Tuesday, 12 February 2019 00:00

ከምርጫ በፊት ሪፈረንደም

Written by  ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
Rate this item
(2 votes)

ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሕዝቡ መሪውን ራሱ እንዲመርጥ የሚያስችለውን አሠራር  (ፕሬዚዳንታዊ መንግስት) ወይም ደግሞ እንደ አሁኑ ፓርቲው መሪውን እንዲመርጥለት የሚያደርገውን አሠራር (ጠቅላይ ሚኒስቴራዊ መንግስት)፤ ከሁለቱ መንገዶች አንዱን መርጦ ፈቃዱን እንዲያስታውቅ፣ ለሕዝቡ በሪፈረንደም ዕድል ይሰጠው ዘንድ ለመሞገት አራት ማስረጃዎች አቀርባለሁ።
1ኛ/ ሕዝቡ አዋቂ ነውና እናውቅልሃለን ከእንግዲህ አይሰራም
እናውቅልሃለን የሚሉ ልሂቃን፤ አንዴ ንጉስ፥ አንዴ ፕሬዚዳንት፥ አሁን አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እያሉ መንግስት መሰረቱ።  የለውጥ አየር እየነፈሰለት እፎይታን በማጣጣም ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በእሳት ተፈትኖ አዋቂ የሆነ ነውና፥ ዛሬ ላይ ቆመን ቀንበር እንደ በፊቱ ባናሸክመው መልካም ነው።  ጊዜውን የሚመጥን አካሄድ በመከተል ሕዝቡ መሪዉን ብቻ ሳይሆን የመንግስቱን ዓይነት /system/ ጭምር እንዲመርጥ ቢደረግ የሚመሰረተው መንግስት፣ የሕዝብ መንግስት ለመሆኑ ዋስትና በመስጠት ያፀናዋል።  ልሂቃን የትኛው እንደሚበጅ፣ በየፊናቸው ጥናታቸውንና አመለካከታቸውን ለሕዝብ በውይይትና በክርክር ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።  ከዚያ ባለፈ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቃት ባገናዘበ ሁኔታ፥ እኛ እናውቅልሃለን ብለው ከመወሰን ተቆጥበው፥ ፍርዱን ለሕዝብ እንዲተው ለህሊናቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።  ይህን አዋቂና ትልቅ ሕዝብ በማክበር፣ ሕዝቡ ያለው እንዲሆን ውሳኔውን ለሕዝብ ይለቃሉ የሚል እምነት አለኝ።
2ኛ/ ሕገ መንግስቱን ማስታመም
ሕገ መንግስቱ ተዐማኒ እንዲሆን ሕዝብ በመረጠው ሞግዚትነት ይፈተሽ ዘንድ ይገባዋል።  ስለዚህ የሕዝብ መንግስት እስኪኖረን ድረስ ወደድንም ጠላንም በዚህ ሕገ መንግስት ታስረናል።  ዝም ብለን በዚህ ሕገ መንግስት ደግሞ ወደ ምርጫው እንዳንሄድ የሕዝብ መንግስት ለመመስረት ብቃት አይሰጠንም።  ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ምርጫውን በተመለከተ ሕገ መንግስቱ ይፈታን ዘንድ ማሻሻያ ማድረግ የግድ ነው።  ይህን የምርጫ ማሻሻያ ለማድረግ ደግሞ ያለው ፓርላማ አሁንም የሕዝብ ስላልሆነ (በሀቀኛ ምርጫ) ውሳኔ ሊያስተላልፍልን አቅም የለውም።  ስለዚህ ሕገ መንግስቱን የማሻሻያ አውድ ሕዝቡ ራሱ እንዲሰጥ፣ የመንግስትን ዓይነት ለመወሰን (ፕሬዚዳንት ወይስ ጠ/ሚኒስትር) ሪፈረንደም ማድረግ የሕዝብን መንግስት ለመውለድ ተዐማኒነት ይሰጣል።
3ኛ/ ሁሉ አቀፍ መግባባት ወሳኝ ነው
ዶ/ር ዐቢይ  እንደ ሽግግር መንግስት ለማገልገል አሁን አይችሉም።  በአሁን ወቅት ተልዕኳቸው የዲሞክራሲ አዋላጅ መሆን ብቻ ነው።  ከአምባገነንነት ወደ ሕዝብ መንግስትነት የሚያሻግረን በመጀመሪያ ምርጫ የሚመሰረተው የሕዝብ መንግስት ነው።  የመጀመሪያ የሕዝብ መንግስት ለወደፊቱ መሰረት የሚጥል፥ ሕገ መንግስቱን ሕዝባዊ የሚያደርግ፥ አሻጋሪ መንግስት ነው።  ስለዚህ የመጀመሪያው ምርጫ ወደፊት ከምናደርጋቸው ምርጫዎች የተለየና ፈር ቀዳጅ ነው።  ስለዚህ ወደዚህ በዓይነቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅ ወደሆነው ምርጫ ስንሄድ፣ ከሞላ ጎደል ሁሉ አቀፍ መግባባት መኖር አለበት።  ለምሳሌ ፕሮፌሰር መረራ ምርጫ እንዳይራዘም ሲሉ፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሊራዘምም ይችላል ሲሉ ይታያሉ።  ሁለቱም የተፈተኑ ንፁህ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ ልባቸው ለኢትዮጵያ ደህንነት እንዲሆን በማለት ብቻ ይህንን ተቃራኒ አሳብ ያነሳሉ።  ታዲያ ሪፈረንደም በሚደረግበት ጊዜ፥ ለዋናው ምርጫ ግብዓት የሚሆን መረጃ /data/ በሁለቱም ጎራ ለተሰለፉ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ይኖራቸዋል።  ሪፈረንደም ሲደረግ የምናየው ሁኔታ ምርጫውን ለማድረግ መቼ መቻልን እንደምናገኝ፣ ፍንጭ በመስጠት መግባባት ላይ ያደርሰናል።

4ኛ/ እንከን የለሽ ምርጫ የግድ ነው
ከዚህ በፊት እንደጠቀስኩት የመጀመሪያው ምርጫ የተለየ ነው።  እንከን የለሽ መሆን ያለበትና ውዝግብ የማያመጣ፣ ፍፁምነትን የተላበሰ፣ ምርጫ ማካሄድ እንዳለብን ለድርድር አይቀርብም።  ታዲያ ከዚህ በፊት የተደረጉት ምርጫዎች ውሸት ስለነበሩ የምንማርበት ሆነው አይጠቅሙንም።  ሪፈረንደም ብናደርግ ግን፥ ለወሳኙ ምርጫ መማሪያና ወደፊት ምርጫም ሲካሄድ እንከን የለሽ እንዲሆን ቀደም ተብሎ ማስተካከያ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል።  ሪፈረንደም ማድረጉ ከታለመለት ዓላማ በተጨማሪ ድምፅ የመስጠት ልምድ የምንቀስምበትና ራሳችንን ለምርጫ የምናበቃበት አድማስ ያሰፋልናል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ። ይጎበኛታልም።
ከአዘጋጁ፡ ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል

Read 4961 times