Saturday, 16 February 2019 14:00

“በሃውልቱ መቆም አፍሪካውያንም ኢትዮጵያውያንም ተደስተዋል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ኢትዮጵያን ከ50 ዓመታት በላይ የመሩት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ፤ ለኪነ ጥበብ ልዩ ፍቅር እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ብሔራዊ ትያትር፣ አምባሳደር፣ ማዘጋጃ ቤት፣ አለ የስነ ጥበብ ማዕከልና ት/ቤት-ወዘተ- በእሳቸው ከተሰሩ የኪነጥበብ ማዕከላት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ በማስፋፋትም ንጉሱ ይታወቃሉ፡፡ በትምህርት የላቁ ወጣቶችን በመሸለምና ወደ ውጭ ልኮ በማስተማርም ስማቸው ይነሳል፡፡ በአጠቃላይ አገራቸውን ከማዘመን ባሻገርም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት የፊት አውራሪነት ሚናውን ተጫውተዋል፡፡ ሃሳብ በማመንጨት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አንድነት ህንጻም በመስጠት ጭምር፡፡ ሆኖም እስካለፈው ሳምንት ድረስ እዚህ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ንጉሱን የሚያስታውስ ምንም  ምልክት  አልነበረም፡፡ በኬንያ ግን መንገድ ተሰይሞላቸዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሃውልት ቆሞላቸዋል፡፡ እኛ ሳናከብራቸው ሌሎች አክብረዋቸዋል፡፡
ቢዘገይም እንኳን ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሃውልት በህብረቱ ቅጥር ግቢ ቆሞላቸዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ “የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር” የቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ካህናት አባይነህ አበበ፣ የማኅበሩ ሊቀ መንበር አቶ ንጉሴ አምቦና የትምህርት ክፍል ኃላፊው አቶ አበበ በቀለን፣ በሃውልቱ እንዲሁም በመታሰቢያ ማህበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ በማነጋገር፣ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አጠናቀሯል፡፡ እነሆ፡-


       ከበርካታ ዓመታት በኋላ የአፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ሐውልት በአፍሪካ ሕብረት መቆሙ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ?
የአፍሪካ ህብረት አሁን ድርሻውን ተወጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችና ፈር ቀዳጅ ንጉሠ ነገሥት እንደሆኑ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ክብርና እውቅና መስጠቱ የሚጠበቅም መሆን ያለበትም ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት መስራችነት ሚናቸውን ለማጉላት ጊዜው ቢዘገይም መታሰቢያ ሐውልታቸው መቆሙ የሚያስመሰግንና የሚያስደስት ነው፡፡ አፍሪካውያን በየዓመቱ አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ ባደረጉ ቁጥር የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን ውለታ ከማስታወስና አንድ መታሰቢያ እንዲቆምላቸው ከማሳሰብ ቸል ያሉበት ጊዜ የለም፡፡ እንዳጋጣሚ እኛ አንድ ልብ ሆነን ይሄን ዕድል መጠቀም አልቻልንም፡፡ ዕድሉን መጠቀም ያልቻልነው በብዙ የተዛቡ አመለካከቶችና አረዳዶች የተነሳ መግባባት ባለመቻላችን ነው፡፡ አሁን በዚህ ዘመን ይሄ ሐውልት መቆሙ፤ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንድንል ያስገድደናል፡፡ አፍሪካውያን ተደስተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ተደስተዋል፡፡
የአፍሪካ መሪዎች አፄ ኃይለሥላሴን በዋናነት በምንድን ነው የሚያስታውሷቸው?
ዋናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ሃሳብ የእሳቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቢመሰረት በርካታ ሃገሮች ነፃ ይወጣሉ የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ እሳቸው በቅኝ ግዛት የተያዙ ሃገሮች ነፃ ከወጡ በኋላ ሃገራት የሚኖራቸውን የጋራ ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና፣ ማህበረሰባዊ ትስስር መፍጠር የሚቻልበትን ሁኔታም አስቀምጠዋል፡፡ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚለው መሰረታዊ ሃሳብ በእሳቸው ነበር የሚራመደው፡፡
ንጉሠ ነገስቱ ለሃገራቸውና ለአህጉሪቱ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ለምን ተዳፍሮ ቀረ?
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የስልጣን ዘመናቸው የተቋጨው በጥሩ ሁኔታ አይደለም፡፡ የለውጥ ሃዋሪያ ነን የሚለው ደርግ፤ የእሳቸውን ህያው የሆነ ክብር ለማጉደፍ ያልሆነ ስም በመስጠት፣ ህይወታቸውን ያለ አግባብ፣ ያለ ፍርድ እንዲያልፍ አድርጓል፡፡ ከዚያን በኋላ ደግሞ የእሳቸው በጎ ነገር ሁሉ እንዳይሰማ አፍኖ ይዞ ነው የቆየው፡፡ የሰሯቸውን ስራዎች በሙሉ በመሰወር፣ 17 ዓመት ሙሉ ታሪካቸውን ለማዳፈን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ በማርክሲስት ሌኒኒስት አስተሳሰብ የተወጠሩት ኢህአፓ እና መኢሶን ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላ አፅማቸውን የማፈላለግ ስራ ነበር በቅድሚያ የተሰራው፡፡ አፅማቸውን በማፈላለግ በኩል በወቅቱ የነበረው መንግስት ጥሩ ሚና ተጫውቷል፡፡ ነገር ግን አፅማቸው ከተገኘ በኋላ ቀብራቸው በስነ ስርዓቱ እንዳይከናወን ከልክሏል፡፡ የቀብር ሥነስርዓቱ አንድ ንጉሠ ነገስት በሚገባው ክብር እንዲፈፀም ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅት አፅማቸው ተቆፍሮ መውጣቱን በሙሉ ልብ የተቀበለውን ያህል አልተቀበለውም ነበር። በዚህም የተነሳ ለአንድ ንጉሰ ነገስት በሚገባው መጠን የተዘጋጀው የቀብር ስነ ስርአት እንዳይሳካ ሆኗል፡፡ ከዚያ በኋላም በተከታታይ የንጉሰ ነገስቱ መታሰቢያዎችን በተመለከተ መንግስት ተገቢውን እውቅና እንዲሰጥ ስንወተውት ብንቆይም፣ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አሁን በዶ/ር ዐቢይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን፤ ቀናነት እያየን ነው፡፡ ስለዚህም ሌሎች ጥያቄዎችም ይመለሳሉ የሚል ተስፋ ሰንቀናል፡፡
በወቅቱ ከመንግስት አካላት ሲሰጣችሁ የነበረው ምላሽ ምንድን ነው?
በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች በሙሉ ወስደው ምንም ሳይሉ ሸፍነው ያስቀምጡት ነበር፡፡ መልስ አይሰጡም፡፡ በሽምግልና ደረጃም በቀድሞ ፕሬዚዳንት ክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በኩል በአግባቡ ምላሽ እንዲገኝ ጥረት አድርገናል። እሳቸውም ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በአቶ መለስ ጊዜ ለንጉሠ ነገስቱ ጉዳይ የተሰጠው ትኩረት ምንም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአቶ ኃይለማርያም ጊዜ አሁንም ፕሬዚዳንት ግርማ ሽምግልናቸውን ገፍተውበት ነበር፡፡ ለክቡር አቶ ኃይለማርያም ያቀረብንላቸውን ጥያቄ፣ ይሄን ጉዳይ ለሚከታተል አካል ነው የመሩት፡፡ ያን ጉዳይ የሚመሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የማህራዊ ዘርፍ አማካሪ የነበሩት አቶ አለማየሁ ተገኑ ነበሩ፡፡ እሳቸውም አንድ ጊዜ ደውለውልን ጥያቄያችንን ከአንደበታችን ከሰሙ በኋላ “የሚሰጠውን ውሳኔ ጠብቁ፤ እንገልፅላችኋለን” አሉን፡፡ እሳቸውን እየጠበቅን ባለበት ወቅት አቶ ኃይለማርያም ከስልጣን ለቀቁና ክቡር ዶ/ር ዐቢይ መጡ፡፡ ለእሳቸውም ደብዳቤ ፃፍን፡፡ ከዚያ በኋላ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በአፍሪካ ህብረት ለቆመው ሐውልትም የጠ/ሚኒስትሩ አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በአፍሪካ ህብረት ሐውልታቸው እንደሚቆም ጠ/ሚኒስትሩ ከገልፁ በኋላ እኛም ከህብረቱና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን፣ እስከ ፍፃሜው ድረስ አብረን ስንሰራ ቆይተናል፡፡
የጋናው የነፃነት ታጋይ ዶ/ር ክዋሜ ንክሩማ ሐውልት በአፍሪካ ህብረት በቆመበት ወቀት በርካታ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ያኔ እናንተ ምን አደረጋችሁ?
የክዋሜ ንክሩማ ሐውልት ከመቆሙ በፊት ጀምሮ ነው እኛ መታሰቢያቸው እንዲሰራ ስንጠይቅ የነበረው፡፡ ነገር ግን እንዳልኩት የሚሰማን አልተገኘም፡፡ በኋላም የንክሩማ ሐውልት ሲቆም፣ እኛ በፅኑ ለመንግስት አሳስበናል፡፡ እንዴት ዋናው የታሪክ ባለቤት ንጉሠ ነገሥቱ እያሉ በህብረቱ ምስረታ አንድ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ንክሩማ ሐውልት ብቻ ይቆማል ብለን ጠይቀን ነበር፤ የሚሰማ አልተገኘም። እኛ የንክሩማ መቆም የለበትም የሚል ሙግት አላቀረብንም፤ ነገር ግን የሞኖሮቪያ እና የካዛብላንካ ቡድን ተባብለው በሁለት ፅንፍ የቆሙ ኃይሎችን “ይሄ ለአፍሪካ አይጠቅምም፣ ጠቃሚው አንድነት ነው” ብለው ሁለቱን አገናኝተው ለማፈራረም እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት ድረስ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው ጥሩ አቀባበል እንዲያደርጉ ንጉሠ ነገስቱ ብዙ ታግለዋል፡፡ አሁን ያ ውለታቸው ምላሽ እያገኘ ነው፡፡ እግዚአብሄር የራሱን ሰው አስነስቶ ታሪክ እየሰራ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስትን አቋም ለማወቅ ጥረት አድርጋችኋል?
አዎ፡፡ እንዲያውም በሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞች ሐውልቱ እንዲቆም ሲጠየቅ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞ ነው ያቀረበው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በወቅቱ እንደተቃወሙ ነው የሚነገረው፡፡ በዚህ በኩል በጣም አዝነናል፡፡ አቶ መለስ፤ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተሸላሚ ተማሪ ናቸው። አፄ ኃይለሥላሴን የሚያመሰግኑና የሚያወድሱ ሰው እንደነበሩም ከብዙ ጓደኞቻቸው ተረድተናል፡፡ በተለይ ቀብራቸው በአግባቡ እንዲከናወን ጥያቄ ባቀረብንበት ወቅት በሽማግሌዎች በኩል የተሰጠን መልስ፤ “እኔ አፄ ኃይለሥላሴን እወዳቸዋለሁ አከብራቸዋለሁ፣ እኔ እንደውም የሳቸው ተሸላሚ ነኝ፤ በእሳቸው ላይ ምንም ቅሬታ የለኝም ግን አንድ ውሳኔ የሚወሰነው በኮሚቴ ነው፤ ስለዚህ ከጓደኞቼ ጋር ተመካክሬ በቀጣይ አሳውቃችኋለሁ” ብለው መልስ ላኩብን፡፡ በኋላም ሽማግሌዎች ሄደው ምላሹን ሲጠይቋቸው፤ “አይ አዝናለሁ፤ ጉዳዩን ጓደኞቼ በሙሉ ተቃውመውታል፤ ምንም ማድረግ አልችልም” ነበር ያሉት፡፡
ይሄ ማህበር ቀብራቸውን ለማስፈፀም እንደተቋቋመ ይነገራል፡፡ ከዚያ በኋላ ምን አይነት ተግባራት  ሲያከናውን ቆየ?
አዎ፤ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ማኅበር የተቋቋመው ቀብራቸውን ለማስፈፀም ነበር፡፡ በኋላ የእሳቸውን ታሪክ ህያው ለማድረግ በሚል ማህበሩ ተጠናክሮ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡ እንደሚታወቀው ግርማዊነታቸው በዋናነት ለትምህርት ነበር ትኩረት የሚሰጡት፡፡ ለትምህርት ካላቸው ፅኑ ፍቅር የተነሳ፣ ንጉሰ ነገስትም የትምህርት ሚኒስትርም ነበሩ፡፡ አንድ ሃገር ሊለማ፣ ሊበለፅግ፣ ሊያድግ የሚችለው በትምህርት ነው የሚል ፅኑ አቋም ነበራቸው፡፡ ለትምህርት የሚያስፈልገውን ሁሉ አቅርቦት ከማሟላት አይቦዝኑም ነበር፡፡ ተማሪዎቻቸውንም ይንከባከቡና የነገዋን ኢትዮጵያ በእነሱ ውስጥ ይመለከቱ ነበር፡፡ ይሄ እሳቸው ልዩ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ አሁንም መቀጠል አለበት ብለን በስማቸው የስኮላርሺፕ ፕሮግራም ዘርግተን፣ አሁን በማህበሩ በኩል ተማሪዎችን እያስተማርን ነው፡፡ ሌላው በመንግስትነት ዘመናቸው፤ የሃገርን ህያው ታሪክና ቅርስ በመጠበቅና በማስጠበቅ ረገድ ግርማዊነታቸው የፀና አቋም ነበራቸው፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ ደግሞ በስማቸው በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ቤተ መፅሐፍት ወመዘክር ለማቋቋም እቅድ ይዘን እየሰራን ነው፡፡ ይሄ እቅዳችን እስካሁን እውን መሆን የተሳነው ከመንግስት ተገቢውን ድጋፍና ቀና አመለካከት ባለማግኘታችን ነው፡፡ መንግስት ፊት በመንሳቱ ብዙ ለመርዳት የሚፈልጉ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ሆኗል፡፡ የተሟላ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ነው ፕሮጀክቱ የዘገየው፡፡ በትምህርት ላይ ግን ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች አሉን፡፡ በእርግጥ አሁንም ቁጥሩ አናሳ ነው፡፡ 350 ያህል ተማሪዎች ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲ አስመርቀናል፡፡ በቀጣይ መንግስት ድጋፍ ካደረገልንና ባለሀብቶች የሚያግዙን ከሆነ የጃንሆይን ራዕዮች ለማሳካት ብዙ እንሰራለን፡፡
ለመንግስት ያቀረባችሁት ሌሎች ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
ዋናው ክብራቸውና መታሰቢያዎቻቸው በሙሉ እንዲመለሱ ነበር ስንጠይቅ የነበረው፡፡ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት የነበረው ከአባታቸው የወረሱትን ቦታ ነው ወደ ት/ቤትነት የቀየሩት፡፡ ያንን ሸጬ ለራሴና ለቤተሰቤ አንድ ነገር አደርግበታለሁ አላሉም፡፡ ለትምህርት ነው ያዋሉት፡፡ ት/ቤቱም “ተፈሪ መኮንን” ተብሎ ነው የተሰየመው፡፡ ነገር ግን ደርግ “እንጦጦ አጠቃላይ” ብሎ አዲስ ስያሜ ሰጠው፡፡ ከአባታቸው በወረሱት ሃብት ንብረት ላይ እንዲህ ያለ ግፍ ተፈፅሟል፡፡ በስማቸው ቢሆን ማን ምን ይጎዳል? ይሄን አሳምኖ የሚያስረዳ ይኖር ይሆን፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ በአባታቸው ቦታ ላይ ያስገነቡት ትልቅ መካነ እውቀት ነው፡፡ “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” ነበር የሚባለው፡፡ ያ ቦታ ከመንግስት የወሰዱት አይደለም፡፡ የራሳቸው የውርስ ቦታ ነው፡፡ ያንን እሳቸው ለህዝብ ሲያበረክቱ፣ እኛ እንዴት ስማቸውንና መታሰቢያቸውን እንኳ መጠበቅ አቃተን? መታሰቢያቸው ለምንድን ነው በስማቸው እንዳይጠራ የተፈለገው? በሌላ በኩል ሆስፒታሎችን ጨምሮ በርካታ የበጎ አድራጎት ተቋማት በእሳቸው የተቋቋሙ ናቸው፡፡
የአካል ጉዳተኞች፣ የህፃናት፣ የሴቶች፣ የቤተሰብ መምሪያ የመሳሰሉ የበጎ አድራጎት ተቋማትን በዘመናዊ መንገድ ያቋቋሙት አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው፡፡ ጦር ኃይሎች አካባቢ የነበራቸውን ርስት፣ ከውጭ ተምረው ሃገራቸውን ለማገልገል ለመጡ ኢትዮጵያውያን መኖርያነት ሰጥተዋል፡፡ ለእነጳውሎስ ኞኞ እና ሪቻርድ ፓንክረስ መኖሪያ 50 ሺህ ካሬ መሬት የሰጡት ከግላቸው ርስት ቆርሰው ነው፡፡ እንዲህ ያለ በጎነት የነበራቸው ንጉስ ናቸው፡፡ አሁን መንግስት በተለይ መታሰቢያቸውን ይመልሳል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ በጎ አድራጎት ድርጅቶቹም ወደ መታሰቢያ ድርጅቱ ሊመለሱ ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበናል፡፡
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ሲመረቅ፤ “ሐውልት እናቁምልዎ” ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡ እሳቸው ለዚህ የሰጡት ምላሽ “የኔ ሐውልት ስራዬ ነው” የሚል ነበር፡፡ ለሐውልቱ ማሰሪያ የተዋጣውን ገንዘብ ለዩኒቨርሲቲው ነበር የሰጡት፡፡ እስከ ዛሬ በራሳቸው በጎ ፍቃድ የተቀረፀላቸው ሐውልት የለም፡፡ አብዛኞቹ የውጭ ሃገር ሰዎች (ህንዶችን መጥቀስ ይቻላል)… ለክብራቸው መግለጫ፣ የቀረፁላቸው ሐውልቶች ናቸው ዛሬ በየመጋዘኑ እንዲጣሉ የተደረጉት። ሲኒማ ኢምፓየር አካባቢ ህንዶች ያቆሙላቸው ሐውልት ነበር፡፡ አሁን ቦሌ አንድ ጋራዥ ውስጥ ተጥሎ ይገኛል፣ ባህል ሚኒስቴር የነበረ ሐውልትም መጋዘን ውስጥ ተቀምጧል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ በየቦታው እንዲጣሉ ተደርጓል፡፡ ይሄ ሁሉ አሁን መቃኘት አለበት፡፡
አሁን በአፍሪካ ህብረት የቆመላቸው ሃውልት እሳቸውን አይመስልም፤ አለባበሳቸው ግርማ ሞገስ አሳጥቷቸዋል… የሚሉ ትችቶች በማህበራዊ ሚዲያ  ተሰራጭተዋል፡፡ የእናንተ አስተያየት ምንድን ነው?
ጃንሆይ የተለያየ አለባበስ ይጠቀሙ ነበር። አንዱ የሚጠቀሙት አለባበስም በሐውልቱ የተንፀባረቀው ነው፡፡ የትኛው አለባበስ ግርማ ሞገስ ያላብሳቸዋል የሚለው እንደ ሰዎች እይታ የሚወሰን ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ያቆሙላቸው ሐውልት ከእነ ኒሻናቸውና ከእነ ጎፈሬ የክብር ቆባቸው ነው፡፡ አሁን በአፍሪካ ህብረት ሐውልት መቆሙና እሳቸው መከበራቸው ብቻ ለኛ በቂ ነው፡፡ ሐውልቱም ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ሐውልት ግን የአፍሪካ ህብረት ያሰራው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ወጪውን ሸፈነ አልሸፈነ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ አሁንም ከህዝቡና ከመንግስት ግርማዊነታቸውን የሚመጥን ሐውልት በአዲስ አበባ ማቆም ይጠበቃል፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ሲጠይቁ የነበረውም፣ ንጉሱ ለነበራቸው የበጎ አድራጎት ተግባርና ለአፍሪካ ላበረከቱት አስተዋፅኦ፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ፊት ለፊት ባለው ፓርክ ውስጥ ሃውልት ሊያቆምላቸው ይገባል፡፡ ውለታቸውን የሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከመንግስት ፍቃዱን ካገኘ ሐውልቱን ማቆም አይከብደውም፡፡    

Read 1381 times