በ65 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው ዘ ዲክታተር በመጀመርያ ሳምንቱ ያስገባው ገቢ 17.4 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ያመለከተው የቦክስ ኦፊስ ሞጆ መረጃ የኮሜዲ ፊልሙ እጅግ አዝናኝ ይዘት ቢኖረውም በገበያው “ዘ አቬንጀርስ” “እና ዘ ባትል ሺፕ” ፊልሞች ያገኙትን ትኩረት መፎካከር እንደተሳነው ገልጿል፡፡ ሳቻ ባሮን ኮሀን በዘ ዲክታተር ፊልም ላይ ለመተወን 20 ሚሊዮን ዶላር እንደተከፈለው ያወሳው የፎርብስ ዘገባ በበኩሉ ተዋናዩ ባለፉት 12 ወራት ማዳጋስካር 3 እና ሪዮ በተባሉ የካርቱን ፊልሞች በድምፅ ተዋናይነት ተሳትፎ ዓመታዊ ገቢው 30 ሚሊዮን ዶላር በመድረስ ከእነ ብራድ ፒት እኩል ክፍያ የሚያገኝ ምርጥ ተዋናይ አድርጎታል ብሏል፡፡እንግሊዛዊው ኮሜድያን ሳቻ ባሮን የካምብሪጅ ምሩቅ ሲሆን አሊ ጂ፤ቡርኖና ቦራት በተባሉ ገፀባህርያቱ ይታወቃል፡፡ ኮሜድያኑ ለሶሻል ሚዲያ እና ለመገናኛ ብዙሃናት ብዙም ትኩረት አለመስጠቱ ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ ቀንሶበታል ያለው የፎርብስ ሀተታ ብዙውን ጊዜ በገፀባህርያቱ ተደብቆ አደባባይ መውጣቱ ሊኖር የሚችለውን ዝና ቀንሶበታል በሚል ትንታኔውን አቅርቧል፡፡ቦክስ ኦፊስ ባይነምበርስ ባሰፈረው አሃዛዊ መረጃ በአንድ የፊልም ስራ ከ15 ሚሊዮን ዶላር ጀምሮ ክፍያ የሚጠይቀው ሳቻ ባሮን በአጭር የትወና ዘመኑ በሰራባቸው 10 የሚደርሱ ፊልሞች 2.02 ቢሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ ገቢ አግኝቷል፡፡