Saturday, 26 May 2012 12:02

ከG8 አገራት ያነሰ ዲሞክራሲ በጄ አንልም! (Think big!)

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(1 Vote)

“የአገር ውስጥ የግል ጋዜጠኞች በስንት ጣዕማቸው!” - ኢህአዴግ

እንደተለመደው ፖለቲካዊ ወጋችንን በቀልድ አሃዱ ብለን ብንጀምረውስ ----  በደረቁ ወደ ፖለቲካው ይ¦ችሁ እንዳልገባ ብዬ እኮ ነው - “ፖለቲካ  በፈገግታ” ቢሆንም፡፡  የተለያዩ የዓለማችን የህክምና ባለሙያዎች አገራቸው ስለደረሰችበት የህክምና ቴክኖሎጂ “እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ” በሚል ፉክክር ያወራሉ፡፡ የእስራኤሉ ዶክተር ይጀምራል “ እኛ አገር ህክምና በጣም ከመራቀቁ የተነሳ ከአንዱ ሰው ላይ ኩላሊት አውጥተን ለሌላኛው እንተክልለትና  በ6 ሳምንት ውስጥ ስራ ፍለጋ እንዲወጣ እናደርገዋለን ” ይላል፡፡ የእንግሊዙ ሃኪም በተራው “እቺ ምን አላት! እኛ አገር ከአንዱ ላይ ሳንባውን አውጥተን ለሌላኛው እንተክልለትና  በ4 ሳምንት ውስጥ ስራ ፍለጋ ይወጣል” አለ - በጉራ እየተቆነነ፡፡  የካናዳው ዶክተር ቀጠለ “ እኔ አገር ህክምና የትናየት ደርሱዋል መሰላችሁ! ከአንዱ ላይ ግማሽ ልቡን እናወጣና ለሌላው እንተክልለታለን” ከዛም ሁለቱም በ2 ሳምንት ውስጥ ስራ ፍለጋ ይወጣሉ” ይላል፡፡ የናይጀሪያው ሃኪም ደግሞ  “አቦ እናንተ በጣም ወደ ሁዋላ ቀርታችሁዋል” እኛ አንድ አዕምሮ የሌለው ሰው ወስደን ፕሬዚዳንት አደረግነውና ይኸው አሁን የአገሩ ህዝብ ሁሉ ስራ ፍለጋ ወጥቱዋል” ብሎ ገላገላቸው፡፡ አሁን ወደ ቁም ነገሩ ብንገባም ያምርብናል---

እኔ እምለው ግን ---- ከተማችን በአንድ ጊዜ ጉደኛ  የኮንፈረንስ ማዕከል ወጣት አይደል!  ሸገር በዚህ ከቀጠለች አንድም ትለማለች አሊያም ትፈርሳለች (It will make her or break her! እንዲሉ) ለምን መሰላችሁ? ኮንፈረንሱና እንግዳው በበዛ ቁጥር ዓለም የለመደውን ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ መስተንግዶና አገልግሎት መስጠት ካቃተን መሳቂያ እንሆናለንና እንትጋ ለማለት ያህል ነው --- እንጂ ሙዋርተኛ ሆኜ አይደለም (እንደ ኢህአዴግ  ለኢትዮáያ ከኔ ወዲያ ላሳር ባልልም እኔም አገሬን እንደምወዳት ይመዝገብልኝ!) የገረመኝ  ታዲያ ምን መሰላችሁ?  በአገሪቱ የሚካሄዱ ኮንፈረንሶች ዘንድሮ  በሁለት ዲጂት አደጉ --- ምናምን የሚል ዘገባ  አለመስማቴ ነው (በኢቴቪ ማለቴ ነው!) የኢኮኖሚ ዕድገት ካልተባለ አይዘገብም ማለት ነው? ለነገሩ የኢኮኖሚው ባለሁለት ዲጂት እድገት የሚመጣው እኮ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚገኙት ገቢዎችም ተደማምረው ጭምር ነው፡፡ እኔ ግን ምን ጠረጠርኩ መሰላችሁ? ኢቴቪ የጉባኤዎቹን ዘገባ ያልሰራው እንደ ኢኮኖሚው ባለሁለት አሃዝ ዕድገት አከራካሪ እንዳይሆን ፈርቶ  ይመስለኛል፡፡ (አይ ሞኞ !) የኢኮኖሚው ዕድገት ያከራከረው እኮ  ለሁሉም እኩል አልታይ በማለቱ ነው፡፡ አንዳንዶቻችንማ  አብስትራክት ስዕል ነገር እየሆነ አስቸግሮናል እኮ - ባለ11 በመቶው የኢኮኖሚ እድገት! እኔ የምለው --- ቻይና የየቤታችንን የኢኮኖሚ እድገት የምንለካበት ዘመናዊ መሳሪያ ለምን አትሰራልንም? ከዛ በሁዋላ ከኢህአዴግ ጋር አድጉዋል አላደገም እያሉ መወዛገብም ይቀርልናል፡፡ ምናልባት እሱ ይፈልገው ይሆን እንዴ? (ውዝግቡን ማለቴ ነው!)

ይኸውላችሁ --- በመዲናዋ የሚካሄዱ  ኮንፈረንሶች መጠን  በ16 ነጥብ 5 በመቶ ጨምረዋል ተብሎ ቢዘገብ እኮ ፈፅሞ አከራካሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም መረጃውን በዝርዝር ማቅረብ አይገድማ - ያውም ከነገቢው፡፡ የኢኮኖሚው ግን ገና በስታትስቲክስ ደረጃ ስለሆነ ከኮምፒውተር ወደ መሬት እስኪወርድ ድረስ  ማወዛገቡ ይቀጥላል፡፡ በእርግጥ እድገቱን በዓይናቸው ማየት የጀመሩ ዜጎች የሉም እያልኩ አይደለም፡፡ ለነገሩ ገና መንግስት ስለዕድገቱ በይፋ ከማወጁ  በፊትም  ባለ11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገቱን መቁዋደስ  የጀመሩም አይጠፉም - በይፋ ባይነግሩንም፡፡ የእኔ ቢጤ ምስኪን ታዲያ “እንዴት ተደርጎ” በሚል ወኔ ዘራፍ ማለት ሊዳዳው  ይችላል- ኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በሚል፡፡ ግን  ምንም አይጠቅመውም፡፡

እኔ የምለው በG8  ስብሰባ ላይ ምንድነው ተከሰተ የተባለው? ጆርጅ ቡሽ በኢራቅ የገጠማቸውን ዓይነት የሚመስል ተቃውሞ ሰማሁ ልበል - ጠ/ሚኒስትራችን ላይ (ያኛው ጫማ ሲወረውር፤ የኛ ደግሞ ተቃውሞ ወረወረ ነው ያሉት) የምር ተቃውሞ ነው ወይስ ታሪካዊ ዝና ፍለጋ? (ለሌላ ሳይሆን ለጠቅላላ እውቀት እኮ ነው!)

ግን እኮ ነገርየው እኔን ብዙም አላስገረመኝም፡፡ እንኩዋን የዳያስፖራ ተቃውሞ የሎካሉም ኢህአዴግን እንደማያስደነግጠው እናውቅ የለ፡፡  ለምን ቢሉ? ለተቃውሞ ጆሮ የለውማ (ቢዚ ነው!) በልማት ተወጥሩዋል፡፡ ሰሞኑን ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ምን ሰማሁ መሰላችሁ? በበለፀጉት አገራት ስብሰባ ላይ “Melese is dictator!”  በሚል አንድ የዳያስፖራ ጋዜጠኛ ተቃውሞውን  ከገለፀ በሁዋላ ኢህአዴግ በሎካል የግል ጋዜጠኞች ላይ የነበረውን አቁዋም ለውጥዋል የሚል ነገር ሰምቻለሁ - “የአገር ውስጥ የግል ጋዜጠኞች በስንት ጣዕማቸው!” በሚል ፀፀት (የባሰ አለና አገርክን አትልቀቅ አሉ!)

ጋዜጠኛው ተቃውሞውን ከገለፀ በሁዋላ በማህበራዊ ድረገፆች ብሽሽቁ ተጡዋጡፉዋል አሉ - በኢህአዴግ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል፡፡ ከደጋፊዎቹ አንዱ እንዲህ ፅፉዋል “ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሉዋ መንገዱዋን ትቀጥላለች” ሌላው ደጋፊ ደግሞ “እንዲህ ከሆነ የምትታገሉት መቼ ከስልጣን ልንወርድ ነው?” ሲል ተሳልቁዋል አሉ (በዳያስፖራ ትግል ላይ) በስብሰባው አዳራሽ ላይ ጠ/ሚኒስትሩን አሳጣ የተባለው ጋዜጠኛ  በዳያስፖራ ዘንድ ጀግና ሆኖዋል ሲባልም ሰምቼአለሁ (የአገር ውስጡን በተመለከተ መረጃ ስለሌለኝ ነው)  እናም የጀግንነት ተጋድሎውን የሚዘክሩ ስንኞች እየጎረፉለት ነው ይባላል - ያ የ27 ዓመት አሜሪካዊ የኮሌጅ ተማሪ በፈለሰፈው ፌስ ቡክ!

ይቅርታ አድርጉልኝና እኔ ግን ብዙም ሊካበድ አይገባም ባይ ነኝ - ተቃውሞው! (አገሩ እኮ አሜሪካ ነው!)  አያችሁ  ----  በስፖርት ማሸነፍና መሸነፍ እንዳለው ሁሉ፤ በፖለቲካም ተቃውሞና ድጋፍ ያለ እኮ ነው፡፡ እንኩዋንስ የአፍሪካ አገር መሪ “በዲሞክራሲ ከኛ ወዲህ ላሳር” ብለው የሚፈጠሙት መሪዎች ሳይቀሩ፤ የእንቁላልና የቲማቲም ውርጅብኝ  ያስተናግዳሉ! ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ” ሁሉንም ህዝብ በአንድ ጊዜ ማስደሰት አይቻልም ሲሉ መናገራቸውን ማስታወስ ተገቢ ነው! ስለዚህ በG8  ስብሰባ ላይ ጠ/ሚኒስትሩን የተቃወሙት ካልተደሰቱት ወገኖች የሚደመሩ ናቸው ማለት ይቻላል (ፔሬድ!)

እኔ የማልስማማው የተቃወሙ  ወገኖች ሁሉ  የአገራቸውን ዕድገት የማይመኙ፤ ፀረ - ኢትዮáያ ምናምን --- ወደሚል  አጉዋጉል ፍረጃ  ሲገባ ነው፡፡ እንዴ መንግስትን የተቃወመ ሁሉ የአገር ጠላት ነው ከተባለማ አገራችንን ልጅ አልባ ልናደርጋት እኮ ነው! (እጄን በእጄ ማለት ይኸኔ ነው) ትንሽ ቅር ያለኝ ነገር ግን አለ - ተቃዋሚዎቹን በተመለከተ፡፡ ያ ሁሉ የዓለም መሪ በተገኘበት አገራዊ  ገፅታችንን ከሚያበላሹት  ስብሰባው ሲጠናቀቅ ለምን ጠጋ ብለው  አይነግሩዋቸውም ነበር - ለራሳቸው ለጠ/ሚኒስትሩ! (ገበና የሚባል ነገር እኮ አለ) ልብ አድርጉ! የኔ ጥያቄ የዲሲፒሊን ጥያቄ ነው ፤ ለምን ተቃውሞ አቀረቡ አይደለም፡፡ ተቃውሞማ እንኩዋን “የዲሞክራሲ እናት ነኝ” በምትለዋ እማማ አሜሪካ ቀርቶም እኛም አገር ህገመንግስቱ ያጎናፀፈን መብት ነው - ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ውድና ብርቅ መብት! (ግንቦት 20 ሰኞ እኮ ነው!)

ይልቅስ እኛም በዚህች አጋጣሚ  ለጠ/ሚኒስትሩ የምናቀርበው ጥያቄ አለን (በጨዋ ወግ) ጠ/ሚኒስትሩ አገራችንን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ወክለው የበለፀጉ አገራት ስብሰባ ላይ ተገኝተው የአገራችንን  ገፅታ በመገንባታቸው  ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል፡፡ ኩራት የወለደው የመብት ጥያቄም ግን አለን፡፡ አገራችን ለG8 ስብሰባ ታጭታ መሰብሰቡዋ ካልቀረ እኛም የ G8 አገራት  አቻ የሆነ የዲሞክራሲና የነፃነት መብት ጥያቄ ለማቅረብ እንወዳለን (እንወዳለን ሳይሆን እንፈልጋለን) የእስካሁኑ ዲሞክራሲስ ምን አነሰው? የሚል ጥያቄ እንደማይቀርልን እናውቃለን ፡፡ ሆኖም እኛም የዋዛ አይደለንም፤ አጥጋቢ መልስ አለን - THINK BIG! የሚል፡፡ ምንም ሆነ ምንም ግን ከG8 ስብሰባ በሁዋላ ወደ ሁዋላ አንመለስም ብለናል፡፡ እውነቴን ነው! ከዚህ በሁዋላ ከG8 አገራት ያነሰ ዲሞክራሲ በጄ አንልም!! ደሞ በፖለቲካው ብቻ አይደለም፤ በኢኮኖሚውም ቢሆን  ከእነዚህ አገራት ያነሰ ነገር ፈፅሞ አንቀበልም፤ ምክንያቱስ የተባልን እንደሆነ - THINK BIG የሚለውን እንጠቅሳለን! (ትልቅ ተመኝ ትልቅ እንድታገኝ ነው ነገሩ)

ባለፈው እሁድ “አንድነት” ፓርቲ ከኪነጥበብ ጋር አዲስ የአጋርነት ውል መግባቱን  ሰማችሁልኝ? እስከዛሬ ፓርቲው የት ከርሞ ነው ብዬ  ልወቅሰው አልኩና ጭርሱኑ ሃሳቡም የሌላቸው ፓርቲዎች መኖራቸው ትዝ ሲለኝ “ማረኝ አንድነት” ብዬ ራሴን ከወቀሳው አቀብኩት፡፡  “ከነአካቴው ከሚቀር ቢዘገይ ይሻላል” ይላሉ ኒዮሊበራሎች (Better late than never!) አንድ ነገር ሳልደብቅ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ (ከናንተ የሚደበቅ ምስጢር ያለኝ አልመስልም?) የኢትዮáያ ፖለቲካ እንጨት እንጨት ብሎኝ ነበር፡፡ ምነው ቢሉ --- ድሮም በኪነጥበብ ያልታሸ ፖለቲካ እኮ አይጥምም!  ያው ፖለቲከኞቻችን ሰው የሚላቸውን አይሰሙም አይደል (በአውራው ፓርቲው ወጥተው!) ከደረቅ ፖለቲካ ጋር ሲያዳርቁን ከረሙ ፡፡

ለነገሩ ከኛ የበለጠ የተጎዱት ራሳቸው ፓርቲዎቹ ናቸው ፡፡ ከኪነጥበብና ባለሙያዎቹዋ  ጋር ቀደም ብለው መስራት ቢጀምሩ ኖሮ ይሄኔ የአባላቶቻቸውን ቁጥር በስንት ሚሊዮን ያሳድጉት አንደነበር አስቡት - እንደኢህአዴግ ፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ የአባላቶቹን ቁጥር ያሳደገው ከኪነጥበብና ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመስራት ነው የሚል ነገር አልወጣኝም! (ስልጣንና ጥበብ እኮ እስከዚህም ናቸው!) የኢህአዴግ የአባላት ቁጥር መተኮስ ምስጢሩ የ1ለ5 አደረጃጀት ስትራተጂ ነው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ገጥመውኛል፡፡ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ደግሞ ምስጢሩ ከአነስተኛና ጥቃቅን ጋር የተገናኘ ነው ባይ ናቸው! (ቆይ ማንን እንመን?) ለነገሩ አሁን አጀንዳችን ገዥው ፓርቲ ሳይሆን ምስኪኖቹ ተቃዋሚዎች ናቸው ፡፡  ምስኪን ያልኩዋቸው በሌላ እንዳይመስላችሁ! ስንት ዓመት ሙሉ ስልጣን እየጎመ¶ ትንሽ እንኩዋን ሳይቀምሱ  መቅረታቸው አሳዝኖኝ ነው፡፡ አሁንማ ሳስበው  ኢህአዴግ  “እንቁልልጬ” እያለ  በየዓመቱ  የስልጣን ልደቱን  ሲያከብር ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የሚወርድበትን ጊዜ ቁጭ ብለው የሚያሰሉ ይመስለኛል፡፡ አሁን ለምሳሌ ኢህአዴግ 40 ዓመት ስልጣን ላይ የመቆየት ሃሳብ አለኝ ብሎ የለ! (ኢዴፓ ክፉኛ ቢቃወመውም)  የፊታችን ሰኞ ደግሞ 21ኛ የስልጣን ልደቱን ያከብራል፡፡ ሁለቱ ሲቀናነስ 19 ዓመት ይቀራል ማለት ነው --- እያሉ ማስላታቸው አይቀርም (አበሻ ተስፋ አይቆርጥም እንዲሉ)  እኔ የምለው ግን --- የ40 ዓመት ስልጣን ሲል የእስካሁኑ ተቆጥሮ ነው ወይስ ከዜሮ ጀምሮ ነው የሚቆጥረው? (ተቃዋሚዎች እድላቸውን ሌላ የአፍሪካ አገር ቢሞክሩ ሳይሻላቸው አይቀርም!)

አንድ ማሳሰቢያ አለኝ - ኢህአዴግ የፊታችን ሰኞ ለሚያከብረው 21ኛ ዓመት ልደቱ ኬክ አሰርቼ በስጦታ ላበረክትለት እፈልጋለሁና ስፖንሰር ማድረግ የምትፈልጉ ባለሃብቶች ልታነጋግሩኝ ትችላላችሁ፡፡ ስፖንሰር ለማድረግ ስትመጡ በዚያው የአባልነት ካርድ ይሰጣችሁዋል፡፡  የምን? እሱ ሰርፕራይዝ ነው! በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግን ሰርፕራይዝ ማድረግ ስለምፈልግ እስከ ሰኞ ድረስ ስጦታውን በምስጢር እንድትይዙልኝ አደራ እላችሁዋለሁ! ይኼን የኬክ ስጦታ የማሰራለት ግን በግንቦት 20 የሃያ አንደኛ ዓመት የድል በዓል ስለደርግ ምንም ትንፍሽ ካላለ ብቻ ነው፡፡

ላለፉት 20 ዓመታት በየግንቦት 20ው በቀድሞ አገዛዝ ላይ የሚያወርደው የውግዘት ውርጅብኝ እኮ አሁንም ደርግ በህይወት ያለ ነበር ያስመሰለው፡፡ በዘንድሮ የድል በዓል ግን  ስለወደቀው ደርግ ሳይሆን በህይወት ስላለው ኢህአዴግ እንዲወራ ነው የምንፈልገው፡፡ ስለደርግ ውድቀት ሳይሆን ስለድልና ስኬት ነው እንዲተረክ የምንሻው፡፡ በሰኞው  የድል በዓል ኢህአዴግ Let bygones be bygones  ብሎ ስለራሱ ብቻ ይንገረን! (የደርግ ነገር በቃን)  ያልኩትን ከሰማኝ የልደት ኬክ አሽረዋለሁ ማለት ነው! ጆሮ ዳባ ልበስ ካለኝ ግን እኔም ጆሮ ዳባ ልበስ እለዋለሁ ማለት ነው!

 

 

 

 

 

Read 3618 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:08