስፈር የታለመ ይመስላል፡፡
የከተማ እድሳት (መልሶ ማልማት) በሚታሰብበት ወቅት የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የአካባቢ የመሬት ባለቤቶች፣ የአካባቢ መሪዎች ተወካዮች፣ ወጣቶች፣… በመሰብሰብ በአማራጮች ላይ ይወያያሉ፡፡ ከእድሳቱ በኋላ በአዲሱ ፕላን ምን ምን እንደሚካተት ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ለተነሺዎቹ የሚሆን መጠለያ ይዘጋጃል፡፡ ተነሺዎችም ምንም ዓይነት ጫጫታ ሳይፈጠር በፈቃደኛነት ራሳቸው መሬቱን ያስረክባሉ፡፡ መንግስታችን ህዝብን ማስለቀስ እንደ ዓላማ ይዞ ካልሆነ በስተቀር በእኛ ሀገር ይህንን ማድረግ ለምን አቃተን?
ቤት የለሽነት፣ የጎዳና ዳር ነዋሪነት የሦስተኛው ዓለም እጣ ፋንታ ብቻ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 በትምህርት ቤቶች በተደረገ ጥናት፤ በአሜሪካ 1.3 ሚሊዮን ተማሪዎች ከቤት አልባ ቤተሰብ የመጡ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በአሜሪካ በድንኳን የሚኖሩ ሰዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ የሥራ መኖር መጠለያ ለማግኘት ዋስትና ሊሆን አለመቻሉም ታይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዋና ዋና ከተሞች እየተገፉ ወደ አጎራባች አነስተኛ መንደሮች መፍለስ የተለመደ ክስተት ነው፡፡ መፍትሄው መብትን ለማስከበር ትግል ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአሜሪካ ከሃያ ከተሞች የተውጣጡ ሰዎች “የቤት የለሾች ብሄራዊ ማህበር” የሚባል ተቋም መስርተው ትግላቸውን የቀጠሉት፡፡ በዚህም መሰረት የአሜሪካ ኮንግረስ “መጋዘን ሳይሆን መኖሪያ ቤት” የሚል ህግ እንዲወጣ አደረጉ፣ ቤት የለሾች መብታቸውን አስከበሩ፡፡ መጠለያ ኖሮን ሥራ ባይኖረን ችግሩ ዝቅተኛ ነው - ለምኖ መብላትም ይቻላል፡፡ መጠለያ ከሌለ ግን ሁሉም ነገር የለም። መጠለያ የማግኘት መብት የለንም ማለት የመኖር ዋስትና የለንም ማለት ነው የሚባለውም በዚሁ ምክንያንት ነው፡፡
የከተማ ማደስ ዋነኛ ዓላማ፤ የመጠለያ ችግርን ለመቅረፍና ከተማውን ለማዘመን ነው፡፡ በኛ ሀገር ግን ህዝብ አፈናቅሎ የሚደረግ የከተማ እድሳት ዓላማ፣ ኢንቨስትመንት አስፋፋለሁ በሚል ሰበብ መሬትን ከድሃ ነጥቆ ለከበርቴዎች የማደል ስልት መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ የሚያሳዝነው “ዓላማ የለሾቹ ከበርቴዎች” ደግሞ ከመንግስት የተሰጣቸውን የከተማ መሬት ከማልማት ይልቅ አጥሮ ማስቀመጥን መርጠዋል፡፡ ሌላው የከተማ ማደስ ዓላማ፤ በአንድ ከተማ ያለን የብሄርና የኢኮኖሚ ብዝሃነት በማስተሳሰር ተደጋግፈው እንዲኖሩ ማድረግ ነው። በእኛ ሀገር እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ በመሆኑ “ባንቱስታኒዝም” እና “ጄሪማንደሪንግ” የሚሉትን ሃሳቦች እንድናስታውስ አድርጎናል፡፡
ካነሳነው አይቀር “ባንቱስታኒዝም” እና “ጄሪማንደሪንግ” ምን ማለት እንደሆነ አይተን እንለፍ፡፡ በዘመነ አፓርታይድ በደቡብ አፍሪካ የ“ባንቱስታን” የሰፈራ መንደሮች ተፈጥረው ነበር። የአፓርታይድ መንግስት ዓላማ ጥቁሮችን በአንድ አካባቢ በማሰባሰብ ራስ ገዝ የጎሣ ግዛቶችን መፍጠር ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአሜሪካ “ጄሪማንደሪንግ” በመባል የሚታወቅ “የፖለቲካ ጨዋታ” ነበር። “ጄሪማንደሪንግ” ማለት በእንግሊዝኛ “The dividing of a state, county, etc., into election districts so as to give one political party a majority in many districts...” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፤ ወደ አማርኛ ስንመልሰው “አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ እንዲያሸንፍ በሚያስችል መልኩ አገርን በምርጫ ወረዳዎች መከፋፈል” የሚል ትርጉም አለው፡፡
“ባንቱስታኒዝም” እና “ጄሪማንደሪንግ” አንድነትም ልዩነትም አላቸው፡፡ “ባንቱስታኒዝም” የዘረኝነት ባህሪ ያለው ሲሆን፤ “ጄሪማንደሪንግ” ደግሞ ፖለቲካዊ ባህሪ አለው፡፡ አሁን በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ተግባር የባንቱስታኒዝምም የጄሪማንደሪንግም ገጽታ ያለው መሆኑ ይስተዋላል፡፡
በየትም ሀገር የከተማ እድሳት (መልሶ ማልማት) የተለመደ የመንግስት ተግባር ነው፡፡ ግን ከተማ የሚታደሰው ለምንና እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ በጥልቀት መታየት የሚገባው ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ ምሁራን፤ የከተማ እድሳት በገዢዎች ፍላጎት ላይ የሚመሰረት ሳይሆን በህዝቡ (በነዋሪው) ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሚገባው ይመክራሉ፡፡ የከተማ እድሳትም ሆነ የከተማ ልማት ሥራ ለድሃዎች ትኩረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ከከተማ ማደስ ጋር ተያይዞ በመንግስት በኩል መከናወን ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ አነስተኛ የኪራይ ዋጋ (Low cost house) ያላቸው ቤቶችን ለተነሺ ዜጎች ማዘጋጀት መሆን ይገባዋል፡፡ በኛ ሀገር ግን የሚታሰበው በተገላቢጦሽ ነው፡፡ በኛ ሀገር የድሃ ቤት አፍርሶ መሬት ለከበርቴ የመስጠት አጥፊ ስልት ነው የምንከተለው፡፡
የፖለቲካ ኃይሉ ድምፅ ያለውን (voter) ብዙሃኑን ህዝብ ማዕከል ማድረግ አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አንድ አካባቢ ለልማት ከተፈለገ ተነሺው ህብረተሰብ በጉዳዩ ላይ እንዲመክር እድል ሊሰጠው ይገባል፡፡ የአንድ አካባቢ ህብረተሰብ በልማትም ይሁን በሌላ ምክንያት ለዘመናት ከኖረበት ቀየ ሲፈናቀል የሚደርሰው ቀውስ መጠለያ ከማጣትና ከማግኘት ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም፡፡ በርካታ ነገሮች አብረው ይናዳሉ፡፡ ቤት ሲፈርስ በዚያ አካባቢ ለረጅም ጊዜ የኖሩ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን ሽማግሌዎች ለዘመናት የገነቡት ዕድር፣ እቁብ፣ መረዳዳትና ሌላውም ማህበራዊ ትስስር (social bondage) ነው የሚበተነው፡፡ ስነ-ልቦናዊ ቀውሱ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በሀገራችን የተደረጉ የከተማ ልማትና እድሳት ጥናቶች፣ መነሻና መድረሻቸው አፍራሹን (መንግስትን) እንዴት ይጠቅማል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንጂ የፈረሳው ሰለባ በሚሆነው ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ትኩረት እንደማያደርግም መገንዘብ ይቻላል፡፡
የአፄውን መንግስት እንተወውና በደርግና በኢህአዴግ የተደረጉትን ከተማ ተኮር ስራዎች በአጭሩ እንቃኝ፡፡ በአፄ ኃ/ስላሴ የመጨረሻ ዓመታት ብቅ ብቅ በማለት ላይ የነበሩት ከበርቴዎች፤ በከተሞች አካባቢ ቤት እየሰሩ ማከራየት ጀምረው ነበር፡፡ ደርግ መጣና የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን ወርሻለሁ ብሎ በማወጅ እነዚያን ቤቶች ወረሳቸው። ደርግ የተወረሱ ቤቶችን በሁለት ከፈላቸው፡፡ ከአንድ መቶ ብር በታች የሚከራዩትን “የቀበሌ ቤት” ብሎ በቀበሌ አስተዳደር ስር አደረጋቸው፡፡ ከመቶ ብር በላይ የሚከራዩትን ደግሞ በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ስር ሆነው እንዲተዳደሩ አደረገ፡፡ የቀበሌ ቤቶች ከ0.25 ሣንቲም ጀምሮ እስከ አንድ መቶ ብር ድረስ የሚከራዩ ሲሆን፤ እነዚህ ቤቶች በዋናነት በዚያ ወቅት ቤት አልባ ለነበሩ ድሃዎች የተከራዩ ነበሩ። እነዚህን ሁኔታዎች ያጠና አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ ከሆነ ደርግ በዚህ አዋጅ የመሬትም የቤትም ባለቤት ያደረገው ለዘመናት መሬት አልባ የነበሩትን ጢሰኞች፣ ሸማ ሰሪዎች፣ አንጥረኞች፣ ሸክላ ሰሪዎች፣ ወዛደሮች፣… ነበር፡፡
ኢህአዴግ መጣና ደርግ መጠለያ የሰጣቸውን ምንዱባን እያፈናቀለ ቀደም ሲል ወደነበሩበት ድህነትና በረንዳ አዳሪነት መለሳቸው፡፡ ታስቦበት ይሁን ሳይታሰብ ኢህአዴግ የዘመተው በድሃዎች ላይ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ኮሚንስት ነኝ፣ ለድሃ ትኩረት እሰጣለሁ (pro-poor ነኝ) ቢልም ተግባሩ በተቃራኒው ነበር፡፡ እንቁላል ሻጩን እያፈናቀለ ከበርቴው እንቁላል የመሰለ ህንፃ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቼም ድሃ ተኮር (pro-poor-ነት)  ሊሆን አይችልም፡፡
የተ.መ.ድ ድንጋጌዎች ስለ መጠለያ ምን ይላሉ?
መጠለያን (መኖሪያ ቤትን) በተመለከተ ሀገሪቱ ከፈረመቻቸው የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ካወጧቸውን ድንጋጌዎች፣ መርሆዎችና መመሪያዎች አለፍ አለፍ እያልን እንያቸው፡፡ “መጠለያ” የማግኘት መብት በተ.መ.ድ የተለያዩ የህግ ሰነዶች ውስጥ እውቅና የተሰጠው የሰብአዊ መብት አካል ነው፡፡ “መጠለያ” በተ.መ.ድ የሰብአዊ መብት ዩንቨርሳል ዲክላሬሽን በአንቀጽ 25፣ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ የማህበራዊና የባህል ስምምነት በአንቀጽ 11፣ በህፃናት መብት ኮንቬንሽን በአንቀጽ 27፣ ማንኛውንም ዓይነት የዘር መድሎ ለማስወገድ በወጣው ኮንቬንሽን በአንቀጽ 5፣… በመሳሰሉት የህግ ሰነዶች ውስጥ ጥበቃ የተደረገለት የሰብአዊ መብት አካል ነው፡፡
ፈረንጆቹ “The Right to Housing is a Human Right” ይላሉ፡፡ ሲተረጎም “መጠለያ የማግኘት መብት ሰብአዊ መብት ነው” እንደማለት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ መጠለያ የማግኘት መብት በበርካታ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶች ውስጥ እውቅና እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 25 የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብትን እንደ የኑሮ ደረጃ መለኪያ አድርጎ ይወስደዋል፡፡ እንዲህ ይላል፡- “ማንኛውም ሰው ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ ጤንነትና ደህንነት በቂ የሆነ መጠለያ የማግኘት መብት አለው፡፡ ይህም መጠለያ ምግብ፣ ልብስ፣ ቤት፣ ህክምናና አስፈላጊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማግኘት… መብትን ያጠቃልላል” ይላል፡፡
በቂ የሆነ መጠለያ የማግኘት መብት እ.ኤ.አ በ1996 በኢስታንቡል በተደረገ ስብሰባ ላይ ዋናው አጀንዳ ሆኖ በኢስታንቡል ስምምነትም ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በዚህ ስምምነት በአንቀጽ 61 ላይ መንግስታት በየሀገሮቻቸው “በቂ መጠለያ የማግኘት መብትን የማበረታታት፣ ጥበቃ የማድረግ እና የማረጋገጥ” ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ እ.ኤአ. በ2001 በተደረገ የተባበሩት መንግስታት የሰፈራ ፕሮግራም ስብሰባ ላይም ይህንን ስምምነት የሚያጸና ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡
መጠለያ የማግኘት መብት ማለት ምን ማለት ነው?
በተመድ ትርጉም መሰረት “መጠለያ የማግኘት መብት” ማለት፤ “በግዴታ ከመፈናቀል፣ ከማስፈራራት እና ከወከባ ህጋዊ ጥበቃ የማግኘት፣ የኪራይ ክፍያው የምግብ-የትምህርት-የጤና ወጪዎችን የማይነካና ተመጣጣኝ የሆነ፣ ለመኖሪያ ምቹ የሆነ በቂ ስፋት ያለው፣ ከቅዝቃዜ፣ ከሙቀት፣ ከዝናብ፣ ከንፋስ ወይም ከሌሎች ለጤና ተስማሚ ካልሆኑ አደጋዎች የመጠበቅ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ-ኤሌክትሪክ-የቆሻሻ ማስወገጃ ያለው፣ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሆነ፣ ለስራ-ለትምህርት-ለጤና ተቋማት ቅርብ የሆነ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ተግባራትን ለመፈጸም ምቹ የሆነ” ማለት ነው፡፡
በዚህ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ድንጋጌ ውስጥ የተጠቀሰው “ምቹ መጠለያ የማግኘት መብት” በየሀገሩ መንግስታት ተግባራዊ መደረጉን የምናረግጥባቸው መስፈርቶች “መጠለያ ማግኘት፣ አለመፈናቀል፣ ቤት የለሽ አለመሆን” የሚሉት መሆናቸው በተለያዩ ሰነዶች ውስጥ ተጠቅሷል፡፡
በተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ድንጋጌ መሰረት፤ እያንዳንዱ ሰው መጠለያ የማግኘት መሰረታዊ ሰብአዊ መብት ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በዚህ መብት መሰረት ሁሉም ሰው ደህንነቱ ተጠብቆ የሰላምና የክብር ኑሮ እንዲኖር ማድረግ የመንግስት ግዴታ መሆኑ እንዲሁም ሰዎች ምቹ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኙት የሚችሉትና በጉልበት የማይፈናቀሉበት መጠለያ የማግኘት መብትን የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበት ጭምር ተገልጿል፡፡
በዚሁ የተ.መ.ድ ድንጋጌ ውስጥ “በግድ ማፈናቀል” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብያኔ (Definition) ተቀምጧል፡፡ በተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ውሳኔ ቁጥር 1993/77 መሰረት “በግዳጅ ማፈናቀል መጠለያ የማግኘት መብትን የማሳጣት የሰብአዊ መብት ጥሰት” መሆኑ ተገልጿል። ከዚህ ድንጋጌ በመነሳት የውስጥ መፈናቀልን በተመለከተ የተቀመጠው መርህ “ማንኛውም ባለስልጣንና ዓለም አቀፍ ተዋንያን በዓለም አቀፍ ህግ የተደነገጉትን ሰብአዊ መብቶችን የማክበር እና መፈናቀልንና መፈናቀልን የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን የመከላከል ግዴታዎችን የመወጣትና የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት” ይላል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው “ቤት የለሽነት መጠለያ የማግኘት መብት አለመከበሩን የሚያሳይ ግልጽና አሳሳቢ ምልክት ነው” ይላሉ፡፡ ከላይ የቀረቡትን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በልባችን እንያዝና ወደ ሰሞኑ የለገጣፎ ሁኔታ እናምራ፡፡
ስለ ለገጣፎ
በፖለቲካ ጡንቻ የታገዘው የለገጣፎ ቤት ፈረሳ የሰሞኑ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር፡፡ በለገጣፎ የሰባት ቀን አራስ አልጋ ላይ እንዳለች ቤቷ ላይዋላይ ፈርሶባታል። ጧት በሰላም ወጥተው የሄዱት ቤት ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ዶጋዐመድ ሆኖ የጠበቃቸው ህፃናት፤ “ቤታችን የት ሄደ?” ብለው ሲጠይቁ በመንግሥት ሚዲያ አይተናል፡፡ በአረብ ሀገር በበርሃ ተጠብሳ ባፈራችው ሳንቲም የሰራቺው ቤት በደቂቃዎች ውስጥ እንዳልነበር የሆነባት ከርታቴ ራሷን ማጥፋቷን ሰምተናል፡፡ አንዱን ቤት አፍርሶ ሌላውን የመዝለልና እንደ ዳማ መጫወቻ መዝጎርጎሩንም ከፍርስራሹ አሻራ ላይ አንብበናል፡፡ ሌሎችም አሳዛኝ ሁኔታዎችን አይተናል፣ ሰምተናል፡፡
እነዚህ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ለኦሮሚያ መንግሥትና ለከንቲባዋ እንደ ስደተኛ የሚታዩ “መጤዎች” እንጂ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆናቸው አልታያቸውም፡፡ ከስደተኛ ካምፕ ነዋሪዎች ጋር እያነጻጸሩ መግለጫ እስከ መስጠት የደረሱት ለዚሁ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ቤታቸው ከፈረሰባቸው ዜጎች ይልቅ አካባቢውን የማያውቁትና የአካባቢውን ማህበረሰብ ስነ-ልቦና ያልተገነዘቡት “መጤ”፣ ራሳቸው ከንቲባዋ መሆናቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቤት ማፍረስ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ የህይወታችን አካል ከሆነ 27 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እናም በለገጣፎ ቤት መፍረሱ አላስገረመኝም፡፡ የገረመኝ ነገር ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2011 የከተማው ከንቲባ በአራት ፖሊስ ታጅበው ወደ ፈረሰው መንደር መጡ፡፡ እኔም በአቅራቢያው ነበርኩ፡፡ ምን ሊያደርጉ ነው ብለን ስንጠብቅ፣ በአቅራቢያው ወደ ነበረው ቤተክርስቲያን ገቡ፡፡ እዚያ ተጠልለው ለነበሩ ዜጎች አንዳች ማበረታቻ ሊያደርጉ ነው ብለን ስንጠብቅ፤ “እነዚህ ሰዎች እዚህ መጠለላቸው የከተማችንን ገጽታ እያበላሸ ስለሆነ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ አንድ ሰው እዚህ አካባቢ እንዳይታይ አስወጡ…” የሚለው የከተማው ከንቲባ ቀጭን ትእዛዝ ግን ማስገረም ብቻ ሳይሆን ልብ ያቆስላል፡፡
የለገጣፎ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ሐቢባ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች፣ በርካታ ተገቢ ያልሆኑ አስተዛዛቢ ሃሳቦችን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ ሐቢባ ቤት ማፍረሳቸው ሳያንስ ቤተክርስቲያን አትጠለሉ ማለታቸው ግን እጅግ የከፋ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ነው፡፡ ወ/ሮ ሐቢባ ከትናንት ጓዶቻቸው የተማሩ አልመሰለኝም፡፡ ዛሬ በየሚዲያው “በዜጎች ላይ ሰብአዊ መብት በመጣስ” ክስ እንደተመሰረተባቸው እየተነገሩ ያሉ ሰዎች እኮ ትናንት እንደ ወ/ሮ ሐቢባ ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ ወ/ሮ ሐቢባ ይህንን ልብ ሊሉት ይገባ ነበር፡፡ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላጠፉት ጥፋት፣ ኦዴፓም ኢህአዴግም አያድኗቸውምና!
የመፍትሄ ሃሳብ
በደርግ ዘመን የመንደር ምስረታ ፕሮግራም የሚባል ነገር ነበር፡፡ የዚህ ፕሮግራም ዓላማ ተበታትነው የተመሰረቱ የገጠር መንደሮችን በአንድ አካባቢ አሰባስቦ ማስፈር ነው፡፡ ደርግ ይህንን ያደረገው ውሃ፣ መብራት፣ ት/ቤት፣ ሀኪም ቤት፣… የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ነበር፡፡
ትልልቅ ከተሞች አቅራቢያ ባሉ፣ ለገጣፎን በመሳሰሉ ትንንሽ ከተሞች፤ ከትልልቆቹ ከተሞች የፈለሱ ሰዎች የየከተማዎቹን ፕላን ያልጠበቀ የቤት ግንባታ እንዲያካሂዱ እድል የፈጠረላቸው በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች በእርሻ መሬታቸው ላይ ቤት እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው መሆኑ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገበሬዎቹ ይህንን እድል በመጠቀም መሬት ሸጣችሁ እንዳይባሉ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ስም የወፍ ጎጆ የሚያህል የጭቃ ቤት እየሰሩ ይሸጣሉ፡፡ ገበሬዎቹ ይህንን የሚያደርጉት መንግስት መሬታቸውን በአነስተኛ ገንዘብ ስለሚወስድባቸው የተሻለ ገቢ ለማግኘት በማሰብ ነው፡፡ የየአካባቢው አመራር አባላት ይህንን ድርጊት ማስቆም ሲገባቸው፣ በጉቦ ራሳቸውን ጠፍረው የችግሩ አካል ሆነዋል፡፡
ስለሆነም፤ መንግስት ገበሬዎቹ ቤት መስራታቸውን ካላስቆመ፣ ህገ ወጥ ሰፈራን ማስቆም አይቻለውም፡፡ ገበሬዎቹ በእርሻ መሬታቸው ላይ ቤት እንዳይሰሩ ከተፈለገ ደግሞ ገበሬዎቹ በአንድ መንደር ተሰባስበው እንዲሰፍሩ በማድረግ በእርሻ ማሳቸው ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳይካሄድ ጥብቅ ክልከላ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላኛው መፍትሄ መንግስት መጠለያን ለዜጎቹ ማቅረብ ሰብአዊ መብትን የማክበር ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ፣ በተለይም አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ኮንዶሚኒየም ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ገንዘብ የሚከራዩ ቤቶችን (Low cost houses) በብዛት መገንባት ነው። መንግስት ለከተሞች መስፋፊያ ከገበሬዎች ላይ መሬት በሚወስድበት ወቅት የሚከፍለው ካሳ፤ የአርሶ አደሩን ህይወት መለወጥ የሚገባው መሆኑም ገበሬው መሬት እንዳይሸጥ እንደሚያደርገው ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ የተንጸባረቀው ሃሳብ፣ ጸሐፊውን ብቻ እንደሚወክል ለመግለጽ እንወዳለን። ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡






Read 839 times