Sunday, 24 February 2019 00:00

“የዶሮ ሻኛ አምጣ” የሚባለው ኤርሚያስ አመልጋ

Written by  መስከረም አበራ
Rate this item
(0 votes)


ኢትዮጵያችን በፖለቲካ ጣሯ ላይ የኢኮኖሚ ደዌ የደረበች ጎስቋላ ሃገር ነች፡፡ “አፍርሻት ልፍረስ” የሚለው የፖለቲካ ዛሯ ተሻለው ሲባል የሚብስበት መሆኑ ብቻ አይደለም ክፋቱ፣ ኢኮኖሚዋንም ይዤ ልሙት ማለቱ እንጂ፡፡ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሲጠፉም ሲለሙም አብረው የሆኑ መንትያዎች በመሆናቸው፣ አንዱን ለይቶ ጤናማ ማድረግ አይቻልም። ፖለቲካው ካለመፈወሱ የተነሳ ኢኮኖሚውም እንዲሁ በህመም ላይ ይገኛል፡፡ ፖለቲካውን የተጣባው ዘረኝነት፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ሴረኝነት፣ ማስሰመሰል፣ እውቀት አልቦነት ሁሉ በኢኮኖሚው ላይም ይንፀባረቃል። ነግዶ ለማትረፍ፣ ተናግሮ ለመሰማት፣ ወጥቶ ለመመግባት ወሳኙ ነገር መርጠን ያልተገኘንበት ዘር፣ መቼ መናገር እንደጀመርን እንኳን የማናውቀው ቋንቋ ሆኗል፡፡
እንዲህ ባለው እጅግ ኋላቀር የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት ከማምጣት ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል፡፡ በውስብስቡ ድህረ-ዘመናዊ ዘመን እየኖርን፣ በቅድመ-የድንጋይ ዘመን ነጠላ የኑሮ ዘይቤ መኖር መርጠናል፤ የሰው ነጠላ ማንነቱ የሚናገረው ቋንቋ ብቻ ይመስለናል። ስለዚህ አሁን ያለንበትን ውስብስብ ዘመን የሚመጥን ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንዲኖር የሚፈልጉ ሰዎችን እስከ አድማስ ዳርቻ እናሳድዳለን። ህልማቸውን፣ አበርክቷቸውን፣ ወደፊት ደግሞ ሊጠቅሙ የሚችሉትን አስበን፣ መንገዳቸውን ከማቅናት ይልቅ ትንሳኤ የሌለው ሞት እንዲሞቱ እንሰራለን። ይህን ለማድረግ ደንባደንቦችን፣ መመሪያዎችን እንደገፋለን። ፖሊሲዎቻችን ህጎቻችን እንዴት እንደሚሳካ ሳይሆን እንዴት እንደማይሳካ ይደነግጋሉ። አለማስቻልን በህግ ደንግገን እንኖራለን። ይህን ጉዳይ በተግባር የሚያሳይ አንድ ገጠመኜን ላጋራ፡፡
በቅርቡ ቪዥን ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የጥናት መድረክ ተገኝቼ ነበር፡፡ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ስራ ለመስራት ከአሜሪካን ሃገር የመጣ አንድ ወጣት፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ ስላሉ ችግሮች ጥናት ሊያቀርብ ተገኝቶ ነበር፡፡ ስራውን ለመስራት ወደ ተግባር ሲገባ የገጠመውን፣ በመመሪያና ደንባደንብ የተጠቀለለ መሰናክል ሲያቀርብ መስማት ራሱ ራስ ያዞራል፡፡ ልጁ በጥናቱ የሃገራችንን በህግ፣ መመሪያና ደንባደንብ የተደገፈ ያለማስቻል ከባቢ፣ ከሌሎች ሃገሮች ጋር እያወዳደረ ሲያቀርብ፣ ሁለት ውስጤ የቀሩ፣ ለአንባቢም ላጋራ የምወደውን ምሳሌዎችን አመጣ - የፌስ ቡክን እና የማይክሮ ሶፍትን ጉዳይ፡፡
ፌስቡክን እና ማይክሮ ሶፍትን የፈጠሩ ስራ ፈጣሪዎች (ማክ ዙከምበርግ እና ቢል ጌትስ) ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ቢሆኑ ኖሮ አንድ እርምጃ ሳይራመዱ በደንባደንብ ዱላ እግራቸውን ተቀልጥመው እንደሚቀሩ አስረዳን። ነገሩ እንዲህ ነው፡- የኢትዮጵያ ህግ፣ አንድ ሰው የሆነ ሥራ ለመስራት ፈቃድ ለማግኘት፣ በሚሰራበት ስራ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖረው ያስፈልጋል ይላል፡፡ በተጨማሪ፣ በድሃዋ ሃገራችን ኢትዮጵያ፣ አንድ ስራ ለመጀመር መንግስት እንዲፈቅድለት፣ ስራ ፈጣሪው  ምን የመሰለ ቢሮ፣ ከእነ ሙሉ ቁሳቁሱ ማሳየት ግድ ይላል፡፡ ማክ ዙከምበርግ አና ቢል ጌትስ ደግሞ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሳይመረቁ አቋርጠው የወጡ፣ ሥራ ሲጀምሩ ቢሮ የሚባል ነገር ያልነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የፌስቡክንም ሆነ የማይክሮ ሶፍትን ሃሳብ ያመጣው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ፣ ፌስቡክ እና ማይክሮሶፍት የሚባሉ ኩባንያዎች በዓለም ላይ አይኖሩም ነበር ሲል ጥናት አቅራቢው፣ በቀላል ምሳሌ፣ የሃገራችንን ከድህነት ጋር በህግ መተሳሰር በደንብ አስረዳን፡፡
በሃገራችን የሚወጡ ህጎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች፤ ሃገሪቱን በሚመራው ካድሬ የእውቀት ልክ የተሰፉ ናቸው፡፡ ከካድሬ የእውቀት አድማስ ሻገር ያለ ነገር ያመጣ ሰው፣ ሃሳብህ ከህግ ማዕቀፍ ውጭ ስለሆነ፣ የምናስተናግድበት ህግ፣ መመሪያና ደንብ የለንም እና ሃሳብህን ይዘህ ቁጭ በል ወይ ወደ መሄጃህ ሂድ ይባላል፡፡ በዚህ ላይ ሃሳቡን ያመነጨው ሰው የተወለደው “ከትምክህተኛ” ይሁን “ከጠባብ” ዘር መሆኑ ደግሞ ዋናው ነገር ነው! በዚህ ምክንያት ሃገራችን ሃሳብ ያለው ሁሉ መጥቶ አይቷት ላይመለስ፣ ጥቁር ድንጋይ ወርውሮባት፣ የሚሄድባት ሆናለች፡፡ የሆላንድ ካርስ ባለቤት፣ የኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ሊሚትድ ባለቤት አቶ ገብረየስ ቤኛ፤ ሃገራችን ካስመረረቻቸው፣ ባለሃብቶችና ስራ ፈጣሪዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ ሃገራችን የታሰረችበት ለእድገት የመይመች ትብታብ፣ አላላውስ ሲላቸው፣ ነገር አለሙን ትተው ስደትን የመረጡ ናቸው፡፡ የልብ ሃኪሙ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩም ሌላ ተጠቃሽ ሰው ናቸው፡፡
ሌላው የካድሬ ፖለቲካ መረብ እጅግ ካወካቸው ሰዎች ውስጥ ተጠቃሹ፣ ታዋቂው ስራ ፈጣሪ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ከዓመታት በፊት ወደ ሃገራቸው በመጡበት ወቅት ያዩት የሃገሪቱ ኋላቀርነት፣ እዚሁ ቀርተው እውቀት ልምዳቸው በሚችለው አቅም፣ የሃገር እድገት ለማገዝ፣ በድንገት እንደወሰኑ ተናግረዋል። በሃገር ውስጥ ቆይታቸው ያፈለቋቸው የስራ ፈጠራዎች፣ በሃገሪቱ ተሰርተው የማያውቁ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን የያዙ፣ ችግር ፈቺ ስራዎች ናቸው፡፡ ስራ ፈጠራ ከችርቻሮ ንግድ የሚለይ መሆኑን በተግባር ያስመሰከሩ ሰው፣ አቶ ኤርሚያስ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሃገሪቱ ለዘመናት ሲፈስ የኖረውን የምንጭ ውሃ፣ አሽጎ ለአገልግሎት የማዋልን ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጡት አቶ ኤርሚያስ ናቸው፡፡ አሁን ከሰማኒያ የሚልቁ ውሃ አሽጎ ሻጭ ነጋዴዎች፣ በሃገራችን ችርቻሯቸውን ሲያጧጡፉ፣ የስራው ጀማሪ አቶ ኤርሚያስ፤ ከስራው እጣ ፋንታ እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ስም ማጥፋቶችና ቢሮክራሲያዊ ጦርነቶች ተደርጎባቸዋል፡፡
በግላቸው በቢዝነሱ ዓለም ያላቸውን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ሲሞክሩ፣ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ያስተዋሉትን እጅግ የተንቀራፈፈ ኋላ-ቀር አሰራር ተመልክተው፣ ዝም ብሎ ከማማረር ይልቅ፣ ዘርፉን ለማዘመን በመወሰን ዘመን ባንክን መሰረቱ፡፡ ዘመን ባንክን ሲመሰርቱ በአንድ ቅርንጫፍ፣ ተገልጋይ ያለበት ድረስ በመሄድ፣ አገልግሎት የመስጠትና ሌሎች ዘመናዊ የባንክ አሰራሮችን ለማስተዋወቅ ነበር ህልማቸው፡፡ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ዘመን ባንክን  በመመስረታቸው ብዙ ግፍ የደረሰባቸው ቢሆንም፣ ሰውየው ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው ፊታቸውን በማዞራቸው ብቻ  በሚገርም ሁኔታ የሃገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ እንዲዘምን ረድተዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው ከመግባታቸው በፊት የሃገራችን ባንኮች ምሳ ሰዓት ላይ ይዘጋሉ፣ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ የውስጥ ስራ ስለምንሰራ ለደንበኛ አገልግሎት አንሰጥም ብለው መስኮት በራቸውን ጠርቅመው ይቀመጡ ነበር። ቅዳሜ አይሰሩም፣ማታ መስራት አይታሰብም፡፡ የመክፈያ መንገዳቸው በቢሯቸው መስኮት ላይ ሰው አሰልፎ ገንዘብ  ማደል፣ ቢበዛ ቼክ ፅፎ መስጠት ነበር፡፡ ቅዳሜን ጨምሮ በምሳ ሰዓት መስራትን፣ በመስኮት አሰልፎ ከመክፈል ባለፈ ደንበኛው ድረስ ወርደው የሚደረጉ የተለያዩ ቀልጣፋ የክፍያ አይነቶችን (ለምሳሌ እነ ኤም ብር አይነት) በስራ ላይ የማዋልን ሃሳብ ያመጡት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የውስጥ ስራ ለመስራት በሚል ለደንበኛ ይከረቸሙ የነበሩት የባንክ ቤት በሮች የተከፈቱት፣ አቶ ኤርሚያስ ለዘመን ባንክ አሰራር ካመጡት ዝመና ጋር አብሮ ለመራመድ ነው። አሁን የእስር ድግስ እየተደገሰላቸው በነበረበት ሰሞን ደግሞ አቶ ኤርሚያስ፣ አሊባባ ከተባለው ታዋቂ ኩባንያ ጋር በመተባበር፣ ማንም ያላሰበውን የኢ-ፋይናንስ አሰራርን በሃገራችን ለማስተዋወቅ እየጣሩ ነበር፡፡ ይህን ህልማቸውን እንዳረገዙ ነው እስር ቤት የተወረወረሩት፡፡          
በሪል እስቴት ኢንዱስትሪው በኩልም ቢሆን አቶ ኤርሚያስ ያበረከቱት አዲስ ነገር አለ፡፡ ከከተማ ዳር ወጥቶ ቪላ ቤት አንጣሎ መኖርን የሚችል አቅም ለሌላቸው፣ ከሃገር ሳይወጡ መሃል ከተማ ላይ አፓርትመንቶችን ሰርቶ ለተጠቃሚ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብን ሃሳብ አመንጭተው ስራ የጀመሩ፣ የመጀመሪያው ሰው አቶ ኤርሚያስ ናቸው፡፡ ሥራ ፈጣሪው ይህን ሲያስቡ፣ ለራሳቸው መኖሪያ ቤት የሌላቸው፣ በኪራይ ቤት የሚኖሩ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ የቸርቻሪ ነጋዴና እንደ አቶ ኤርሚያስ ንግድን በእውቀት የሚያስኬድ ስራ ፈጣሪ ልዩነታቸው ይሄ ነው፡፡ ቸርቻሪ ነጋዴዎች፣ ለደንበኛ የመኖሪያ ቤት የሚያቀርብ ቢዝነስ  ውስጥ የሚገቡት፣ ለራሳቸውና ለልጅ ልጆቻቸው፣ አንድ ቀበሌ የሚያክል ግዛት ላይ ቤተ-መንግስት የሚመስል ቤት ከደረደሩ በኋላ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት “ራስ ደህና” ባይ ነጋዴዎች፤ እስርም ክስም አጠገባቸው አይደርስም። በአንፃሩ ስራ ፈጣሪው አቶ ኤርሚያስ፣ “የዶሮ ሻኛ አምጣ” እየተባሉ ፍርድ ቤት ይመላለሳሉ፡፡ የመንግስት ቢሮክራሲ አዝግሞ እስኪደርስ ቀድሞ ስራውን አጠናቆ መጠበቅም ኤርሚያስ ጋር ሲደርስ ወንጀል ሆኖ ያስከስሰዋል። ሰውየውን ከዘመን ባንክ እጣ ፈንታ ያጎደላቸው፣ ባንኩን ለመመስረት የተያዘው ገንዘብ፣ ሁለት አመት በመንግስት ቤት ተዘግቶበት እስኪቀመጥ ድረስ እሳቸው ስራ ከመፍታት ብለው፣ የራሳቸውን ገንዘብ አውጥተው፣ የሰራተኛ ቅጥርን ጨምሮ፣ ለባንኩ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ቀድመው በማሟላታቸው ነበር፡፡
ብዙ ብዙ ያዩበት፣እጅግ ስማቸው የተነሳበት የአክሰስ ሪል ስቴት ግንባታ መዘግየት መነሻ ሰበቡ፣ የመንግስት ብድግ ብሎ ግንባታ ማገድ ነው፡፡ ግንባታው ሲታገድ ለደምበኛ ሰርቶ ለማስረከብ የተገባውን ቃል፣ በቀነ ቀጠሮው ማድረስ የማይቻል ነገር እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ችግር ችግርን እየወለደ፣ የአንድ ወገን ብቻ እውነት እየተሰማ ስለቀጠለ፣ አቶ ኤርሚያስ ከጥፋታቸው በላይ ጥፋተኛ ሆነው ብዙ ችግር ደረሰባቸው። በዚህ ሁኔታ የአቶ ኤርሚያስ ጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል አንድ ነጥብ ግንባታው ሲታገድ፣ የገንዘብ ዲፕሪሽየሽንን ለመቀነስ ሲሉ፣ የመሬት ግዥ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ይህ እጃቸው ላይ ያለው ገንዘብ እንዲያልቅና ገንዘብ ይመለስልን ለሚሉ ደንበኞች፣ ቃል በገቡት መሰረት፣ ገንዘቡን መመለስ እንዳይችሉ አደረጋቸው፡፡ ይህ ራሱ ጥፋት ነው ለማለት አስቸጋሪ የሚሆነው ደግሞ አንድም፣ የቻሉትን ያህል ለደምበኞቻቸው ገንዘባቸውን ለመመለስ መሞከራቸው፣ ሁለትም ወደ መሬት ግዥ የገቡት ግንባታው ሳይካሄድ በቆየ መጠን ሊመጣ የሚችለውን የገንዘብ ዲፕሪሽየሽኑን ለመከላከል ነበር፡፡ እንዲህ ያለ የዕቅድ መዛባት ሲገጥመው ሌላው የሃገራችን ነጋዴ፣ ሪስኩን ሁሉ ጠቅልሎ የሚጭነው ደምበኛ ላይ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ግን ይህን ማድረግ ስላልፈለጉ ነበር መሬት ግዥ ውስጥ የገቡት፡፡
ሌላው የአቶ ኤርሚያስ ጥፋት ተብሎ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ፣ በመጀመሪያ ወደ ገበያው ሲገቡ፣ አለቅጥ ለደምበኞቻቸው ያደላ ቃል መግባታቸው ነው፡፡ ከደምበኞቹ ጋር ውል ሲገቡ፣ አንደኛ፤ ደምበኞች በማንኛውም ሰዓት ቤቱን አንፈልግም ብራችን ይመለስ ካሉ፣ ብራቸውን እንደሚመልሱ ቃል ገብተዋል፡፡ ሁለተኛ፤ ቤቱን ሰርቶ ለማስረከብ ቃል በገቡት የጊዜ ገደብ ሰርተው ማስረከብ ካልቻሉ፣ የደምበኞችን ብር ከነወለዱ እንደሚመልሱ ቃል ገብተዋል፡፡ እነዚህ ሁለት አለቅጥ ለደምበኛ ያደሉ ሁኔታዎችን ማድረግ ያስፈለጋቸው፣ ያለ ምንም ማዛባት፣ ቤቶቹን ሰርቼ አስረክባለሁ የሚል መተማመን አቶ ኤርሚያስ ዘንድ ስለነበረ፣ ሁለትም የቤት ሽያጩ ዋጋ፣ ለገዥ እጅግ አጓጊ በመሆኑ፣ ገዥ ገንዘቤን መልስልኝ ሊል አይችልም ከሚል እርገጠኝነት  ሆን ይችላል፡፡ ትልቁ ስህተት ያለው እዚህ ጋ ነው፡፡
ህወሃትን የመሰለ ዘረኛና አምባገነን ቡድን በሚመራት ሃገር፣ ሁሉም ነገር ሙሉና ዝግጁ ሆኖ ስራዬን እሰራለሁ ብሎ ማሰብ ኢትዮጵያን አለማወቅ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ያዩት፣ የራሳቸውን ስራ ዳር የማድረስ ጉጉትና እሳቸው ሊቆጣጠሯቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች መሰናዳት ነው፡፡ ዋናው ነገር ያለው ግን ከሳቸውም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብም አቅም በላይ በሆነው ህወሃት እጅ ነበርና የሆነው ሆነ፡፡ በዚህ ላይ የራሳቸው ርካሽ አጀንዳ ያላቸው የሚዲያ ባለቤቶች፣ አዛኝ መስለው ቀርበው በአቶ ኤርሚያስና በደምበኞቹ መሃከል ያለውን ግንኙነት አበለሻሹት፡፡ መደማመጥ ጠፋ! ፍረጃው በረከተ፡፡ ይሄኔ ድሮም ይፈልገው የነበረው ህወሃት፣ ቢለዋውን ስሎ መጣ፡፡  
ህወሃቶች አቶ ኤርሚያስን የሚያሳድዱት የሚሰሯቸው ነገሮች ሁሉ፣ ከአቅማቸውና ግንዛቤቸው በላይ ስለነበረ ነው፡፡ በዚህ ላይ የጎጣቸው ሰው ስላልሆኑ ይፈሯቸዋል፡፡ የሚሰሯቸው ነገሮች ሁሉ ከጭንቅላታቸው በላይ ስለሆነ፣ በዚህ ላይ ብዙ አመት ከሃገር ውጭ፣ ያውም በዎልስትሪት ሲሰሩ የኖሩ ሰው በመሆናቸው፣ እነሱ በማይደርሱበት መንገድ የተቃውሞውን ፖለቲካ የገንዘብ ዝውውር የሚረዱ መስሎ ሳይሰማቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን በእውቀት አልቦ ፍርሃት ይከታተላሉ፡፡ በተለይ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንዳይገቡ የፈለጉት ለዚህ ነው፡፡ ለዚህ ማመሳከሪያው፤ አንድን የብሄራዊ ባንክ ሰው፣ ለምን እንዲህ እንደሚያንገላቷቸው ሲጠይቁ፣ በግልፅ፤ “ኤርሚያስ እኛኮ አንተ የምትሰራውን ነገር በደንብ ስለማናውቀው፣ በጣም እንፈራሃለን አሉኝ” ሲሉ፣ ራሳቸው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ለJTV ተናግረው ነበር፡፡ ለሃገር የሚያስብ መንግስት ቢኖር ኖሮ፣ አቶ ኤርሚያስ የሚያመጧቸውን ነገሮች ባለማወቁ፣ የሰውየውን እግር አልነበረም የሚያስረው፡፡ ይልቅስ ከኤርሚያስ ጋር በእውቀት የሚተካከሉ አዋቂዎችን አማካሪ አድርጎ ጉዳዩን መከታተል ይቻል ነበር፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ጥፋት ኢትዮጵያን አለማወቃቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በድህነቷ ሃብታም መሆን የሚፈልጉ፣ ከእውቀት የተጣሉ ሰዎችን በላይዋ ላይ ሾማ የምትንፏቀቅ ሃገር ነች፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ አቶ ኤርሚያስ አይነት ስራ ፈጣሪዎችን የሚፈልጉት ሃሳባቸውን ዘርፎ እነሱን እስር ቤት ለመወርወር እንጅ ህልማቸውን እንዲኖሩ አይደለም፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ህልም መሳካት የሚሰራው፣ የገንዘባቸውና የክላሻቸው ምርኮኛ ደግሞ ብዙ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ በበኩላቸው፤ እዚህ ሃገር በተለይ በአገልግሎቱ ዘርፍ ያለውን ስር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ፣ ህልማቸውን ብቻ ተከትለው የሚነጉዱ ህልመኛ ሰው ናቸው፡፡ ህልም ደግሞ ህልም ብቻ ነው - እውን የሚያደርገው ስርዓት ካልተዘረጋ በቀር፡፡
ኢትዮጵያን ሳያውቁ ህልማቸውን ብቻ ተከትለው የተጓዙት አቶ ኤርሚያስ፣ ጥፋት ካጠፉም፣ የጥፋቱ ስር መሰረት፣ መበለጥን የማይፈልገው የኢህአዴግ መንግስት አሰራር ነው፡፡ ኢህአዴግን አይነት እንቅፋት ባይገጥማቸው ኖሮ አቶ ኤርሚያስ ሊያጠፉ የሚችሉት፣ ማንኛውም የሚሰራ ሰው ሊሰራቸው የሚችሉ ውስን ጥፋቶችን ነበር፡፡ በግሌ የሚገርመኝ ነገር አቶ ኤርሚያስ ኢህአዴግን የመሰለ እንቅፋት ተቋቁመው፣ ለመኖር እንጂ ተመልሰው ወደ መጡበት ለመሄድ አለማሰባቸው ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ አቶ ኤርሚያስ ከበደሉት የተበደሉት ይበልጣል። አምጠው ከወለዱት ዘመን ባንክ እንደ ዋዛ ተባረዋል፣ የአገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን አስበው፣ የሞከሩት  በጎ  ምኞታቸው ከዘራፊ አስቆጥሯቸዋል፡፡ የእርሳቸው እውነት ታፍኖ የአንድ ወገን የሸር ጩኽት ብቻ ሲሰማ በመኖሩ፣ “በአጭበርባሪነታቸው” ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ ትልቅ የሞራል ስብራት ያመጣል፡፡ የአቶ ኤርሚያስ ፈተና፣ ህወሃት ከስልጣን ሲነሳም፣ አለማብቃቱ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡
የህወሃትን ከስልጣን መነሳት ተከትሎ፣ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት፣ መልካም ዘመን ለመምጣቱ ምልክት ይሆነን ዘንድ እስረኞችን ፈትቷል፣ከስራ ተባርረው የነበሩ ምሁራንን ወደ ሥራቸው መልሷል፣ማዕረጋቸው የተወሰደባቸውን የውትድርና ባለሙያዎች ማዕረጋቸውን መልሷል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ምርኮው ያልተመለሰላቸው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡ ከዘመን ባንክ ጀምሮ ቢወራ የማያልቅ ግፍ የተሰራባቸውን ሰው፣ ጉዳዩን በአግባቡ መርምሮ፣ የሚገባውን እንዲያገኝ፣ እርሱም ያጠፋውን እንዲያስተካክል፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሲገባ፣ ለሌላ ዙር እስር ተዳርገዋል፡፡ አሁን የታሰሩት ደግሞ “ሆቴልህን ለምን በውድ ዋጋ ለሜቴክ ሸጥክ?” በሚል የዶሮ ሻኛ አምጣ አይነት፣ አስገራሚም፣ አሳዛኝም ነገር ተከስሶ ነው፡፡
ለዚህ አቶ ኤርሚያስ ለፍርድ ቤት መልስ ሲሰጡ፣ ኢምፔሪያል ሆቴልን የገዛው በ18 ወር ተከፍሎ በሚያልቅ 47 ሚሊዮን ጥሬ ብር ሊከፍል እና ሆቴሉ ያለበትን 23 ሚሊዮን ባንክ እዳ ሊከፍል ተስማምቶ እንደነበር፣ በመሃል ሜቴክ ሆቴሉን መግዛት ሲፈልግ ኤርሚያስ የተስማማበትን የሆቴሉን እዳም ሆነ ጥሬ ገንዘብ ከፍሎ ስላልጨረሰ፣ የሆቴሉ ስመ-ሃብት በኤርሚያስ ስም  አልዞረም ነበርና፣ ግዥ እና ሽያጩ የተፈፀመው በመጀመሪያው የሆቴሉ ባለቤት እና በሜቴክ መሃከል ነበር፡፡ አሁን አቶ ኤርሚያስ እስር ቤት የተወረወሩት በሌሉበት ግዥና ሽያጭ ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ ላይ አስወድደህ ሸጠሃል የተባሉት ሆቴሉ የነበረበት የባንክ እዳ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው አቶ ኤርሚያስ የታሰሩት  ህወሃት ከስልጣን ቢወርድም አዋቂን የማይወደው የፓርቲው ባህል፣ አሁንም በተግባር ላይ እንዳለ ነው። ሁለትም የታሰሩት  የታሳሪ ሙሰኞችን የብሄር ተዋስኦ ለማብዛትና ከወደ ትግራይ የሚመጣውን “የብቻችንን ታሰርን” ጩኽት ለማርገብ ነው እንጂ አቶ ኤርሚያስ 77 ቢሊዮን ብር አመድ ካደረጉ ባለስልጣናት የበለጠ ጥፋት ስላጠፉ አይደለም። በዚህ ላይ በመታሰራቸው ግር ብሎ ወጥቶ መንገድ የሚዘጋላቸው የዘራቸውን  ጎረምሳ ቀድሞ ያላደራጁ የስራ ሰው ስለሆኑ  ነው እስሩ እምብዛም የማያስፈራው፡፡
እንደ አቶ ኤርሚያስ ያሉ ከጥፋታቸው ልማታቸው የሚበልጥ ስራ ፈጣሪዎችን እስር ቤት እየዶለ ያለው መንግስት፤ እድገት ማምጣትም የሚያምረው መሆኑ ነው አስቂኙ ነገር፡፡ ብናውቅበት፣ አቶ ኤርሚያስ ሃገሪቱ ብትመቻቸው፣ ብዙ ደረጃ የሚደርስ አቅምና እውቀት ያላቸው ሰው ነበሩ፡፡ ኑልን እያልን የምንለምናቸው አፍሪካዊ ኢንቨስተሮችን፣ እነ ዳንጎቴን እና ሞኢብራሂምን አይነት ባለሃብት ሊወጣቸው የሚችሉ ሰው ናቸው፤ አያያዙን ብናውቅበት፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ገና የምንመራበት ስርዓት ከዘር ቆጠራ፣ የኋሊት ጉዞ ያልተፈወሰ ነውና፣ ማር እንደማይጥማት እንስሳ፣ ደህና ነገር አይወድለትም፡፡ ሰው የደረሰበት መድረስ የሚፈልግ፣ ዘመኑን የሚመጥን የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ዜጋ ሁሉ ግን፣ ይህን የመንግስት አካሄድ ሃይ ማለት ይገባዋል፡፡ በውሃ ቀጠነ የሚታሰሩት አቶ  ኤርሚያስ አመልጋ፤ ለሃገር የሚጠቅሙት ከእስር ቤት ውጭ  በመሆኑ፣ በአስቸኳይ መፈታት እንዳለባቸው አጥብቆ መጠየቅ፣ ወደፊት መራመድ የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ፣ የሞራል ግዴታ ነው፡፡  


Read 2349 times