Saturday, 12 January 2019 14:32

ቃለ ምልልስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምን ይላሉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 የተማሪዎች ግጭት፣ የዘረኝነት መስፋፋት፣ ሥራ አጥነት፣ የማህበራዊ ሚዲያው ሚና

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፤ ተቋሙን ለ11 ዓመታት በከፍተኛ አመራርነት እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ ውድድር ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ አሸናፊ በመሆን ከትላንት በስቲያ በቤተ መንግስት በተካሄደ ሥነሥርዓት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ተገኝተው ሽልማቱን ተረክበዋል። ይሄ ቃለ ምልልስ ግን የትኩረት አቅጣጫው ከዚህ ወጣ ይላል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት
ዮሴፍ፤ ፕሬዚዳንቱን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚነሱ ግጭቶች፣ መንስኤዎችና ዘላቂ መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ጥልቅ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ሃሳቦችንና ምክሮችን ለግሰዋል፡፡ እነሆ፡-

     የዘንድሮ የተማሪዎች ቅበላ ምን ይመስል ነበር?
እንደምታስታውሺው፣ በአዲስ አበባ፣ በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና በትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌታ ሰብሳቢነት በተካሄደው ስብሰባ፣ በአገራችን ስላለው ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ ውይይት ተደርጐ ነበር፡፡ በዚህ ውይይት የሀይማኖት አባቶች፣ የዩኒቨርሲቲና የከተማ አመራሮች፣ ከንቲባዎች፣ የከተማ መስተዳድሮችና ሌሎችም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ እንደሚታወቀው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ተማሪዎች ከውጭ የመጡ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቀባበል ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ተካፍለዋል፡፡ የተለያዩ ግጭቶችም አስተናግደዋል። ይህ ማለት ተማሪዎች በተለያዩ ክስተቶች ውስጥ ቆይተው ነው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚመጡት፡፡ እነዚህን ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ትምህርት ለማስገባት ያስቸግራል፡፡ የውይይቱ ዓላማም የዩኒቨርስቲና የከተማ አመራሮች ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር፣ የተማሪዎችን አቀባበልና የትምህርት ጅማሮውን መልካም ለማድረግ ነበር፡፡
ከቅበላው በፊት ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ነበር ያደረጋችሁት?
ከውይይቱ እንደተመለስን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የአገር ሽማግሌዎችን፣ ወጣቶችንና የሀይማኖት አባቶችን በመጋበዝ፣ ስብሰባ አድርገን፣ እያንዳንዱ የከተማው ማህበረሰብ ጉዳዩ ያገባኛል ብሎ እንዲሰራና ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን የሀይማኖት አባቶችና ተጽእኖ ፈጣሪና ታዋቂ ግለሰቦች ጣልቃ ገብተው ነገሩን እንዲያበርዱ ተስማምተን ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን አድርገን፣ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ተማሪዎች ምን ሃሳብ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ? ተማሪዎች ለትምህርት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው? በሚል ተወያይተን፣ በጥንቃቄና በብልሃት ካልተሰራ አመቱ አደገኛና ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ገምግመናል፡፡ በኋላም ተማሪዎችን በጥሩ ሁኔታ ተቀብለን፣ ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን መስጠት ጀመርን፡፡ ስለ አጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ህግና ሥርዓቶች፣ አስተዳደራዊ ደንቦች እንዲሁም ሌሎችም ጉዳዮች ለተማሪዎች አስተዋውቀን ነው- የመማር ማስተማር ሂደቱ የቀጠለው፡፡
ሆኖም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ ሁከት የተማሪዎች ህይወት ማለፍን ተከትሎ፣ በእናንተም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት ሶስት ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡---
እንዳልሽው…እኛ ይህን ሁሉ ሂደት አልፈን፣ በጥሩ ሁኔታ መማር ማስተማሩ ከተጀመረ በኋላ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የአራት ተማሪዎችን ህልፈት ተከትሎ፣ በእኛም ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተማሪዎች ሰልፍ ወጥተው ነበር፡፡ ሰልፉን የጠራው “የአማራ ተማሪዎች ማህበር” የተባለ ነው፡፡ ዋናው የሰልፉ አላማ “የትኛውም ተማሪ ሊማር በሄደበት ዩኒቨርሲቲ መሞት የለበትም” የሚል ነው፡፡ በአማራ ተማሪዎች ማህበር የፌስቡክ ገጽ ላይም ጥሪ አስተላልፈዋል። ለአንድ ሳምንት ትምህርት ይቁም የሚል አቋም ይዘው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አሁን ካለንበት ማራኪ ግቢ ወደ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ፋሲል ካምፓሶች እንቅስቃሴ ሲጀመር፣ ችግር እንዳይፈጠር ጉዳት እንዳይደርስ፣ የጐንደር ከተማ ወጣቶችን አንፀባራቂ ልዩ ልብስ አልብሰን አሰማራን። ለምን? በመሃል የሚፈጠረው አይታወቅም፡፡ ይህን እያደረግን እያለን፣ አፄ ቴዎድሮስ ካምፓስ ግጭት ተነሳና ሶስት ከባድ ጉዳቶች ደረሱ፡፡ አንዱ ራሱን፣ አንዱ እግሩን የተመቱ ተማሪዎች ነበሩ፡፡
የሞተስ ነበር?
የሞተ የለም፡፡ ሶስቱንም ወደ ህክምና ወስደናቸው ነበር፡፡ ሌሎች ወደ 10 የሚሆኑት ቀላል ጉዳቶች ነበር የደረሰባቸው፡፡ ሶስቱ እንደነገርኩሽ ለከፍተኛ ህክምና ተልከው የነበረ ሲሆን አንዱ ታክሞ ወደ ትምህርት ገበታው ተመልሷል፡፡ አንደኛው ከዚህ ቀደምም ተሰብሮ የተጠገነ ስለነበረ አዲስ አበባ ተልኳል፡፡ ሌሎቹ፤ ራሱን የተመታውም ጭምር ታክመዋል፡፡ የሞተ የለም፡፡
ግጭቱን እንዴት ማብረድ ተቻለ?
ይህንን ግጭት ሲሰሙ የሀይማኖት አባቶች (ቄሶች፣ ፕሮቴስታንቶችም) መጥተው የማረጋጋት ስራ ሰርተዋል፡፡ ሰልፉም ሆነ ግጭቱ ከአንድ ቀን በላይ አልዘለቁም፡፡ ነገር ግን ከዚያ ቀጥሎ በየግቢው የምናያቸው ምልክቶች ጥሩ አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ ተማሪዎች ለመንቀሳቀስም ወደ ውጭ ለመውጣት ስጋት ስላደረባቸው፣ ፌደራል ፖሊስና የክልሉን ልዩ ሀይል አስገብተን ለማረጋጋት ሞክረናል፡፡ አምናም አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተነሳ ግጭት ሳቢያ ነው እኛም ጋ የተቀሰቀሰው፡፡ ዞሮ ዞሮ በየትኛውም አካባቢ ለትምህርት የሚሄዱ ተማሪዎች በሰላም ተምረው፣ ህልማቸውን ማሳካት እንጂ መሞት የለባቸውም፡፡ ይሄ አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው፤ ነገር ግን በግጭትና በጉዳት መታጀብ የለበትም፡፡ እኛም ተማሪዎች በየዶርሙና በየክፍሉ ጥያቄ ሲያነሱ፣ መደበኛ ባልሆነም መንገድ ስናወያይ፣ ጥያቄ ስንመልስና ስናረጋጋ ቆየን፡፡ ከዚያም ከፌደራል መንግስት የተላኩ ሶስት ሰዎች መጥተው ውይይት ተደርጐ፣ ተማሪዎች በየክፍላቸው ትምህርት ጀምረዋል፡፡ ይህ ማለት የተማሪዎች ጥያቄ ቆሟል ማለት አይደለም። ለምሳሌ፡- ተማሪዎቹ ከፌደራል መንግስት ለመጡ ተወካዮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ምን አይነት መልዕክት?
አንዱ፤ “በየትኛውም ቦታ ተማሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ መማር አለባቸው” የሚል ነው፡፡ ሌላው፤ “ስለ አብሮነታችንና ስለ ታሪካችን በቅጡ አላስተማራችሁንም” የሚል ነው፡፡ “ስለ ብሔር ብሔረሰቦች እንማራለን ግን ብሔር ብሔረሰቦች እንዴት በአብሮነትና በፍቅር እንደሚኖሩ አልተማርንም” ብለዋል፡፡ “የተማሪዎች የታሪክ ትምህርትም አናሳና በትኩረት የሚሰጥ አለመሆኑ አሁን ላለንበት ውጥንቅጥ ዳርጐናል” በማለትም፤ “በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ ያሉ ችግሮች ተገምግመው፣ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ይደረግ፤ የታሪክ ትምህርት ተጠናክሮና ተስፋፍቶ ይቀጥል፤ በዩኒቨርስቲ አካባቢም የአስተዳደር ክፍተቶች ተሞልተው፣ ተማሪው በአግባቡ ሊማር ይገባል” የሚሉ መልዕክቶች ለትምህርት ሚኒስቴር አስተላልፈዋል፡፡    
የፌደራል መንግስት ተወካዮችም በዩኒቨርስቲ ደረጃ ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች በዩኒቨርስቲ፣ በትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ በአጠቃላይ በፌደራል ደረጃ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች እንደየ ችግሮች አይነትና መጠን በየደረጃው መፈታት አለባቸው በሚለው ላይ ተነጋግረን፣ የቤት ስራ ወስደው ሄደዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ትምህርት በጥሩ ሁኔታ  ተጀምሮ እየሄደ ነው፡፡ ይሄ ማለት ዘላቂ መረጋጋት ነው ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተማሪው እንደ ዩኒቨርስቲ ተማሪ፣ በሌላ ቦታ ያለ ወገኑ ሲሞት ሲፈናቀል ዝም ብሎ አይማርም፡፡ በየቦታው የሚፈናቀለው የሚሞተው ቤተሰቡ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ የሚገቡት ከተለያየ ቦታ መጥተው ነው፤ ቢያንስ መፈናቀልና ሞት ከሚደርስበት ቤተሰብ የሚመጣ ተማሪ አይጠፋም፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ዘላቂ መረጋጋት ከሌለ ነገሩ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
ዘላቂ መረጋጋት እንዲፈጠር  ማን ምን ማድረግ ይጠበቅበታል ይላሉ?
እንግዲህ ዘላቂ መፍትሔ ይምጣ ከተባለ፣ ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ድረስ መሰራት ያለባቸው በርካታ ስራዎች ይኖራሉ፡፡ ከቤተሰብ ብጀምርልሽ… ልጆቻችንን የምናሳድግበት መንገድ ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ ቤት ውስጥ ዘር ስንቆጥር፣ ልጆች የማያዳምጡ ይመስለን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ልጆች በጨቅላ አዕምሯቸው እየመዘገቡ፣ ግራ እየገባቸው ነው የሚያድጉት። ወላጅ የሚናገረውን ነገር  መጠንቀቅ አለበት፡፡ ልጆች ስለ ሰው ልጅ እኩልነትና ወንድማማችነት፣ አብሮነትም ጭምር እየሰሙና እየተማሩ ማደግ ነው ያለባቸው፡፡ ቤተሰብ ትልቅ ተቋም በመሆኑ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ሌላው ደግሞ ልጅ ከቤተሰብ ወጥቶ ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትን ይቀላቀላል። ለምሳሌ ትምህርት ቤት፣ ቤተ-እምነቶችና ሌሎችም አሉ፡፡ አሁን ዘር ከሀይማኖት ገዝፏል። አንድ ሰው በፈጣሪው በትክክል ካመነ፣ ስለ ሰው ልጅ እኩልነትም ማመን አለበት፡፡ አሁን የምናየው በተቃራኒው ነው። ይሄ ትክክል አይደለም። የትኛውም የሀይማኖት አስተምህሮ፤ ስለ ሰው ልጅ እኩልነት፣ ስለ ሰላምና ፍቅር በደንብ ያስተምራል። ይህን አስተምህሮ አጥብቀን ስላልያዝነው፣ ዘረኝነትን አጉልተን እያየንና እርስ በርስ እየተጋጨን እየተጠፋፋን ነው፡፡ አንዳችን በአንዳችን ላይ እጃችንን እያነሳን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሃይማኖት ተቋማት አተኩረው መስራት አለባቸው፡፡ በነገራችን ላይ ዘረኝነት የሃይማኖት ተቋማትም ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህንን የሃይማኖት አባቶችም ይነግሩሻል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሃይማኖት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ከዘረኝነት የፀዱ አይደሉም፡፡
ከትምህርት ተቋማትስ ምን ይጠበቃል?
 ከስርዓተ ትምህርቱ ብንጀምር፣ የታሪክ ትምህርት በስፋት መሰጠት አለበት፡፡ ታሪክ በአንድ አካባቢ የሚገደብ ሳይሆን መላ ሀገሪቱን የሚሸፍን ነው። ከበቂ በላይ ጀግኖች አሉ፣ ታሪክ ሰሪ ግለሰቦችም ህዝብም አሉ፡፡ ሲቪክስ የሚባለው ትምህርት ስለ ዜግነት ብቻ ሳይሆን ስለ ስነምግባር በደንብ ማስተማር አለበት፣ ስለዚህ ሲቪክስም መለወጥ አለበት፡፡ ከአንደኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የስነ ምግባር ትምህርት በአግባቡ መሰጠት ይኖርበታል። በአንድነት ውስጥ ልዩነት፣ በልዩነት ውስጥ አንድ ሆኖ ተዋዶ መኖር እንዳለብን ማስተማር አለበት፡፡ ህብረ-ብሔራዊነትን ከማጠናከር አንፃር የሚቀረፁ ስርዓተ-ትምህርቶች ትኩረት ይሻሉ፡፡ በዩኒቨርስቲም ስንመጣ የትምህርት ጥራት ችግር አለ፡፡ የትምህርት ጥራት ስንል፣ የላብራቶሪ መኖር ወይም አለመኖር ጉዳይ አይደለም፡፡ የትምህርት ጥራት ማለት አንድን ዜጋ በትክክል ማሰብ የሚያስችል እውቀት ማስጨበጥ መቻል ነው፡፡ አንድ ተማሪ በፈተና ውጤቱ በተግባርም በንድፈ ሃሳብም “A” ሊያመጣ ይችላል። ኬሚስት ወይም ፊዚስት ሊሆንም ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ሰው በዚህ እውቀቱ ቦንብ ሰርቶ ሰው የመጨፍጨፍ አባዜ ከተጠናወተው፣ የትምህርት ጥራት ተጠብቋል ልንል አንችልም፡፡
የትምህርት ጥራት፤ መልካም ስነምግባርን በሰው አዕምሮ መቅረጽ አለበት፡፡ በትምህርት ውስጥ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት አሉ፡፡ እነዚህን በተማሪው ላይ ማስፈን ይኖርበታል፡፡ በሁሉም ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ያለው እውቀትና ክህሎት በግሬድ ይለካል፡፡ አመለካከት በአንፃሩ በግሬድ የሚሰፈር አይደለም፡፡ ያልተሰራውም አመለካከት (Attitude) ላይ ነው፡፡ እዚህ ላይ መሰራት አለበት፡፡ ይሄ ተከታታይ ስራ ይጠይቀናል፡፡
በመምህራንም ላይ የዘረኝነት አስተሳሰብ እየሰረፀ በመሆኑ ሊሰራበት ይገባል፡፡ መምህራን የትውልድ መሀንዲስ ሆነው፣ ይህ አመለካከት ካላቸው ዋጋ የለውም፤ ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተሰብ፣ ት/ቤቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎችም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መስራት አለባቸው፡፡ በሩዋንዳው የሁቱና ቱትሲ ግጭት፣ ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ  ህዝብ አልቋል። በመቶ ቀናት ውስጥ ነው እልቂቱ የተፈፀመው፡፡ ብዙ ህፃናትና ሴቶች አልቀዋል፤ተደፍረዋል፡፡ የእነ ስታሊንን፣ የናዚን ውጤት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ አሁን በማይናማር እየተፈፀመ ያለውም ከዘረኝነት ጋር የተቆራኘን ጥፋት ሊያስተምረን ይገባል፡፡ እነ ሶሪያና የመን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ይታወቃል። በሩዋንዳና ሶሪያ ቤተሰቡ ሲያልቅ እያየ በህይወት የተረፈ ህፃን አለ፡፡ ምን አይነት ዜጋ ነው የሚወጣው? ተከታዩን ትውልድ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው 24 ሰዓት እያደረሰ ያለው ጥፋት እልባት ያስፈልገዋል ባይ ነኝ፡፡
በቅርቡ በጭልጋና በአካባቢው በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ፣ “በግጭቱ የቅማንት ምሁራን እጅ አለበት” በሚል ፍረጃ የእርስዎም ስም ተነስቶ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ?
እንዳልሺው በቅርቡ ቅማንትነቴን በማስመልከት እኔን ሊወክሉ የማይችሉና ከሰብዕናዬ ጋር የማይገናኙ ውንጀላዎች ተካሂደውብኝ ነበር፡፡ እኔም በዚህ ምክንያት ለሁለት ሶስት ዓመታት አልፈልግም ብዬ የተውኩት ፌስቡክ ላይ ተመልሼ ምላሽ ለመስጠት ሞክሬያለሁ፡፡ የዶ/ር ዐቢይን መምጣት ተከትሎ፣ አበረታች ለውጦች መጥተዋል፤ ምንም እንኳን ለውጡ ብዙ ችግሮችን አስከትሎ ቢመጣም፡፡ በ2008 እና ከዚያም በኋላ ብዙ ወጣቶች፣የህይወት መስዋዕትነት በመላው ኢትዮጵያ ከፍለዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ዘግናኝ የሆኑ የህፃናትና የአዋቂ አስከሬኖች በየፌስቡኩ ይለቀቃሉ፡፡ ይሄ ተስፋ አስቆራጭ በመሆኑ ፌስቡክን እርም ብዬ ትቼ ነበር፡፡ አሁን የተመለስኩት በተከተፈብኝ ዘመቻ ቢያንስ ግንዛቤ ለመስጠት ነው፡፡
“ደሳለኝ ቅማንት ስለሆነ የቅማንትና አማራ ግጭት ውስጥ እጁ አለበት” የሚል ነው ዘመቻው። እኔ ተወልጄ ያደግሁት ጐንደር ነው፡፡ ከቄስ ት/ቤት ጀምሮ ጐንደር ነው የተማርኩት፡፡ 1ኛ ደረጃን ቀይ አምባ ት/ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን አፄ በካፋ፣ 3ኛ ደረጃ አፄ ፋሲል ት/ቤት ተምሬ፣ በጐንደር ባህል ቋንቋና ሥነ ሥርዓት ነው ያደግሁት፡፡ ሥነ ልቦናዬም ጐንደሬነት ነው፡፡
ከጐንደሬነት አልፎ ኢትዮጵያዊነቴ የማይነካ የማይነቃነቅ ነው፡፡ ቤተሰቤ ወንድም እህቶቼም እንደዚሁ የስነ ልቦናዬ ተጋሪ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ዶርም ውስጥም የሀረር፣ የድሬ፣ የጋምቤላ፣ የአፋር ልጅ ከመባባል ያለፈ ብሔር አይጠየቅም፤ አናውቅም፡፡ ከዓመታት በፊት የቅማንት ማንነት ጉዳይ ሲነሳ፣ እንዳልኩሽ፣ ያደግሁበት ማህበረሰብ፣ ባህልና ሀይማኖት ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው፡፡ የሚመራኝ አዕምሮዬ እንጂ ዘሬ አይደለም፡፡ እኔ ያደግሁበት ስነ ልቦና፣ ይዤው የመጣሁት አስተሳሰብ አለ፡፡ የኔን ስም የሚያጠፉትና ያልሆንኩትን የሚሉት ጥቂት ግለሰቦች ናቸው፡፡
የውንጀላው መንስኤ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?
በዩኒቨርስቲው ውስጥ አልፎ አልፎ የሚካሄዱ ስርቆቶች አሉ፡፡ ይህ ተጣርቶ ስደርስበት ህግና ስርዓትን ተከትዬ ቅጣት የምጥልባቸው ብሎም የማሰናብታቸው የተቋሙ ሰራተኞች አሉ፡፡ በተለያየ መንገድ ያልተገባ ስራ ሲሰሩ ሳገኝ እርምጃ እወስዳለሁ፡፡ በተለያየ መንገድ ሊወነጅሉኝ አስበው ክፍተት ሲያጡ፣ የቅማንትና አማራ ግጭት ሲነሳ፣ በዚህ ሰበብ፣ እኔን ለማጥቃት ዘመቻ መክፈታቸው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ስለ እኔ የጐንደር ህዝብ፣ በተለይ ወጣቱ፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና የስራ ባልደረቦቼ እንዲሁም በግቢው ቆይተው የሚወጡ ተማሪዎች መመስከር ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጐንደሬነት ነው፤ ባህሌም ህይወቴም ማንም ምንም ቢለኝ፣ ከአቋሜ የምዛነፍም አይደለሁም፡፡ በስራዬ በትጋት እቀጥላለሁ፤ ህዝብና አገሬን ማገልገሌን እገፋበታለሁ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ አገለገሉ?
በመካከለኛ አመራር አንድ አመት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት 6 ዓመት፣ በፕሬዚዳንትነት አራተኛ አመቴ፣ እንደ አመራር ስሰራ ደግሞ 11ኛ ዓመቴ ነው ማለት ነው፡፡ ከቆየሁባቸው 13 ዓመታት መካከል 11ዱ በከፍተኛ አመራርነት ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ካመጡት ከጓደኞቼና ከቀደምቶቼ፣ አሁንም ካሉት ጋር ትልቅ አሻራ ትቼአለሁ፡፡ በዩኒቨርስቲው ብቻ ሳይሆን በጐንደር ከተማም ጭምር እየሰራሁ ነው ያደግሁት፡፡ አሁንም ለወጣቶች ተጠቃሚነት ብዙ እሰራለሁ፡፡ አንድ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ከልምድ እንደምናየው፤ ብዙ ጊዜ የሚጓዘው ወደ ውጭ አገር ነው፡፡ እኔ ግን ታች አርማጭሆ-- ቋራ፣ መተማና በለሳ ሳይቀር ያልሄድኩበት የለም፡፡ ሆስፒታሎችን፣ ጤና ጣቢያዎችን እናያለን፤ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ከቋራ እስከ መቅደላ እየተጓዝን ታሪክን ስንዘክር ነው የምናሳልፈው፡፡ እኔ ለምን ይህን ታፔላ ሊለጥፉብኝ እንደቻሉ ይገርመኛል፡፡ የሚገርምሽ ቅዳሜ ገበያ ሲቃጠል፣ ቦታው ላይ ብቻዬን ሄጄ አልቅሻለሁ፤ አልቅሼም ዝም አላልኩም፡፡ መጥቼ ማኔጅመንቱን አስተባብሬና አሳምኜ፣ 2.1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገን፣ እንደገና ኮንቴይነሮቹ እንዲሰሩና መልሰው እንዲቋቋሙ አድርገናል፡፡ በእኔ እምነት፤ ይሄ የሰጠናቸው ብር ወደ እኛ የመጣው ከግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ተሰብስቦ ነው የሚል ሎጂክ አለኝ። እነዚህ በቃጠሎ ንብረታቸውን ያጡ ሰዎች ግብር ከፋዮች ናቸው፤ የሰጠናቸውም የከፈሉትን ነው፡፡
ፋሲል ከነማን ስንደግፍም ስፖርት ለምን ይደግፋል የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ወጣቱ ጫት ቤት እየዋለ ነው፡፡ መሸታ ቤት እያደረ ነው፡፡ ከዚህ ተላቆ ስፖርት እያየ፣ ኳስ ሜዳ ቢውል  ምን ክፋት አለው? ስፖርት ያልተደገፈ ምን ይደገፋል? ፋሲል ከነማን ስንደግፍ ስፖንሰርሺፕ ተከለከለ። በእኔ እምነት፣ ክልከላው አግባብነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ስፖርት ጤናማና አምራች ትውልድን ያፈራል፡፡ እኛ ፋሲል ከነማን መደገፍ በጀመርንበት አመት ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ወዲያው ነው የተሸጋገረው፤ ባዶ የነበረ ሜዳ በተመልካች ተጨናንቆ ቦታ ሁሉ እስኪጠፋ ደርሶ ነበር፡፡ በ8 እና በ9 ሰዓት ጫት ቤት ይውል የነበረው ወጣት ነው ኳስ ሜዳውን ማጨናነቅ የጀመረው፡፡
በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉ የሰላም እጦት መንስኤው የወጣቱ የስራ እጦት ነው፡፡ በእኛ ዩኒቨርስቲ 17 የወጣት ማህበራት፤ በኮብልስቶን ስራ፣ በመንገድ ማንጠፍ፣ በግንባታ፣ በሱቅ፣ በፎቶ ኮፒና በመለስተኛ ምግብ ቤት ሥራ ላይ ተሰማርተው፣ ከ5300 በላይ ወጣቶች ህይወታቸውን እየመሩ ነው። እኛም ለአነስተኛና ጥቃቅን ቢሮ ከፍተንላቸው፣ ወጣቶች እያደራጁ ያመጣሉ፤ ሥራ እንሰጣለን፡፡ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች አነስተኛና ጥቃቅን ቢሮ የላቸውም። እኛ ይህን እድል ፈጥረናል፡፡ ለዚህ ሥራ የጐንደር ወጣቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ላደግኩበት ከተማና ህዝብ የምችለውን ሁሉ መልካም ነገር እያደረግሁ ነው፡፡

Read 2081 times