Saturday, 26 January 2019 13:28

ማራኪ አንቀጾች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በወንዶች አለም ውስጥ አንዲት ሴት


     የአዲስ አበባ ወንድ የመልበሻ ቤት መስተዋት ሆኗል፡፡ ሴቶቹ በሱ ፊት ላይ አለባበሳቸውን ያያሉ፤ የአዲስ አበባ መንገዶች፣ ካፌዎች፣ ባሮች፣ ቢሮዎች፣ ሆቴሎች፣ የፀሎት ቤቶች … አለባበስ ማሳያ መድረኮች ሆነዋል፡፡
ወንዱ የጥሞና ጊዜ ተነፍጓል፡፡ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ ሲሰራ፣ ሲፀልይ፣ ታክሲ ሲጠብቅ … በሞዴሎች ተከቦ ነው፡፡ ህይወቱ የናይት ክለብ ውስጥ እስረኛ ሆናለች፡፡ ሲወለድ ሳውና ባዝ የገባ ሲሞት ይወጣል፡፡ ኑሮው በላብ መጠመቂያ ስፍራው ሆናለች፡፡ አይኑ ሸሽቶ የትም አይደርስም፡፡ እድሜ ልኩን መስክ መካከል እንደቆመ ሁሉ በአበባ ተሰላችቷል፡፡ …ትቢያ… ናፍቆታል፡፡
ሴቶች፤ የወንዶች አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ሆነዋል፡፡ አይኑን ያገለግላሉ፣ ልቡን ያገለግላሉ፣ ስሜቱን ያገለግላሉ … የሴቶች የመጨረሻ አማራጭ … የወንዶች ገበያ .. እንደሚፈልገው ሆኖ መገኘት ነው። ህይወታቸው በወንዶች ህልም የተፈበረከ ነው፡፡ ከሰው የሚጠበቀው ከዘንድሮ ሴቶች አይገኝም፡፡ ወንድ የሚፈልገውን ግን አያጣም። አይኑ፣ ጆሮው፣ አፍንጫው፣ ምላሱ … በሴቶች ትጋት ሥር ተጠምዶ ተደናቅፏል፡፡ አንዲት ሴት ከአንዲት አበባ ጋር በንፅፅር ቆማለች፡፡ የወንድ ቀልብ እንደ ንብ ሲጠመድላት ከማየት ውጭ ሌላ ህልም የላትም፡፡
እንግሊዛዊው ደራሲ ዲ.ኤች ላውረንስ ይሄንን ታዝቦ አንዲት የመረረች መጣጥፍ አቅርቦ ነበር፡፡ “Give her a pattern” ይላል ርእሱ “The real trouble about women is that they must always go on trying to adapt themselves to men’s theories of women, as they always have done.” ብሏል፡፡ (የሴቶች ዋነኛ ችግር ወንዶች ስለሴቶች የሚኖራቸውን ፅንሰ ሃሳብ አሟልተው ለመገኘት ሁልጊዜም መጣራቸው ነው)
የዘንድሮ ሴቶች ሴት የመሆን መብት የላቸውም፤ ወንድ የሚፈልገው አይነት ሴት እንጂ፡፡ ሴቶች የወንዶችን ህልም ለመተርጎም ህይወታቸውን የሚሰዉ ጭዳዎች ናቸው። በመሰልጠን ስም እራሳቸውን ለፆታ ባርነት አጋልጠዋል፡፡ ኧረ እንዳውም ከባርነት ወርደው ለአሻንጉሊትነት ተዳርገዋል፡፡ ሁኔታውን “Living Doll” ይለዋል Cliff Richard የተባለ አቀንቀቃኝ፡፡ … ህያው አሻንጉሊት … እንደማለት ነው፡፡ “I got myself a sleeping, walking, crying, talking Doll” (እራሴን የምትተኛ፣ የምትሄድ፣ የምታለቅስ፣ የምታወራ አሻንጉሊት ሆኜ አገኘሁት) የዘንድሮ ሴቶች ሰው መሆናቸው የሚረጋገጠው ስለሚተኙ፣ ስለሚሄዱ፣ ስለሚያለቅሱና ስለሚያወሩ ብቻ ነው፡፡ እንደ አበባ … ንብ.. መጥራት የህይወት ትርጉማቸው ሆኗል፡፡  
(ከዓለማየሁ ገባላይ
“መለያየት ሞት ነው”
2010 ዓ.ም፤ የተቀነጨበ)

Read 3965 times Last modified on Saturday, 26 January 2019 13:30