Saturday, 26 May 2012 11:52

ሰዎች የጣሉብኝን ኃላፊነት በመወጣቴ ደስተኛ ነኝ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ወደ ቦንጋ የሄደ እንግዳ ሰው፣ “የት ልረፍ? ጥሩ አልጋ የት አገኛለሁ?” በማለት ፊት-ለፊቱ ያገኘውን የከተማዋን ነዋሪ ድንገት ቢጠይቅ “ማኪራ! ማኪራ ሆቴል ይሻልሃል” የሚል ምላሽ እንደሚያገኝ እገምታለሁ፡፡በከተማዋ ካሉ በጣት ከሚቆጠሩ ሆቴሎች አንዱ የሆነው “ማኪራ ሆቴል” በከተማዋ እንብርት መገኘቱ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ብዙ አልጋዎች መያዙ፣ … የሚያስመርጠው ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ ግን በከተማዋ ያሉ ሆቴሎች “ጥሩ አይደሉም፤ ደረጃቸውን አልጠበቁም፤ … እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ በቅርቡ፣ የቡና መገኛ መሆኗ የሚነገርላትን ማኪራ ቀበሌና እናት ቡና፣ እንዲሁም በቦንጋ ከተማ እየተሠራ ያለውን ብሔራዊ የቡና ሙዚየምና ዓለም አቀፍ የቡና መረጃ ማዕከል ለመጐብኘት ወደ ቦንጋ የሄዱት በርካታ አርቲስቶች ያረፉት፤ ጋዜጠኞችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሙሉ በሁለቱ ቀን ቆይታችን ቁርስ የተመገብነው በማኪራ ሆቴል ነበር፡፡ ጉብኝቱን አጠናቀን እንደተመለስን መድኃኒት ልገዛ ፋርማሲ ገብቼ የተዋወቅሁት ሰው ከጓደኛው ጋር በሆቴሉ ሲዝናና አገኘሁትና እንድቀላቀላቸው ጋበዘኝ፡፡ በጨዋታ መኻል ሆቴሉ የማን እንደሆነ ጠየኩት፡፡

ዞር ብሎ የለስላሳ ሳጥን እየሰበሰቡና ሁለቱንም ቀን ቁርስ ስንበላ ከሠራተኞች እኩል ወዳስተናገዱን ሰው አመልክቶ “የእሱ ነው” አለኝ፡፡ “እሳቸውኮ ጧት ቁርስ ስንበላ ሲያስተናግዱን የነበሩ ሰው ናቸው” አልኩት፡፡ “እሱ የሥራ ሰው ነው፡፡ ገንዘብ አለኝ ብሎ ሥራ አይንቅም፡፡ ጥሩ ታሪክ ስላለው ለምን አታነጋግረውም?” አለኝ፡፡ “ጨዋታችን ቀና እንዲሆን አስተዋውቀኝ” አልኩትና ተያይዘን ወደ ሰውዬው አመራን፡፡

ስምዎን ማን ልበል?

ማፊጦ ማሞ እባላለሁ፡፡

ሥራዎ ምንድነው?

ነጋዴና የዚህ (የማኪራ) ሆቴል ባለቤት  ነኝ፡፡

የት ተወለዱ? የት አደጉ? የት ተማሩ?

የተወለድኩት በካፋ ዞን ጌሻ ወረዳ ነፃነት ቀበሌ ነው፡፡ ከ1-6ኛ ክፍል ደካ ት/ቤት ተማርኩ፡፡ ወደ 7ኛ እንዳለፍኩ በኡራ 2ኛ ደረጃ ሽታ እስከ 11ኛ ክፍል ተማርኩ፡፡ ከዚያ ትምህርቴን አቋርጬ በ1976 በንግድ ሥራ መተዳደር ጀመርኩ፡፡

ምን ነበር የሚነግዱት?

አነስተኛ ንግድ ነበር፡፡ ብትን ጨርቆች ልባሽ ልብሶች (ሳልባጅ) ሹራብ፣ … የመሳሰሉትን መንገድ ዳርና ገበያ ውስጥ መሬት ላይ ዘርግቼ እነግድ ነበር፡፡ ከዚያም፣ ቦንጋ ከተማ ውስጥ ነዳጅ ማደያ አልነበረም፡፡ ሦስት ሆነን ነዳጅ ማደያ በሼር ከፈትን፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ትራንስፖርት ዘርፍ ገባሁ፡፡ በአንድ አይሱዙ ጀምሬ አምስትና ስድስት የተለያዩ መኪኖች ገዝቼ መሥራት ቀጠልኩ፡፡ በመኻሉ፣ ልጆች አፍርቼ ስለነበር እነሱን ለማስተማር አዲስ አበባ ገብቼና ቤት ሠርቼ 15 ዓመት ኖርኩ፡፡ የአዲስ አበባ ኑሮዬ ጥሩ ነበር፡፡

ንግድ ሲጀምሩ ካፒታልዎ ስንት ነበር?

በጣም ትንሽ ነበር፡፡ ተማሪ እያለሁ ያጠራቀምኩት 1ሺህ 500 ብር ነበረኝ፡፡ በዚያ ነው የጀመርኩት፡፡ አባቴና ታላቅ ወንድሜ አነስተኛ ንግድ ስለነበራቸው ከእነሱ በቀሰምኩት ልምድ እየተረዳሁ ደረጃ በደረጃ ዕድገት እያሳየሁ አሁን ያለሁበት ደረጃ ደርሻለሁ፡፡

አዲስ አበባ ሲገቡ ንግድ ተው?

አልተውኩም፡፡ መኪኖች አሉኝ ብዬህ የለ? በእነሱ መነገድ ቀጠልኩ፡፡ ከቦንጋ፣ ከሾካ፣ ከቤንች ማጂ፣ … የመንግሥት ንብረትም ሆነ የግለሰቦች ሸቀጥ በኃላፊነት ተረክቤ አመላልስ ነበር፡፡ ከዚያም ውጭ ቦንጋ ውስጥ ሌሎች ሥራዎችም ነበሩኝ፡፡ በደሌ ቢራ አከፋፍላለሁ፤ ነዳጅ ማደያውም አለ፡፡ መቼም ነጋዴ በአንድ ሥራ ብቻ አይወሰንም - የተለያዩ ነገሮች እሠራ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ጥሩ ኑሮ ከነበርዎት ለምን ወደ ቦንጋ ተመለሱ?

እዚህ (ቦንጋ) አካባቢ ሆቴሎች የሉም፡፡ ስለዚህ እንግዶች ሲመጡ የሚያርፉበት ስፍራ አልነበረም፡፡ ችግሩ ያሳሰባቸው ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ እነሱ “ከአንተ የተሻለ ሰው የለም፡፡ አንተን ብናስቸግር ይሻላል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ሥራ” ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔ እንኳ በሆቴል ዘርፍ የመሰማራት ፍላጐት አልነበረኝ፡፡ አባኮራን ሰፈር ያለው የዳሽን ባንክ ሥራ አስኪያጅ ጋር በጣም ጥሩ ወዳጆች ነን፡፡ እሱ በግድ “ቦንጋ ሄደህ አንድ ነገር መሥራት አለብህ” አለኝ፡

በዚያ ወዳጄ አነሳሽነትና ግፊት ወደ ቦንጋ ተመለስኩ፡፡ ይህ ቦታ (አሁን ሆቴሉ የተሠራበት) የገበሬ መሬት ነበር፡፡ በስፍራው ለነበሩ ጥቂት ባለ ይዞታዎች ካሳ ከፍዬ 1500 ካ.ሜ በነፃ ተሰጠኝና በ2000 ዓ.ም መጨረሻ ሥራ ጀመርኩ፡፡ በ2001 ዓ.ም የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ በጣም እየናረ ሄደ፡፡

የራሴ ገልባጭ መኪኖች ስለነበሩኝ ሌትና ቀን አዲስ አበባ እየተመላለስኩ ሁሉንም ዕቃ ማለት ይቻላል ያመጣሁት ከአዲስ አበባ ነው፡፡ አሸዋ የተጫነው ከሞጆ ነው፡፡ ከዚህ አካባቢ ያገኘሁት ድንጋይና የቀን ሠራተኞችን ብቻ ነው፡፡ የሕንፃ ግንባታ ባለሙያ እዚህ ስለሌለ ከደሞዝ በተጨማሪ መኖሪያና ቀለብ ችዬ ከአዲስ አበባ አምጥቼ፣ እንደምንም በሁለት ዓመት የሕንፃውን ግንባታ ጨርሼ ለአገልግሎት አብቅቻለሁ፡፡

በርካታ ችግሮችን አልፈው ሆቴሉ ሥራ ሲጀምር ምን ተሰማዎት?

እኔ በጣም ደስ ያለኝ ለችግር ሳልንበረከክ፣ ጓደኞቼና የከተማዋ ሕዝብ የጣሉብኝን እምነትና ተስፋ ማሳካቴ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ይህን ሆቴል ሲያዩ ይደሰታሉ፡፡ ወደ ሆቴሉ የሚመጡ ሰዎች ሁሉ ከተገለገሉ በኋላ ተደስተው አመስግነውና አበረታተውኝ ነው የሚሄዱት፡፡ እኔ አሁን እንግዶቼ ተደስተውና ረክተው በሚሰጡኝ ማበረታቻ፣ ትልቅ ሞራልና ክብር እየተሰማኝ ነው፡፡

እስቲ ስለ ሆቴሉ ይንገሩኝ… ስንት ክፍሎች አሉት?

ከጀርባ ባለሦስት፣ ከፊት ባለሁለት ፎቅ ሲሆን 55 ክፍሎች አሉት፡፡ ከታች አንድ ፀጉር ቤትና የባህላዊ ዕቃዎች መሸጫ ሱቆች አሉ፡፡ ሌሎች ክፍሎችም አሉ - በአጠቃላይ 60 ይደርሳሉ፡፡ የመኝታ አገልግሎት የሚሰጡት 55 ናቸው፡

የክፍሎቹ ደረጃ እንዴት ነው?

35ቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ የግል ሻወር፣ ቲቪ፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ተሟልተውላቸዋል፡፡ 20ዎቹ የጋራ መታጠቢያ ያላቸው ሲሆኑ ዕቃዎቹ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በፈቀደው ከቀረጥ ነፃ ዕድል ከቻይናና ከሌሎች አገራት የተገዙ ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሆቴሉ ግንባታ ወቅት ድጋፍ ላደረጉልኝና ላበረታቱኝ በሙሉ በተለይም ለልማት ባንክ፣ ለዞኑ ም/ቤት፣ ለዞኑ አስተዳዳሪዎች ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡

ለሆቴሉ ግንባታና ለዕቃዎቹ ግዥ ምን ያህል ገንዘብ ወጣ?

ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሦስት ሚሊዮኑ የባንክ ብድር ሲሆን ቀሪው የራሴ ነው፡፡

የወደፊት ዕቅድዎ ምንድነው?

አሁን የያዝኳቸው ሥራዎች በደሌ ቢራ አከፋፍላለሁ፤ ነዳጅ ማደያና ይህ ሆቴልም አለኝ፡፡ በ250 ሄክታር መሬት ላይ ቡና እያለማሁ ነኝ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ ብዙ የተማሩና ሀብት ያላቸው የቦንጋ ተወላጆች አሉ፡፡ እነሱ ወደዚህ ተመልሰው እንደ እኔ ኢንቨስት እንዲያደርጉና በልማት እንዲሳተፉ እየቀሰቀስኩ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ቀደም ሲል የካፋ ቡና ወደ አዲስ አበባ ተጭኖ፣ ከሌላ አካባቢ ከሚመጣ ቡና ጋር ተደባልቆ ሲሸጥ ነበረ፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማችን የቡና ቅምሻ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን እዚህ መጋዘን የለም፤ ያለውም ጠባብ ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ያሉ የቦንጋ ተወላጆችን አስተባብረን ትልቅ መጋዘን ለመሥራትና አዲስ አበባ ሳይሄድ እዚሁ ተበጥሮ፣ ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚደረግበት መሳሪያ ለመትከል ዝግጅት ላይ ነን፡፡

አካባቢያችን ብዙ የሚጐድለው ነገር አለ፡፡ ከሌሎች ጋር በመሆን የሚጐድለንን እያየን፣ በቅደም ተከተል በእርሻውም በአግሮ ኢንዱስትሪውም በመሳተፍ፣ አካባቢውን ለማልማት ፕሮፖዛል እየተዘጋጀ ነው፡፡

ከአጐራባቾቻችን ጋር በመተባበር ስንሰራ አካባቢያችንን እናለማለን፣ እንለውጣለን፣ ለበርካታ ወገኖቻችንም የሥራ ዕድል እንፈጥራለን፡፡ አቶ ማፊጦ ማሞ የ55 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ሲሆኑ አምስት ልጆች አፍርተዋል፡፡ ወንዱ ልጃቸው ሌላ ቦታ ተመድቦ ይሠራ ነበር፡፡ ከእሳቸው ጋር ሆኖ ልምድ እንዲቀስም በማለት ጠርተውት አብሯቸው እየሠራ ነው፡፡ አንዷ ሴት ልጅ በዲቪ አሜሪካ ሄዳለች፡፡ ሁለቱ ሴት ልጆች ዩኒቨርስቲ እየተማሩ ሲሆን የመጨረሻዋ ልጅ የ11ኛ ክፍል የመሰናዶ ተማሪ ነች፡፡

 

 

 

Read 6234 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 12:02