Sunday, 24 February 2019 00:00

እውነት ከሐሰቶች መሀል ለምልማ የምትወጣ ጸጋ ናት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

(ለአቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ከዘመን ባንክ የተሰጠ ምላሽ)

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በሚል ተጽፎ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅጽ 20 ቁጥር 996፣ ዘመን ባንክ እንደ ይሁዳ (አጽንቼ ያቆምኩትን ባለውለታውን ዞሮ የወጋው ዘመን ባንክ) በሚል ርዕስ የታተመውን ጽሑፍ ተከትሎ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአካልና በስልክ ስለ ጉዳዩ መረጃዎችን እየጠየቁ በመሆኑ፣ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ በማህበራዊ ገጾች ጭምር የተለያዩ አመለካከቶች በመንጸባረቃቸው፣ ይህም በባንኩ ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ገጽታ ሊኖረው ስለሚችል በጉዳዩ ላይ በባንኩ በኩል ያለውን አቋም መግለጹ ብዥታዎችን ማጥራት ብቻ ሳይሆን ተገቢው መረጃ ለህዝብ መድረስ አለበት ብለን በማመናችንም ጭምር ነው፡፡
አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ የዘመን ባንክ መሥራች ብቻ ሳይሆኑ የሀሳቡ ጠንሳሽና በምሥረታው ወቅት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ፣ ለባንኩ መመሥረት ጉልህ ሚና የተጫወቱ ግለሰብ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህም ተግባራቸው የባንኩ ባለአክሲዮኖች፣ ቦርዱና ሠራተኛው በባንክ ኢንዱስትሪ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡ ታዲያ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ያለው ግንኙነት እንዴት ወደዚህ ደረጃ ተቀይሮ፣ “አጽንቼ ያቆምኩትን ባለውለታውን ዞሮ ወጋ” በማለት ባንኩ በእርሳቸው ላይ ክህደት እንደፈፀመባቸውና በወንጀል ጭምር እንደከሰሳቸው በሚመስልና አንባቢን ባሳሳተ መልኩ ጽሑፉን ሊያወጡ ቻሉ? የሚለው ጉዳይ ለሁላችንም ግልጽ መደረግ ያለበት እውነታ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ጄቲቪ በተባለው የቴሌቪዥን መስኮት ላይ ቀርበው ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ላይ የተሳሳተ መረጃ ቢሰጡም፣ ምላሹን መስጠት ጊዜ ማጥፋትና የባንኩንም ደረጃ አይመጥንም ብሎ በማሰብ፣ መልስ ሳንሰጥ ያለፍነው ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ በጋዜጣና በማህበራዊ ድረ-ገፆች ጭምር የባንኩን ስም ለማጉደፍ የተኬደበት መንገድ ግን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ሆኖ በመገኘቱና ህብረተሰቡም እውነታውን እንዲያውቅ የማድረግ ኃላፊነት ያለብን በመሆኑ፣ ለአንባቢያን እውነታውን በአጭሩ አቅርበናል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የተያዙ በመሆናቸውና የፍትህ ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ በማሰብ ዝርዝር ነገሮችን ለመግለጽ ባለመቻላችን በቅድሚያ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
አቶ ኤርሚያስ በፅሁፋቸው ላይ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልሠሩ፤ ይህም በኦዲተሩ እንደተረጋገጠና በእርሳቸው ላይ በደል እንደተፈፀመባቸው ቢናገሩም፤ በሌላ በኩል ደግሞ እውነታውን ደፍረው ለመግለጽ አልሞከሩም።  በአንጻሩ ግን “በቅንነት የፈፀምኳቸውን ተግባራት የግል ጥቅሜን ለማሳደድ ያደረኩት ዝርፊያ በማስመሰል ያለ ሥራዬ የወንጀል ክስ ተመሥርቶብኛል፣ እንዲሁም በፍርድ ቤት የተወሰነልኝን የመሥራችነት ጥቅም ባንኩ የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደርና የተለያዩ የጥቅም ግጭቶች በማንሳት ሊከፍለኝ አልቻለም” በማለት በጽሑፋቸው ላይ በባንኩ እንደተበደሉ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በእርሳቸውና በባንኩ መካከል ያለው የፍትሃ ብሔር ጉዳይ የተጀመረው ከ1 ዓመት ከ10 ወራት በፊት ሆኖ እያለና የፍርድ ሂደቱ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ እንዲሁም ለባንኩ በጽሑፍም ሆነ በቃል ያቀረቡትን ጥያቄዎች ተቀብሎ ያነጋገራቸውና በጽሑፍም ጭምር ምላሽ የሰጣቸው መሆኑን እያወቁ፣ በዚህ መልኩ የተሳሳተ መረጃ ይዘው ወደ ሚዲያ ለመምጣት ለምን እንደፈለጉ ለባንኩ ግልጽ ሆኖ አልተገኘም፡፡
በዚህ አጋጣሚ በአሁኑ ሰዓት አቶ ኤርሚያስ በማረሚያ ቤት የሚገኙበት ሁኔታ ከባንኩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውና ከሜቴክ ጋር በነበራቸው የሥራ ግንኙነት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑን አንባቢያን እንዲረዱልን እንፈልጋለን፡፡ የዚህን ዓይነት ስም የማጥፋትና ሀሰተኛ ይዘት ያለው ጽሁፍ ለህዝብ ማቅረባቸው የጉዳያቸውን አቅጣጫ ለማስቀየር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ካልሆነ በስተቀር ቀደም ተብሎ ምላሽ በተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ በሀቅ ተንተርሰው ያደረጉት ነው ለማለት አያስደፍረንም፡፡ ከዚህ በመነሳት ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አቶ ኤርሚያስ ባነሷቸው ዋና ዋና ሀሳቦች ላይ ብቻ በመመርኮዝ፣ አጠር ያለ ምላሽ እንደሚከተለው ለአንባቢያን እናቀርባለን፡፡
1ኛ.  “በፍርድ ቤት ቢወሰንልኝም ባንኩ ክፍያ ሊፈፅምልኝ አልፈለገም” ለተባለው በእርግጥም አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ከሌላው መሥራች አባል ጋር የሚካፈሉት ብር 10,359,105.69 በፍርድ ቤት ተወስኖላቸዋል፡፡
ነገር ግን ልዩነቱ የመጣው አቶ ኤርሚያስ፣ ሰኔ 19 ቀን 2000 ዓ.ም. በሰበሰቡት 12ኛው የዘመን ባንክ አ.ማ. የዲሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ ላይ የባንኩን የዕለት ተዕለት ወጪ ለመሸፈን ከብር 6,000,000.00 ያላነሰ ከኪሳቸው ገንዘብ ማውጣታቸውን ገልፀው፣ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ወደፊት ሂሳቡ በኦዲተር የሚመረመር መሆኑ ሳይቀር ብር 4,000,000.00 እንዲከፈላቸው የጠየቁና ቦርዱም ይህንኑ ጥያቄ በበጐ በመቀበልና በማጽደቅ፣ ወደፊት በኦዲተር የሚመረመርና እላፊ ቢኖር የማስተካከሉ ኃላፊነት እንዳለ ሆኖ፣ ብር 4,000,000.00 በታሳቢነት እንዲከፈላቸው በቃለ-ጉባኤ ተወስኖ ነበር፡፡
በዚህ ውሳኔ መሠረት ሰኔ 2ዐ ቀን 2000 ዓ.ም. ከአቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ለባንኩ በተፃፈ ማመልከቻ ገንዘቡ አቢሲንያ ባንክ ፍልውሃ ቅርንጫፍ በሚገኝ የአክሰስ ካፒታል አ.ማ. ሂሳብ ውስጥ ገቢ እንዲደረግ በጠየቁት መሠረት፣ አቢሲንያ ባንክ እ.ኤ.አ. በ27/06/2008 ባንኩ ወደ አቢሲንያ ባንክ ሂሳብ ገንዘቡን ገቢ አድርጓል፡፡  በዚህም የተነሳ አቶ ኤርሚያስ በውሳኔው መሠረት አውጥቼዋለሁ ያሉትን ወጪ በህጋዊ ሰነድ አስደግፈው ባለማቅረባቸው ባንኩ ገንዘቡ እንዲመለስለት ወይም ሰነዱ በአግባቡ እንዲቀርብለት ቢጠይቅም፣ በዚህ ረገድ የቀረበ ነገር ባለመኖሩ፣ ባንኩ ገንዘቡ እንዲከፈለው ጥያቄውን ለፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ ስለዚህ የወሰዱትን ገንዘብ በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንዳዋሉት ማስረጃ አቅርበው እንዲያወራርዱ መጠየቅ ስህተቱ የት ላይ ነው? አቶ ኤርሚያስም ስለወሰዱት ገንዘብ ምንም ሳይገልጹ በማለፍ፣በደፈናው የተወሰነልኝ ገንዘብ አልተከፈለኝም ብቻ በማለት ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢነት የለውም፡፡ የወሰድኩትን ገንዘብ በዚህ መልኩ ጥቅም ላይ አውየዋለሁ በማለትና ማስረጃውንም ለማቅረብ ለምን አልደፈሩም? የባንኩ ማኔጅመንት ባንኩን የማስተዳደርና የባለ አክሲዮኖችን ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ የተጣለበት መሆኑ እየታወቀ፣ ይህንን ጥያቄ ለማለፍ የሚያስችለው መንገድ እንደሌለ አንባቢያን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
2ኛ.   አቶ ኤርሚያስ በዘመን ባንክ አ.ማ. ምስረታ ወቅት ከአክሲዮን ሽያጭ የተሰበሰቡ ገንዘቦች ለዚሁ ተብሎ በዘመን ባንክ አ.ማ. ስም በተከፈቱት ዝግ ሂሳቦች ውስጥ መግባት የሚገባው ብር 7,897,909 ያለ ሕግ አግባብ፣ ወደ አክሰስ ካፒታል አ.ማ. ሂሳብ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ ይህ ድርጅት (አክሰስ ካፒታል አ.ማ.) በሌላ በኩል ደግሞ ከአክሲዮን ሽያጭ ላይ 3 በመቶ እየተከፈለው ለባንኩ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት እ.ኤ.አ. 15/3/2007 በተፈረመ ውል (ኩባንያውን በመወከል አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ፈርመዋል) የሚሠራ ተቋም ነበር፡፡ በተጨማሪም ከአክሲዮን ሽያጭ ኮሚሽን የተሰበሰቡ ገንዘቦች ብር 4,706,319.00 በተመሳሳይ መልኩ በዘመን ባንክ ሂሳብ ውስጥ መግባት ሲገባቸው፣ በአክሰስ ካፒታል አ.ማ. ሂሳብ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡  
ስለዚህ በባንኩ ስም የተሰበሰቡ ገንዘቦች ወደ ትክክለኛው ሂሳብ ገቢ መደረግ ሲገባቸው ገንዘቡን ከአራት ዓመት ተኩል በላይ በአክሰስ ካፒታል ስም በማስቀመጥና በመጠቀም፣ ባንኩ ከዚህ ገንዘብ ሊያገኝ ይገባ የነበረውን ጥቅም እንዲያጣ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ባንኩ አጥቼዋለሁ ያለውን ጥቅም በማስላት ሊከፈለው የሚገባውን ጥቅም በፍ/ቤት ጠየቀ እንጂ በጋዜጣ ወይም በማህበራዊ ድረ-ገጽ አቤቱታ አላቀረበም፡፡
አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ በአንድ በኩል፣ የባንኩ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን በሌላ በኩል ደግሞ አክሰስ ካፒታልን በመወከል ለባንኩ የማማከር ውል የፈረሙ በመሆኑ የተሰበሰበው ገንዘብ በባንኩ ስም በተከፈተው ዝግ ሂሳብ መግባት ሲገባው ባለመግባቱ፣ ለቆየባቸው ከ4 ዓመት ተኩል በላይ ጊዜያት ያቀረቡትን የጥቅም ጥያቄውን ባንኩ ማቅረቡ ስህተቱ የቱ ላይ ነው? የዝግ ሂሳቡስ የተከፈተው የባለአክሲዮኖችን ገንዘብ ከጉዳት ለመጠበቅ አይደለምን? በተጨማሪም ከአክሲዮን ሽያጭና ከኮሚሽን የተሰበሰበውን ገንዘብ አሳልፎ ለአክሰስ ካፒታል መተው ከጥቅምም በላይ በባንኩ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ ለመገመት የሚያዳግታቸው ካለመሆኑም በተጨማሪ በቅንነት የተሰራ ነው ሊያስብል የሚቻል ፍሬ ነገር በውስጡ አላገኘንበትም፡፡ በሌላ በኩል ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚገባው ከህዝብ ተሰብስቧል የተባለው ገንዘብ በባንኩ ሂሳብ ውስጥ አለመገኘቱ በባንኩ ምስረታ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር መገመት እንደ እሳቸው ላለ አዋቂ ሰው ከባድ አይመስለንም። ይሄ ሁሉ ሁኔታ ተፈጽሞ ባለበት ሁኔታ ጽድቅ እንጂ ኩነኔ የለብኝም ብሎ በድፍረት መናገር ራስን ከማስገመት በላይ የሚያስገኘው ውጤት ያለ አይመስለንም፡፡  
ከዚህ በተጓዳኝ ግን ባንኩን መስርቻለሁና የፈለኩትን ባደርግም በቅንነት ስለሆነ አትጠይቁኝ፣ ለኔ የሚገባኝን ገንዘብ ያለ ምንም ጥያቄ ካልከፈላችሁኝ፣ ወ.ዘ.ተ … ብሎ የባንኩን ስም አለአግባብ ማንሳት ዝርዝሩን የማያውቁትን አንባቢያንን ከማሳሳት ባለፈ ባለአክሲዮኖችንና ህብረተሰቡን መናቅ ይሆናል፡፡ ለዚህ ድፍረትዎ ማሳያ የሚሆነው የአንድን ባንክ አክሲዮን ማህበር የቦርድ አባላት በእርሶ ውሳኔ ብቻ እንዲወርዱና ሌሎች እንዲመረጡ አደረኩኝ በማለት የጻፉት ጽሁፍ ምስክር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ጉዳዮችን ማቅረብ ቢቻልም፣ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ ስለሆነ ከዚህ በላይ መሄድ በፍ/ቤቱ ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ በመስጋት ዝርዝር ሁኔታ ባለማቅረባችን አንባብያንን በድጋሚ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
3ኛ.   አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ በፅሑፋቸው ላይ በዝርዝር ለመጥቀስ ያልፈለጉትና በደፈናው ተጐድቻለሁ፣ የውጭ ኦዲተሩ የሰራው ሥራ ላይ ያገኘው ጥፋት የለም በማለት ያነሱ ሲሆን በኦዲት ሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱት ስህተቶች ውስጥ አንዱን ብቻ ለአንባቢያን ግንዛቤ ይሆን ዘንድ አቶ ኤርሚያስ ባሉትና በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት የሚያስረዳውን የኦዲተሩ ሪፖርት እንደዚህ ይነበባል፡፡
“…. Meanwhile, although Ato Ermias Amelga had contributed only Birr 1,400,000, the above mentioned Birr 800,000 was considered as his own contribution and the total amount registered at DARO in the name of Ato Ermias was raised to Birr 2,200,000. We are of the opinion that treating the ex-shareholders’ contributions kept in a blocked bank account as his own contribution and overstating the share capital registered at DARO does not appear to be appropriate”
የአማርኛው ትርጉም በትርጉም አገልግሎት ድርጅት በሚከተለው አኳኋን ቀርቧል፡፡
“…ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ 1,400,000.00 ብቻ አስተዋጽኦ አድርገው እያለ ከፍ ብሎ የተመለከተው ብር 800,000.00 የራሱ አስተዋፅኦ እንደሆነ ተቆጥሯል። እንዲሁም በአቶ ኤርሚያስ ስም ያለው ዲኤአርኦ የተመዘገበው ድምር መጠን ወደ ብር 2,200,000 ከፍ ተደርጓል። የበፊት ባለአክሲዮኖችን አስተዋፅኦ በዝግ የባንክ ሂሳብ እንደራሱ የገዛ አስተዋፅኦ መያዝ እና ዲኤአርኦ የተመዘገበውን የአክሲዮን ካፒታል በትክክለኛ መጠኑ በላይ ማስቀመጥ በኛ አስተያየት ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡”
ይህም እንግዲህ የሌሎች ሁለት አክሲዮን ገዢዎች የነበሩትንና ከመዝገብ የተሰረዙትን ነገር ግን ገንዘባቸው በዝግ ሂሳብ የተቀመጠውን የራሳቸው በማስመሰልና ወደ እርሳቸው ድርሻ ላይ በመደመር ያደረጉት ሥራ በኦዲት ሪፖርቱ በግልጽ ተቀምጦ እያለ፣ እርሳቸው ጥፋት አልፈፀምኩም ይላሉ፡፡ ሰነዶቹ የሚናገሩትም ሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ እራሳቸው ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ ለማያውቁ አንባቢያን እርሳቸው ንፁህ መስለው ቢታዩም ህሊናቸውና ማስረጃዎቹ ግን ከእርሳቸው በተቃራኒ የሚቆሙ መሆናቸው ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል።
4ኛ.   ሌላው አቶ ኤርሚያስን ለማስታወስ የምንፈልገው በአክሰስ ካፒታል አ.ማ. 80% (ሰማንያ በመቶ) የባለቤትነት ድርሻ የተቋቋመው ፓዩኒር አግሮ ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግ.ማህበር የተባለው ድርጅት ያለምንም ዋስትናና የስራ ልምድ እርስዎ የቦርድ ሰብሳቢ በነበሩበት ዘመን በወሰደው ብድር ምክንያት ዘመን ባንክን ለምን ያህል ኪሳራ እንደዳረገው እንደማይዘነጉት ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ለዘመን ባንክ ያደረጉትን መልካም ነገሮች ብቻ ሳይሆን ፅሁፍዎ ሚዛናዊ እንዲሆን አክሰስ ካፒታል ዋና ባለቤት የነበረው ተቋም ያልመለሰውን ገንዘብ ሲያስቡ፣ በተዘዋዋሪ በእርስዎ ወይም በድርጅቱ በባንኩ ላይ የደረሰውን ጉዳት እያወቁ እርስዎ ለዘመን ባንክ ሁሉንም ነገር ማድረግዎን ብቻ ሲናገሩ ነገሩን ማን ነው ይሁዳ አያስብልምን? ችግሩ እርስዎ የተሳሳቱትን ነገር ደፍረው ለመናገር አለመፈለግዎ ነው፡፡ ባንኩ ግን በሰከነ መንገድ በመጓዝ እነዚህንና የመሳሰሉትን ተግዳሮቶች አልፎ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑ ሊታወቅለት ይገባል፡፡
ውድ አንባቢያን፤ እንድትረዱልን የምንፈልገው ባንካችን አቶ ኤርሚያስንም ሆነ የማንንም ገንዘብ /መብት/ ከህግ አግባብ ውጪ መያዝ የማይፈልግና የማይችል መሆኑን፤ እንዲሁም የአቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ በፍርድ ቤት የተወሰነላቸው ክፍያም ያልተፈፀመው ከላይ በተራ ቁጥር 1 እና 2 በተጠቀሱት ምክንያቶች ባንኩ ከእርሳቸው የሚፈልገውን ገንዘብ እንዲመልሱ ጥያቄ በማቅረቡና ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ባንኩ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት መፈጸሙን ተገንዝቦ እርምጃ መውሰዱ የባንኩን ማኔጅመንት የሚያስመሰግን እንጂ ለወቀሳ የሚዳርግ እንዳልሆነ አበክረን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
ከዚህ ውጪ ባንካችን ቀደም ብለው የተሰሩ ስህተቶችን ማረምና ሕጋዊ እርምጃን ማስወሰድ የሞያ ተግባራችን መሆኑን እየገለጽን ከዚህ ውጭ የተደረገ ነገር የሌለ መሆኑን በድጋሚ እናስገነዝባለን፡፡  ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ፍላጐቱ አለኝ የሚል አካል ባንኩ ድረስ በመቅረብ አስፈላጊ ማስረጃዎችን መመልከት የሚችል መሆኑን በማክበር እንገልፃለን፡፡
በመጨረሻም ለተከበራችሁ የዘመን ባንክ አ.ማ. ባለአክሲዮኖች፣ ደንበኞች፣ እንዲሁም ለመላው ማህበረሰብ በዚህ አጋጣሚ ዘመን ባንክ አ.ማ. ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ሁሉ በማለፍ በአሁኑ ጊዜ ትርፋማነቱን በማስቀጠልና የባለአክሲዮኖቹን ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በማስፋት የተከፈለ ካፒታሉንም ከ 1.3 ቢሊዮን ብር በላይ በማድረስ እንዲሁም ለደንበኞቹ ከ30 በላይ በሚሆኑት ቅርንጫፎቹ እንደ ሁልጊዜውም በቀልጣፋና ምቹ መስተንግዶ የዘመነ አገልግሎት በመስጠት በቀናኢነት ተግቶ እየሠራ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የጽሁፉን መውጣት ተከትሎ በተፈጠረው ብዥታ ለባንኩ ያላችሁን ቀናኢነት በራሳችሁ ተነሳሽነት ድጋፋችሁን ለሰጣችሁን ወገኖቻችን ከፍተኛ ምስጋና እያቀረብን፣ መረጃውን ባለማወቅ ቅሬታችሁን ለገለጻችሁልን ደግሞ በአቀረብነው መረጃ በመንተራስ፣ ሚዛናዊ የሆነ አስተያየት እንደምትሰጡን እምነታችን የጸና ነው፡፡ የዘመን ባንክ መላው ሠራተኛና ማኔጅመንት፣ ሁላችሁንም ከልብ እያመሰገነ፣ በቅንነት ልናገለግላችሁ ሁሌም ዝግጁዎች መሆናችንን በትህትና እንገልጻለን፡፡
ከማክበር ሠላምታ ጋር
ዘመን ባንክ አ.ማ.
        

Read 1459 times