Saturday, 12 January 2019 14:26

ምን ያልተሰራ ጉድ አለ? ግን ምን ግድ አለን?

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(10 votes)

 • አገር ተሳከረ። ኑሮ ከሰረ። የሰው ሕይወት ረከሰ።
   • ዘረኝነት እየተዋዛ የአገሬው ምሳና እራት እስኪመስል ድረስ ቢሳካላቸው፣... ወይም ዘረኝነት በጥሬ እንደ ሰደድ እሳት አገሬውን
ከዳር ዳር እስኪያነድ ድረስ ምኞታቸው ቢሟላ፣... ከዚያስ አመድ ለመሆን ነው? ቢሳካልን ምን ይውጠናል?” ብለው አያስቡም ማለት ነው።
 

     እዚህ አገር ያልተሞከረ የስህተትና የጥፋት አይነት የለም ሲሉ የተናገሩት ወደው አይደለም። ከአስቀያሚ እስከ አስፀያፊ፣ ከአሳፋሪ እስከ ወራዳ፣ እስከ ዘግናኝ ጭካኔ ድረስ... ብዙ ጥፋት ተሰርቷል - በድብቅና በግላጭ በአደባባይ፣ በተናጠልና በመንጋ።
ዝርፊያ፣ በአሳቻ ቦታና ሰዓት የሚፈፀም ወንጀል መሆኑ ቀርቶ፣ በዋና መንገድ በጠራራ ፀሐይ፣ በሞተርሳይክል አጀብና በሆታ፣ ቀልድና ጨዋታ እስኪመስል ድረስ አየን። መንገድ መዝጋት መብትን የሚጥስ ድርጊት መሆኑ ቀርቶ፣ በተገላቢጦሹ እንደ መብት ተቆጥሯል።
ህግንና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ የዜጎችን መብት ከመጠበቅ ይልቅ፣ ጥፋት የሚፈፅሙ ህግ አስከባሪዎች ላይ ማማረር ቀረና፣... ከተማ መንደሩ በወንጀለኞች ሲወረር - ነዋሪዎች ሲሰቃዩ፣ ሲደፈሩና ከህፃን እስከ አዛውንት እንደ እባብ ተቀጥቅጠው ሕይወታቸውን ሲያጡ፣... ህግ አስከባሪዎች አይተው እንዳላዩ፣ ምንም እንዳልተፈጠረና እንደማይመለከታቸው ሆነው ሲቀመጡ ተመለከትን።
ፖለቲካ፣... ኑሮን በነፃነት ለመምራት፣ ሕግና ሥርዓትን ለማስፈን ሊያገለግል እንደሚገባ ተረስቶ፣ የሰዎች ሕይወትና ኑሮ በመስዋዕትነት የሚገበሩለት የበላይ ጣዖት አስመስለነዋል። ኑሮና ሕይወት የፖለቲካ መቆመሪያ ሆነዋል።   
በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ሳቢያ፣ አገሪቱ በአስፈሪ ፍጥነት የገደል አፋፍ ላይ መድረሷ፣ እጅጉን ሊያስጨንቃቸውና እንቅልፍ አጥተው መፍትሄ ለመፈለግና ለማበጀት በቅንነት፣ በእውነትና በትጋት እንዲጣጣሩ የሚጠበቅባቸው ምሁራንና ጋዜጠኞች፣ ከተቃዋሚውም፣ ከገዢውም ፓርቲ በርካታ ፖለቲከኞች፣... ይባስኑ፣ ዘረኝነትን ለማጦዝና ለማግለብለብ በሽሚያ ሲረባረቡም እየታዘብን ነው። መጠባበቂያ ብቻ ሳይሆን ብዙ ተቀያሪ አገር ያስቀመጡና እንደ አዲስ መፍጠር የሚችሉ ነው የሚመስሉት። ግን፣ እንኳንና አገር የመፍጠር አቅም ይቅርና፣ ድሮ የተፈጠረውን አገር አፅንቶ የማቆየት አቅም እንኳ የላቸውም። በጭፍን ስሜት አገርን የሚያተራምስና የሚያፈርስ ጥላቻ ከመዝራት የመቆጠብ አቅምም ይጥፋ?
ዘረኝነትን ከሚያራግብ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ውጭ፣ ሌላ አንዳች ሃሳብ ጨርሶ ከአገሬው የፖለቲካ አየር መጥፋቱን እያዩ፣ ትንሽ አያሳስባቸውም?  ያንኑን ዘረኝነት፣ እያገላበጡና እያዟዟሩ፣ አንዳንዱ ዘረኝነትን የማዋዛት የብልጣብልጥነት ፉክክር ያምረዋል። አንዳንዱ ዘረኝነትን ገልቦ ሌጣውን የማጋጋልና የማቀጣጠል እሽቅድምድም እንዲሟሟቅ ይሟሟታል። ተሳክቶላቸው አብረው ለመጥፋት? ዘረኝነት እየተዋዛ የአገሬው ምሳና እራት እስኪመስል ድረስ ቢሳካላቸው፣... ወይም ዘረኝነት በጥሬ እንደ ሰደድ እሳት አገሬውን ከዳር ዳር እስኪያነድ ድረስ ምኞታቸው ቢሟላ፣... ከዚያስ አመድ ለመሆን ነው? ዘረኝነት በየትኛውም መልክ፣ ቦታና ጊዜ፣ ከክፉ ጥፋት ውጭ ሌላ መጨረሻ እንደሌለው አይታያቸውም? “ቢሳካልን ምን ይውጠናል?” ብለው አያስቡም ማለት ነው።        
ዘረኝነት እየተዋዛም ሆነ በግርድፉ፣ አገራችንን ለማተራመስና ለመበታተን ከደጃፋችን የደረሰ የጥፋት ጐርፍ፣ ከ”ሰው”ነት ተራ የሚያወጣ፣ ኑሮን የሚያሳጣና ሕይወትን የሚያጠፋ ክፉኛ የሚፋጅ በሽታ እንደሆነ እለት ተእለት በየአካባቢያችን እያየንም፣... ይህንን ክፉ በሽታ መከላከልና መፍትሄ ማበጀት፣ የሕልውና ጉዳያችንና የእለት ተእለት ተግባራችን መሆን አልነበረበትም? ነበረበት፣ አላደረግነውም እንጂ። በተቃራኒው በሽታውን የሚዘራ፣ የሚያራባና የሚያዛምት ነው በየቦታው እየጎላ፣ ጩኸቱም እየገነነ የመጣው።
እውነትም ትልቅ ውድቀት ነው። አገር ተሳከረ። ኑሮ ከሰረ። የሰው ሕይወት ረከሰ።
አገር ሰላምና እርጋታ ርቆት፣ ያለ ፋታ እየታመሰና እየተናጋ ይቅርና፣ ለወትሮውም የአገሬው ኢኮኖሚና የዜጎች ኑሮ ከአደጋ መዳን ያቃታቸው፣ ከችጋር መላቀቅ እንደ ሰማይ የራቀው መከረኛ ሕይወት ነው።
ዋና ዋናዎቹን ብቻ መመልከት ትችላላችሁ። እንደካቻምናው፣ ኤልኒኖ እና ድርቅ እንደገና ቢከሰት ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት፡፡ ወይም ደግሞ ለኢኮኖሚ እድገት በቀዳሚነት እንደ ዋነኛ ቁልፍ የሚቆጠረውን ኤክስፖርትን እዩ። ባለፉት አራት አመታት ከኤክስፖርት የተገኘው ገቢ፣ በ2004 ዓ.ም ከነበረው ያንሳል። እጥፍ ድርብ እንዲያድግ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ኤክስፖርት፣ ከመደንዘዝም አልፎ፣ እየወረደ ነው። ከ3 ቢ. ዶላር በታች አሽቆልቁሏል።


----

          (ከገንዘብ ሚኒስቴር የሩብ ዓመት ሪፖርቶች የተሰበሰበ መረጃ)

    ብድር ሲጎርፍ፣ እዳ ሲከማች፣ የዋና እዳ ክፍያ ብቻ ሳይሆን፣ ወለዱም ይቆለላል። ከኤክስፖርት ገቢ ውስጥ፣ ከግማሽ በላይ የሚውለው፣ ለውጭ እዳ ክፍያ ነው። በ2010፣ መንግስት ለውጭ እዳ ክፍያ 1.6 ቢ. ዶላር  አውጥቷል።
ከዚህ ውስጥ 440 ሚሊዮን ዶላሩ፣ የወለድ ክፍያ ነው።
እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ፣ መንግስት፣ ለወለድ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ አይከፍልም ነበር። ዛሬ፣ ለወለድ አስር እጥፍ ይገፈግፋል።


          የውጭ እዳ በቢሊዮን ዶላሮች

የውጭ እዳ በቢሊዮን ዶላር
1999 2.3
2000 2.8
2001 4.4
2002 5.8
2003 8.0
2004 9.1
2005 11.4
2006 14.2
2007 19.2
2008 21.7
2009 23.7
2010 26.1


 ወለድ

1996 35 ሚ. ዶላር
1997 35 ሚ. ዶላር
1998 35 ሚ. ዶላር
1999 35 ሚ. ዶላር
2000 30 ሚ. ዶላር
2001 25 ሚ. ዶላር
2002 40 ሚ. ዶላር
2003 60 ሚ. ዶላር
2004 105 ሚ. ዶላር
2005 135 ሚ. ዶላር
2006 160 ሚ. ዶላር
2007 260 ሚ. ዶላር
2008 300 ሚ. ዶላር
2009 435 ሚ. ዶላር
2010 440 ሚ. ዶላር


  የእዳ ክፍያ ከነወለዱ

1996 100 ሚ. ዶላር
1997 110 ሚ. ዶላር
1998 110 ሚ. ዶላር
1999 100 ሚ. ዶላር
2000 90 ሚ. ዶላር
2001 80 ሚ. ዶላር
2002 110 ሚ. ዶላር
2003 240 ሚ. ዶላር
2004 420 ሚ. ዶላር
2005 570 ሚ. ዶላር
2006 670 ሚ. ዶላር
2007 1,000 ሚ. ዶላር
2008 1,140 ሚ. ዶላር
2009 1,300 ሚ. ዶላር
2010 1,600 ሚ. ዶላር


የመንግስት የአገር ውስጥ እዳ (ቢሊዮን ብር)

2003 65
2004 105
2005 150
2006 175
2007 200
2008 245
2009 290
2010 360
 

Read 8494 times