Saturday, 19 January 2019 00:00

ደብረብርሃን ዘመቻ ላይ ነች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 የአፄ ዘርያዕቆብንና የአፄ ምኒልክን ሃውልት ለማሰራት ዝግጅት እየተደረገ ነው
           

    ከአዲስ አበባ ከተማ በ130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውና በጥንታዊነቷና በታሪካዊነቷ የምትታወቀው የደብረብርሃን ከተማ፤ “ፍቅር ሠላም በደብረብርሃን” የተሰኘ ዘመቻ መጀመሯ ተገለፀ፡፡
ትናንት በኢሊሌ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የከተማ ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊው አቶ ብርሃን ገ/ህይወት እንደተናገሩት፤ ከተማዋ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት፣ የአየር ንብረቷ አመቺ፣ በአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝና በርካታ የቱሪስት መስህቦች ያሏት ከተማ ብትሆንም የሚገባትን ያህል ዕውቅናና ገቢ እያገኘች አይደለም፡፡ ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ እንዲሁም፣ የሰው ኃይል በብዛት የሚገኝባትና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ እስከ አሁን ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በስራ ላይ እንደተሰማሩ ተናግረዋል፡፡
ከተማዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝምና የቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ም/ከንቲባው፤ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ከተማዋን የቆረቆሩት የአፄ ዘርአያዕቆብ ሃውልትን በሃበሻ ቢራ ስፖንሰር አድራጊነት ለማሰራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ለከተማዋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን የአፄ ምኒልክን ሀውልት ለማሰራትም ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንና ዲዛይኖችን በመምረጥ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ደብረብርሃን በርካታ ታሪካዊ ቦታዎችና አስደናቂ ገዳማት ያሉባት ጥንታዊት ከተማ መሆኗን የገለፁት ከንቲባው፤ በእነዚህ ጥንታዊ የቱሪስት መስህቦቿ በአግባቡ ለመጠቀም እንድትችል ለማድረግ በተጠናከረ መልኩ ዘመቻ ለማድረግ መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተማችንን የቱሪስት መዳረሻ፣ የኢንቨስትመንት ከተማና የኢንዱስትሪ መንደር ለማድረግና የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል ያሉት በከተማዋ የዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ ደምሳሽ ኃ/ገብርኤል፤ ይህንኑ ከተማዋን የማስተዋወቅና ለቱሪስትም ሆነ ለኢንቨስትመንት አመቺ መሆኗን የማሳየት ዘመቻ “ፍቅርና ሰላም በደብረ ብርሃን” በሚል መሪ ቃል መጀመሩን አብስረዋል፡፡ ዘመቻው የተለያዩ ፓናል ውይይቶችን፣ የባለሀብቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች ጉብኝቶችን፣ የከተማዋ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ውይይቶችን እንደሚያካትት የጠቆሙት አቶ ደምሳሽ፤ በዚህም የከተማዋን ገጽታ ለአለም ለማሳየትና ከተማዋም ሆነች ነዋሪዎቿ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ እንቅስቃሴው ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ተጀምሮ ለ15 ቀናት ይቆያል በተባለው የንግድ ትርኢትና ባዛርም፤ አንጋፋውን ድምፃዊ ፋሲል ደመወዝን ጨምሮ በርካታ ድምፃውያንና አርቲስቶች እንደሚገኙና ይህም ከተማዋን ለማስተዋወቅ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ እንደታመነበት የአፍሪካ ሚዲያ ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ እንዳለ በዚሁ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡



Read 1122 times