Print this page
Monday, 28 January 2019 00:00

አጐንብሶ የሚበላን ተኝተህ ቀላውጠው

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት የድሬዳዋ ጓደኛሞች እርስበርስ ይከራከራሉ።
“የት ከብበ እንመገብ?” አለ አንደኛው፡፡
ሁለተኛው፤
“ጫልቱ ቤት” አለ፡፡
አንደኛው፤
“ይሄ መልካም ነው! ጫልቱ ጋ እንሂድ”
ሁለተኛው፤
“ነው ወይስ ክበባችን ሄደን እንብላ?”
አንደኛው፤
“እዛም እንችላለን፡፡ ግን እዚያ ምግብ ቶሎ ያልቃልኮ!”
“አንተ ስለምትጠላቸው ነው!”
“የመጥላት አይደለም!”
“ታዲያ ምን መላ አለው?”
ቀስ ቀስ እያሉ … እዚህ እንብላ፣ እዚያ እንብላ በሚል በክርክር ተካረሩ። ጭራሽ ወደ ድብድብ ዘለቁ፡፡ ብዙ ተዳሙ!! ሰው ገላገላቸው፡፡
በነጋታው ሁለቱ ጓደኞች፤ አብረው ገበያ ውስጥ ተቃቅፈው ሲገበያዩ ታዩ፡፡ ሰው ተገረመ፡፡
“ትላንት እንደዚያ ደም በደም እስክትሆኑ ድረስ የተቋሰላችሁ ልጆች፤ ዛሬ እንዴት እንዲህ ተቃቀፋችሁ?” አላቸው፡፡
ሁለቱም ባንድ ድምፅ መለሱ፡-
“ያማ ትላንትና ነው!!”
***
የሚገርመው የሀገራችን የኢትዮጵያ ችግር ያለ ጥርጥር ቂም በቀልን መርሳት ነው። ከዕለታት አንድ ቀን አፄ ኃይለስላሴ የጣሊያንን ወረራ አስመልክታ፣ ኦሪያና ፋላቺ የተባለች ጋዜጠኛ እንዲህ ስትል ጠየቃቸው።
“የጣሊያንን ወረራ እንዴት ያዩታል?”
በተፃፈበት ቋንቋ ብናስቀምጠው
“We forgive but we don’t forget!”
“ይቅርታ እናደርጋለን፣ ግን እናስታውሰዋለን”ብለዋል፡፡
ዛሬ ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡ ይቅርታ እናደርጋለን፤ እንረሳለን ብለን አምነናል፡፡ ግን ይሄ እንደ ባህል ከባድ ትግል ይጠይቀናል፡፡ ጠልቀን ካልገባንበት፣ ቀላልና ውል ለማስያዝ የሚያስቸግር መሆኑን ልብ እንበል። ምክንያቱም የእኛ አገር የቋንቋ ጉዳይ፤ ልክ እንደ ፖለቲካችን ሁሉ ወረት የበዛውና ድግግሞሽ የወረረው ነው! ብዙ የተጠላላን፣ ብዙ የተጠላለፍን፣ ብዙ የተጣጣን፣ ግን ዛሬ ሁኔታዎች ተለዋውጠው እንኳ ሙሉ በሙሉ ያልታረቅን መኖራችን፣ ሙሉ በሙሉ ይቅር ያልተባባልን አያሌ መሆናችን አሁንም ዕውነት ነው! ነገሮች የለበጣ አይሁኑ፡፡ እየለወጥንና እየተለወጥን ነን እያልን አንገበዝ!
ዋናው ነገር የምንሠራውን ከህዝባችን አንሸሽግ - ለጊዘው ያላወቀ መስሎን ይሆናል። ግን ያውቃል!
 ስለዚህ ማንም ቢሆን ምንም፣ ከህዝብና ከሀገር ተሸሽጌ ልብላ ቢል “አጐንብሶ የሚበላን ተኝተህ ቀላውጠው” የሚል የማይተኛ ዐይን እንዳለ ይገንዘብ ዘንድ ግድ ነው!

Read 7954 times
Administrator

Latest from Administrator