Saturday, 19 January 2019 00:00

የጃንሜዳ ስፒልና ሀርሞኒካ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ትናንትና ዛሬ ጃንሜዳ ትደምቃለች፡፡ ስሙኝማ የምር ግን እንደ ጃንሜዳ በብዛት አድቬንቸር የተሠራበት የአዲስ አበባ አካባቢ ይኖራል! እንደውም…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በአገራችን የቤተሰብ ምስረታ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውና ዋናው ምእራፍ ለጃንሜዳ መሰጠት አለበት፡፡ ስንትና ስንት ትዳር የቆመው እኮ እድሜ ለጃንሜዳና ለጥምቀት በዓል!
ሰውየው ለቃለ መጠይቅ ቀረቡ እንበል፡፡
“ከባለቤትዎ ጋር እንዴት እንደተገናኛችሁ ሊነግሩኝ ይችላሉ?”
“ልክ የዛሬ ሀያ ዓመት ጃንሜዳ የጥምቀት እለት ነው የተገናኘነው፡፡”
“እስቲ ስለሁኔታው አጫውቱኝ፡፡”
“በቃ ለከፍኳትና ተዋወቅን፡፡” (ስሙኝማ በአሁኑ ጊዜ “ለከፍኳትና…” የሚል ነገር ቢነገር የሆነ ፖለቲከኛ ወይ አክቲቪስት ወይ ‘ምናምኒስት’… አለ አይደል… “ለመሆኑ ከለከፋት በኋላ ሆስፒታል ሄዳ የራይቢስ ክትባት ተከትባለች?” ሊል ይችላል፡፡)
የምር ግን ዘንድሮ እያንዳንዷ ድርጊትና እያንዳንዷ ቃል ቀለበት መንገድ ይመስል በምትጠቀለልበት ዘመን “ለከፍኳትና…” አይነት ቃላት የማህበራዊ ሚዲያ አጄንዳ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
“እኮ በምን ዘዴ ነው እንደዛ ያደረጉት፣ ሎሚ ወረወሩባት?”
“ሎሚ አልወረወርኩባትም፡፡ ረጅም ዱላ ይዤ ነበር፡፡ ዱላው ጫፍ ላይ ስፒል አድርጌ በስፒሉ ነካ አደረግኋት፡፡” (ስፒል! አዎ ስፒል፡፡ የዛን ዘመን ስፒል እንዳሁኑ ዘመን ቪትዝ በሉት!) ስሙኛማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ዘንድሮ እንደ አብሮ አደግ ማህበር አይነት፣ “የእንትን ትምህርት ቤት፣ የእንትን ዓመተ ምህረት ምናምነኛ ክፍል ተማሪዎች ማህበር፣ የእንትን ሰፈር ተፈናቃዮች ማህበር” እየተባለ ይቋቋም የለ፣ ‘የጃንሜዳ ስፒል ባለውለተኞች ማህበር” የማያቋቁምሳ!
ስሙኝማ…በዚህ ዘመን አይደለም በዱላ ጫፍ ስፒል ተደርጎ ‘ጠበሳ’ ስፒል የሚለውንም ቃል ምን ያህል ሰው እንደሚያውቀው ጥናት ቢካሄድ ውጤቱ ‘ሰበር ዜና’ ነገር ይሆን ነበር፡፡ “መጠይቁ ከቀረበላቸው ሰዎች የስፒልን ምንነት እናውቃለን ያሉ ከ5.5% አይበልጡም፡፡”
“ስማ ስፒል ፈልጌ ነበር… ትንሽ ይኖርሀል?”
“ስፒል! ስፒል ምንድነው?”
እና ዘንድሮ “በስፒል ነካ አድርጌያት…” ቢባል እሱን አያድርገኝ! አሀ...የማህበራዊ ሚዲያ ‘አንገብጋቢ አጄንዳ’ ሊሆን ይችላል፡፡ ፖለቲከኛው… “የጠላቶቻችን ተላላኪ የሆኑ አካላት ስፒል በመጠቀም ሴቶችን ያለፍላጎታቸው እሺ ለማሰኘት እያደረጉ ያሉትን ሙከራ የምናወግዝ ሲሆን በተቻለው ሁሉ የምንዋጋው ነው፣” የሚል የአቋም መግለጫ ሊያወጣ ይችላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ “የአገሪቱ መጻኢ አድል ያረፈው በስፒል ላይ ስለሆነ ይህን ግብ ለማድረስ የአስር ዓመት መሪ እቅድ እየነደፍን ሲሆን ከጥገኝነት ለመውጣት መጀመሪያ የምንወስደው እርምጃ በተለያዩ አካባቢዎች የስፒል ፋብሪካዎችን መገንባት ነው፣” ሊል ይችላል፡፡
አመኑኝ….ዘንድሮ ‘አጄንዳ’ እየተደረጉ ከምንሰማቸው ነገሮች አንጻር ያ ሁሉ ትዳር እንዲመሰረት ምክንያት የሆነችው ስፒል አጄንዳ የማትሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡
ሀርሞኒካስ! የሀርሞኒካ ውለታስ መረሳት አለበት! አገሪቱ በ‘ሲንግል’ ለቃቂዎች ‘ጊነስ ቡክ ኦፍ ሬከርድስ’ መግባት ቢኖርባትም ሀርሞኒካን የመሰለ ‘እሱና እሷን’ ያጣመረ የሙዚቃ መሳሪያ መኖሩ በጥናት መረጋገጥ ያለበት ነው፡፡ ደግነቱ እኮ “ሜጀሩ ጥሩ ሆኖ ማይነሩ ላይ አጎረነነውና አበላሸው፣” የለ... “ከሀቲ ሜር ሳሀቲ ፊልም ላይ መንትፎ ነው፣” ብሎ ነገር የለ…ዋናው ነገር ከሀርሞኒካዋ ለውዝዋዜ የሚያመች ድምጽ ማውጣት ነው… አለቀ፡፡
ሌላው ተንታኝ ምናምን ነገር ደግሞ… “እዚህ ላይ ዋናው ነገር ስፒሉ ሳይሆን ከስፒሉ ጀርባ ያሉት እነማን ናቸው የሚለው ነው ይልና ስፒልን የሆነ የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ሊከታት ይችላል፡፡ “ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ ስፒል አታመርትም። ሊጠየቅ የሚገባው ስንት የሚያስፈልጉን ምርቶች እያሉ እንዴት ነው ለስፒል ቅድሚያ ተሰጥቶ አገር ውስጥ እንዲገባ የተደረገው የሚለው ነው፡፡ ስለዚህም ቢሮክራሲው መፈተሽ አለበት፡፡ ከስፒል ኢንዱስትሪዎች ጋር  በልዩ ጥቅም የተሳሰሩ ሊጋለጡ ይገባል፣” ሊል ይችላል፡፡
እመኑኝ… አሁን ባለው አንድ ሺህ አንድ የሴራ ፖለቲካ፤ ስፒል የሴራ ፖለቲካ አካል የማትሆንባት ምክንያት የለም፡፡ የሆነ ‘አክቲቪስት’ ደግሞ “ስፒልን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ አስራ አምስት ቀን የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ…” የሚል ሊጀምር ይችላል፡፡
ደግሞላችሁ ሌላው ስልጣኔው ግንባሩ ላይ ቸፍ፣ ቸፍ ሲል  “በዚህ በሶሻል ሚዲያ ዘመን ስፒልን መሰል ያፈጀን ያረጀ ነገር መጠቀም ኋላ ቀርነት ነው፡፡ እንደውም ለአገሪቱ ኋላ ቀርነት ከዋነኞቹ ምክንያቶች መሀል የጃንሜዳ ስፒልና ሀርሞኒካ ናቸው፣” ሊል ይችላል፡፡
የሞሪንሆ ደጋፊ ደግሞ “ከጆሴ መባረር ጀርባ ዋናው ድሮግባ ሆነ ብሎ ያሳይ ከነበረው ዳተኝነት በተጨማሪ የጃንሜዳ ስፒል ሳይኖርበት አይቀርም፣” ሊል ይችላል፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) በዚህም፣ በዛም ግን የጃንሜዳን ስፒልና ሀርሞኒካ ውለታ መርሳት አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ አኮ ውለታ የሚባል ነገር የተረሳ ነው የሚመስለው፡፡
ለምሳሌ እሱዬው የላሚቷን ወተት በየቀኑ በሊትሮች ሲጋት ይኖራል፡፡ ፊቱ የተፈጥሮ ሳይሆን በምርጥ ሰም የተወለወለ ይመስላል፡፡ ጭማሪ ስጋ መጨመር የሚችለው ሰውነት ክፍል ሁሉ  ቀዩንም ነጩንም ጨማምሮ… አለ አይደል… ሲገዛው “ይሄ ነገር ሰፍቶኝ ሱሪ ሳይሆን ጆንያ ያጠለኩ ነው የሚመስለኝ የተባለላቸው ይጠቡና… “ይሄ ነገር እኮ ከጉልበቴ አላልፍ አለ!” ምናምን ይባላል፡፡ (አኛ ዘንድ ውፍረት የምቾት ምልክት ነው…አሁንም ቢሆን፡፡) እናላችሁ… ያቺው ላም ወይ በጤና መታወክ ወይ በእርጅና ትመነምናለች፡፡
“ስማ ያቺ ወተቷን ስትጠጣ የኖርካት ላም… አይቻት እንዴት እንዳሳዘነችኝ!”
“የምን ላም ነው የምታወራው?” (ሰውየው ምንድነው የሚለው… አርጅቶ የተጣለ የከሰል ምድጃ የመሰለውን ግንባርህን ያወዛችው ነቻ!)
“ያቺ ቡራቡሬዋ ናታ! ተው አንጂ ወተቷን ስትጨልጥ ኖረህ የቷ ትለኛለህ!”
“ማን፣ እኔ ነኝ የእሷን ወተት የምጠጣው! ስማ አይደለም ወተቷን ልጠጣ እሷን ማየት ከመጠየፌ የተነሳ ከሩቁ ነው የምሸሻት!” ብሎ አርፍ፡፡ (አጅሬው… ‘ወዝ’  ይቆይ መስሎሀል!)
እናላችሁ… ዘንድሮ በተለያየ መልኩ በቀረበላቸው ወተትና ጮማ…ሲወዙ ከርመው አሁን ጊዜ ዘወር አለች ተብሎ፣ አሁን አዲሰ ዘፈን መጣ ተብሎ….ውለታ መርሳትን እያየን ስለሆነ…በዘመኑ ወጣቶች ዘይቤ… “ኸረ ሼም ይያዛችሁ!” ማለት ያስፈልጋል፡፡
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡
“ስማ… ትናንት ከሰዓት በኋላ እንገናኝ ተባብለን የት ነው የጠፋኸው?”
“እባክህ ደከመኝና እንትን የሚባለው ፋይቭ ስታር ሆቴል ሳውና ገብቼ፣ እዛው ምሳ ምናምን ስል ሰዓቱ አለፈብኝ፡፡” ፋይቭ ስታር ሆቴል! አዛው ምሳ! እንዲህ አኮ የሚያወራላችሁ ፒያሳ መሀል የመገናኛን ሚኒባስ ታክሲ ለመያዝ ከመለስተኛ ጦርነት ያላነሰ ግፊ ውስጥ ሆናችሁ ነው፡፡
ለነገሩ… ‘ፋይቭ ስታሩ’ ሆቴሉ ሳይሆን ‘ቀደዳው’ ነው፡፡ (ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ ‘ውሸቱ’ ለማለት ነው፡፡ ‘የፖለቲካ ተንታኞች’ የፈለጉትን ትርጉም የመስጠት መብታቸው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡)
ዘንድሮ፣ “ለዋልኩት ውለታ በምላሹ ምስጋና አገኛለሁ፣” ብሎ የሚያስብ ሰው የሚያገኘው የተላጠ ጨጓራ ብቻ ነው! እናላችሁ…  “ለውለታዬ ምላሽ አገኛለሁ፣” “ውለታዬ ይታወስልኛል፣” ማለት ሞኝነት ሆኗል፡፡
ለጃንሜዳ ስፒልና ሀርሞኒካ ውለታ ኮንሰርት ይዘጋጅልን፡፡
መልካም የበዓል ሰሞን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2376 times