Monday, 18 February 2019 00:00

ከብሄር ፖለቲካ ወደ ርዕዮት ፖለቲካ ለመሻገር.....

Written by  በሚለር ተሾመ
Rate this item
(4 votes)

ይህችን መጣጥፍ እንዳሰናዳ ያነሳሱኝ ሁለት ምክንያቶች ናቸው፡፡ አንደኛ አሁን ያለንበትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት፣ የብሄር ፖለቲካን ወይም አራማጆችን መርገምና የርዕዮት የዜግነት ፖለቲካን ማወደስ በቂ እንዳልሆነ ተገንዝበው፣ የርዕዮት (የዜግነት) ፖለቲካ አራማጆች በተግባር መራመድ መቻል አለባቸው ብዬ ማመኔ ነው፡፡ ሁለተኛ የብሄር ፖለቲካ የትግል መንስኤዎችና አበርክቶት በመገንዘብ፣ ወደ የርዕዮት ፖለቲካ ሳይረፍድ ለመሻገር ይረዳሉ ያልኳቸውን ሀሳቦች ለውይይት ይረዳን ዘንድ ማካፈል መፈለጌ ነው፡፡
የብሄር ፖለቲካ የጀመሩ ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሻዕቢያ እስከ አማራ ብሔራዊ  አብን በበቂ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቹ የብሄር ፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች የትግል ስትራቴጂና ታክቲክ አልስማማም፡፡ ለችግራቸው ዘለቄታዊ መፍትሔና መድረሻ ነው ብዬም አላምንም፡፡
እንደ መንደርደርያ.....
ዛሬውን ማስተካከል ያልቻለ ህዝብ በትናንትናው ይኖራል፤ ዛሬን በጥበብ፣ በፍቅርና በጥንካሬ የሚኖር ህዝብ፣ ከታሪኩ በጎውን ከመጥፎ፣ ፍሬውን ከገለባው መለየት አያቅተውም፤ ለትናንትናው ያለው ትርጉም መማሪያ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት የትናንትና ግሳንግሱ ወይም በረከቱ አይከተለንም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ግሳንግሱን ማቃናትና በረከቱን ማስቀጠል (ማሳደግ)፣ ህዝቡ የዛሬ ግዴታው እንደሆነ አያጣውም፤ ግዴታውን በተለያየ ምክንያት ያልተወጣ በትናንትናው መፈገግና ጥርስ መንከስ ‘ኑሮው’ ይሆናል፡፡ ታድያ ዛሬን ለማስተካከል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍትህን ከማስፈን ባሻገር፣ በደመቀው ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ብዙ ቀለሞችን መጨመር አንዱ መንገድ ነው ብዬ አምናለው፡፡ ይህ እውን ይሆን ዘንድ ሀገር አቀፍ የጋራ ማንነት ማጠናከሪያ ስራ ልንሰራ ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው ፖለቲካ የሕዝብን ዘለቄታዊ ጥቅም የምናስጠብቅበት መሳሪያ ነው፤ አሁን ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ ከማንነት ፖለቲካ ይልቅ የርዕዮት ፖለቲካ የተሻለ ጠቀሜታ ወይም ፋይዳ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ታዲያ የማንነት ፖለቲካ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ዋናው መስመር ከመሆኑ በፊት፣ እንዲጠነሰስ ገፊ ምክንያቶቹ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የብልጽግና፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና ሌሎች ታሪካዊ ጥያቄዎች መሆናቸው ይታወቃል። ስለዚህ ከማንነት ፖለቲካ ወደ ርዕዮት ፖለቲካ ለመሻገር እነዚህ ጥያቄዎች ታሪካዊ ኩነቶችንና ማህበራዊ ሀብቶችን ባማከለ መንገድ፣ ሳይንሳዊ መልሶችን ማግኘት አለባቸው፡፡  የሽግግር ሂደቱን እውን  ለማድረግ ይረዳል ያልኩትን ሀገር አቀፍ የጋራ ማንነት ማጠናከሪያ ንድፈ ሀሳብ አካፍላለሁ። በሀገር አቀፍ የጋራ ማንነት ማጠናከሪያ ንድፈ ሀሳብ፣ ሶስት ጉዳዮች ላይ አተኩራለሁ፤ እነሱም ታሪክና የታሪክ ጀግኖቻችንን፣ የቋንቋ ጉዳይና ባህላዊ እውቀትን ለሀገራዊ ጥቅም ማዋል ናቸው፡፡
ታሪክ እና ታሪካዊ ጀግኖቻችንን ......
የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ በጥልቀትና አካታች በሆነ መልኩ ተጠንቷል ማለት ያስቸግራል ፤ ከዚህ በፊት ከተጠኑት ባሻገር ያልተጠኑት ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተፈትሸው ወደ ጋራ ታሪካችን ሊካተቱ ይገባል፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች አከራካሪ የሆኑ የታሪክ ጉዳዮችና የታሪክ ጀግኖቻችንን በአዲስ አቀራረብ ወይም እይታ ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ ሊያቀርቡ ይገባል፤ ይህ ማለት ታሪክን ለፖለቲካ ባሪያ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁን የታሪክ ባለሞያነት የሚጠይቃቸውን ስነ ምግባር ተጠቅመው፣ የደበዘዘውን ኩነት (Fact) ያጥሩት ማለት እንጂ፡፡
በዚህ ረገድ ምንም እንኳን የታላቋ ሀገር አሜሪካን ታሪክ የሚተቹ ብዙዎች ቢኖሩም፣ ለኛ በአርአያነት የምንወስደው ብዙ መልካም ነገር አለው፡፡ እንደሚታወቀው የአሜሪካን የዛሬ ስልጣኔዋ በድንገት የተከሰተ አይደለም፤ ዘመናትን የፈጀ የተለያዩ ትግሎች ድምር ውጤት እንደሆነ አይጠፋንም፡፡ የሰራተኞች አመጽ፣ የጥቁር አሜሪካውያን  አመጽና ትግል፣ የሴቶች እኩልነት ትግል፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ መብት ተሟጋቾች ትግል ድምር ውጤት ናት፡፡ አሜሪካውያን የጋራ ማንነትን ለማሳደግ፣ የጋራ ታሪካቸውን ሁሌም አካታች ለማድረግ ይጥራሉ፣ ይሰራሉ፡፡ ምንም እንኳን የታሪኩ አውድ ከሀገራችን ቢለይም፣ ለአብነት የቁር አሜሪካውያን አመጽና ትግል (Black Movement) እንዴት እንደተካተተ እንመልከት፡፡
ጥቁሮች በዘራቸው ምክንያት ፣ በህጋዊ መዋቅር የደረሰባቸውን ሁሉ አቀፍ መገፋት በተለያየ መልኩ ታግለዋል፤ ከሰላማዊ ትግል እስከ ነፍጥ ማንሳት (Buffalo solidiers) ተጋፍጠዋል፡፡  በሰላማዊ ትግል ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ማርክስ ጋርቨይ፣ ማልኮም ኤክስ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ እኚህ መሪዎች በዘመናቸው ባነሱት የሰብአዊ መብት ጥያቄ፣ በጊዜው መንግሥት ታስረዋል፣ አሸባሪ ተብለው ተፈርጀዋል፣ በመጨረሻም ባልታወቀ አካል ተገድለዋል፡፡ የኋላ ኋላ የታገሉለት ዓላማ  በጆን ኦፍ ኬነዲ ዘመን ትክክል እንደሆነ ታምኖ፣ መንግስታዊ ውሳኔ ካገኘ በኋላ፣ እኚህ የጥቁር ህዝብ ታጋዮች ጀግና ተብለው ተሸልመዋል፡፡ በስማቸው ሀውልት ቆሞላቸዋል፣ አደባባይ፣ ትምህርት ቤት፣ ቤተ-መፅሐፍት፣ ጎዳናዎች ተሰይሞላቸዋል፡፡ የግል ታሪካቸውና የጥቁር ሰዎች ትግል፣ ከአሸባሪነት ወደ ጀግንነት የታሪክ ማህደር ተሻግሯል፡፡
ታዲያ ይሄ ሲደረግ ከጆን ኦፍ ኬነዲ በፊት ሀገራቸውን የመሩ ፕሬዚዳንቶችን በጎ ስራ ማጥላላት ወይም ሀውልታቸውን ማፍረስ አላስፈለጋቸውም፤ የተሳሳቱትን አርመው በጎውን አጽንተው፣ የጋራ ማንነታቸውን ለመገንባት ተጉ እንጂ፡፡ አሜሪካዊያን በመንግስታዊ መዋቅር ደረጃ የዛሬዋ ሀገራቸው፣ የእነ አብረሃም ሊንከን በጎ ስራ ውጤት ብቻ ሳትሆን የእነ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጭምር እንደሆነች ያምናሉ፡፡  
ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ይህን የመሰለ በጎ ልምድ ያለን አይመስለኝም፤ የረጅም ዘመን የጋራ ታሪክ፣  እሴትና ብዙ ጀግኖች ቢኖሩንም የጋራ ማድረግ ተስኖን፣ የጥንካሬ ምንጭ በመሆን ፈንታ የግጭት መንስኤ እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ከዚህ በተለየ ሁኔታ፥ ግጭቱ መታረቅ የሚችል እንደሆነ የአሜሪካዊያን ልምድ ያሳየናል፡፡ የዛሬዋ ውዷ ሀገራችን፣ በጀግናውና ባለ ራዕዩ መሪ አጤ ምኒልክ በጎ ስራ ብቻ የቆመች ሳትሆን፣ በጀግናውና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጄኔራል ታደሰ ብሩ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል፤ እዚህ ጋ ልብ እንዲባል የምፈልገው፣ የጠቀስኳቸው ጀግኖቻችን የፖለቲካ ግባቸውን እንዲወክሉ ብቻ ነው፡፡ የዛሬው ህብረ-ብሄራዊ ኢትዮጵያዊ ማንነት የተገነባው፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊ (ከባንዳዎች በስተቀር) መሆኑን የሚያስገነዝብ አካታች ታሪክ፣ ሳይንሱን ጠብቀን  መገንባት ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ፡፡
የቋንቋ ጉዳይ ......
በተለያዩ ኩነቶች በቋንቋ ጽንሰ ሀሳብ ላይ የሚደረገውን እሰጣ-ገባ በአስተዋልኩ ቁጥር ስለ ‘ቋንቋ’ ያለን አረዳድ ኋላ ቀር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ብዙ ሰዎች ‘ቋንቋ መግባቢያ ነው’ ሲሉ ሰምቻለሁ። ይሄ ትክክል አይመስለኝም፤ ቋንቋ መግባቢያ ብቻ አይደለም፣ ቋንቋ የሁሉም ነገር መነሻ ይመስለኛል፣ ‘መጀመሪያ ቃል ነበር’ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ ልብ በሉ፤ ቋንቋ አይደለም የሚለው፣ ቃል እንጂ፡፡ በቋንቋው ያልሰለጠነ ህዝብ በሌላ ዘርፍ ለመሰልጠን፣ ለመግባባትና አብሮ ለመኖር ይቸገራል፡፡ ለዚህም ነው ባቢሎናውያን የጠፉት፡፡ ይልቁንም ቋንቋ፤ የአንድ ማህበረሰብ አይነተኛ የጥበብና ዕውቀቱ መገለጫ ፣ ቤተ መጻሕፍትና ለቀጣዩ ትውልድ ጥሪት መቋጠሪያው ነው ማለት ይቻላል፡፡
በሀገራችን የቋንቋ አረዳድ በብዙ ችግሮች የተወጠረ ነው፡፡ ከነዚህም ለመጥቀስ የመጀመሪያው፣ የአማርኛ ቋንቋን የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ የሚመለከቱበት መንገድ ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ ከአማራ ህዝብ ውጭ መነገር የጀመረው ከአጤ ምኒልክ ዘመን በኋላ ይመስላቸዋል፤ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ ከሩቁ ዘመን መሳብን ትተን፣ በትንሹ እንኳን አጼ ዮሐንስ የመንግሥታቸው የአፍ ቋንቋ አድርገውታል፡፡ አማርኛ የሀገራችን የስራ ቋንቋ ለመሆን ከሚያስችሉት ምክንያቶች ዋነኛዎቹ ከአማራ ህዝብ በተጨማሪ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለረጅም ዘመን ለሁሉ አቀፍ ግንኙነት መጠቀማቸው፣ ይህም የተናጋሪውን ቁጥር ከፍ እንዲል ማድረጉ፣ ለረጅም ዘመን በጽሑፍ የዳበረና የተሰነደ መሆኑ እንዲሁም ብዙ የመገናኛ ብዙሃን መኖራቸው አንኳሮቹ ናቸው።
ሁለተኛው ችግራችን ስለ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ያለን መረዳት ኋላ ቀር መሆኑ ነው፡፡ በተለያዩ ሀገራት ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋ እንዳላቸው የተለያዩ ድርሳናት ያስረዳሉ፤ ኢትዮጵያን የነፃነት ተምሳሌት አድርጋ፣ ከቅኝ ግዛት እራሷን ነፃ ያወጣችው ደቡብ አፍሪካ እንኳን ከአምስት ያላነሱ የስራ ቋንቋዎች አሏት፤ ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ የተጨማሪ ቋንቋ ሀሳብ ከሳይንሳዊ አመክንዮ ይልቅ በአንድነታችን ላይ የተቃጣ ዱላ ተደርጎ ቅዋሜ ሲገጥመው ታዝቤያለሁ፤ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ለአብነት የኦሮሚኛ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ መሆንን  ብንመለከት፣ የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ ብዛት፣ በጎረቤት ሀገራት የሚነገር ቋንቋ መሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ያለው የህትመትና የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር፣ በቂና አጥጋቢ አመክንዮ መስሎ ይታየኛል፡፡ ታዲያ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እንዲኖረን ስናደርግ፣ አተገባበሩ ከፖለቲካዊ ስሜት እንዲፀዳ መጠንቀቅ፣ ጥልቅ ጥናት ማድረግና  ሳይንሳዊ ጊዜ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ በዚህ መርህ መሰረት ኦሮሚኛ ቋንቋ ተካቶ፣ ከአተገባበሩ ልምድ ቀስመን ወደ ሌሎች ቋንቋዎቻችን ትግርኛ፣ ሶማሊኛ ወዘተ መሻገር የምንችል ይመስለኛል፡፡
ባህላዊ እውቀትን ለሀገራዊ ጥቅም ማዋል የሚችል ተቋም ግንባታ....
የኢትዮጵያ ህዝብ የባህል ሀብታም እንደሆነ ይታወቃል፤ በርግጥ አንድ ማህበረሰብ ባለው የተፈጥሮ ሀብት፣ በገጠመው ችግር፣ ዘመን በሚያሳድረው ጫና ምክንያት የሚሰለጥንበት ዘርፍ ይለያያል፡፡ ከሚሰለጥንበት ዘርፎች መሀከል ንግድ፣ አስተዳደር፣ ጦርነት ፣ ትምህርት፣ ማህበራዊ ዋስትና፣ ከተሜነት፣ መድሃኒት ማዘጋጀት፣ ኪነ ህንፃ፣ ልብስ፣ ኪነ ጥበብ፣ የግብርና ጥበብ፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ ተፈጥሮን መንከባከብ፣ የቤተሰብ መስተጋብርና መሰል ስልጣኔዎች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ወደ ራሳችን ብንመለከት የኢትዮጵያ ህዝብ የፈርጀ ብዙ ባህላዊ እውቀት ባለቤት ቢሆንም በአግባቡ የተጠቀመበት አይመስለኝም፤ ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ ሲከበር (ሲወርድ ሲዋረድ አላልኩም) የነበረው የባህል ሀብት፣ መንግስታዊና ተቋማዊ መስመር ይዞ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ መገልገል ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይሄን ለማድረግ ከየዘርፉ የተውጣጡ ምሁራን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እያጠኑ፣ ለሀገር በሚጠቅም መልኩ ባህላዊ እውቀትን ለማደራጀትና በሁሉም ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ህይወት ፋይዳ እንዲኖረው ማድረግ የሚችል የጥናት ተቋም ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ባህላዊ እውቀትን በዘመናዊ መልኩ፣ በተዋረድ በየመስሪያ ቤቱ ብንገለገል፣ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊና ሳይንሳዊ ጥቅም ባሻገር፣ የጋራ  ማንነት ለማጠናከር የሚጫወተው ሚና ትልቅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የተቋሙ ዋና አላማ፣ በአንድ አካባቢ ታጥሮ የሚገኘውን ባህላዊ እውቀት፣ የመላው ኢትዮጵያውያን እውቀት፣ ከዛም አለፍ ብሎ የአለም ህዝብ እውቀት ማድረግ ነው፤ ተመሳሳይ እሴቶቻችንን በማጉላት፣ በሳይንሳዊ መንገድ እየፈተሹ፣ ጠንካራ የሆነውን በማዳቀልና በማሳደግ፣ የጋራ ማንነትን ማጠናከር መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የቄስ ትምህርት ተሞክሮ (ሞዴል)- በትምህርት ስርአት፣ የገዳ ስርዓት- ለመንግስታዊ መዋቅር፣ የኮንሶ ማህበራዊ ዋስትና ማስጠበቂያ ባህል- ለማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ወዘተ በሚሆን መልኩ ማዘጋጀት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻም.....
የሰው ልጅ ሲፈጠር ሲሜት እንጂ ሀሳብ የለውም፤ በዚህ ምክንያት ከሀሳብ ይልቅ ለስሜቱ ቅርብ ነው። በምድር ላይ በጥንካሬና በስልጣኔ ለመኖር ከስሜት ፈቃድ ይልቅ የሀሳብ ሀልዮት ጠንካራ መሰረት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ስለዚህም የብሄር ፖለቲካ አራማጆች በአጭር ጊዜ ብዙ ተከታይ ያገኛሉ፤ የርዕዮት (የዜግነት) ፖለቲካን አቀንቃኞች አቀፍ ባልሆነ መልኩ ተግባራዊ ተደርጎ ቀርቶ፣ እንዲሁም ሀሳብ በራሱ የስሪቱ ሂደት የግለሰቦችን አቅምና ጊዜ የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለዚህም ካለንበት ችግር  ተላቀን፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት፣ የርዕዮት/ዜግነት ፖለቲካ በአዋጅ መሻገር ያለብን ይመስለኛል፡፡
እንደሚታወቀው፣ የሰው ልጅ መተንፈስ ስያቆም ይተላል፤ ትል የሚባል ፍጡር ሕይወት ይዘራል። ይህ የሆነው በትሉ ጥንካሬ ሳይሆን የሰው ልጅ በበሽታና አደጋ ምክንያት መተንፈስ ባለመቻሉ ብቻ ነው፡፡ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች (አራማጆች አላልኩም) የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎትና ራዕይ፣ ዘመኑ በደረሰበት ሳይንሳዊ እውቀት መፍታት ካልቻሉ፣ በኋላ ቀርና ኢ-ፍትሃዊ የፖለቲካ ዘይቤያቸው ታንቀው እራሳቸውን ይገላሉ፣ በመቃብራቸውም ላይ የብሄር ፖለቲካ ይፈጠራል፡፡
በመጨረሻ፣ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ሁሌም መስራት ያለባቸው፣ ለብሄር ፖለቲካ ገፊ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ዘመኑ በፈቀደ መጠን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ፣ የማህበረሰቡን ፍላጎት በትኩረት አጢነው፣ በፕሮግራማቸውና በተግባራቸው መመለስ አለባቸው፡፡ የብሄር ፖለቲካን ለማዳከምና የጎንዮሽ ጉዳቱን ለመቀነስ፣ ገፊ ምክንያቶችን በጊዜና በቀናነት ተረድቶ አፍጣኝ መፍትሔ ማበጀት፣ ዋነኛውና ሳይንሳዊ መንገድ ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ከአዘጋጁ፡- ሚለር ተሾመ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር ሲሆን በመጣጥፉ ላይ አስተያየት ያላቸው አንባቢያን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይችላሉ።

Read 8575 times