Saturday, 26 May 2012 12:11

ማርሽ ቀያሪው - ምሩፅ ይፍጠር Yifter the Shifter

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ምሩፅ ይፍጠር፤ በሙኒክ ኦሎምፒክ በአስር ሺ ሜትር ሶስተኛ ወጥቶ የነሃስ ሜዳሊያ ካገኘ በኋላ፤  በአምስት ሺ ሜትር ለምን እንዳልተወዳደረ አልተናገረም፡፡ ወደ አገር ሲመለስም፤ ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ለምን እንደታሰረ አስተያየት ሲሰጥ አልተሰማም፡፡ ምሩፅ፤ ብዙ የመናገር ልምድ ያለው አይመስልም፡፡ ተግባሩና ጀግንነቱ ግን ራሳቸው ብዙ ይናገራሉ፡፡ ወደ አትሌቲክስ ስፖርት ለመግባት የቻለውም በንግግር አሳምኖ ሳይሆን፤ በተግባር ብቃቱን በማሳየቱ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ በአዲግራት የተወለደው ምሩፅ ይፍጠር፤ በወጣትነቱ ከጋሪ ነጂ ጀምሮ፤ በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡ እንዲህ በአስመራ እየኖረ ሳለ ነው አትሌቲክስን ስራዬ ብሎ የጀመረው፡፡ ነገሩ የአጋጣሚ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ነገር ግን አጋጣሚውን ለመፍጠርና በአጋጣሚው ለመጠቀም በቅድሚያ ብቃትን አዳብሮና ተዘጋጅቶ መጠበቅ የግድ ነው፡፡

ጎዳና ላይ የተዘጋጀ የአየር ሃይል የአትሌቲክ ውድድሮችን የተመለከተው ምሩፅ ይፍጠር፤ በአትሌቶቹ በእጅጉ ከመማረኩ የተነሳ አጠያይቆ ወደ ሻምበል ጉዲና ኮቲ ሄደ፡፡ የአየር ሃይል የአትሌቲክስ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ የቡድናቸው አባል እንዲሆን አልጠየቀም፡፡ ከቆፍጣናዎቹ አትሌቶች ጋር ነው መሮጥ የፈለገው፡፡ ውድድሩ ውስጥ እንዲያስገቡት ሲጠይቃቸው፤ ሻምበል ጉዲና፤ ምናልባት ፍላጎቱንና ቁመናውን በማየት ይመስላል ፈቀዱለት፡፡ በ1500፤ በ5ሺና 10ሺ ሜትር ውድድሮች መካፈል መቻሉ አስደስቶታል፡፡ በውድድሩ ያሳየው ብቃትና ያስመዘገበው ውጤት ግን ለራሱም አስደናቂ ነበር፡፡ ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት በተመልካቾች ተደነቀ፤ አሰልጣኞችም ተስፋ የሚጣልበት አትሌት ሊሆን እንደሚችል እምነት አደረባቸው፡፡

በውድድሩ ውጤት በእጅጉ የተበረታታው ምሩፅ፤ ጉጉቱ ስልጠናና ልምምድ ለማግኘት ነበር፡፡ በወቅቱ ለሜክሲኮ ኦሎምፒክ የተዘጋጀውን ብሄራዊ ቡድን ያሰለጥኑ የነበሩት ንጉሴ ሮባ፤ ምሩፅ ሲያነጋግራቸው፤ አበረታች ብቃቱን አይተዋል፡፡ ግን ከብሄራዊ ቡድን ጋር እንዲለማመድ በቀረበላቸው ጥያቄ ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ ይሁንና፤ በአየር ሃይል የአትሌቲክስ ቡድን ውስጥ መደበኛ ስልጠና ቢያገኝ ብቃቱን ማዳበር እንደሚችል በማመን፤ የተለያዩ አሰልጣኞችን አነጋግረውለታል፡፡ ጀአየር ሃይል ቡድን አሰልጣኞች በሻምበል ጉዲናና በሻምበል መኩሪያ አበበ ድጋፍ፤ አትሌት ምሩፅ  ቡድኑን በመቀላቀል ለመደበኛ ስልጠና ወደ ደብረዘይት መጣ፡፡

እውነትም የምሩፅ ሃሳብና የአሰልጣኞቹ ግምት ትክክል ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ጠንካራ ልምምድ ብቃቱን አሻሻለ፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የመካፈል ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ በአፍሪካ፤ ኤስያና በአውሮፓ በተዘጋጁ ውድድሮች በተለይ በ5ሺና በ10ሺ ሜትር፤ በሄደበት ሁሉ ልቆና ጎልቶ ይወጣል፡፡ ተለይቶ የሚታወቅበት ልዩ ምልክቱም፤ ዝነኛነቱን ጨምሮለታል፡፡ ውድድር ውስጥ ከተፎካካሪዎቹ ጋር ሲመራ የሚቆየው ምሩፅ፤ ሁለት ወይም ሶስት መቶ ሜትር ሲቀረው አዲስ ሃይልና ጉልበት ከየት እንደሚያመጣ ባይታወቅም፤ አፈትልኮ ይወነጨፋል - ማርሽ እንደቀየረ መኪና፡፡ በዚህም ማርሽ ለዋጭ የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ ምሩፅ ወደ ሜክሲኮ ኦሎምፒክ ከሚሄዱ ምርጥ አትሌቶች ጋር የመለማመድ እድል ባያገኝም፤ ከአራት አመታት በኋላ በጀርመን ሙኒክ ለሚካሄደው ኦሎምፒክ የብሄራዊ ቡድን አባል ሆኖ ተመረጠ - በአምስትና በአስር ሺ ሜትር፡፡ በኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ተወዳድሮ ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት የነሀስ ሜዳሊያውን ያጠለቀው ምሩፅ፤ በስኬቱ መደሰቱ ባይቀርም፤ እንደኦሎምፒኩ ሁሉ አሳዛኝ ሁኔታ ገጥሞታል፡፡ በጥረት የተገኘ ብቃትንና ጀግንነትን አጉልቶ በማሳየት ለአለም ህዝብ የመንፈስ ብርታት ያጎናፅፋል ተብሎ በሚታመንበት ኦሎምፒክ ላይ ፍቅርና ብሩህ መንፈስ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ይሁንና በአሸባሪዎች ዘግናኝ ጥቃት 11 የእስራኤል አትሌቶች በመገደላቸው፤ የሙኒክ ኦሎምፒክ ያልተጠበቀ የሃዘን ጥላ አጠላበት፡፡ ምሩፅም እንዲሁ ደስታን የሚበርዝ ሃዘን ነው ያጋጠመው፡፡ በአስር ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ያገኘው ምሩፅ፤ በአምስት ሺ ውድድር ሳይሳተፍ እንደቀረ እንጂ ምክንያቱ በግልፅ አይታወቅም፡፡ ምን ችግር እንዳጋጠመው አልተናገረም፡፡ ይሁንና ብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን፤ አትሌቶችን በእጅጉ እያደነቅን ብንወዳቸውም፤ ብናከብራቸውም፤ ችግራቸውን አንረዳላቸውም፡፡ ከፍተኛ ሃላፊነት እንጥልባቸዋለን፤ አንዳንዴም ከማንኛውም አቅም በላይ፡፡ እንደጠበቅነው ሳይሆን ሲቀር በጣም ይከፋናል፤ አትሌቶችን ቅር የሚያሰኝ ነገር እንፈፅማለን፡፡ የሙኒክ ኦሎምፒክ ተጠናቅቆ አትሌቶቹ ወደ አገር ሲመጡ፤ ምሩፅ የጀግና አቀባበል አልጠበቀውም፤ እንደ ከሃዲ  ተቆጥሮ ነው የታሰረው፡፡ እንዲህም ሆኖ የምሩፅ ፅኑ የአትሌቲክስ መንፈስ አልተሰበረም፡፡ እንደተፈታ ወዲያውኑ ወደሚወደው አትሌቲክ ተመለሰ፡፡ ግን ብዙዎች እንደተመኙት፤ ከአራት አመት በኋላ በካናዳ በተካሄደው ኦሎምፒክ ጀግንነቱንና ብቃቱን የማሳየት እድል አላገኘም፡፡ በኦሎምፒኩ ላይ የደቡብ አፍሪካ ቡድን መካፈሉን በመቃወም በርካታ የአፍሪካ አገራት ራሳቸው ከውድድሩ ሲያገልሉ፤ ኢትዮጵያም ሳትካፈል ቀረች፡፡ ይህም ቢሆን፤ ለምሩፅ ተስፋ አስቆራጭ የሆነበት አይመስልም፡፡ በ1972 ዓ.ም. የተካሄደው የሞስኮ ኦሎምፒክ የምሩፅ ነበር፤ አለምን ጉድ ያሰኘበት፡፡

በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ኢትዮጵያን በመወከል የተወዳደረው ምሩፅ፤  በፍፁም ብቃት በማሸነፍ ነው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ሊያገኝ የቻለው፡፡ በሁለቱም ርቀቶች በኦሎምፒክ ያሸነፈ አትሌት እስከዛሬ ምሩፅ ይፍጠር ብቻ ነው፡፡ በእርግጥም ማርሽ ለዋጭ መሆኑን ለአለም እንደገና በማስመስከሩ፤ ስያሜውን በዘላለማዊ ማህተም ህያው አደረገ፡፡ ከአትሌት አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ ወዲህ፤  የኢትዮጵያን ድል በማሳካት ባሳየው ጀግንነት ከፍተኛ ክብር አገኘ፡፡አትሌት ምሩፅ፤ በአትሌቲክስ ከ410 በላይ ውድድሮች የተሳተፈ ሲሆን፤ በ210 ውድድሮች አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመቀዳጀት አስደናቂነቱን በታሪክ አስመዝግቧል፡፡ በዚህ አስደናቂ ስኬትም ነው፤ አለም አቀፍ  የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የወርቅ የክብር ሽልማት የሰጠው፡፡ ምሩፅ ውድድር ሲያቆም ከአትሌቲክስ አልራቀም፡፡ ጀግና ጀግናን ያፈራል፡፡ እንደሱ የኦሎምፒክ ጀግኖችን፤ እነቀነኒሳ በቀለን፤ እነሚሊዮን ወልዴንና ገዛኸኝ አበራን በማሰልጠን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

 

 

Read 5702 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:25