Print this page
Saturday, 19 January 2019 00:00

ባሉ ሳይገኝ ሚዜ መረጠች

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ምናምኒት ፀጉር ራሳቸው ላይ የሌላቸው መላጣ ጓደኛሞች ረዥም መንገድ ሊሄዱ ተቀጣጥረው ተገናኙና ጉዞ ጀመሩ፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ ከርቀት አንድ እንደወርቅ የሚያበራ ነገር አዩ፡፡
አንደኛው፤
“መጀመሪያ ያየሁት እኔ ስለሆንኩኝ ለእኔ ይገባኛል” አለ፡፡
ሁለተኛው፤
“አንተ አይደለህም፡፡ እንዲያውም ያ ምን ይሆን? እንደወርቅ ያበራልኮ ብዬህ አልነበረም?”
አንደኛው፤
“አይደለም፡፡ እኔ አልተናገርኩም እንጂ መጀመሪያ ዐይኔን ጥዬበት ነበር፡፡”
ጭቅጭቃቸው እንደዋዛ ተጀምሮ መክረርና መምረር ያዘ፡፡ ዕቃው የኔ ነው የኔ ነው ሆነ ጉዳዩ፡፡  ቀስ በቀስ ወደ ቡጢ ተሸጋገሩ፡፡ አንዱ በቴስታ ሌላኛውን አደማው፡፡
የደማው በንዴት ድንጋይ አንስቶ ባለ ቴስታውን ተረከከው፡፡ ደም በደም ሆነው ተናነቁ፡፡ አንዱ አንዱን ጥሎት ከላይ ሆኖ ይቀጠቅጣል፡፡ ጥቂት ቆይቶ የታችኛው ይገለብጠውና ይቀጠቅጠዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን አንድ ጠና ያሉ አዛውንት በዚያ መንገድ ያልፉ ኖሮ፤ ሁለቱ ሰዎች ደክሟቸው ዝለው ሲዘረሩ ጠብቀው፤
“ለምንድነው እንዲህ እስክትደሙ የተደባደባችሁት”
“አባት እዚያ ከሩቅ የሚያበራውን ዕቃ አይተውታል?”
አዛውንቱም፤
“አዎን አሁን አየሁት” አሉ፡፡
“እኔ ነኝ ያየሁት፤ እኔ ነኝ ያየሁትና ለእኔ ይገባል አለ እሱ፡፡ እኔ ደሞ መጀመሪያ ያየሁት እኔ ነኝና ለእኔ ነው የሚገባው አልኩ፡፡ የጠባችን መነሻ ይሄው ነው”
አዛውንቱም፤
“መልካም፡፡ እኔ ሄጄ ላምጣውና ትካፈሉም እንደሆን የሚቻለውን መፍትሔ እናግኝለት” እንዳሉት ሄደው ዕቃውን ይዘው ተመለሱ፡፡ እየሳቁ ነው የመጡት፡፡
ከዚያም፤
“ለመሆኑ በዚህ ዕቃ የሚጠቀም ማነው?” ብለው በጣም ሳቁ፡፡ ለካ ዕቃው ማበጠሪያ ኖሯል!
***
ከላይ የተረክነውን ተረት ፈረንጆችም ይጠቁሙበታል፡፡ ከዚህ የሚገኘውን ትምህርት ሲጠቁሙም ሁለት ምርጫ ይሰጣሉ፡፡ እነዚህም፡-
የስስት መጨረሻው አሳዛኝ ነው (Greed leads to unhappiness)  
የጥንቱ አባባል እዚህ ላይ ይሠራል - “የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለም” (all that glitters is not gold)
ሁለቱም ምክሮች ለእኛ ያገለግላሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር የምንጣላበትን ጉዳይ ማወቃችን ላይ ነው፡፡ የፖለቲካችን ስፋት፣ የችግሮቻችን ጥልቀት፣ የመፍትሔዎቻችን ከአፍንጫችን ሥር መሆን፣ ወደ ዘላቂ ዕድገት የሚያሸጋግሩን ዓይነት አይደሉም፡፡ ይልቁንም የሚያብለጨልጩት ነገሮች እየደለሉን ፋይዳ ያለውን ጉዳይ፣ ከፋይዳ - ቢሱ መለየት አቃተን፡፡ ትክክለኛውን ሀሳብም ሆነ የመታገያ መድረክ አንጥረን አላየንም፡፡ መንገድ አልመረጥንም፡፡ አዲስ ለውጥ መጥቷል እንላለን እንጂ እኛ አልተለወጥንም፡፡ ዛሬም የአሳዳጅ - ተሳዳጅ ፖለቲካ ነው እያራመድን ያለነው፡፡ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ወደተሻለ ህይወት የሚያሸጋግራት፣ አዕምሮ ከአዕምሮ ስንናበብ ነው፡፡ በወረት (Fashion) ከተጓዝን መፈክር ከማስገር የዘለለ ነገር አይኖረንም! የሚያስብ
ሰው (Thinker) መፍጠር እንጂ መንገኝነት አይጠቅመንም፡፡ ፈረንጆቹ Herdism amputates thinking ይላሉ፡፡ ያለአሳቢ ሰው ዕድገት ሽባ ይሆናል። ቀዳሚውንና ተከታዩን በጊዜ ካልለየን፣ ተገቢውንና የማይገባውን በአግባቡ አንጥረን ካልጠየቅን፣ ዋናውን ጉዳይ ሳናበስል እንክልካዩ ላይ ተጥደን እንቀራለን። ስለዚህ መሬት የረገጠውንና ተንሳፋፊውን አበጥረን እናስቀምጥ፡፡ አለበለዚያ “ባል ሳይገኝ ሚዜ መረጠች” የሚባለው ምሳሌ በእኛ ላይ ደረሰ ማለት ነው፡፡ ከጊዜ ጋር እንፍጠን! እርምጃዎቻችን ሥር የሰደዱና አንኳር አንኳሩ ላይ ያተኮሩ ይሁኑ!  

Read 4479 times
Administrator

Latest from Administrator