Print this page
Saturday, 26 May 2012 12:11

‹ሚስተር ሄንግሎ› በመጨረሻው 10ሺ የለንደን ተሳትፎውን ይወስናል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በሆላንዷ ከተማ ሄንግሎ ውስጥ ነገ በሚደረገው 30ኛው የኤፍቢኬ ጌምስ 10ሺ ሜትር ውድድር ላይ ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በርቀቱ የመጨረሻውን ውድድር ሊሳተፍ  ነው፡፡  በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው በ10ሺ ሜትር የሚሰለፉ አትሌቶች ለመምረጥ በሚካሄደው የሄንግሎው ትንቅንቅ ለመሳተፍ የወሰነው ኃይሌ ለለንደን ኦሎምፒክ ለማለፍ የመጨረሻ ሙከራውን ለማድረግ መነሳቱ ትኩረት ስቧል፡፡  በ10ሺ ሜትር ሩጫው ከኃይሌ ጋር ስለሺ ስህን፤ ኢማና መርጋ፤ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያምና አሊ አብዶሽ እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል፡፡ በትንቅንቁ ከ1 እሰከ 3 የሚወጡ አትሌቶች  በቀጥታ ለኦሎምፒክ የማለፍ እድል እንደሚኖራቸው እየተገለፀም ነው፡፡  በሄንግሎ የኢትዮጵያ አትሌቶች የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ሪኮርዶችን መስበራቸው የሚታወስ ሲሆን በርካታ አትሌቶች በርቀቱ ምርጥ ሰዓታቸውን የሚያስመዘግቡባት ምቹ የውድድር ከተማቸው መሆኗ በተደጋጋሚ አጋጥሟል፡፡  ኃይሌ በ10ሺ ሜትር የትራክ ውድድር ሁለት ጊዜ እንዲሁም ቀነኒሳ እስካሁን በእጁ የሚገኘውን የ5ሺ ሜትር ሪኮርድ በከተማዋ አስመዝግበዋል፡፡

“ሚር ሄንግሎ” ተብሎ በተወደሰባት የሆላንዷ ሄንግሎ ከተማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በ10ሺ ሜትር እንደሚወዳደር እየተገለፀለት የሚገኘው ኃይሌ ገብረስላሴ ተስፋ ላልቆረጠበት የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ ውድድሩን በከፍተኛ ትኩረት ገብቶበታል፡፡  ከሳምንት በፊት በማራቶን የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው አየለ አብሽሮ፤ የቤጂንግ ኦሎምፒክ የማራቶን ነሐስ ሜዳልያ ባለቤቱ ፀጋዬ ከበደና በበርሊን የማራቶን  ሪኮርዱን  የነጠቀው ኬንያዊ ፓትሪክ ማኩ በተሳተፉበት የማንችስተር የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ማሸነፍ የቻለው ኃይሌ በውድድሩ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በ27 ደቂቃ ከ39 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ አስመዝግቧል፡፡ ከሳምንት በፊት

 

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም የታንዛኒያ አቻውን የሚገጥም ሲሆን ሁለቱ ቡድኖች በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚያሸንፈው በኢኳቶርያል ጊኒ ለሚዘጋጀው 8ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ይበቃል፡፡ ሉሲ የሚባለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከነገው ጨዋታ በፊት በተደረገው የቅድመ ማጣርያ ጨዋታው የግብፅ አቻውን 6ለ4 በማሸነፍ እንዲሁም ተጋጣሚው የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ናሚብያን 7ለ2  በማሸነፍ ለዚሁ ወሳኝ የመጨረሻ  የማጣርያ ምእራፍ ደርሰዋል፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሆቴል በተከናወነ ስነስርዓት ለ14 ቋሚ ተሰላፊዎች አምስት አምስት ሺ፤ለአራት ተጠባባቂዎችና ለዋና አሰልጣኙ ለያንዳዳቸው አራት ሺ፤ለቡድን መሪና ለረዳት አሰልጣኞች የሶስት የሶስት ሺ ብር በአጠቃላይ የ102ሺ ብር ሽልማት በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ተሰጥቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ካረጋገጠ ጠቀም ያለ ሽልማት እንደሚያዘጋጅ ቢያስታውቅም አስተያየት ሰጭዎች ሉሲዎች ካስመዘገቧቸው አንፀባረቂ ድሎች አንፃር የተሰታቸው ማበረታቻ አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ ተችተዋል፡፡ መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ሆቴል ያደረጉት ሉሲዎች ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚያደርጉትን ወሳኝ የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታዎች በብቃት ለመወጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳላቸው ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡ ቡድኑ በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ስፖርት አፍቃሪው ወደ ስታዲየም በመግባት በተለመደ ድጋፉ ማበረታታቱ ለውጤቱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

በአሰልጣኝ አብራሃም ተክለሃይማኖት የሚመራው ቡድኑ ለ3 ዓመታት ባደረጉት ዝግጅት ደረጃውን የጠበቀ ኢንተርናሽናል የወዳጅነት ግጥሚያ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ሉሲዎች በዝግጅታቸው በከፍተኛ ሞራልና ህብረት ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ለአቋማቸው መፈተሻ ከተለያዩ የክፍለ ከተማ ቡድኖች ጋር ሲጋጠሙ ቆይተዋል፡፡

የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ለነገ ጨዋታ ባደረገው ዝግጅት በመጀመርያ ከዚምባቡዌ ጋር የተጫወተ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ተገናኝቶ 7ለ2 ተሸንፏል፡፡ ለነገው ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ከዳሬሰላም የተነሳው የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በስብስቡ በቱርክ ለሚገኝ ክለብ የምትጫወት ሶፍያ ሙዋሲኪሊ የተባለች ቁልፍ ተጨዋቹን ሳይዝ መሆኑ እንዳሳሰባቸው ረዳት አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡ 25 ልዑካንን የያዘው የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከነገው ጨዋታ በኋላ በማግስቱ ወደ ዳሬሰላም እንደሚመለስ ያወሳው ዘ ሲትዚንስ ዴይሊ ያለእረፍት ከ20 ቀናት በኋላ ከሉሲዎች ጋር ለሚኖረው የመልስ ጨዋታ ዝግጅቱን በከፍተኛ ደረጃ እነደሚቀጥል ዘግቧል፡፡ የታንዛኒያው ቢራ ጠማቂ ኩባንያ ሰረንጂቲ ብሪዌሪስ እና የአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ ዘ ትዊጋ ሲስተርስ ወይንም የታንዛኒያ እህትማማቾች ለሚባለው ብሄራዊ ቡድኑ እስከ 22 ሺ ዶላር ለተለያዩ ወጪዎችና እና ለአዲስ ትጥቅ እንደለገሱም ታውቋል፡፡

የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ከ2 ሳምንት በኋላ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ይደረጋል፡፡  ሉሲዎችና የታንዛኒያ እህትማማኞች ከ2 ዓመት በፊት በተመሳሳይ የማጣርያ ምእራፍ ተገናኝተው እዚህ አዲስ አበባ ላይ ታንዛኒያ 3ለ1 ካሸነፈች በኋላ ሉሲዎች በመልሱ ጨዋታ ዳሬሰላም ላይ 1 እኩል አቻ ቢወጡም በድምር ውጤት 4ለ2 ተረትተው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

 

 

Read 1712 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:25