Saturday, 12 January 2019 14:20

የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?

Written by 
Rate this item
(19 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያለ ህፃን እያለቀሰ ያስቸግራል፡፡ ቢያባብሉት፣ እሹሩሩ ቢሉት አሻፈረኝ አለ፡፡ በማባበል እምቢ ሲል ማስፈራራት ጀመሩ፡፡
“እንግዲህ ዝም ካላልክ ለአያ ጅቦ ልንሰጥህ ነው” አለች እናት፡፡
“ዋ በመስኮት ነው የምወረውርህ!” አለው አባት፡፡
ይህንን ሲሉ ለካ አያ ጅቦ ደጅ ሆኖ ያዳምጥ ኖሯል፡፡ ይጠብቃል … ይጠብቃል … ይጠብቃል… ልጁ አልተወረወረም፡፡ አሁንም ያዳምጣል፡፡ ተስፋ ሳይቆርጥ መጠበቁን ቀጠለ፡፡ ምንም ዝር ያለ ነገር የለም፡፡
የልጁ ለቅሶ ግን ቀጥሏል፡፡
አሁንም እናቱ፤
“ዋ! ለአያ ጅቦ ነው አስረክቤህ የምመጣው!!”
አባትም ዳግም፣
“ዛሬ ነግሬሃለሁ ለአያ ጅቦ ነው የምጥልህ” አለው፡፡
ልጁ ማልቀሱን ቀስ በቀስ አቆመ፡፡ አያ ጅቦ ምራቁን እያዝረበረበ፣ ቆበሩን እየደፈቀ ቀረ፡፡ በመካያውም አንድያውን ጥሎ ለመሄድ፤ “ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” ብሎ ጠየቀ፡፡ ቄሱም ዝም፣ ዳዊቱም ዝም፤ ሆነ!
***
አንድ የሀገራችን ዕውቅ ገጣሚ፤ የደርግ ሥርዓት አብቅቶ የኢህአዴግ ሥርዓት ሲጀምር፤
“ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ከምሮ እየናደ፣ ንዶ እየከመረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ ማለቂያው ጀመረ” ብሎ ፅፎ ነበር፡፡
ዕውነትም የማያልቅ ዘመን የለም፡፡ አዲስ ሁሉ ያረጃል፡፡ የማይለወጥ አንዳችም ሥርዓት የለም። የአዲሱ አሸናፊነትም አይቀሬ ነው፡፡ አጠራጣሪው በየትኛው መንገድ ይለወጣል? የሚለው እንጂ ለውጥ መቼም ቢሆን መቼ መምጣቱ የማይቀር ሂደት ነው፡፡ ፈረንጆቹ፤
Everything changes
Except the law of change የሚሉት የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡
“ከቶም ከለውጥ ህግ በስተቀር የማይለወጥ ነገር የለም” እንደማለት ነው፡፡ እነሆ ለውጥ መምጣቱ ግድ ከሆነ ለለውጥ ዝግጁ መሆን ዋናውና አስፈላጊው ጉዳይ ነው፡፡ የሀገራችን ሰው አንድ ለውጥ ባገኘ ቁጥር በዚያው ተወስኖና ያንን ፍፃሜ - ነገር አድርጎ ማሰብ ይቀናዋል፡፡ ሆኖም መሰረታዊ ችግሩ የጊዜ - ቀመር አለማበጀት (Time - plan አለመኖር) ነው፡፡ መልካም የጊዜ ግምት ማጣትን የመሰለ ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት የለም፡፡ “ጊዜ የስልጣን እጅ ነው” ይለናል፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን። ጊዜ የሚታዘዘው ሰው ብቻ ነው - ዕውነተኛ ባለስልጣን! ለሁሉም፤ ትክክለኛ ምክር ሰሚ መሆን ታላቅነት ነው፡-
“ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት
ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ …
ምንኛ ታድሏል የሰነፍ አዕምሮ
 እንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና!
አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
ይሉናል ገጣሚ ከበደ ሚካኤል፡፡ ካልተደማመጥን ወንዝ አንሻገርም፡፡ ካልተጋገዝን አገር አትንቀሳቀስም፡፡ አሉታዊ ገፅታዎቻችንን ብቻ እየነቀስን በማጉላት ለውጥ የሚመጣ የሚመስለን በርካቶች ነን፡፡ ሀገራችን ለሶስት ሺህ ዘመን ያጠራቀመችው በቂ አሉታዊ ነገሮች አሏት፡፡ እነዚህን በማጉላት ምንም አናተርፍም፡፡ ይኸውም ልዩ ዕውቀት እየመሳሰለን የምንደገግ ብዙ ነን፡፡ ስለ ሰው ክፉ ክፉውን በመናገር፣ ዘራፍ ማለት የአሸናፊነት ስሜት መፍጠሩ ዕውነት ነው፡፡ ሆኖም በትክክለኛ መፍትሄ ካልታገዘ ጎጂ ባህል ይሆናል፡፡ ለመፍትሄ ያልተዘጋጀ ህብረተሰብ፣ የአፍራሽነት ሥነ-አዕምሮ ይዞ የሚጓዝ ስለሆነ ከለውጥ ይልቅ ወግ-አጥባቂነትን ያዘወትራል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለው ማህበረሰብ ከጅምሩም ተራኪ (Story-teller) ህብረተ-ሰብ ነው፡፡ ከተግባራዊነት ይልቅ አፍአዊነት ይቀናዋል፡፡ አፍአዊነቱም በጥናት ላይ አለመመስረቱ ደግሞ ነገረ - ዓለማችንን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ነው የወሬ አገር ሆነን የቀረነው፡፡
ያለምነውንና የተመኘነውን ዲሞክራሲ እስከምናገኝ ብዙ ዳክረናል፡፡ ብዙ ፈግተናል፡፡ ልጃቸውን ይወረውሩልኛል ብሎ በር በሩን ሲያይ እንዳመሸው አያ ጅቦ፤ በመጨረሻው ዘጋግተው እንደሚተኙ እንዘነጋለን፡፡ እንደ ህፃኑ ልጅ የሚያስቸግረውንም የኢትዮጵያ ህዝብ አባብለው እንደሚያስተኙት ግልፅ እየሆነ ሲመጣ፤ የእኛ ትርፍ “ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” ማለት ብቻ ከሆነ አደጋ ላይ ነን፡፡ ዲሞክራሲ ከራሳችን የሚፈልቅ እንጂ ማንም የሚሰጠን ምፅዋት ወይም ዳረጎት አይደለም!

Read 9315 times