Saturday, 09 February 2019 12:21

አና ጎሜዝ የፊታችን አርብ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የኢሳት ጋዜጠኞች ወደ ሃገራቸው ይገባሉ

     በምርጫ 97 የአውሮፓ ታዛቢ ልኡክ መሪ የነበሩት እና ጎሜዝ፤ የፊታችን አርብ  ለ3 ቀናት ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሲሆን ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር እንደሚወያዩና በሚሌኒየም አዳራሽ ለህዝብ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡  
የአውሮፓ ፓርላማ አባሏ አና ጎሜዝ፤ በሃገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ጋዜጠኞችና ታዋቂ ግለሰቦችም ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ይወያያሉ ተብሏል፡፡ የ97 ምርጫ ቀውስን ተከትሎ “ኢትዮጵያ ነፃ እስክትወጣ እታገላለሁ፤ከነፃነት በኋላ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአዲስ አበባ ጎዳና እንሸራሸራለሁ” ማለታቸው የሚነገርላቸው ጎሜዝ፤ “አሁን ያንን ቃሌን የምፈፅምበት ጊዜው ደርሷል” በማለት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እንደተዘጋጁ የአቀባበሉን ስነ ስርአት ያሰናዳው ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
አና ጎሜዝ ለሶስት ቀን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ማረጋገጡን የጠቆሙ የአቀባበል ኮሚቴው፤ ከህዝብ ጋር በሰፊው የሚገናኙበት መድረክም ቅዳሜ የካቲት 9 በሚሌኒየም አዳራሽ በሚከበረው የኢሳት ቀን ላይ ይሆናል ብለዋል፡፡
ከዚሁ የኢሳት ቀን ጋር በተያያዘም የጣቢያው ጋዜጠኞች ከረጅም አመታት በኋላ አርብ የካቲት 8 ቀን ወደ አገር ቤት እንደሚገቡ ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ገላው፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና፣ ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን፣ ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው፣ እንግዱ ወልዴ፣ ወንድማገኝ ጋሼ እና ሌሎች የኢሳት ቤተሰቦች ይመጣሉ ተብሏል፡፡  
በመጪው ቅዳሜ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የኢሳት ቀን መርሃ ግብር ላይም እስከ 25 ሺህ የሚደርሱ የኢሳት ደንበኞች፣  እንግዶችና አድናቂዎች  ይታደማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሆኗል፡፡

Read 7727 times