Wednesday, 06 March 2019 09:43

የኮንስትራክሽን መጓተትና ሙስናን የሚያስቀር ሶፍትዌር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


ከንቲባው ቢሮአቸው ተቀምጠው፣ የግንባታ ሳይት መከታተል ይችላሉ


በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ አቤል ገብረአናንያ፣ኢዮኤል አፈወርቅ እና አሞን ኢሳያስ ይባላሉ፡፡በ2010 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡፡ ወጣቶቹ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ ግን እንደ አብዛኛው ምሩቃን ወደ ከተማዋ የስራ ማስታወቂያ
ሰሌዳዎች አላመሩም፡፡ የራሳችንን ድርጅት ማቋቋም አለብን ብለው ወሰኑ፡፡በተመረቁ በሁለተኛው ወር መጠነኛ ገንዘብ አዋጥተው፤ “ሀበን ሶፍትዌር
ዲዛይን” የተሰኘ ድርጅት ማቋቋማቸውን ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያ ሥራቸው፣በሃገሪቱ ያለውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተግዳሮቶች መፈተሽ ነበር፡፡ በዚያም መሰረት፣ አዲስ ሶፍትዌር መሥራታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ሶፍትዌሩ ምንድን ነው? ምን ይፈይዳል?ውጤታማነቱስ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በዚህ ዙሪያ
ወጣቶቹን በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፡፡

ኩባንያውን እንዴት አቋቋማችሁ?
ሶስታችንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አራት ኪሎ ካምፓስ፣ በኮምፒውተር ሳይንስ፣(በሰኔ 2010 ዓ.ም) ከተመረቅን በኋላ በቀጣይ ምን እናድርግ ብለን ተመካከርን፡፡ ለምን ለኛም ለሃገርም የሚጠቅም ሥራ የምንሰራበትን ድርጅት አናቋቁምም ብለን ተወያየን። በኋላም “ሀበን” ተመሰረተ፡፡
የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራችሁ  ምንድን ነው?
እኛ በዋናነት ድርጅታችንን ስናቋቁም፣ ሰፋፊ ችግር ቀራፊ የሆኑ የምርምር ስራዎች በመስራት፣ መፍትሄ ማምጣት ላይ ትኩት ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህም የእኔ (አቤል) የአክስቴ ልጅ፣ በኮንስትራክሽን ስራ ላይ ወደ 10 ዓመት አሳልፏል፡፡ ከሱ ጋር ብዙ ጊዜ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉ ችግሮችን እንነጋገር ነበር። የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለበት ችግር ላይ መጠነኛ ጥናት አደረግን፡፡ አብዛኞቹ ኮንስትራክሽን በመረጃ አያያዝ ድክመት ለኪሳራ እንደሚጋለጡ፣ አሰሪዎችም ንብረታቸውን በወቅቱ መረከብ እንደማይችሉ፣ ለዚህ ደግሞ የመረጃ ልውውጣቸውና አደረጃጀታቸው ደካማነት አስተዋፅኦ ማድረጉን ተገነዘብን። ለችግሩም መፍትሄ ማስቀመጥ እንዳለብን ወሰንን። ሐምሌ መጨረሻ ላይ ይሄን ነገር አጠናቀን፣ ነሐሴ ላይ ችግሩን የሚፈታ ሶፍትዌር ለማዘጋጀት ተነጋገርን፡፡ በዚህ መሰረት ወደ ሥራ ገባን፡፡
ምንድን ነው የሰራችሁት?
ሶፍትዌሩን ኮን ዲጂታል ብለን ነው የሰየምነው። ኮንስትራክተሩና አሰሪው የግንባታ አካሄዱን፣ የወጪ አይነቱንና የወጪ መጠኑን የሚለዋወጡበት፣ ሁለቱ አካላት ብቻ በሚያውቁት አካውንት የሚዘጋጅ፣ በይለፍ ቁልፍ የሚዘጋና የሚከፈት የመረጃ መለዋወጫ ሶፍት ዌር ነው፡፡ ለሶፍትዌሩ ኮንትራክተሩ አስፈላጊውን ዝርዝር የግንባታ መረጃ ያቀርባል፤ ሶፍትዌሩ ያንን አስፈላጊ ከሆነ በግራፍ፣ በሰንጠረዥ ሰርቶ ያስቀምጣል፡፡ ያንን መረጃ አሰሪው በቀላሉ ማየትና በየጊዜው መከታተል ይችላል፡፡
ይህ ግኝታችሁ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል?
አዎ! በሁለት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ላይ ሞክረን፣ እነሱም ወደውታል፤ውጤታማም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሶፍትዌሩ  እንደሌለ አረጋግጣችኋል?
እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ አፍሪካ ውስጥም የኛን የሚመስል፣ ለአጠቃቀም ቀላል የሆነ ሶፍትዌር እንደሌለ በተቻለን ሁሉ ለማረጋገጥ ሞክረናል። በሌሎች የውጭ ሃገራት የተለያየ አይነት አሰራር አለ፡፡
ይህ ሶፍትዌር ለኮንትራክተሩ፣ ለአሰሪው ምንድን ነው የሚጠቅመው በዝርዝር ብታስረዱን?
ሶፍትዌሩን የሚጠቀም አንድ ኮንስተራክተር፣ ለግንባታ የሚያስፈልገውን የግብአት ዋጋ ዝርዝር፣ የግንባታ ጊዜ ሰሌዳና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች በሙሉ ለሶፍትዌሩ ያስገቡለታል። ከዚያም ሶትዌሩ የተቀበለውን ጥሬ ዳታ (መረጃ) አስልቶና አደራጅቶ ያቀርባል፡፡ ስለዚህ ኮንትራክተሩ ያዋጣኛል አያዋጣኝም ከሚለው ጀምሮ የስራው ሂደት እያከሰረኝ ነው ወይስ እያተረፍኩበት ነው የሚለውን በአግባቡ እንዲረዳ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኮንትራክተር የመሰረት ሙሌት ሃሳብና የአዋጪነት ሁኔታን ለማወቅ ከፈለገ፡፡ ግንባታው የሚያርፍበትን ቦታ፣ ቁመትና ርዝመት የመሳሰሉ መረጃዎችን ለሶፍትዌሩ ያስገባል፤ ከዚያም ሶፍትዌሩ አጠቃላይ የግንባታውን ዋጋ፣ የሚያጠናቅቅበትን ጊዜና የሚፈጀውን የግንባታ ግብአት አስልቶ ያቀርባል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ስራ እየተሰራ የሚወጣ ወጪ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ የሰው ኃይል፣ የመሳሰሉት። ይህን መረጃም ኮንትራክተሩ ለሶፍትዌሬ ያስገባል። ከዚያም አካሄድህ አትራፊ ነው ወይም አክሳሪ ነው የሚል መረጃ ይሰጠዋል፡፡ ለአሰሪው ደግሞ የሚሰጠው ጠቀሜታ፤ አንደኛ ግንባታው የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው በአካል ቦታው ሳይሄድ በቀላሉ መከታተል፣ እየወጣ ያለውን የወጪ መጠን ማወቅ ያስችለዋል፡፡ በተያዘለት ጊዜ ግንባታው እየተከናወነ ነው አይደለም፣ በዚህም ኮንትራት የሰጠውን ግንባታውን መከታተል ያስችለዋል። መንግስት ይሄን ሶፍትዌር ቢጠቀምበት በዋናነት የግንባታ መጓተትን እንዲሁም ሙስናን ሊያስቀር ይችላል፡፡  
ፈጠራችሁን  ለመንግስት አካላት አላቀረባችሁም?
በቀጣይ እናቀርባለን፡፡ እንዲያውም ሶፍትዌሩን ለመንግስት በነፃ ሰጥተን፣ ከመንግስት ኮንትራት ለሚወስዱ ተቋራጮች በሽያጭ ለማቅረብ እቅድ አለን፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ የቤቶች ግንባታ ተጓተተ፣ ተመዘበረ ይባላል። ይሄን ሶፍተዌር ቢጠቀሙ ግን ከንቲባው ራሳቸው ቢሮአቸው ተቀምጠው፣ እያንዳንዱን የግንባታ ሳይት መከታተል፣ የደረሰበትን የግንባታ ደረጃ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ አንፃር መገምገም  ይችላሉ፡፡
ወደፊት  ምን እቅድ አላችሁ?
አሁን በቀላሉ ከህንፃ ግንባታዎች ነው መጀመር የፈለግነው፡፡ በቀጣይ በመንገድና በድልድይ ግንባታ ላይ ሶፍትዌሩን ለማበልፀግ እቅድ አለን፡፡ የፋብሪካ ግንባታዎችም በዚህ ሶፍትዌር ማካሄድ ይቻላል፡፡
በዋናነት ይህ ሶፍትዌር ለማን ነው የሚጠቅመው?
ለሁሉም ነው፡፡ ኮንትራክተሩን ከኪሳራ ይታደጋል፡፡ በትክክል ትርፍ እና ኪሳራውን እያሰላ እንዲቀጥል ይረዳዋል፡፡ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲከናወኑም ያስችላል፡፡

Read 1077 times