Saturday, 02 February 2019 15:21

ቃለ ምልልስ የ50 ዓመቱ ዕድሜ ጠገብ ፓርቲ ምን አስቧል?

Written by 
Rate this item
(2 votes)


             “ሠላምና መረጋጋት ሳይፈጠር የሚደረግ ምርጫን እንቃወማለን”

    ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ አራት ወራትን ያስቆጠረው የ50 አመቱ የዕድሜ ባለፀጋ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፤ ራሱን በአዲስ መልክ እያደራጀ እንደሚገኝ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ መርሻ ዮሴፍ ይናገራሉ፡፡ ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም የሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተል ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ያብራሩት ሊቀመንበሩ፤ ባለፉት አራት ወራት ሲያከናውናቸው በነበሩ ሥራዎች፣ በመጪው ምርጫ፣ በአገሪቱ የለውጥ እርምጃ ወዘተ-- ዙሪያ የአፍታ ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ


    ኢህአፓ ወደ ሀገር ቤት ከገባ ከ4 ወራት በላይ አስቆጥሯል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን  አከናወነ?
እስካሁን ሁለገብ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ ዋናው ስራችን የምንለው ኢህአፓን እንደገና የማደራጀት ስራ ነው፡፡ ኢህአፓ እንደሚታወቀው፣ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የመጀመሪያው ነው፤ በ1964 ዓ.ም ነው የተመሠረተው፡፡ ባለፉት ዘመናት ብዙ ታግሎ ያታገለ ፓርቲ ነው፡፡ 17 አመት በደርግ፣ 27 አመት በወያኔ ስር ህገ ወጥ ሆኖ፣ ከሀገር የተባረረ ድርጅት ነው፡፡ ሀገር ውስጥ ይታገድ እንጂ  በውጪ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በህቡዕ ሲንቀሳቀስ ነበረ፡፡ ከመጣን በኋላ በተለይ ከቀድሞ አባላት ውስጥ በህይወት ያሉትን እያገኘን እያሰባሰብን ነው፡፡ ጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ አድርገን፣ የአዲስ አበባ የኢህአፓ ኮሚቴን በይፋ አቋቁመናል፡፡ ዘጠኝ የአመራር አባላት ተመርጠዋል፡፡ በዚያኑ እለት ጐንደር ላይ የኢህአፓ ኮሚቴ ተመስርቷል፡፡ ከዚያ በፊት ደሴ ላይ፣ ባህርዳር፣ አርባምንጭ፣ ባሌ ጐባ፣ ሃዋሣ---አባላት እንደገና እየተደራጁና ኮሚቴም እያቋቋሙ ነው ያሉት፡፡ ይህን የፖለቲካ ማደራጀት ስራ እየሠራን ጐን ለጐን፣ ከህብረ ብሄራዊ  የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት፣ የጀመርናቸው  የትብብር ውይይቶች አሉ፡፡
ከእነማን ጋር ነው የትብብር ውይይት እያደረጋችሁ ያላችሁት?
እሱ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ቢገለጽ ይሻላል። ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር ግን ንግግር እያደረግን ነው፡፡ ከቀሩት የብሔር ድርጅቶች ጋር ግን ሰፋ ያለ ግንኙነት አድርገን ሀገራዊ የፖለቲካ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበትን ተሞክሮ እያጋራን ነው፡፡ በጠ/ሚኒስትሩ አነሳሽነት በተጀመረው የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ውይይት መድረክ ላይም ተሳታፊ ነን፡፡ በሌላ በኩል፤ ይህቺ ሀገር ሠላምና መረጋጋት እንዴት ነው የምታገኘው? ህዝቡ በመረጠው ቦታ ያለ ምንም መሳቀቅ መኖር የሚችለው እንዴት ነው? የሚለው በጣም ስለሚያስጨንቀን፣ የሠላምና መረጋጋት ጉዳይ ቅድሚያ እንዲያገኝ፣ በሁሉም መድረኮች እየወተወትን ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንገብጋቢ ጉዳይ፣ ምርጫ ሳይሆን ሠላምና መረጋጋት ነው፡፡ ሀገሪቱ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት እስከሌለ ድረስ ሮጦ ምርጫ ውስጥ መግባት ምንም ጥቅም አያመጣም፡፡ ስለዚህ ሠላምና መረጋጋት ሳይመጣ፣ ሁሉም ዜጋ ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ሳይፈጠር፣ ወደ ምርጫ መሄድ የበለጠ ቀውስን መጋበዝ ነው፡፡
በዚህ ሰዓት ወደ ምርጫ ሂደቱ መግባት፣ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ በምርጫው ላይ ስለሚያደርግ  አንፃራዊ ሠላም ያስገኛል የሚሉ ወገኖች አሉ -----፡፡
እንደውም በምርጫ ወቅት ሁሉም ከሌላው በልጦ የራሱን ሃሳብ ለማስበለጥ በሚፍጨረጨርበት ወቅት የበለጠ ለግጭት በር ይከፍታል ባይ ነን፡፡ ለምን ከተባለ? አሁንም በማህበረሰባችን ውስጥ መረጋጋትና ነገሮችን በሠከነ መንገድ የማየት ልማድ ገና አልዳበረም። አንዳንድ ቦታ እኮ አሁንም “አትግቡብን፤ ይሄ የእናንተ ቦታ አይደለም፤ የኛ ብቻ ነው” እየተባለ ነው፡፡ ይሄ የክልል ፖለቲካ የፈጠረው መከፋፈል፣ መጠራጠርና እርስ በእርስ የመቧደን ነገር እልባት ሳያገኝ ወደ ምርጫ መግባቱ የበለጠ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡
በበርካታ አካባቢዎች አባላትን እያደራጀን ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሂደት የገጠሟችሁ ተግዳሮቶች አሉ?
እስካሁን የገጠመን የከፋ ችግር የለም፡፡ ላለፉት 27 አመታት ህወሓት ህዝቡን ለብጥብጥ የማዘጋጀቱን ያህል ችግር እያጋጠመ አይደለም። ወጣቱ ትውልድ፣ በየቦታው፣ በዘርና በጐሣ ስለተከፋፈለ፣ በፖለቲካው ላይ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደ ድሮው አይነት ጠንካራና ዘላቂ የፖለቲካ ተሣትፎ በወጣቱ በኩል አላየንም፡፡ ይሄ በተወሰነ የማደራጀት ስራ የሚለወጥ ይመስለናል፡፡
ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመዋሃድ አላሳባችሁም?
ውህደት የሚፈጠረው የአላማ አንድነት ሲኖር ነው፡፡ የሚስማማንን ካገኘን እንዋሃዳለን፤ አሁን ግን ጥድፊያ ውስጥ አንገባም፡፡ በመጀመሪያ ድርጅቱ በሁለት እግሩ ቆሞ፣ የራሱን አባላት አሰባስቦ፣ የራሱን የፖለቲካ ማንነቱን አሳውቆ፣ ተጠናክሮ ከወጣ በኋላ፣ ከሌሎቹ ጋር የመዋሃድ ጉዳይ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይህ እስኪሆን ግን ውህደት አይፈጠርም፡፡
በመጪው አገራዊ  ምርጫ ትወዳደራላችሁ?
በሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ተፈጥሮ፣ ምርጫ ከተካሄደ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መሳተፍ እንችላለን፡፡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት ሳይኖር ምርጫ የሚደረግ ከሆነ አንሳተፍም፡፡ ሠላምና መረጋጋት ሳይፈጠር የሚደረግን ምርጫም በግልጽ እንቃወማለን፡፡ እኛን የሚያሳስበን በምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን መያዝ ሳይሆን በዋናነት የሀገሪቱና የህዝቦቿ ሠላምና መረጋጋት ነው። ምርጫ ምርጫ የሚሆነው፣ ህዝቡ በነፃነት፣ ከስጋት በፀዳ፣ ፍፁም ሠላማዊነት እየተሠማው ሲሳተፍ ነው፡፡ ተቋማት እንደገና ነፃ ሆነው መደራጀት አለባቸው፡፡ በተቋማት ነፃነት ላይ ፍፁም መተማመን መፈጠር አለበት፡፡ ይሄ ነው ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራት የሚገባው፡፡ እንጂ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ አድርጐ ስልጣን መቀራመት አይደለም ቁም ነገሩ፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስትን የለውጥ እርምጃዎች እንዴት ታዩታላችሁ?  
እኛ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ የለውጥ (ሪፎርም) መንግስት ተግባራትን በሙሉ እናደንቃለን፡፡ ጥሩ እቅድና ጥሩ ጅምር ነገሮች አሉት፡፡ ሁሉም ጥሩ እቅዶች በተግባር መሟላት አለባቸው፡፡ ምናልባት መሰናክሎቹ በዝተውባቸው ሁሉንም አቅዶች አልተገበሩ ይሆናል፡፡ እኛም ሁሉንም ነገር በአንዴ አንጠብቅም፡፡ እስካሁን ድረስ አካታች የሆኑ የእርቅና የሠላም ስራዎች ግን በበቂ እየተሠሩ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለን የምናስበው፡፡
ፓርቲያችሁ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቧል?
ኢህአፓን ህጋዊ ለማድረግ እንድንችል የድጋፍ ፊርማ እያሰባሰብን ነው፡፡ እኛ መጠነ ሠፊ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ ካሟላን በኋላ እንመዘገባለን፡፡ አሁን በስፋት ወጣቶችን ጭምር ወደ ፓርቲው እያሰባሰብን ነው፡፡ ፓርቲውን፣ መሠረቱን በሀገር ውስጥ የማጠናከር ሥራ እየሠራን ነው፡፡
የምትከተሉት ርዕዮት  ዓለም ምንድን ነው?
ሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምን ነው የምንከተለው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ በጣም አስፈላጊ ነው ብለን የምናምንበት ርዕዮት ዓለም ነው፡፡ ተሣክቶልን ይሄን ርዕዮት ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ካመጣነው ትምህርት በነፃ፣ ህክምና በነፃ፣ በዋናነት የማህበራዊ ዋስትና ጉዳይ ላይ ብዙ እንሠራበታለን፡፡ የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል ታሣቢ ያደረገ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ በብዙ ሀገሮች ተፈትኖ ያለፈ ርዕዮት ስለሆነ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ርዕዮተ ዓለም ስር  ወጣቶችን በስፋት እናሳትፋለን፡፡




Read 1268 times